ኢትዮጵያ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ድል ያጣጣመችበት፤በሌላ መልኩ ደግሞ በሰላም እጦት የተፈተነችበት ነበር ። በገጠማት ከባድ ፈተና የማንባቷን ያህል ለዜጎቿ የተስፋ ብርሀን የሚፈነጥቁ ተግባራትን ለማከናወንም ደፋ ቀና ስትልም ከርማለች። በእነዚህና በሌሎችም ሀገራዊና ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ የፓርላማ አባላት የሕዝብ ውክልናቸውን እንዴት ተወጡ? ምንስ አጎደሉ? ስንል ለዛሬው የወቅታዊ እንግዳ አድርገን የመረጥናቸው የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር የተከበሩ አቶ ተስፋዬ ቤልጅጌን ነው። ከእሳቸው ጋር የነበረንን ቆይታ እንደሚከተለው አጠናቅረነዋል።
አዲስ ዘመን፡- ባልተለመደ መልኩ በአዲስ ስብስብ ሥራውን የጀመረው ፓርላማ ምን አዲስ ባህል መተግበር ቻለ?
አቶ ተስፋዬ፡- ፓርላማው ሥራ የጀመረው መስከረም 24 ቀን 2014 ዓ.ም ነው። በአሁኑ ወቅት በዚህ ፓርላማ የሚገኙ አባላት በ2013 ዓ.ም በተካሄደው ጠቅላላ ምርጫ የሕዝብ ድምጽ ያገኙ ናቸው። በስድስተኛው ዙር የተካሄደውን ምርጫ ስንመለከት በጥቅሉ ከሁሉም ምርጫዎች በተነጻጻሪ በተሻለ የምርጫ አካሄድ አልፈው የመጡ የፓርላማ አባላት ያሉበት ነው። በዚህ ፓርላማ ውስጥ በትምህርት ዝግጅታቸው ብቁ ናቸው የሚባሉ፣በኅብረተሰቡ ከፍተኛ ተቀባይነት ያላቸው እንዲሁም የተለያየ የብቃትና የሙያ ስብጥር ያላቸውን ሰዎች የያዘ ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል። ምርጫው እንከን አልባ ነው ባይባልም እያደገ በሚሄድ የዴሞክራሲ ባህል ውስጥ የተመረጠ ፓርላማ ነው።
6ኛው ዙር አገራዊ ምርጫ ለዴሞክራሲ መሠረት የጣለ ምርጫ ነው ማለት ይቻላል። በዚህ ሂደት ፓርላማውን አባላቱ ተቀላቅለው ሥራ ጀምረዋል። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢትዮጵያን ሕዝብ የሚወክል ተቋም ነው። ስለዚህ ኢትዮጵያ አሁን በምትተዳደረው ሕገ መንግሥት መሠረት ትልቁ የፖለቲካ ስልጣን ያለው አካል ነው ማለት ነው።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አራት ዋና ዋና ተልዕኮዎች አሉት። አንደኛው ሕግ ማውጣት ነው። በሀገሪቱ ተግባራዊ የሚሆኑ ሕጎችን ማመንጨት ወይም ስልጣን በተሰጣቸው የተለያዩ አካላት የመነጨውን ሕግ መርምሮ ሥራ ላይ እንዲውል ማድረግ ነው። ስለዚህም ሕግ የሚመነጨው ከዚህ ቤት ነው። ሁለተኛው ደግሞ ክትትልና ቁጥጥር ማድረግ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የመንግሥት ሥርዓት ሶስት ዋና ዋና የመንግሥት አካላትን የያዘ ነው። ሕግ አስፈጻሚው፣ ሕግ አውጪውና ሕግ ተርጓሚው ነው። እነዚህ ሶስቱ አንዱ ሌላውን የሚከታተልበት ሕገ መንግስታዊ ሥርዓት ፤ የፓርላሜንታዊ ዴሞክራሲ የሚባለው እየተገነባ ነው ያለው።ስለዚህ ፓርላማው ሕግ አስፈጻሚውና ሕግ ተርጓሚው የወጣውን ሕግ በአግባቡ እየተተረጎመና እየተሠራ ነው ወይ?ኅብረተሰቡ የሚጠይቃቸው ጥያቄዎች ምላሽ እያገኙ ናቸው ወይ? ዴሞክራሲና መልካም አስተዳደር እየሰፈነ ነው ወይ? የሚለውን ነገር የመከታተል ስልጣን በሕገ መንግሥቱ የተሰጠው ለፓርላማ ነው። ስለዚህ ሁለተኛው የፓርላማው ተግባር የክትትልና የቁጥጥር ሥራ ነው።
ሶስተኛው የፓርላማው ሥራ በፓርላማ አማካይነት የሚሠራ የዴሞክራሲ ሥራ ነው። ይህ በአንድ በኩል የተለያዩ አህጉራዊና ዓለም አቀፍ ተቋማት ውስጥ ኢትዮጵያን ወክለው የፓርላማ አባላት ወይም አመራሮች የሚገኙበት ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ከተለያዩ ዓለም አቀፋዊ ተቋማት ውስጥ የፓርላማ አመራርና አባላት ሀገርን ወክለው በሚሳተፉበት የሚሠራው ሥራ የፓርላማው ዲፕሎማሲ ነው የሚባለው። አራተኛው የፓርላማ ተልዕኮ የሚባለው የሕዝብ ውክልና ነው። እያንዳንዱ የፓርላማው አባል ከተለያየ የኢትዮጵያ ክፍል ተመርጦ የመጣ ስለሆነ ከመራጩ ሕዝብ ዘንድ የሚነሱ ጥያቄዎችን እያወያዩ በአግባቡ ምላሽ አግኝተዋል፤ አላገኙም የሚለውን የሚከታተልበትና የሚያስፈጽሙበት በመሆኑ የውክልና ሥራ ይባላል።
ይህን ፓርላማ ለየት ከሚያደርገው አንዱ ካለፉት ሁለት ምርጫዎች የተፎካካሪ ፓርቲዎች ያሉበት በመሆኑ ነው። የኢትዮጵያ ፓርላማ አምስት አካላትን ይዟል። አንደኛ ብልጽግና ፣ ሁለተኛ አብን ፣ ሶስተኛ ኢዜማ፣ አራተኛ ጌህዴድ (ጌዴኦ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት) እና የቁህዴድ (የቁጫ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት) የወከሉ የምክር ቤት አባላትን ይዟል ። በጥቅሉ አምስት ተፎካካሪ ፓርቲዎች በጋራ የሚሠሩበት ተቋም ነው ማለት ይቻላል። ከእነዚህ በተጨማሪ አምስት በግል ተወዳድረው የገቡ የምክር ቤት አባላት አሉ።
አዲስ ዘመን፡- ፓርላማውን ለየት የሚያደርገው ታዲያ ምንድን ነው?
አቶ ተስፋዬ፡-መንግሥት ዴሞክራሲ እውን እንዲሆን የተለየ ትኩረት ሰጥቷል። በሀገራችን የዛሬ አራት ዓመት የለውጡ እንቅስቃሴ በተጀመረበት ጊዜ ልዩ ትኩረት ከተሰጣቸው ሥራዎች ውስጥ አንዱ ዴሞክራሲን በኢትዮጵያ እውን ማድረግ ነው። ዴሞክራሲ የሚገነባው የዴሞክራሲ ተቋማት በአግባቡ ሥራ ሲሠሩ ነው። ፓርላማው አንዱ የዴሞክራሲ ባህልና የዴሞክራሲ ሐሳብ የሚጎለብትበት አንድ ተቋም ነው። ከዚህ አኳያ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር በሚያለያዩን ጉዳዮች የየራሳችንን ሐሳብ ይዘን በሐሳብ ክርክር የመግጠም ባህላችን እንደተጠበቀ ሆኖ ሀገራዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ በጋራ እየተንቀሳቀስን ነው የቆየነው። ይህ ትልቅ ልምድ ነው። ለዚህ አንድ አብነት መጥቀስ እችላለሁ። ኢትዮጵያ በተገባደደው በ2014 በጀት ያሳለፈችው ሁኔታ ፈታኝ ነው። ሰው ሠራሽም ሆነ የተፈጥሮ ፈተናዎች የተገዳደሯት ዓመት ነበር። ለምሳሌ የኮሮና ወረርሽኝ፣ የአንበጣ መንጋና ጎርፍ ተጠቃሾች ናቸው። ከሁሉም በላይ ግን አሸባሪው ሕወሓት የከፈተብን ወረራ እና በሀገር ውስጥ በየቦታው ያሉ ባንዳዎች በየአካባቢው የፈጠሩት ግጭት በጣም አደገኛ የነበረ ነው።
በዚህ ሂደት የፓርላማ አባላት የየራሳችን የተለያየ አመለካከት መኖሩ እንደተጠበቀ ሆኖ በኢትዮጵያ ሰላም ጉዳይ ግን አብረን እየሠራን ነው። ይህ ትልቅ ጅምር ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል። ለምሳሌ በሕወሓት አማካይነት ጦርነት የታወጀብን ጊዜ በጦርነቱ ምክንያት የሚፈጠረውን ጉዳት ለመቀነስ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲጸድቅ ሲደረግ የፓርላማ አባላቱ አዋጁን ያጸደቁት በአንድ ድምጽ ነው። የተለያየ አመለካከት ያለን አባላት በፓርላማው ውስጥ ብንገኝም የሀገር ሰላም የጋራ ነው በሚል በጋራ ስንሠራ ቆይተናል። ገዥው ፓርቲ አሊያም ተፎካካሪ ፓርቲ ሳንባባል በኢትዮጵያ አንድነት፣ ሉዓላዊነት፣ በሕዝቦች ሰላምና ነጻነት ጉዳይ ላይ ፓርላማው በጋራ እየሠራ ነው የቆየው። ይህ ትልቅ የዴሞክራሲ ባህል ነው። ከሁሉም በላይ ደግሞ ሀገርን የማስቀደም ባህል የታየበት በመሆኑ መልካም ጅምር ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል። ለምሳሌ አሁን የጸጥታ ችግር፣ ጦርነት፣ መፈናቀል እንዲሁም ግጭት አለ። እነዚህ ጉዳዮች ተራ የሰፈር ጉዳይ አይደሉም። የውጭ ቋሚ ጠላቶች እና የውስጥ ባንዳዎች በጋራ ግንባር ፈጥረው ወይ ኢትዮጵያ በጣም ደካማ አገር እንድትሆን፣ ከተቻለም እንድትፈርስ እና ትናንሽ አገር እንድትሆን የሚሠሩ ኃይሎች የሚዘምቱብን ጉዳይ ነው።
ለዚህም በርካታ ምክንያቶች አሉ። አንደኛው በተፈጥሮ ሀብታችን ተጠቅመን እንዳንበለጽግ ለማድረግ ነው። ለዚህ ደግሞ አንዱ ማሳያ የህዳሴ ግድብ ነው። ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ኢትዮጵያ የተረጋጋች ሀገር ሆና ገንብታ ብታጠናቅቅ ልክ ተደጋግሞ እንደሚጠቀሰው እንደ ዓድዋ ድል ለአፍሪካም ለራሷም ትልቅ ትምህርት ነው የሚሆነው። ሁለተኛው እኛ ያለንበት ቀጣና በዓለም ላይ ስጉ ከሚባል ቀጣናዎች ውስጥ አንዱ ነው። ቀጣናው ቀይ ባህር ያለበት አካባቢ ነው፤ የአፍሪካ ቀንድ ነው። የበለጸጉ አገሮችም ሆኑ እየበለጸጉ ያሉ አገሮች ሁሉ ይህን ቀጣና ፈላጊ ናቸው። በዚህ ቀጣና ውስጥ ካሉ ትልቋና ተፈላጊዋ ሀገር ኢትዮጵያ ናት። የኢትዮጵያ ሕዝብም ወደ 120 ሚሊዮን የሚጠጋ እንደመሆኑ በአፍሪካ ሁለተኛዋ ትልቅ አገር እንድትሆን አድርጓታል። ከሁሉም በላይ ደግሞ በታሪክ ወደር የሌላት አገር ናት። በቅኝ ያልተገዛች አገር ከመሆኗ በተጨማሪ ኢትዮጵያ በራሱ የሚተማመን ሕዝብ ያላት አገር ናት። በዚህ ምክንያት ኢትዮጵያ ላይ የሚካሄደውን የሐሰት ፕሮፖጋንዳና ጦርነትን በመመከቱ ረገድ አንዱ ርብርብ ሲያደርግ የነበረው ፓርላማው ነው። ስለዚህ በፓርላማው ውስጥ የሚፈጠር የትኛውም መከፋፈል ወይም የትኛውም አይነት ቀውስ ሀገርን ሊጎዳ ስለሚችል ፓርላማው ላይ ከፍተኛ ዘመቻ ሲደረግበት ነበር። የኢትዮጵያ ፓርላማ ግን ሀገርን፣ ሕዝብን የኢትዮጵያ አንድነትና ሉዓላዊነት ለማሻገር በጋራ ቆሞ ይህን ታሪካዊ ተልዕኮ ሲወጣ የነበረ ስለሆነ ይህ ትልቅ ጉዳይ ነው ሊባል ይችላል። የተለያየ የፖለቲካ አመለካከት ያላቸው ፖለቲከኞች ወይም ሌሎች አካላት በአንድ ላይ ለሀገር በጋራ መሥራት በአገራችን ታሪክ የበለጠ መጎልበት ያለበት ስለሆነ ይህ ትልቅ ልምድ ነው። ከዚህ ውጭ በዚህ ፓርላማ መልካም ነበር በሚል ያየነው ጉዳይ በጋራ መሥራታችንን ነው።
በፓርላማው ውስጥ አባላቱ የሚሠሩባቸው ዋና ዋና የሚባሉ አደረጃጀቶች አሉ። ለምሳሌ አማካሪ ኮሚቴ እንዲሁም ቋሚ ኮሚቴ አለ። ሌሎች የተለያዩ እንቅስቃሴዎችም አሉ። እነዚህ ተግባራት ውስጥ ሁሉ ተፎካካሪዎች አሉበት። ተፎካካሪዎች ያሉበት ዋናው ምክንያት በምርጫው ያገኙት ድምጽ የግድ በአደረጃጀቶቹ ውስጥ እንዲገቡ የሚያደርግ ስለሆነ ብቻ አይደለም። መንግሥት ዴሞክራሲ እውን እንዲሆን ከተፎካካሪዎች ጋር በጋራ ለመሥራት ጠንካራ አቋም በመውሰዱ ነው። ስለዚህ ተፎካካሪ ፓርቲና ገዥው ፓርቲ በጋራ ዴሞክራሲ እውን እንዲሆን ተባብሮ የመሥራት ልምዱ በዚህ ዓመት ከተገኘ ምርጥ ልምድ አንዱ ነው። ለዚህ ደግሞ አንዱ መነሻ መንግሥት በለውጡ ጊዜ ለሕዝቡ ቃል የገባው ነው። እንደሚታወቀው በምርጫው ያላሽነፉ ሶስት የካቢኔ አባላት የአስፈጻሚው ካቢኔ ውስጥ ወሳኝ ኃይሎች ናቸው። ስለሆነም በለውጡ ዴሞክራሲን እንገነባለን በሚል መንግሥት ቃል የገባውን በተጨባጭ ሥራ ላይ ማዋል የጀመረበት ዓመት ስለሆነ መልካም ጅማሮ ነው ማለት ይቻላል።
አዲስ ዘመን፡- የተፎካካሪ ፓርቲ ተወካዮች በፓርላማ ውስጥ የሀሳብ ብዝኃነትን በመገንባት ሂደት ያላቸው ሚና እንዴት ይገለጻል?
አቶ ተስፋዬ፡- ያለፈውን የአንድ ዓመት ቆይታችንን ስንመለከት ጥቂት መስተካከል ያለባቸው ጉዳዮች እንደተጠበቁ ሆነው የተፎካካሪ ፓርቲ አመራርና አባላት በጋራ ለመሥራት ያላቸው ዝግጁነት እንደመንግሥት የምንመለከተው በመልካም ጎኑ ነው።
ለምሳሌ የእኛ አገር የፖለቲካ ባህል ያደገው በተዛባ መንገድ ነው። የፖለቲካ ባህላችን በኢትዮጵያ የተገነባው በሐሳብ የበላይነት በመተማመን አይደለም።የፖለቲካ ባህላችን በእልህ፣ በውጥረት፣ የእኔ ሐሳብ ካላሸነፈ ሞቼ እገኛለሁ ወይም እኛ በእነርሱ መቃብር ላይ እንለመልማለን፣ እነእከሌ ካልጠፉ እኛ መኖር አንችልም የሚል አይነት እጅግ ኋላቀር የሆነ ባህል ነው። እናም የፖለቲካው ባህል በሴራ የተሞላ ነው። ለምሳሌ ኢትዮጵያ ውስጥ በኋላቀር የፖለቲካ አካሄዳችን ምክንያት የእርስ በእርስ ጦርነት ሲካሄድ ቆይቷል። ይህ የፖለቲካ ባህል መቀየር አለበት ብሎ መንግሥት ያምናል።
ይሁንና ይህ ጉዳይ ለዘመናት የተገነባ ስለሆነ በቀላሉ መቀየር ከባድ ነው። ዴሞክራሲ ስለተፈለገ ብቻ አይገነባም። ለምሳሌ እኛ አገር ላይ ልንጨቃጨቅባቸው ያልተገቡ ጉዳዮች ነበሩ። እንደአለመታደል ሆኖ እነዚህ የምንጨቃጨቅባቸው ጉዳዮች የሚያጨቃጭቁን መሆን ያልነበረባቸው ናቸው። ለምሳሌ በእኛ አገር ጉዳይ ሰላምን፣ልማትንና የሕዝብን ለውጥ ፣ የኢትዮጵያ አንድነትን እንዲሁም የኢትዮጵያን የጋራ መለያ የሆኑ ምልክቶችን ፣ ሰንደቅ ዓላማንና ብሔራዊ በዓላት እና ሕገ መንግሥትን በተመለከተ በአብዛኛው የፖለቲካ አባላትና በአብዛኛው ልሒቃን መካከል የጋራ የሆነ የተቀራረበ ሐሳብ ሊኖር ይገባ ነበር። የረጅም ጊዜ ታሪክ ያላት ሀገርና ሕዝብ ወሳኝ በሆኑ ሀገራዊ ምልክቶች ላይ የጋራ
መግባባት የለም። ለምን ሲባል ፖለቲካችን የተሞላው በእልህ ስለሆነ ነው። ፖለቲካችን አሸናፊ ሲሆን ሌላውን አጥፍቶ በመነሳት ነው። በመጠፋፋት ላይ እና በአብዮት አዙሪት ውስጥ የቆየ ነው።
አሁን እንደ አገር የተለኮሰው ለውጥ ከዚህ አዙሪት ማውጣት ነው። ትናንት ሁሉ ነገር መጥፎ አልነበረም፤ እንዲሁም ሁሉም ደግሞ ወርቅ አልነበረም። ዛሬ ላይ ያለ ሰው በትናንት አይጨቃጨቅም። ከትናንት መውሰድ ያለብን ትምህርት ነው። ለምሳሌ ኢትዮጵያ ውስጥ አንዱ የጸብና የግጭት መንስዔ የሆነው ከመቶ ዓመት በፊት የተሠራ ታሪክ ነው። የዛሬ መቶ ዓመት ታሪኩን የፈጸሙ ሰዎች የሉም። አገር ግን ይቀጥላል። ስለዚህ የሰለጠነ ኅብረተሰብ ማድረግ ያለበት ከትናንት ትምህርት መውሰድ ነው። ትናንት የነበረው መልካም ነገር ደግሞ እንዳለ ለዛ አይደገምም። ነገር ግን ትናንት የነበረውን መልካም ነገር ከዛው ጋር በማጣጣም እንዲጎለብት ማድረግ ይቻላል። ትናንት የነበረ ደካማ ነገር ካለ ደግሞ ያንን በመተው ዛሬ ላይ ሌላ መልካም ታሪክ መሥራት ነው። በታሪክ ወደመጣላትና መጨቃጨቅ አይሄድም ። በዚህ ሀገር ሁሉም ነገር ፖለቲካ ነው የሚሆነው። ታሪኩም ፖለቲካ ነው። ነገር ግን ታሪክ ፖለቲካ መሆን አይችልም። ታሪክ ታሪክ ነው። ወይ ሆኗል፤ ወይ አልሆነም። ታሪክ አርትዖት አይሠራበትም። ከታሪክ ትምህርት ብቻ ነው የሚወሰደው። ነገር ግን ከመቶ ዓመት በፊት የተሠራን ታሪክ መነሻ አድርገን እንጨቃጨቃለን። ስለዚህ ከዚህ አኳያ ይህን ችግር ይፈታል ተብሎ በመንግሥት ደረጃ ታምኖ አንድ የተቋቋመው የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ነው። ስለዚህ በአገራችን ውስጥ ያለው ይህ የፖለቲካ ባህል በአንዴ አይቀየርም። ነገር ግን በምክር ቤቱ አሁን እየታየ ያለው የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ አባላት በጋራ የምንሠራው ፕሮግራም በተመለከተ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የመግባባት፣ የመቀራረብና የመመካከር ለዚህ ጉዳይ ደግሞ ከራሳቸው ከተፎካካሪ ፓርቲዎች የተሻሉ ሐሳቦች የመምጣት እና የተሻለ ሐሳብ የምክር ቤቱ የመሆን ሁኔታ ነው እየታየ ያለው።
ለአብነት ያህል በተለያየ ጊዜያት እንደምክር ቤት የተወያየንባቸውና በጋራ አቋም የወሰድንባቸው በርካታ ነገሮች አሉ። ስለዚህም በተፎካካሪ ፓርቲዎችም አገር ለመገንባት የተጀመረው ጥረት በመልካም ጎኑ የሚታይ ነው። ነገር ግን እንደግለሰብ አንዳንድ ጊዜ የውስጥ ሐሳባቸውን የመግለጽ ሁኔታ ይታያል። ትልቁን ሀገራዊ ምስል ከማየት ይልቅ በወቅታዊ ሞቅታዎች ውስጥ የመግባት ነገሮች ይኖራሉ። ይሁንና በቀጣይ እየተስተካከለ ይሄዳል የሚል እምነት አለኝ።
አዲስ ዘመን፡- አንዳንድ የምክር ቤት አባላት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሚያቀርቧቸው ጥያቄዎች አንጻር ሲታዩ ችግሮችን የመከታተልና የማጣራት ባህል እምብዛም አይታይባቸውም፤ ይልቁኑ ሥራውን ወደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመግፋት ሁኔታ ሲንጸባረቅ ይስተዋላልና ይህ ሥራቸውን ጎዶሎ አያደርገውም?
አቶ ተስፋዬ፡- የክትትልና ቁጥጥር ሥራው ዋና ዋና የሚባሉ ዓላማዎች አሉት። ማዕከል ከሚያደርጋቸው አንዱ ምክር ቤቱ በቋሚ ኮሚቴው በኩል የሚከታተለው እያንዳንዱ ተቋም በሕግና በአሠራር መሠረት ነው እየተንቀሳቀሰ ያለው? ወይስ ከሕግ ውጪ እየሄደ ነው ? የሚለውን ያያል። ሁለተኛ ደግሞ መንግሥት ለሕዝብ ቃል የገባቸውን ጉዳዮች በአግባቡ እየሠራ ነው ? ምክንያቱም ለምሳሌ ፓርቲዎች መንግሥት ሆነው መንግሥትን ከመመሥረታቸው በፊት በምርጫ ቅስቀሳ ጊዜ ቃል ይገባሉ። መንግሥት ከሆኑ በኋላ ቃል የገቡበት ጉዳይ እየተሠራ ስለመሆኑ ክትትል የሚደረገው በቋሚ ኮሚቴዎች አማካይነት ነው። ሶስተኛው ጉዳይ የመንግሥት ሀብትና ንብረት ከሙስና እና ብልሹ አሠራር በጸዳ ሁኔታ እየሄደ ነው ወይ? የሚለውን ይቆጣጠራል። በአጠቃላይ ለሕዝብ የሚሰጠው አገልግሎት፣ ሀገርን ለመገንባት እየተካሄዱ ያሉ ሥራዎች እንዴት እየተካሄዱ ነው የሚሉትን ነው የሚከታተለው። ከዚህ አኳያ የክትትልና የቁጥጥር ሥራችን በጣም ጥሩ ጅምር ላይ ነው ።
አንቺ ወዳነሳሽው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚቀርቡ ጥያቄዎችን በተመለከተ ሰዎች የሚጠይቁት በተረዱትና በገባቸው ልክ ነው። አስተውለሽ እንደሆነ ይህ ዓመት ደግሞ አብዛኛው በሚያስብል ሁኔታ ሀገራችንን ፈተና የተጋረጠባት ዓመት ሆኖ ነው ያለፈው። ከዚህ የተነሳ ሰው አንዳንዴ ከስሜቱ ተነስቶ ጥያቄ ሊጠይቅ ይችላል። አንዳንዴ ደግሞ ኢትዮጵያን የሚመጥን ሀገራዊ ምክር ቤት ውስጥ ሆኖ የአካባቢውና የሰፈሩ ጉዳይ አሸንፎት ችግር ይዞ ሊመጣ ይችላል። የምክር ቤት አባላት የመናገር ነጻነት ስላላቸው ባላቸው አረዳድና ባላቸው ግንዛቤ ልክ ጥያቄያቸውን ይጠይቃሉ። እንዲያም ሆኖ መልካም ጅምር አለ ብለን ነው የወሰድነው። ነገር ግን መሻሻል ያለባቸው ነገሮች አሉ፤ አንዳንዴ ከጥያቄ አጠያየቅ ኢትዮጵያ የሚወክል ፓርላማ ውስጥ ከመሆንም አኳያ መሻሻል ያለባቸው ነገሮች አሉ።
አዲስ ዘመን፡- የክልልና የፌደራል መንግሥት ጉዳዮችን ያለመለየት ችግርም በአንዳንድ የምክር ቤት አባላት ላይ ይታያል፤ በዚህ ዙሪያስ ምን ይላሉ?
አቶ ተስፋዬ፡- ምክር ቤት የሚገቡ አባላት ተጠሪነታቸው ለሕዝባቸው፣ ለሕገ መንግሥትና ለሕሊናቸው እንደሆነ ሕገ መንግሥት ላይ ተመላክቷል። በዚህ ምክንያት ሀገራዊ የሆነውን ጉዳይ እና ታች ያለውን ጉዳይ የማመዛዘን ነገር ወደሰፈሩ ሲሄድ ከሚያየው ችግር የተነሳ ላያስተውለው ይችላል። ለምሳሌ አባሉ ወደአካባቢው ሲሄድ ጎርፍ ጉዳት ሲያደርስ ሊመለከት ይችላል። ወይ ደግሞ መኪና የሚያስኬድ መንገድ አለመኖሩን ያያል። አሊያም ደግሞ በአካባቢው የሚገኝ አንድ አመራር ቤተሰቡን እየበደለ መሆኑን ሊያስተውል ይችላል። በዚህም ሊረበሽ ይችላል። ከዚህም የተነሳ ስሜታዊ ሊሆን ይችላል። ይህ የረበሸውን ጉዳይ ከሚመለከተው አካል ጋር እዛው ከመወያየት ይልቅ በተገኘው አጋጣሚና መድረክ ሊያነሳው ይችላል።
እንደገለጽኩልሽ ፓርላማው ዴሞክራሲን የምንለማመድበት ቤት ነው። በሐሳብ ዙሪያም ክርክርና ውይይት ብሎም የሐሳብ ፍጭት ማድረግን የምንለማመድበት ነው። ይህ ደግሞ አመለካከትም፤ ክህሎትም ነው። ስለዚህ ወደከፍታ የሚወጣው በአንድ ጊዜ አይደለም። በትምህርት ደረጃው በጣም ብቁ የሆነ ሰው በፓርላማ ሥራ ላይ በጣም ብቁ ላይሆን ይችላል። በአንድ ዘርፍ ላይ በጣም የተሳካለት ሰው በፓርላማ የክርክር መድረክ ላይ ደግሞ ብዙ ላይሆንለት ይችላል። ስለዚህ ይህን መነሻ አድርገን የፓርላማ አባላት አቅማቸውን የሚያጎለብቱበት ተከታታይ ስልጠናዎችን ስንሰጥ ቆይተናል። በክልልም ከክልል በታች ባሉ የአስተዳደርና በፌዴራል መንግሥት ደረጃ የሚሠሩ ሥራዎች ምንድን ናቸው ከሚለው ተነስቶ የተለያዩ ስልጠናዎችን ሰጥተናል። ስለዚህ ፓርላማው በኢትዮጵያ ትልቁ የስልጣን ቁንጮ ነው ስለተባለ ሁሉንም ነገር ያደርጋል ማለት አይደለም።ሥራ የሚሠራው በሕገ መንግሥት ነው። በፌዴራል ደረጃ የሚሠሩ ሥራዎችን የኢፌዴሪ ምክር ቤት፣በክልል ደረጃ የሚሠሩ ሥራዎችን ደግሞ የክልል፣ የወረዳ ብሎም የቀበሌ ምክር ቤቶችም አሉ። ስለሆነም የክልል ምክር ቤቶችም በክልል የሚሠሩ ሥራዎቻቸውን ይከታተላሉ። እኛ ሀገር ተቋም መገንባት ላይ ገና ስለሆንን ሁሉንም ነገር ፌዴራል እንደሚሠራ ተደርገው ይታያሉ። ተቋም እየገነባን ስንሄድ እያንዳንዱ ተቋም ደግሞ የየራሱን ሥራ ሲሠራ ሕዝቡም በዚህ ዙሪያ በሚገባ ግንዛቤ ሲጨብጥ የየተቋሙ አባላትም ስለተቋማቸው የበለጠ ሲረዱ እየተሻሻለ ይሄዳል። የፓርላማ አባላት አቅማቸውን ሊያጎለብት የሚያስችላቸው ስልጠናዎች እየተሰጣቸው ነው።
አዲስ ዘመን፡- ጊዜው የለውጥ ከመሆኑ አንጻር በሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች ዙሪያ ስሜታዊነት በስፋት ይታያል፤ ይህ ወቅቱን በፅናት ከመሻገር አንጻር ሊያመጣ የሚችለው ክፍተት እንዴት ይታያል?
አቶ ተስፋዬ፡-በመጀመሪያ ፓርላማው ከዚህ አኳያ ያለው መልካም ነገሩ ይበልጣል። በዚህ እየተጠናቀቀ ባለው በጀት ዓመት ብዙ ሰው ሠራሽና ተፈጥሯዊ ተግዳሮቶች አጋጥመው እንደነበር አስቀድሜ ጠቅሻለሁ። ከሰው ሠራሽ ችግሮች መካከል በአሸባሪው ሕወሓት የተከፈተብን ጦርነት ተጠቃሽ ነው።በተጨማሪም በሀገር ውስጥ ካሉ አካላት ጋር የውጭ ኃይሎች ሲሠሩም ቆይተዋል። ይህ ደግሞ ባንዳዎች የሚፈጥሩት ችግር ነው። ለምሳሌ ኢትዮጵያ ውስጥ ሀገርን ችግር ውስጥ ለማስገባት ታስበው እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች ሁለት ዋና ዋና ነገሮችን በመጠቀም ነው እንቅስቃሴ የሚደረግባቸው።
አንደኛው ብሔርን ነው።ኢትዮጵያ የብሔር ብሔረሰቦች አገር ናት። በብሔር ብሔረሰቦች መካከል ግጭት፣ ልዩነት ብሎም አለመተማመን ከተፈጠረ ኢትዮጵያ በቀላሉ እናፈርሳለን ብለው የሚያልሙ አካላት አሉ። አንዱ ለምሳሌ ኢትዮጵያ ውስጥ ግጭትም፣ መፈናቀልም ሆነ ሞትም በመፍጠር ከፖለቲካ ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸውን ንጹሓንን በመግደል ለማትረፍ የሚቃጣቸው አሉ። በተለይ ፍላጎታቸው ደግሞ አንዱ ብሔር በሌላው ላይ እንዲነሳ ነው። ሁለተኛው ስልታቸው ሃይማኖት ነው። ይህ የፓርላማ አባል ደግሞ ብሔርም ሃይማኖትም አለው። ስለዚህ በተለያዩ አካላት ብቻ ሳይሆን በብሔር እንዲሁም በሃይማኖት አማካይነት አንዱን ሌላው ላይ የማነሳሳትና እርስ በእርስ ግጭት እንዲኖር የሚሠሩ አካላት በመኖራቸው የፓርላማ አባላት ከዚህ አኳያ ጫና ውስጥ እንዲገቡ በብዙ መልኩ ይሞከርባቸዋል።
ነገር ግን ኢትዮጵያን የሚወክል ፓርላማ እንደመሆኑ መጠን ስሜት ውስጥ ሊያስገቡ የሚችሉ ነገሮች ቢከሰቱም እጅግ አብዛኛው የፓርላማ አባል ኢትዮጵያንና የኢትዮጵያን ሰላም፣ ሉዓላዊነትና ነጻነት እንዲጠበቅ አስቀድመው በጋራ ሲቆሙ ነው የታየው። ይህ በመልካም ጎኑ መታየት አለበት። በዛው ልክ ደግሞ ጥቂት ሆነው የተለያየ ስሜት ውስጥ የሚገቡ አሉ። አንዳንዴም ኢትዮጵያውያኑን የሚወክሉ የታላቁ ምክር አባላት ሆነው በማኅበራዊ ትስስር ገጽ ምክር ቤቱን በማይመጠን መልኩ የሚንቀሳቀሱ፣ የሚከሰቱ የየዕለት ትኩሳት ወዲያውኑ የሚነካቸው የምክር ቤቱ አባላት አሉ፤ ቢሆንም አጠቃላይ ምክር ቤቱን ግን አይገልጸውም። ከዚህ በመነሳት የምክር ቤታችን አቅጣጫ የሚሆነው በጉዳዩ ዙሪያ በመወያየትና ክፍተት ካለም አቅማቸውን መገንባት ነው። ከዚህ አልፎ የሚሄድ ከሆነ ግን ምክር ቤቱ በጣም የተደራጀ ምክር ቤት ስለሆነ የራሱ የሆነ የአሠራር ሥርዓት አለውና የኢትዮጵያን ሕዝብ በማይመጥን መንገድ የሚንቀሳቀስ ሰው ተጠያቂ ወደሚሆንበት ሥርዓት መሄድ የሚያስችል ነው።
በድምሩ ግን አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ እየተፈጠሩ ያሉ ቀውሶች ኢትዮጵያውያን በአንድነት እንዳይቆም ለማድረግ የሚሠራ ሥራ ከመሆኑ ጎን ለጎን ልክ እንደዚህ ሁሉ የፓርላማ አባላት በአንድነት እንዳይቆሙ ጥረት ተደርጎ ነበር። በአንድነት በመቆም ኢትዮጵያን ለማሻገር ያላቸው ቁርጠኝነት የፓርላማ አባሉ ነው። አንዳንዴ አንዳንድ ሚዲያዎች ፓርላማው የማይረባ ነው፤ ይህ ሁሉ ሲሆን ዝም ብሎ የሚመለከት ነው፤ ዝም ብሎ እጁን ብቻ የሚያወጣ ነው፤ ምንም የማያስብ ነው በሚል ጫና ለመፍጠር ይጥራሉ። ነገር ግን በሚያስገርም ሁኔታ በፓርላማው ውስጥ ያሉ ተመራጮች በትምህርት ዝግጅታቸው፣ በሥራ ልምዳቸው፣ በተሠማሩበት የሥራ መስክ ስኬታማ በመሆን እጅግ በጣም የተሳካላቸው አባላት ስለሆኑ ማመዛዘን፣ ማየት ብሎም ለአገር የመቆም ኃላፊነታቸውን በጋራ የሚወጡ ናቸው ማለት ይቻላል። በመንግሥት ደረጃም እየተወሰደ ያለው በዚህ አግባብ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ለፓርላማው ተጠሪ የሆኑ ተቋማት በፓርላማው ሪፖርት ሲያቀርቡ፣ በመስክ ጉብኝትም የተሰጣቸውን ግብረመልስ ምን ያህል ይተገብራሉ ?
አቶ ተስፋዬ፡- በጣም ጥሩ ጥያቄ ነው፤ በመጀመሪያ ደረጃ የክትትል፣ የቁጥጥርና የድጋፍ ሥራችን በድምሩ ውጤታማ ነው። ውጤታማ ነው የሚያሰኘው አንዱ ቋሚ ኮሚቴዎች ሄደው ተከታትለው ጉድለት የሚባሉ ነገሮችን ለይተው መስተካከል የሚገቡ ጉዳዮች ላይ አቅጣጫ አስቀምጠው የተመለሱባቸው ጉዳዮች ተሻሽለውና እድገት አሳይተው ተስተውለዋል። አንዱ የዚህ ማሳያ ፓርላማው በቋሚ ኮሚቴዎች የሚከታተሏቸውን ተቋማት ከተከታተለ በኋላ ችግርና ጉድለት አለባችሁ ተብለው ለተለዩ ተቋማት ግብረ መልስ ከተሰጠ በኋላ ችግሩና ጉድለቱ ተስተካክሎ መታየቱ ነው።
እንደሚታወቀው ዓመቱ ጦርነት ውስጥ የቆየንበት ነው። ኢትዮጵያ በብዙ መልክ በጣም ጠንካራ ሀገር ናት። ጦርነትም ግጭትም ውስጥ ሆኗ ተቋማት ሥራቸውን በአግባቡ እየተወጡ ነበር። ፈተናን ተቋቁሞ ውጤታማ መሆን የምንችል ሀገር መሆናችንን ያሳየንበት ዓመት ነበር። እነዚህ ውስጥ አንዱ ፓርላማው ነው። የፓርላማው ጥንካሬ የታየበት ነው። በጦርነቱ ወቅት ከፓርላማው እኔን ጨምሮ በርካቶችም ዘምተው ነበር። ኢትየጵያ ችግር እየገጠማትም የልማቱን ሥራ በአግባቡ መሥራት እንደምትችል ያሳየችበት ዓመት ነው።
የምክር ቤት አባላት በዓመት ሁለት ጊዜ መጋቢት ወር እና ክረምት ላይ ከመረጣቸው ሕዝብ ጋር ይገናኛሉ። መጋቢት ውስጥ ሄደው የመረጣቸውን ሕዝብ አወያይተው መጥተዋል። አወያይተው ከመጡ በኋላ በፌዴራል መንግሥት የሚሠሩ እንደመሠረተ ልማትና መሰል ሥራዎችን በተመለከተ በመለየት ለእያንዳንዱ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤትና ተጠሪ ተቋማቱ በኩል በፍጥነት ምላሽ ተሰጥቶባቸው ለምክር ቤቱ ሪፖርት እንዲያቀርቡ አስተላልፈን ነበር። እነርሱም ሪፖርት አቅርበው የነበረ ሲሆን በዚህ ሂደትም በጣም ትልቅ ለውጥ መጥቷል። ለምሳሌ አንዱ የፕሮጀክቶች አፈጻጸም ነው። በጦርነት ውስጥ ሆነን አዳዲስ የሆኑና የተጀመሩ ፕሮጀክቶች በአግባቡ መሠራታቸው አንዱ የምክር ቤቱ የክትትልና የድጋፍ ሥራ አካል ነው። የመንገድ፣ የመስኖ፤ የመጠጥ ውሃ ፣ የመብራትም ሆነ የቴሌኮሙኒኬሽን ሥራ ተጠቃሽ ነው። የለውጡ መንግሥት መገለጫ ነው የተባለው ዋና የሆነው ጉዳይ የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን ማጠናቀቅ እንዲሁም አዳዲስ መጀመርና በተባለው ጊዜና በታሰበው ጥራትና ዋጋ ማጠናቀቅ ነው። በፓርላማው ደረጃ ደግሞ በፕሮጀክት አካባቢ ተጓቷል ተብለው የመጡ ችግሮች ላይ ከፍተኛ መሻሻል እየተደረገ መሆኑን ማስተዋል ተችሏል።ስለዚህ ምክር ቤቱ ከሚከታተላቸው ተቋማት አንጻር ምክር ቤቱ በሚሰጠው አቅጣጫ መሠረት አፈጻጸማቸውን የማሻሻል ልምድን ስንመለከት በከፍተኛ ደረጃ እየተሻሻለ ነው። እንዲህ ሲባል ግን ክፍተቶች የሉም ማለት አይደለም። በቀጣይ የተቀመጠው አቅጣጫ ግን ተቋማትን በየደረጃቸው በመለየት ተጠያቂነትን ማስፈን ነው።
አዲስ ዘመን፡- ለቀና ትብብርዎ ከልብ አመሰግናለሁ።
አቶ ተስፋዬ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
አስቴር ኤልያስ