የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ‹‹ስለኢትዮጵያ›› በሚል ርዕስ በተለያዩ ከተሞች በተለያዩ ሀገራዊ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የሚመለከታቸውን አካላት እያወያየ ይገኛል ። በጅግጅጋ፣ በሀረር፣ በድሬዳዋ፣ በሀዋሳ፣ በአርባምንጭና ጅማ ከተሞች በተካሄዱ መድረኮችም በሰፋፊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የመነሻ ጽሁፎች እየቀረቡ በተሳታፊዎች ውይይቶች ተደርገዋል ። በዚህም ችግሮች ተነስተው መፍትሄዎች ተመላክተዋል፤ ተሞክሮዎችም ተጠቁመዋል ።
የውይይት መድረኮቹ አንድ ሁለት እያሉ ስድስተኛው ላይ ደርሰዋል ። ስድስተኛው የውይይት መድረክም ሰሞኑን በጅማ ከተማ ተካሂዷል ። የጅማው መድረክ ርዕሰ ጉዳይ ደግሞ ‹‹ብሩህ ሃሳብ፤ ሥራና ክሕሎት ስለ ኢትዮጵያ›› የሚል ነበር ። በመድረኩም ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና የተለያዩ አካላት ተገኝተዋል ። ከሀገራችን አብይ አጀንዳዎች መካከል አንዱ በሆነው የስራ እድል ፈጠራ ላይ በሚመለከታቸው አካላት የመነሻ ጽሁፎች አቅርበዋል፤ ይህን ተከትሎም፤ በተሳታፊዎች ሰፊ ውይይት ተካሂዷል።
በመድረኩ ከቀሩበት የመወያያ ጽሁፎች መካከል የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አንዳለማው መኮንን የቀረበው ጽሁፍ አንዱ ነው ። በዛሬው ንግድና ግብይት አምዳችንም ይህን የውይይት መነሻ ጽሁፍና እሱን ተከትሎ ለተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች በአቶ አንዳለማው መኮንን የተሰጡ ምላሾችንና ማብራሪያዎችን ይዘን ቀርበናል ።
አቶ እንዳለማው በጽሁፋቸው በአገሪቱ የንግድ ሥርዓት ዙሪያ፤ እየተከናወኑ ስላሉ ተስፋ ሰጪ ሥራዎችና በንግዱ ዘርፍ እየታዩ ስላሉ ተግዳሮቶችና በቀጣይ መወሰድ ስላለባቸውና ስለሚወሰዱ እርምጃዎች ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል ። በተለይ በወጪ እና ገቢ ንግድ መካከል እየታየ ስላለው ሰፊ ልዩነትና በቀጣይ መከናወን ስለሚኖርባቸው ተግባሮች ጠቁመዋል ።
ኢትዮጵያ በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ መሆን እንድትችል በማንኛውም ዘርፍ በሚገባ ታስቦ መሰራት ይኖርበታል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው ፣ በተለይም የአገር ውስጥ ምርቶችን በብዛት፣ በጥራትና በአይነት በማምረት እንዲሁም እሴት በመጨመርና ከተለመደው አሰራር ወጣ በማለት በዓለም የገበያ ሰንሰለት ውስጥ መግባት የግድ መሆኑን በማንሳት ለዛም መዘጋጀት እንደሚያስፈልግ ያብራራሉ ።
ሥርዓት ጠብቆ ለሚሰራው ሰው ንግድ ትልቅ ሥራ እንደሆነና አዋጭ እንደሆነም ጭምር አስታውቀው፣ አንድ አገር የተፈራና የተከበረ እንዲሆን ጠንካራ መከላከያ፣ ጠንካራ መከላከያ ደግሞ ጠንካራ ኢኮኖሚን እንደሚፈልጉ አብራርተዋል ። ጠንካራ ኢኮኖሚም እንዲሁ ዜጎች በሰላም ወጥተው ገብተው ሠርተው ግብር ገብረው የሚኖሩበትን የተደላደለ ሥርዓት ይፈልጋል፤ የተደላደለ የንግድ ስርዓትን ለመፍጠርም ጠንካራ መንግሥት ይፈልጋል፤ ጠንካራ መንግሥትም እንዲሁ ጠንካራ ፖሊሲን ይፈልጋል ሲሉ ሚኒስትር ዴኤታው ይገልጻሉ ።
ስለንግድ አሰራሩ ተግዳሮቶች ሲያብራሩም፤ ከንግድ አንጻር እንደ አገር ጠንካራ የንግድ ፖሊሲ አለመኖሩ አንዱ ችግር መሆኑን ጠቅሰዋል ። የንግድ ህጉ ላለፉት 60 ዓመታት ሶስት የተለያየ ባህሪ ያላቸውን መንግሥታት አስተናግዷል ሲሉ አስታውቀዋል ። ቴክኖሎጂ ባደገ ቁጥር ብዙ የተለወጡ ነገሮች ቢኖሩም ውስጡን መለወጥ ግን አልተቻለም ያሉት አቶ አንዳለማው፣ ዜጎች በአነስተኛ፣ በመካከለኛና በከፍተኛ ደረጃ ንግድን በቀላሉ ጀምረው በቀላሉ የማይወጡበትና በሩቁ የሚፈራ ሆኖ መቆየቱን ነው ያብራሩት ።
እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ገለጻ፤ የትኛውም ሥራ ቢዝነስ ነው፤ ንግድ ነው ። ስለዚህ ንግድ ማንኛውም ሰው በቀላሉ ገብቶበት በቀላሉ ስርዓት ይዞ ሊወጣበት የሚችል አሰራርን ይፈልጋል ። ለዚህም የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር በአዲሱ ሪፎርም ጠንካራ ፖሊሲና ጠንካራ ህግ የሚያስፈልግ መሆኑን በማመን ስርዓቱን በመፈተሸ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል ።
የንግድ ፖሊሲን በተመለከተ ንግድ የሚመራበት ፖሊሲ ኢትዮጵያ ኖሯት እንደማያውቅ ጠቅሰው፣ አዲስ የንግድ ፓሊሲ ተረቅቆ በአሁኑ ወቅት የመጨረሻው ረቂቅ ተዘጋጅቷል ሲሉ ይጠቁማሉ ። ይህም እንደ አገር በንግድ ስርዓት ውስጥ ያሉ ቁልፍ ችግሮች ምንድናቸው
የሚሉ ጥያቄዎችን መመለስ የሚያስችል መሆኑንም ነው ያመለከቱት ። ፖሊሲው የተለዩትን ቁልፍ ችግሮች ሊፈታ የሚችል መሆኑንም ጠቁመው፣ ይህን ጠንካራ የንግድ ፖሊሲ ተግባራዊ ማድረግ ከተቻለ በንግድ ስርዓቱ ውስጥ የሚታየውን ምስቅልቅልና ወጣ ገባ አሰራር መፍታት ይቻላል ብለዋል ።
የሀገረቱን የወጪና ገቢ የንግድ ሚዛን ክፍተትን በተመለከተም ሲያብራሩ እንደ ዜጋ እጅግ በጣም የሚያሳስብ መሆኑን ነው የጠቆሙት ። 18 ቢሊዮን የሚደርስ የአሜሪካ ዶላር ለገቢ ንግድ እንደሚወጣ ጠቅሰው፣ በአንጻሩ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ባለፈው በጀት ዓመት ከወጪ ንግድ 3 ነጥብ ስድስት ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ማስገባት መቻሉን ይገልጻሉ ። 15 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር የንግድ ልዩነት እየታየ መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህ ምን ማለት ነው ሲሉም ይጠይቃሉ ። እዚህ ላይ አርቆ ማሰብና መስራት የሚችል የሰው ኃይል ያስፈልገናል ይላሉ ።
እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ማብራሪያ፤ አገሪቷ አሁን ባለችበት ውስብስብ ችግር ውስጥ ሆና በተያዘው በጀት ዓመት በወጪ ንግድ/ ኤክስፓርት/ የሚገኘውን ገቢ አራት ነጥብ አንድ ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ማድረስ ተችሏል ። ስለዚህ ጠንክሮ መሥራት ከተቻለ እና ጠንካራ ተቋማት ከተገነቡ ከዚህም በላይ ውጤት ማስመዝገብ ይቻላል ። የተለመደውን ዓይነት ምርት ይዞ ወደ ገበያ በመውጣት አሁን እየታየ ያለውን የንግድ ሚዛን ጉድለት መሙላት አይቻልም ። ለእዚህም የኤክስፓርት ገቢውን የሚያሳድግ የኤክስፖርት ስትራቴጂው እየተዘጋጀ ነው ። በውስጡ የተለያዩ ጉዳዮች የተካተቱበት የስትራቴጂው ረቂቅ ላለፉት አስር ወራት ሲዘጋጅ ቆይቶ አሁን የመጨረሻው ሰነድ ላይ ደርሷል ።
አሁን ያለው ሁለት አይነት ምርት ሲሆን አንደኛው ከግብርና ቀጥታ ተመርቶ ወደ ውጭ ገበያ የሚቀርብና አገሪቷ ጥገኛ ሆና የኖረችበት የወጪ ንግድ ነው ። ሁለተኛው ደግሞ በማምረቻ ተቋማት በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ እሴት ተጨምሮበት የሚወጣ ምርት ነው ። እሴት የሚጨመርበትን ይህን ምርት አሁን ካለው በበለጠ በአይነት ማበራከት ያስፈልጋል ። ስለዚህ የተዘጋጀው የንግድ ሥርዓት ፖሊሲና ስትራቴጂ የተለያዩ ምርቶችን እሴት ጨምሮ ወደ ውጭ ገበያ መላክን አንዱና ወሳኝ ጉዳዩ ያደረገ ነው ።
ሁለተኛው የገበያ መዳረሻዎችን ማስፋት ነው አሁን ያሉት ነባር አገሮች እንዳሉ ሆነው፣ የገበያ መዳረሻ አገራትን ማበራከት ያስፈልጋል ። ባለፈው አመት በጦርነት ወቅት አሜሪካ ኢትዮጵያን ከአግዋ የገበያ ዕድል እንድትሰረዝ ማድረጓ ይታወሳል ። ይህ ምን ማለት እንደሆነ ይታወቃል ። አግዋ ደሃ አገራት የማምረት አቅማቸው ደካማ ስለሆነ ጥራት በሚፈለገው መንገድና መጠን ተደራሽ ማድረግ ስለማይቻሉ ከታሪፍ ነጻ ማቅረብ ቢችሉ የተሻለ ያመርቱ ይሆናል በሚል የተዘረጋ የንግድ ስርዓት ነው ።
የማምረት አቅማችንን ማሳደግ ከተቻለና ተቀባይ አገራት በሚፈልጉት የጥራት ደረጃ ጥራቱን አሟልቶ ማቅረብ ከተቻለ አግዋን የመሰለ የገበያ ዕድል መፈለግ አይጠበቅም ። የትኛውም ገበያ ውስጥ ዘልቆ መግባትና ተደራሽ መሆን ይቻላል ።
‹‹የትኛውም ገበያ የተለየ እይታ፣ ክህሎትና አሁን ካለው በተሻለና እጅግ በጣም ያማረ ሥራ ይፈለጋል ። አሁን ያለው ውድድርም ይሄው ነው ። ውድድሩ ብዙ የሚያስፈራ አይደለም ። ነገር ግን መጪው ጊዜ ግን ያስፈራል›› ሲሉ ሚኒስትር ዴኤታው ይገልጻሉ፤ የተለያዩ አገራትን ዝግጅት እያደረጉ ያለው ዝግጅት እና በእኛ አገር እየተደረገ ያለው ዝግጁነት እንደሚለያዩ ጠቅሰው፣ የኢትዮጵያ ዝግጅት በቂ አንዳልሆነ ይገልጻሉ ።
እንደ አቶ እንዳለማው ማብራሪያ፤ ዓለም አቀፍ ጽንሰ ሃሳብን መሰረት ባደረገ መልኩ ኢትዮጵያ የት እንዳለችና የት መድረስ እንዳለባት ማየት ተችሏል ። ለዚህም ከተለመደው አሰራር ወጣ በማለት በተለየ እይታ ብሩህ የሆነ እሳቤን ይዞ መሄድ የሚችል ትውልድ ያስፈልጋል ።
ይህ ትውልድ ጎጥን የተሻገረ፣ መንደርን ያለፈ፣ ወንዝ ተራራን የተሻገረ ሙሉ አገራዊ እይታ ያለውና አህጉራዊ እሳቤን የተላበሰ መሆን እንዳለበት አስገንዝበው፤ በዚህ መልኩ የሚገነባው ትውልድም ዓለም አቀፍ የምርት ሰንሰለት ውስጥ መግባት ይችላል፤ ዓለም አቀፍ የምርት ሰንሰለት ውስጥ መግባት ሲቻል ደግሞ ያለንን ሃብትና ኢኮኖሚ በሚገባ ማሳደግና የንግድ ሰንሰለት ውስጥ መግባት ይቻላል ብለዋል ።
ሀገሪቱ ያለፉት በርካታ ዓመታት ሶስት አብዮቶችን ሳትጠቀምባቸው ማለፏን ያስታወሱት አቶ እንዳለማው፤ በአሁኑ ወቅት ያለንበትንና አራተኛውን የኢንዱስትሪ አብዮት በሚገባ ልንጠቀምበት ይገባል ብለዋል ። አሁን ያለንበት የኢንዱስትሪ አብዮት ዓለምአቀፋዊ መሆኑን ጠቅሰው፣ ገበያው ለሁሉም አንድ በመሆኑ በዓለም ገበያ ሁላችንም አንድ ነን ይላሉ ። በምርትና ምርታማነት እንዲሁም በጥራት ተወዳዳሪ መሆን እንደሚገባ አስገነዝበው፣ በአራተኛው የኢንዱስትሪ አብዮት ውስጥ ዘልቀን ለመግባት የተጀመሩ ስራዎችን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚያስፈልግ አስታውቀዋል ።
እሳቸው እንዳሉት፤ በቅርቡ ኢትዮጵያ የአፍሪካ የንግድ ቀጠና ስምምነትን የፈረመች ሲሆን፣ ከኤርትራ ውጭ ከ54 አፍሪካ አገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ በመሆን ስምምነት አድርጋለች ። በዚህ ውስጥም ሶስት ነጥብ አምስት ትሪሊዮን የአሜሪካ ዶላር ትልቅ ገበያ አለ ማለት ነው ። ስለዚህ የዚህ ገበያ ተቋዳሽ መሆን የሚቻለውም እንደ አገር የሚገነባው ሲስተምና የሚገነቡት ተቋማት ከዚሁ ጋር የተቃኙ መሆን ይኖርባቸዋል ።
በአሁኑ ወቅትም ኢትዮጵያ የዓለም የንግድ ድርጅት / WTO/ አባል ለመሆን በሂደት ላይ ትገኛለች ። ይህ ሂደት ሲጠናቀቅ ኢትዮጵያ አባል ትሆናለች ። አባል ስትሆን ደግሞ የንግዱ ማህበረሰብና አምራቹ እንዴት ተጠቃሚ መሆን እንደሚችሉ ማሰብና መስራት ያስፈልጋል ። ለእዚህም በክህሎትም ሆነ በአመለካከት ብሩህ የሆነ እሳቤ ይዞ ለመገኘት መዘጋጀት ያስፈልጋል ።
የአለም ንግድ ድርጅት በአለም አቀፍ ደረጃ ትልቁ ገበያ እንደመሆኑ ትልቅ እድልና ፈተናን ይዞ የሚመጣ ነው ያሉት አቶ እንዳለማው፣ ስለሆነም ዕድሉን ለመጠቀም ከዛሬ አንስቶ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል ።
እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ገለጻ፤ ዓለም አቀፍ የንግድ ድርጅቱ 165 አገራትን በአባልነት ይዟል፤ 22 አገራት ደግሞ አባል ለመሆን በሂደት ላይ ይገኛሉ፤ 11 አገራት ደግሞ ምንም ውስጥ የሉበትም፤ ኢትዮጵያ ነገ አባል መሆን በምትችልበት ሂደት ላይ ትገኛለች ።
አቶ እንዳለማው በንግድ ዙሪያ ያቀረቡትን የውይይት መነሻ ሀሳብ መሰረት በማድረግ እንዲሁም በአጠቃላይ በሀገሪቱ የንግድ አንቅስቃሴ ላይ ከተሳታፊዎች ጥያቄዎችና አስተያየቶች ቀርበዋል፤ እሳቸው በሰጡት ምላሽና ማብራሪያም አብዛኞቹ አስተያየቶችና ማብራሪያዎች ገንቢና በቀጣይ ሊሰራባቸው የሚገቡ የቤት ሥራዎች ናቸው ብለዋል ። በንግዱ ዘርፍ የሚስተዋሉ ችግሮችን በዝርዝር በማየት የመፍትሔ አቅጣጫ ማስቀመጥ እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል ።
የዓለም የንግድ ድርጅት 98 በመቶ ንግድ የሚካሄድበት እንደመሆኑ ከዛ ውጭ መሆን አይቻልም፤ የዓለም የንግድ ድርጅት ውስጥ መግባት የግድ ነው ብለዋል ። ለእዚህም በቂ ዝግጅት እየተደረገ እንደሆነም ገልጸው፣ ብቃት ያላቸው ተቋማትን ማዘጋጀት አንዱ መሆኑን ተናግረዋል፤ እዚህ ውስጥ የትምህርት፣ የማምረቻና የምርምር ተቋማት ትልቁን ድርሻ ይወስዳሉ ። በተጨማሪም ማህበረሰቡ ድርሻ ያለው በመሆኑ በእዚህም ላይ አስቀድሞ መስራት ያለባቸውን ሥራዎች መስራት ያስፈልጋል ብለዋል ።
ከውጪ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡትን ምርቶች የሚተኩ ምርቶችን በአገር ውስጥ በማምረት ማስቀረት እንደሚቻል ጠቅሰው፣ የተለመደውን ከግብርና በቀጥታ ምርትን ወደ ውጭ ገበያ መላክን በማስቆም እሴት ጨምሮ መላክ እንደሚገባ አስገንዝበዋል ። ቡናን በአብነት ጠቅሰውም ቡናን በቀጥታ በጥሬው ስንልክ ኖረናል ያሉት አቶ እንዳለማው፣ ወደፊትም ጥሬውን ቡና ስንልክ አንኖርም ። ስለዚህ እሴት የጨመረ ቡናን መላክ አለብን፤ ለዚህም ቴክኖሎጂው አለ ሲሉ አብራርተዋል ። ይህን ቴክኖሎጂ በመጠቀም በምንሰራው ሥራ የሥራ ዕድል ከመፍጠር ባለፈ ኢኮኖሚው ላይ የምንፈጥረው በጎ ተጽዕኖ ጎላ ይሆናል ብለዋል ። ይህን ማድረግ ሲቻል እየታየ ያለውን የገበያ ጉድለት በአጭር ጊዜ ማሟላት እንደሚቻልም በመጠቆም በንግዱ ዘርፉ ወደፊት ያለውን ተስፋ አመላክተዋል ።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 13/2014