በዛሬው ዓምዳችን በ1960 የታተሙት ጋዜጦች ለመቃኘት ሞክረናል ፤በክረምቱ ወቅት የተከሰቱ የሚያሳዝኑ ሁኔታዎች የተካተቱበት ነው፡፡የሚያሳዝኑ ዜናዎች ቢሆኑም ፈገግ የሚያሰኝ ዜናም አካተናል፡፡
ለደስታ የተተኮሰ ጥይት ፩ እድምተኛ ገድሎ ሌላ አቆሰለ
አዲስ አበባ (ኢ-ዜ-አ-)፡- በሠርግ በዓል ላይ ለደስታ መግለጫ የተተኮሰው ፴ ጥይት ከዕድምተኞቹ መካከል አንድ ሰው ወዲያውኑ ሲገድል ሌላ አንድ ሰው በጽኑ ያቆሰለ መሆኑን የሸዋ ፖሊስ ማስታወቂያ ክፍል ትናንት ገለጠ።
የቈሰለው ሰው ናዝሬት ኃይለማርያም ማሞ ሆስፒታል በመታከም ላይ የሚገኝ መሆኑ ታውቋል ።
አደጋው የደረሰው በየረርና ከረዩ አውራጃ በአዳማ ወረዳ ገዳምሶ ከተባለው ቀበሌ ሰኔ ፲፩ ቀን ፷፬ ዓ/ም ከምሽቱ ፩ ሰዓት ላይ ቱጂ ያኢ የተባለው ሰው ጋብቻ በዓል በሚከበርበት ጊዜ ሙሽራዎቹ ለደስታ መግለጫ ጥይት ሲተኩሱ መሆኑ ተገልጧል።
ስለ አደጋው ሁናቴ የሸዋ ፖሊስ ማስታወቂያ ክፍል በዝርዝር ሲያስረዳ የሙሽራው ዕድምተኞች ከሙሽራዋ ቤት ሲመለሱ ለደስታ መግለጫ ከ፴ ጥይት በላይ በማከታተል በመተኰስ ከዕድምተኞቹ መካከል አንዱ ማሞ ጉርሙ የተባለው በጥይት ተመትቶ ወዲውኑ ሲሞት ፤ባልቻ ኦዳ በጽኑ ቆስሎ በሆስፒታል በመታከም ላይ ይገኛል ካለ በኋላ፤ ሟችና ቁስለኛው በማንኛው ጥይት እንደተመቱ ባለመታወቁ ምርመራውን አስቸጋሪ ያደረገው መሆኑን ጠቅሶ፤ይህ ዓይነቱ አደጋ በገጠር ሥፍራዎች አልፎ አልፎ የሚደርስ በመሆኑ ፤የጋብቻ በዓላቸውን የሚያከብሩ ሁሉ ይህንን ዓይነት ከንቱ ልማድ እንዲተዉና ደስታቸውን ወደ ሀዘን ከመለወጥ እንዲታገዱ አሳስቧል ።
(ሰኔ 22 ቀን 1964 ዓም የወጣው አዲስ ዘመን)
በዛሬው ዓምዳችን በ1960 የታተሙት ጋዜጦች ለመቃኘት ሞክረናል ፤በክረምቱ ወቅት የተከሰቱ የሚያሳዝኑ ሁኔታዎች የተካተቱበት ነው፡፡የሚያሳዝኑ ዜናዎች ቢሆኑም ፈገግ የሚያሰኝ ዜናም አካተናል፡፡
አምስት አንበሶች ሁለት ሰው ገደሉ
ነቀምቴ፤-(ኢ-ዜ-አ-) በወለጋ ክፍለ ሀገር በሆሮ ጉድሩ አውራጃ በእመራ ቀበሌ ውስጥ ፭ የአንበሳ መንጋዎች ሁለት ሰዎችና አንድ በሬ ገድለው አንድ ሌላ ሰው ደግሞ ማቁሰላቸው ተገለጠ፡፡
እነኝሁ የአንበሳ መንጋዎች በዚሁ አካባቢ ካለው በረሃ ውስጥ በመውጣት የአቶ ታዬ ቶሌራን አንድ በሬ ይዘው ከበሉ በኋላ ለርዳታ የደረሱትን የበሬውን ባለቤትና አንድ ሌላ ሰው ነክሰው መግደላቸው ታውቋል፡፡
ከዚህም በቀር የቀበሌው የሕዝብ ደህንነት ጥበቃ ጓድ አባሎች ከሥፍራው ደርሰው ርዳታ ለማድረግ በመጣር ላይ እንዳሉ፤ አንደኛው አባል በአንበሶቹ ከተነከሰ በኋላ ይዞት የነበረውም ጠብመንጃ አንደኛው አንበሳ አስጥሎት በጥርሱ ንክሻ በመሸሽ ላይ እንዳለ በአንድ ሌላ ሰው በተተኰሰ ጥይት ተገድሏል፡፡
የቀሩት አራቱ አንበሶች ግን ሸሽተው ወደ ጫካ መግባታቸውን የወረዳው አስተዳደር ጽሕፈት ቤት አስታውቋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ፤በነቀምቴ አውራጃ በዋማ ሀገሎ ወረዳ አስተዳደር ውስጥ የሚገኙት አርሶ አደሮች ፤ፀረ ሰብል የሆኑትን ፪፻፷ አውሬዎች መግደላቸውን ጽሕፈት ቤቱ ጨምሮ አስታውቋል፡፡
(ሐምሌ 9 ቀን 1969 ዓ.ም የወጣው አዲስ ዘመን)
በደሴ የመሬት መንቀጥቀጥ 2 ሰዎች ሲሞቱ 3 ቆሰሉ
ደሴ (ኢ-ዜ-አ-)፡- በወሎ ክፍለ ሀገር በደሴ ከተማና አንዳንድ አውራጃዎች ሐምሌ ፩ ቀን ፷፱ ዓ/ም/ ከጧቱ ፫ ሰዓት ከ፳ ደቂቃ ላይ ደርሶ በነበረው የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ ሁለት ሰዎች መሞታቸውን ፫ ሰዎች ደግሞ ከባድና ቀላል የመቁሰል አደጋ የደረሰባቸው መሆኑ ተገለጠ፡፡
የደሴ ዙሪያ ወረዳ አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ስለዚሁ በሰጠው ዜና የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ አልፎ አልፎ ጉዳት ማድረሱን ገልጦ፤ከደሴ ፵ ኪሎ ሜትር ያህል ወደ ገጠር ገባ ብሎ ጦሳ ፈላና በተባለው ቀበሌ ነዋሪ የሆኑ አንሻ ሙሄና ፋጤ ሙሄ የተባሉ ሁለት ልጃገረዶች እንጨት ለቀማ ሥራ ላይ እንደተሠማሩ በመሬቱ ንዝረት ናዳ ስለተጫናቸው ወዲያውኑ ሞተዋል፡፡ ሌሎች ሦስት ሰዎች ደግሞ ከባድና ቀላል የመቁሰል አደጋ ደርሶባቸው በሕክምና ላይ እንደሚገኙ ተረጋግጧል፡፡
እንዲሁም በቃሉ አውራጃ በፋርጡማ ወረዳ ውስጥ በተመሳሳይ ሁኔታ የመሬት መንቀጥቀጥ መድረሱንና በሕይወት ላይ ጉዳት አለማድረሱን የወረዳው አስተዳደር አስታውቋል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ በደሴ ዙሪያ ወረዳ በሐራ ወደሎ ቀበሌ ባለፈው ሐሙስ በጣለው ኃይለኛ ዝናብ ወቅት በወደቀው መብረቅ እሸቱ የሱፍ የተባለው ሰው ከሁለት በሮችና አንዲት ላም ጋር በዛፍ ሥር እንደተጠለሉ ተመትተው መሞታቸውን የወረዳው የገበሬ ማኅበር የልማት ተጠሪ አረጋግጠዋል፡፡
(ሐምሌ 3 ቀን 1969 ዓ.ም የወጣው አዲስ ዘመን)
ባላገሮችን ያታለሉ ተፈረደባቸው
‹‹ከሀብታሞች ዘንድ ወስደን ገንዘብ እናሰጣለን ››በማለት ከገጠር የሚመጡትን ገበሬዎች ከመንገድ እየጠበቁ አታለው ገንዘብ የወሰዱት ሁለት አታላዮች የ፲፭ ዓመት እሥራት ተፈረደባቸው፡፡
ከአሩሲ ጠቅላይ ግዛት ከአርባ ጉጉ አውራጃ የመጡት አቶ ኢንካ አብዲን ‹‹ ሀብታሞች ለድሃ ገንዘብ ይሰጣሉ›› በማለት ፴ ብርና አንድ ጋቢ አጭበርብሮ የወሰደው ታደሰ ቢነግዴ የ፲ ዓመት እሥራት ትናንት ተፈረደበት፡፡ ከሸዋ ጠቅላይ ግዛት ከሜታ ሮቢ የመጡት አቶ ጐንፋ ሙለታን ‹‹ትልልቅ አዛውንት ገንዘባቸውን በነፃ ለሕዝብ ስለሚያድሉ በኪስዎ ያለውን ገንዘብ ከእኔ ዘንድ አስቀምጠው ብዙ ገንዘብ ተቀብለው ሲመጡ ይወስዳሉ ›› በማለት ፩፻ ብር የወሰደባቸው አሰፋ መንገሻ በ፭ ዓመት እሥራት እንዲቀጣ የአዲስ አበባ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ትናንት በየነበት ፡፡
ሁለቱም አታላዮች ወይም እንደፖሊሶቹ አጠራር ‹‹እነ ቁጭበሉ ›› በአዲስ አበባ ከተማ አንዳንድ ባላገሮች በማታለል ‹‹ለአርበኞች ፤ለአገለገሉ ፤ለሸመገሉና ምንም ለሌላቸው ሰዎች ገንዘብ በነፃ ይሰጣል፡፡ የያዛችሁትን ሁሉ ከኛ ዘንድ አስቀምጣችሁ ስትመለሱ ትወስዳላችሁ ›› በማለት ይዘው እየጠፉ የሚያታልሉ መሆናቸው ተመስክሮባቸዋል፡፡
ወንጀለኞቹ ደኅና ልብስ እየለበሱ ታማኞችና ሽማግሌዎች በመምሰል ባላገሮችን ‹‹ገንዘብ በነፃ ለመቀበል በምትሄዱበት ጊዜ ተፈትሻችሁ ገንዘብ ከኪሳችሁ የተገኘ እንደሆነ ትወረሳላችሁ ፤ደኅና ልብስ የለበሳችሁ እንደሆነ ትገፈፋላችሁ በማለት›› የሚያታልሉ መሆናቸው በምስክር ተረጋግጦባቸዋል፡፡
( ሰኔ 15 ቀን 1964 ዓ.ም የወጣው አዲስ ዘመን)
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 12/2014