«እለ ከርሦሙ አምለኮሙ ( እነሆድ አምላኩ) ፤ ያሰባችሁት እኛን የመከፋፈል ሴራ ሳይሳካ ቀረ» እያለ ዋርካው ስር ከሚገኘው ድንጋይ ላይ ቆሞ ወፈፌው ይልቃል አዲሴ መጮህ ሲጀምር፤ በሰፈራችን የሚኖር ከትንሽ እስከ ትልቅ የሚገኝ አንድም ሰው ሳይቀር ዋርካው ስር ወደሚካሔደው ስብሰባ ተመመ፡፡
በነገራችን ላይ ወፈፌው ይለቃል አዲሴ በፖለቲካዊ ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ፍልስፍና ይዘቶች ባላቸው ክርክሮች የሰፈራችን እና የእድራችንን አስተዳደር አቶ ሲራጅ ይመርን ከረታ ወዲህ ወፈፌ የሚለው ስም ባይነሳለትም አብዝቶ ቀለም የዘለቀው እና ጤነኛ ስለመሆኑ ግን ማንም የሰፈራችን ሰው አይጠራጠም፡፡
ይልቃል አዲሴ በሰፈራችን በሚገኘው ዋርካ ስር ትልቅ ድንጋይ ላይ ቆሞ መናገር ሲጀምር ከስብሰባው ከቀራችሁ ከሸማቾች ዘይት እና ስኳር አትሰጡም የተባለ ይመስል አንድም ሰው አይቀርም፡፡ በተለይ ይልቃል አዲሴ ንግግር በጀመረ ቅጽበት ደግሞ አንድም ሰው ከዋርካው ስብሰባ አይንቀሳቀስም፡፡ አንድ አንድ ቀንማ ዋርካው ስር ያልተሰበሰበ በንግግር ጊዜ ወጣ ገባ ያለ ማንኛውም ሰው የአርባ በስልሳ እና ሃያ በሰማኒያ የጋራ መኖሪያ ቤት እጣ አይወጣለትም የተባለ ይመስላል፡፡
የዛሬው የይልቃል አዲሴ ንግግር ደግሞ ከወትሮው የተለየ እና በግዕዝ ቅኔዎች የታጀበ እና የታጀለ ሆኗል፡፡ በግዕዝ ሲናገር ቅኔው የገባቸው ጥቂት ሰዎች ቀድመው ያጨበጭባሉ፡፡ ያልገባቸው ደግሞ በግዕዝ የተናገረውን በአማርኛ ከተተረጎመ በኋላ ስለሚያጨበጭቡ መጀመሪያ ላይ በግዕዝ የተናገረው ቅኔ እንዳልገባቸው ያሳብቅባቸው ነበር፡፡
ከላይ እንደተመላከተው ይልቃል አዲሴ የዛሬ ንግግሩን የጀመረው «እለ ከርሦሙ አምለኮሙ( እነሆድ አምላኩ) ብሎ ነበር ፡፡ ነገር ግን ወደ ዋርካው ስር ስብሰባ ዘግይቶ የደረሰው አብሾአሙ ክንፈ ጉደታ እያለከለከ ደርሶ ይልቃል አዲሴን ከመጀመሪያው እንዲጀመር ስለጠየቀው ይልቃል አዲሴ እንደገና ንግግሩን ለመጀመር ጉሮሮው ጠራርጎ ….
«እየውላችሁ» አለ ….. የሰፈራችንን እና የእድራችንን እድገት እንደ አባ-ጨጓሬ እየኮሰኮሰ ሰላም የሚነሳቸው ፤ እንደእፉኝት ልክፍት ክፉኛ እየጠዘጠዘ አላስተኛ አላስቀምጥ ያላቸው ምስር እና መሰል ታሪካዊ ጠላቶችን ሰፈራችንን እና እድራችንን በብሔር ከፋፍለው በማፍረስ «ወደነበርንበት» ለመቀየር አስበው በከፍተኛ ደረጃ አንድነታችንን ሲፈታተኑት መሰንበታቸው የአደባባይ ሚስጥር ነው ፡፡
ነገር ግን ከሰሞኑ እየተካሄደ ባለው የአለም አትሌቶች የሩጫ ውድድር እና እንደ ሀገር ከተመዘገበው ውጤት ጋር ተያይዞ በመላው ሰፈራችን በታየው እውነታ መገንዘብ እንደተቻለው የሰፈራችን እና የእድራችን አንድነት በምስል እና መሰል ታሪካዊ ጠላቶቻችን የቱንም ያህል በክፋት መርዝ ቢለወስም ትንሽም እንኳን መሰነጣጠቅ ሊያጋጥመው እንደማይችል የተረጋገጠበት ወቅት ነው፡፡ በአትሌቶቻችን ውጤትም ሁሉም ሰው ከሰሜን እስከ ደቡብ፤ ከምስራቅ እስከ ምዕራብ «የብሔራችንን ሰንደቅ አይደለም ያውለበለብነው፤ የኢትዮጵያን ነው፤ ከፍ ብላ የታየችው ኢትዮጵያ እንጂ ዘር ማንዘር አይደለም » ሲል በየአደባባዩ በደስታ በእንባ ሲራጭ ተመልክተናል፡፡
በዚህም ታሪካዊ ጠላቶቻችን በማንኛውም መልኩ የእኛን የሰፈር እና የእድር አንድነት ምንም ማድረግ እንደማይችሉ በመገንዘባቸው ክፉኛ ቁዘማ ውስጥ መግባታቸውን እያስተዋልን እንገኛለን፡፡ በግራም በቀኝም ጦርነት ሲያውጁብን የነበሩትም መለሳለስ እያሳዩ ነው፡፡
ይልቃል አዲሴ ንግግሩን ቀጠለ… እንደሚታወቀው እነኝህ ታሪካዊ ጠላቶቻችን የሰፈራችንን እና የእድራችንን ህልውና እየተፈታተኑት ያለው በሁለት ሃይሎች አማካኝነት ነው፡፡ አንደኛው ከላይ እንደነገርኳችሁ «እለ ከርሦሙ አምለኮሙ( እነሆድ አምላኩን) በነዋይ በመግዛት ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ በውጭ ሀገር በተማሩ ሰዎች ነው፡፡ እነኝህ ሰዎች የራሳቸውን ቋንቋ ንቀው በፈረንጅ አፍ የሚያወጉ ናቸው፡፡
የራሳቸውን ቋንቋ ንቀው በፈረንጅ አፍ ስላወሩ ብቻ ራሳቸውም ሆኑ የሰፈራችን ሰዎች እንደአዋቂ ይቆጥሯቸዋል፡፡ የሚገርመው እኮ! እነኝህ ኃይሎች እገሌ የተባለው የአውሮፓ ወይም የአሜሪካ ምሁር እንዳለው ከማለት ውጪ ይህ ነው የሚባል ችግር ፈቺ እውቀት ያላቸውም፡፡ ነገር ግን እነኝህ አካላት ራሳቸውን በምሁር መርከብ አሳፍረው በመሸምጠጥ በወዶ ገብነት ከታሪካዊ ጠላቶቻችን ምንም ገንዘብ ሳይቀበሉ ሎሌ በመሆን እንደኩራት የተቀበሉ እና በእጅ አዙር የታሪካዊ ጠላቶቻችን የጥፋት አጀንዳ አስፈጻሚዎች ናቸው፡፡
እነኝህ ሁለት ተላላኪ የጥፋት እሳት ተሸካሚ ፈረሶች በሰፈራችን እና በእድራችን በተለያየ ቦታ እና ሁኔታ የተቀመጡ ናቸው፡፡ አንዳንዶቹ በሰፈራችን በእድራችን የአስተዳደር መዋቅር ውስጥ ናቸው፡፡ አንዳንዶቹ ሰፈራችንን እድራችንን ለማስተዳደር በሚፎካከሩ ሃይሎች ስም የተደራጁ ናቸው፡፡ ሌሎቹ ደግሞ በሃይል የሰፈራችንን እና የእድራችንን ስርዓት ለማፍረስ ነፍጥ ያነገቡ ናቸው፡፡
እውነት እላችኋለሁ ነፍጥ ያነገቡት የቱንም ያህል ቢንፈራገጡ የትም አይደርሱም፡፡ ምክንያቱም አንዴ ጠላታችን መሆናቸውን ስላወቅን በመጡበት ልክ እናስተናግዳቸዋለን፡፡ እዚህ ላይ አንድ አስረግጬ መናገር እፈልጋለሁ ! ሁሌም ጠላታችሁን ሳይሆን ወዳጃችሁን ፍሩ! በዚህ ጊዜ በዋርካው ስር የተሰባሰቡ ሰዎች እርስ በርስ እየተያዩ አጉረመረሙ፡፡
ይልቃል አዲሴ ድምጹን ጮክ አድርጎ ንግግሩን ቀጠለ.. ጠላትማ አንዴ ጠላት ነው! ቢመቸው ያጠፋችኋል ፤ ቢመቻችሁ ታጠፉታላችሁ ! አስቸጋሪ የሚሆነው ወዳጅ ነው ፡፡ ምክንያቱም አንደኛ ከአጠገባችሁ ሆኖ እናንተ የምትጠፉበትን ደካማ ጎን ጠንቅቆ ያውቃል፡፡
ሁለተኛ ይሁዳ ለነዋይ ብሎ ክርስቶስን አሳልፎ እንደሰጠው ሁሉ በመካከላችሁ የሚገኝ ወዳጅ የሚመስል ነገር ግን በጠላታችሁ የነዋይ ፍርፋሪ የተገዛ የሰፈራችሁን እና የእድራችሁን ህልውና አደጋ ላይ ሊጥል የሚችል ሰው በመካከላችሁ ሊኖር እንደሚችል በማሰብ ለአፍታም መዘናጋት አይገባችሁም ፡፡ ስለሆነም ሁሌም ወዳጆቻችሁን ነቅታችሁ ጠብቁ፡፡
እነኝህ በመካከላችን የሚገኙ ወዳጅ መሳይ ተኩላዎች በአንድ በኩል ወዳጅ መስለው ለእድራችን እና ለሰፈራችን መሪ እልፍኝ አስከልካይ ( የመሪ አማካሪ) ሆነው ላይ ታች ሲሉ ይውላሉ፡፡ በሌላ በኩል የታሪካዊ ጠላቶቻችን የጥፋት ተልዕኮ ይዘው ለዓመታት ተዋዶ እና ተከባብሮ አብሮ የኖረን ህዝብ በማጣላት እርስ በርሱ እንዲጠራጠር በማድረግ ሀገር ለማፍረስ ሲላላጡ ይታያሉ፡፡
«ኢትክሉ ተቀንዮ ለክልኤ አጋኣዝት (ለሁለት ጌታ መገዛት አይቻልም !)» እንዲሉ አበው እነኝህ በመካከላችን የሚገኙ ወዳጅ መሳይ ተኩላዎች በሰፈራችን እና በእድራችን ላይ የከፋ ጉዳት ሳያደርሱ አሁኑኑ ታድነው ለክፋታቸው ማሳሪያ መድሃኒት ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ አለበለዚያ ጠላቶች ባዘጋጁት ንፍር ውሃ የተሞላ ጉድጓድ ውስጥ ላንመለስ መቀበራችን የማይቀር ነው፡፡
በምሁር ስም ስለሚነግዱት ታሪካዊ ጠላቶቻችንን የጥፋት እሳት ተሸካሚ ፈረሶች የተወሰነ ማለት እፈልጋለሁ ብሎ ንግግሩን ቀጠለ… እነኝህ ምሁራን ነኝ ባይ የጥፋት አሽከሮች ጠላት በወገን ላይ የሚለኩሰውን የጥፋት እሳት የሚያፋፍሙት በሁለት መንገድ ነው፡፡ አንድም በገንዘብ ተገዝተው ፤ ሁለትም ያወቁ መስሏቸው እንዲሁ «ኢትልበሱ ልበሰ ሐራ ወይም የማይገባችሁን ልብስ አትልበሱ፡፡» የአባቶቻችንን ምክር በመዘንጋት ነው፡፡
በተለይ ፊደል ቆጥረናል ብለው ራሳቸውን በምሁራን መርካብ ላይ ያሰፈሩ አላዋቂዎች በሰፈራችን እና በእድራችን ለሚፈጠሩ ችግሮች መፍትሄ በሚጠየቁ እከሌ የተባለው የታሪክ ምሁር፣ እከሌ የተባለው ፈላስፋ ፣ እከሌ የተባለው ታዋቂ ኢኮኖሚስት ፣ወዘተ እንዳለው የሚል አባባል ይቀናቸዋል፡፡ እገሌ እንዳለው የሚለውን ምሁራን ነን ባይ የአላዋቂዎች ንግግር ካነሳሁ አይቀር የሌኒን፣ ኤንግልስ እና ማርክስን ፍልስፍና እንደ ሃይማኖታዊ አስተምሮ በሃገራችን በሚከበርበት ወቅት የተባለ አንድ እውነተኛ ገጠመኝ ላስታውሳችሁ……
አንድ ወቅት የተፎካካሪ ፓርቲዎች እና የገዥው መንግስት ስራ አስፈጻሚዎች በአንድ የወረዳ ስብሰባ ላይ ተገናኙ፡፡ ስብሰባውን የጠራው እና የሚመራው ከመንግስት የተወከለው ሰው ነበር፡፡ በዚህ ስብሰባ የታደሙት ተፎካካሪዎቹ ትንሽ ፊደል የጠነቆሉ እና የማርክሲዝምን ፍልስፋን ጭልጥ አድርገው የተጋቱ ናቸው፡፡ በስብሰባው ላይ እድል አግኝተው ንግግር ያደረጉት ተፎካካሪዎች በሙሉ ንግግር ባደረጉ ቁጥር በረባ ባረባው ማርክስ እንዳለው ፣ ሌኒን እንዳለው ፣ ኤንግልስ እንዳለው ፣ በሶስተኛው ሶሻሊስት ጉባኤ ስታሊን እንዳለው …. እገሌ እንዳለው እያሉ ወጋቸውን ይጠርቃሉ፡፡
በቀደመው የመንግስት ዘመን ከገዢው መንግስት በኩል ስብሰባውን እንዲመራ የተቀመጠው ሰው ግን በቤተ ክህነት ትምህርት ቤት «ሀ፣ሁ» ፊደልን የቆጠረ እና በልምምድ የአንድን የስብሰባ ቃለ-ጉባኤን ከመጻፍ ውጭ ሌላ የፈረንጅ ፍልስፍና የማያውቅ ነበርና የዘመናዊ ትምህርት ፊደል የጠነቆሉት ተፎካካሪዎች በንግግራቸው መካከል እከሌ እንዳለው ፤እከሌ እንዳለው ሲሉ ሲሰማ «እንዳለው» የሚለው ቃል የሰው ስም ይመስለውና አቶ እንዳለው የተባሉት ሰው እንዴ በዚህ ልክ ለሀገራቸው የሚጨነቁ ልጆችን ወልደው እያለ ስለምን እውቅና አልተሰጣቸውም ? እያለ በውስጡ ያብሰለሰል ኖሮ ማጠቃለያ ንግግር ሲያደርግ ምን ቢል ጥሩ ነው? …«ልጅ ቢሮጥ አባቱን አይቀድም» አይደል የሚባለው፤ እናንተ ልጆች ስለሆናችሁ የልጆችን የእነማርክስን ፣ ሌኒን እና ስታሊን ንግግር የወጋችሁ ማጣቀሻ አደረጋችሁ፡፡ እኔ ግን የእነሱ አርአያ የሆኑትን አባታቸውን አቶ እንዳለውን ጠቃሚ ምክረ ሃሳቦች በማቅረብ የአብዮታችን ጉዞ ከየት ወደየት እንደሆነ በሚቀጥሉት ቀናት በሚኖሩን ስብሰባዎቻችን ላይ ይዤ እንደምመጣ ቃል እገባለሁ» ሲል የባለስልጣኑ ግብዝነት ያሳዛናቸው ወጣት ተማሪዎች አንዴ በሳቅ አዳራሹን አናጉት፡፡
የሳቁ ምክንያት ምንም ያልገባው ግብዙ አመራር ራሱን ከእነሱ በላይ ቆልሎ እናንተ ስላላችሁ ወይም ስላላላችሁ አይደለም! አቶ እንዳለው ለአብዮታዊ ጉዟችን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረጉ ቅን ሰው ስለሆኑ ቀድሞውኑም እርሳቸውን ለመሸለም እቅድ ይዘናል ሲል አሁንም አዳራሹ በሳቅ ተናጋ፡፡ ወደ ነበርኩበት ልመለስና አሁን ላይ ከታሪካዊ ጠላቶቻችን ጋር የረከሰ ጋብቻ በመፈጸም የሰፈራችን እና የእድራችን ሰላም ለማናጋት እንቅልፍ አጥተው እየሰሩ ለሚገኙ አካላት «ኢትልበሱ ልበሰ ሐራ (የማይገባችሁን ልብስ አትልበሱ)» የሚል ምክር መስጠት እፈልጋለሁ፡፡ ነገር ግን የማይገባችሁን እና የማታውቁትን ልብስ ካልለበስን ሞተን እንገኛለን የምትሉ ከሆነ ሰፈራችንን እና እድራችንን ለማጥፋት ብዙ የእውር ድንብር ጉዞ ታደርጉ ይሆናል እንጂ የእውር ድንብር ጉዟችሁ ልትወጡት ወደማትችሉት አዘቅት ውስጥ እንደሚጨምራቸው ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡
«ኢትኩኑ ከመ መደልዋን (እንደ ግብዞች አትሁኑ) » እንዳሉት አባቶቻችን ተማርን ያሉት ሰዎች በፈረንጅ አፍ ስላወጉ ብቻ በግብዝነት አትከተሏቸው ሲል ተሰብሳቢዎችን ገሰጸ፡፡ ከጀርባቸው ምን ተልዕኮ ሊኖር ይችላል ብላችሁ መርምሩ፡፡ ይህን ካደረጋችሁ ከሰሞኑ በሩጫ ያገኘውን ድል መድገም እንችላለን ሲል አስረዳ ፡፡
እለ መጥባሕተ ያነሱኡ በመጥባሕተ ይመውቱ (በሾተል የገደሉ በሾተል ይሞታሉ) እንዲሉ እመኑኝ እነኝህ እለ ከርሦሙ አምለኮሙ … እነሆድ አምላኩ የሆኑ ሰዎች በገንዘብ በተገዛ ሌላ የምስር እና መሰል የሰፈራችን እና የእድራችን ታሪካዊ ጠላቶች በገንዘብ ተገዝተው መገደላቸው የማይቀር መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡
በመጨሻም «ኩን ጠቢበ ለእድውከ (ለባላጋራህ ብልህ ሁንበት) እንዲሉ አባቶች፤ እነኝህ ጠላቶቻችን በብልሃት እና በጋራ ቆመን ልንመክታቸው ይገባል! መልዕክቴ ነው ብሎ ይልቃል አዲሴ ንግግሩን ሲጨርስ ተሰብሳቢው የሰማውን ምክር በአዎንታዊ የተቀበለ መሆኑን ለመግለጽ እጅግ በደመቀ ሁኔታ በማጨብጨብ ስብሰባውን ቋጩት፡፡
ሙሉቀን ታደገ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 14 ቀን 2014 ዓ.ም