“አሸንፈን አሸንፈን አሸንፈን
ከፍ አለልን ከፍ አለልን ባንዲራችን
በወርቃችሁ በብራችሁ እኛ ኮራን
ደስ ብሎናል ደስ ብሎናል ደስ ይበለን…”
ኢትዮጵያ በዓለም የአትሌቲክስ መድረኮች በጀግኖች አትሌቶቿ ሁሌም ትደምቃለች።በየሄዱበት የውድድር መድረኮች በድላቸው የሚያደምቋት ጀግኖቿም በተለያዩ የጥበብ ስራዎች ከድላቸው ማግስት ይሞካሻሉ።የድል ዜናቸው በአዳዲስ የድል ዜማዎች ይደምቃሉ።አትሌቲክሱ በጥበብ ደምቆ፤ሩጫው በኪነት ገኖ ከፍ ያለ ድል እያጎናፀፈን ዘመን ይሻገራል።
በአትሌቲክሱ ዓለም በድላቸው ለኢትዮጵያ ክብርን ያጎናፀፉ፣ ሰንደቃላማዋን በዓለም አደባባይ ከፍ አድርገው ያውለበለቡና ብሔራዊ መዝሙሯ ተደጋግሞ እንዲዘመር ያደረጉ ጀግኖች አትሌቶቿ የድል ብስራታቸው ነጥፎ አያውቅም።አሁን አሁን እየቀዘቀዘ መጣ እንጂ ቀደም ባሉት ዓመታት እነዚህ ጀግኖች ዘመን ተሻጋሪ በሆኑና ለጆሮ በሚጣፍጡ ጥበባዊ ዜማዎች ሲወደሱ ማየት የተለመደ ነው። በዛሬው የዘመን ጥበብ አምዳችንም እንቁ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በ18ኛው የኦሪገን የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና እያስመዘገቡ የሚገኘውን ተደጋጋሚ ድል ምክንያት በማድረግ ከአትሌቶቻችን ድል ማግስት ኪነጥበብ በተለይም ሙዚቃና የድል ዜማዎችን እንዳስሳለን።
አትሌቶቻችን ከድላቸው ማግስት በግጥምና ዜማ መወደስ የጀመሩት አበበ ቢቂላ ግዙፉን ታሪክ በሮም ኦሊምፒክ ከፃፈበት ወቅት አንስቶ ነው።ያንን የማይረሳ የባዶ እግር ገድል የፈፀመው ታላቁ አበበ ወደ አገሩ ሲመለስ ጥበብ ባዶ እጇን አልጠበቀችውም።የዘመን ተሻጋሪ ዜማዎችና የኢትዮጵያ ሙዚቃ ንጉሱ ድምፃዊ ጥላሁን ገሰሰ ታላቁን ድል በመረዋ ድምፁ አድምቆታል።ጀግናውንም እንዲህ ሲል አወድሶታል፡፡
ደስ ብሎናል በጣም ምኞታችን ሞላ
አሸንፎ መጣ አበበ ቢቂላ
አትሌቶቻችን አንፀባራቂ ድል አስመዝግበው በሙዚቃ ከያኒያን ከተከሸኑ ውብና ዘመን ተሻጋሪ ስራዎች አንዱ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የህብረት ዜማ ያህል አሁንም ድረስ የማይረሳው አንድ ድንቅ ዜማ አለ።
አሸንፈን አሸንፈን አሸንፈን
ከፍ አለል ከፍ አለልን ባንዲራችን
በወርቃችሁ በብራችሁ እኛ ኮራን
ደስ ብሎናል ደስ ብሎናል ደስ ይበለን
በወቅቱ ከፍተኛ ተደማጭነት የነበራቸው ድምፃዊያን ሀይማኖት ግርማ፣ጌዲዮን ዳንኤል፣ዮሴፍ ገብሬ፣ማያድና ናትናኤል ዜማውን በጋራ ያንቆረቆሩልን ድምፃዊያን ናቸው፡፡ይህ ዜማ ኢትዮጵያ በተለያዩ የዓለም መድረኮች በአትሌቲክሱ ዘርፍ በተለይም በሩጫ ድል ስትጎናፀፍ የድል ብስራቱ ነጋሪዎች የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ዜናዎች ማድመቂያ ሆኖ ዛሬም ድረስ ይደመጣል።
የአበበ መንፈሱን በማራቶን
በጀግናዎች ታየ ይሄው አሁን
ጥንትም ስንጀምረው ማሸነፉን
በባዶ እግር ቀድሞ ማሰለፉን
በ1960ው የሮም ኦሊምፒክ ማራቶን በባዶ እግሩ ሮጦ ዓለምን ጉድ ያሰኘው ኢትዮጵያዊ ጀግና አትሌት ሻምበል አበበ ቢቂላ የማይረሳ ታሪክና ጀብዱው በዚህ ውብ ዜማ ተዳሷል።የዚያ የጥቁር ሕዝቦች ድል ፋና ወጊ አትሌት የአሸናፊነት መንፈስ፣ ፅናትና አልበገር ባይነትን የተከተሉ የዘመኑ ጀግኖች አትሌቶች ዛሬም እንደ ጥንቱ ድል አስመዝግበው አበበን በዚያ ዜማ አስታውሰውታል። ይህ ውብ ዜማ ትናንትን ከዛሬ ሁነት ጋር አስታርቋል።
በእርግጥ ጥበብ ትዝታን ከዛሬ ጋር በማዛነቅ የራስዋ ልዩ ምስል ትከስታለችና አበበን በዛሬዎቹ የአትሌቲክሱ ጀግኖች ድጋሚ ለማየት አስችሏል። ጀግኖች አትሌቶቻችን ዛሬም እንደ ትናንቱ በድል ደምቀው እንደቀጠሉት ሁሉ የዚህ ዜማ ስንኝ የአትሌቲክስ ድላችንን የትውልድ ቅብብሎሽ ጎልቶ የሚያሳይ ነው፡፡
ጥንካሬያችን መለያችን ነው፣ ኢትዮጵያዊነት ሁልጊዜም ማሸነፍ ነው፣ የኢትዮጵያዊያን አንድነት ለአገር ቤዛ ለወገን መከታ ሆኖ በህብረት መቆም የተለመደ እንደሆነ በማፅናት፤ አትሌቶቻችን በመወዳደሪያ ሜዳ የሚያሳዩት የትብብር መንፈስ ከኢትዮጵያዊያን ህብረትና አንድ ሆኖ መቆም እሴት ጋር እያገናኘ ትስስሩን አጉልቶ ለጆሮ በሚስማማ ውብ ዜማ ይነግረናል። አብሮነት ማሸነፍ መሆኑን፣ አንድነት የድል ሚስጥር እንደሆነም አስተማሪ የሆኑ ስንኞች በውብ ዜማ ታሽተው እናገኛቸዋለን።
ሌላም አይረሴ የድል ማግስት ዜማ አለ። ይህን ዜማ የአሁኑ ትውልድ በተለየ ያስታውሰዋል። እንዲያውም ዘወትር ያዜመዋል መባል ይችላል።ያን ወቅት ሁላችንም ልብ ውስጥ የዛሬ ሁነት ያህል ምስል ከሳች በሆነ ትዝታ ሰፍሮ ይገኛል። ኢትዮጵያ ተደጋግሞ ስሟ የተጠራበት ውድድር፣ ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች የነገሱበት ፉክክር። እኤአ 2000 ላይ በሲድኒ ኦሊምፒክ አትሌቶቻችን አሁንም ድረስ የምንኮራበትና ከዚያ በኋላ ያልተደገመ አንፀባራቂ ድል አስመዝግበው ወደ አገራቸው የተመለሱበት ወቅት ነበር። እነሱ በድል አሸብርቀው ሲመለሱ ጣፋጩ ድላቸው ጣፋጭ ዜማ ወለደ።
በዚህ ታላቅ ውድድር ላይ ከታዩት ክስተቶች መካከል ጀግናው አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ ከኬንያዊው ታላቅ አትሌት ፖል ቴርጋት ጋር በመጨረሻ ሰዓት ያደረገው ትንቅንቅና ያስመዘገበው ጣፋጭ ድል በኢትዮጵያዊያን አሁንም ድረስ ልዩ ቦታ ይሰጠዋል።አትሌቶቻችን በድሉ ማግስት ወደ አገር ቤት ሲመለሱም ጥበብ እንዲህ ብላ ተቀበለቻቸው።
ከፍ አለ ከፍ ከፍ ከፍ አለ
ተውለበለበ ባንዲራችን
በሲዲኒ ኦሊምፒክ ጀግኖቻችን
በሲዲኒ ኦሊምፒክ አትሌቶቻችን ለአገራችን ያስገ ኙትን አንፀባራቂ ድል ተከትሎ በወቅቱ ተደጋግሞ የተደመጠ የህብረት ዜማ ከጥበበኞቹ ተበርክቶ የድሉ ማድመቂ ነበር።
የድል ማግስት ዜማዎች ሲታወሱ እንደ ሌሎች ሙዚቃዎች ዘወትር አሁንም ድረስ ሲደመጥ የሚስተዋለው አንድ ዜማ ከሁሉም በላይ ጎልቶ ይጠቀሳል።ተወዳጁ ድምፃዊ፣ የግጥምና ዜማ ደራሲ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች በተለይም ኃይሌ ገብረስላሴ፣ቀነኒሳ በቀለና ስለሺ ስህን እኤአ በ2004 የአቴንስ ኦሊምፒክ ስለ ኢትዮጵያ የሆኑትና ያደረጉትን ገድል ተመልክቶ በአንድ ሌሊት ለጆሮ ያበቃው ተወዳጅ ግጥምና ዜማ በሁሉም ኢትዮጵያውያን ዘንድ ዛሬም ይደመጣል።
መርቆ ሸኝቶ ሀገር አሲዞ ሰንደቅ አላማ መ ር ዶ ነው ለወገናችን ማሸነፍ ካቃተንማ….
የዚያ ዘመን ተሻጋሪ ሙዚቃ መግቢያ ነው።በአትሌቲክሱ ዘርፍ ኢትዮጵያ የረጅም ዘመን የድል ታሪክ ባለቤት ናትና ህዝብ አትሌቶችን ወደ ውድድር ልኮ በድል እንዲመለሱ በፅኑ ይመኛል።አትሌቶችም የህዝብ አደራ ይዘው ነውና እዚያ የወድድር መስክ ላይ የሚገኙት ብርቱ ተጋድሎን ያደርጋሉ። የሰንደቅ አላማ ክብር የህዝብ አደራና አገራዊ ስሜት እዚህ የዜማው መጀመሪያ ስንኞች ላይ ቴዲ አፍሮ በጉልህ አንጸባርቆታል። ቴዲ ቀጥሏል፡፡
ልሰለፍ ህመሜን ችዬ እሮጬ ላሯሩጣቸው
ትልቁን እምነት በእናንተ ጥለናል
እንግዲ አይዟችሁ
ለኢትዮጵያ በአትሌትክሱ ዘርፍ በብርቱ እግሮቹ ሮጦ ክብርን ያጎናፀፈው ጀግናው ኃይሌ ገብረስላሴ ከቀነኒሳ በቀለ ጋር ያደረጉትን መተጋገዝ፣አብሮነት፣ አገራዊ አደራን በጋራ ለመወጣት ያላቸውን ቁርጠኝነት እዚያ የውድድር ሜዳ ላይ የሆኑትን ሁሉ ጣፋጭ ጥበባዊ ለዛ ባላቸው ስንኞቹ አስቀምጧቸዋል።ኃይሌ ያኔ በዘርፉ የነገሰበትን ዙፋን ለቀነኒሳ በክብር የሚያስረክብበት ቀነኒሳም የታላቁን ንግስና አጎንብሶ በትህትናና በፍቅር አንገቱን አጠማዞ በስስት እያየ የተረከበበት ነበር።
ከበደኝ ትቼህ ለመግባት፤
ከበደኝ የወኔ አባቴን
ከበደኝ ባይኔ ፈለኩህ፤ ከበደኝ
አዙሬ ፊቴን
ቀነኒሳ ስለ ኃይሌ እዚያ ውድድር ላይ ያሳየው ስሜት አንገቱን አጠማዞ የሆነውን ቴዲ በጥበብ በራሱ ተርጉሞ በዚህ መልክ አቅርቦልን በአትሌቶቻችን ድል እና ፍቅር ተደስተን በቴዲ ዜማ በጋራ አዚመናል፤ በአገር ፍቅር ስሜት አንብተናልም።እዚሁ ዜማ ላይ ኃይሌ ምክሩን ቀጥሏል፤ቴዲም መጠበቡን አላቆመም።
በል ፍጠን ድሉ ናፍቆታል ፤
በል ፍጠን ባብቷል ወገኔ
በል ፍጠን እንዳትቀደም፤ በል
ፍጠን አትይ ወደኔ
የኃይሌን መልእክት ሰምቶ ቀነኒሳም እግሩን ወደፊት እየወረወረ ኃይሌን ተጠማዞ ወደኋላ እያየ ያስባል አልያም እንዲህ ይላል ብሎ ዜማው በሚስረቀረቅ ውብ አራራይ ዜማ ቴዲ ይነግረናል።
አልሆንልህ አለኝ እኔ አልሆንልህ አለኝ
አንተን ጥሎ መግባት
ኃይሌ አልሆንልህ አለኝ (2)
የአትሌቶቹ የእርስ በርስ መተሳሰብና ልዩ ፍቅር፣ አብሮነትና አገራዊ ስሜት በጉልህ ያመላከተው ይህ ስንኝ ጥበብ ስሜትን ኮርኳሪ የሰዎችን ውስጠት የሚቆጣጠር ልዩ ጉዳይ መሆኑ በጉልህ ያስረዳል።
አንበሳ ቀነኒሳ አንበሳ
ታሪክ ሰራ የማይረሳ
ቴዎድሮስ ካሳሁን በአንድ ሌሊት ሁነቱን አይቶ ገጥሞ ዜማ ሰርቶና ቅንብሩን አሰርቶ እንካችሁ ያለን ይህ “አንበሳ” የተሰኘው ዜማ ዛሬ ድረስ በሁላችን ልብ ውስጥ አንዳች የሞቀ ስሜት መፍጠሩን ቀጥሏል።ቴዲ የተመለከተውን በጥበብ አዋዝቶ ኃይሌና ቀነኒሳ በእዝነ ልቦናው በወቅቱ የተመላለሱት አልያም በስሜት የተነጋገሩት የተቀረፀውን ለእኛ መንገሩን ቀጥሏል።
ኃይሌ ከኋላ ቀነኒሳ ፊቱን እየመራ ስለሺ ስህን ደግሞ በሁለቱ መሀል ሆነው ከሌሎች አገራት አትሌቶች ጋር ብርቱ ትግል ያደርጋሉ።ቀነኒሳ ኋላ ያሉትን ሀይሌና ስለሺ ፍለጋ የሚባትቱት ዓይኖቹ ከፊቱ ባለ መሮጫ ትራኩ ላይ እንዲያደርግ ኃይሌ መጎትጎቱን ቀጥሏል።
አደራ የአቅሜን ሰራሁኝ አደራ እኔ ላገሬ
አደራ የ5 የ10 ሺህ በኦሎምፒክ ልሸኝ
ነው ዛሬ
እዮሃ ከባንዲራው ነው እዮሃ ቃልኪዳናችን
እዮሃ አታፍርም በኛ እዮሃ ኃይሌ አባታችን
አልሆንልህ አለኝ እኔ አልሆንልህ አለኝ እኔ
አንተን ጥሎ መግባት ኃይሌ አልሆንልህ
አለኝ እኔ
አለልህ ስለሺ ደጀን በርታ ቀነኒሳ
ይልቅ አሸንፈህ ቶሎ ባንዲራውን አንሳ
አልሆንልህ አለኝ እኔ አልሆንልህ አለኝ እኔ
አንተን ጥሎ መግባት ኃይሌ አልሆንልህ
አለኝ እኔ
አለልህ ስለሺ ደጀን በርታ ቀነኒሳ
አንተ ነህ ያሁኑ ዘመን ተተኪው አንበሳ
እዮሀ ውሮ ወሸባ እዮሀ ታሪክ ሰራችሁ
እሁ ያገሬ ልጆች እዮሀ ኑ ልቀፋችሁ
እዮሀ በል አንሳን ፎቶ እዮሀ ለብሰን ባንዲራ
እዮሀ ብለህ ፃፍበት እዮሀ ታሪክ ተሰራ
እልል በል ያገሬ ጎበዝ ለእምዬ ሁለታ
ወርቅ አመጣሁላት ይሄው ለክብሯ ስጦታ
ተወዳጁ ድምፃዊ በማይነጥፍ የጥበብ መክሊቱ በዚያ ውድድር መድረክ ላይ የሆነውን ታሪካዊ ክስተት ቁልጭ አድርጎ በጥዑም ዜማ ይቀኘዋል። በማይጠገብ ልዩ ጣዕመ ዜማ ያንቆረቁረዋል።ቴዲ ቀጥሏል፤እኛም ያኔ የሆነውን ዛሬ ላይ አሁን የሆነ ያህል ምስጋና ለጥበብ ይግባውና አውቀነዋል። የዜማውን መቋጫ ስን ኖችም መደምደሚያችን ይሁኑ፡፡
እዩት ንጉሱን ግርማ ሞገሱ
ዘውድ ሸለመው ሰጠው ላዲሱ
ይቺ ባንዲራ ናት እኮ የኛ
ዛሬም አኮራት ቀነኒ ኬኛ
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 14 ቀን 2014 ዓ.ም