በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በተለያዩ የኃላፊነት ቦታ አገልግለዋል። በፌደራል ደረጃም በሚኒስትር ዴኤታነት ከአንድም ሁለት መስሪያ ቤቶችን መርተዋል። በቅርቡ ደግሞ የውጭ ጉዳዮች ኢንስቲትዩትን የመምራት ኃላፊነት ተረክበዋል – የዛሬው የአዲስ ዘመን የ‹‹ወቅታዊ ›› እንግዳ ያደረግናቸው ዶክተር ደሳለኝ አምባው። ሦስተኛ ዲግሪያቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በፌደራሊዝም እና አስተዳደር ጥናት ካገኙትና የውጭ ጉዳዮች ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ከሆኑት ዶክተር ደሳለኝ ጋር ቆይታ አድርገናል። መልካም ንባብ።
አዲስ ዘመን፡- የተቋሙ ዋና ዓላማ ነው የሚባለው ምንድን ነው ከሚለው ነጥብ ቃለ ምልልሳችንን እንጀምር?
ዶክተር ደሳለኝ፡– ኢንስቲትዩቱ ከዚህ ቀደም የውጭ ግንኙነት ኢንስቲትዩት በመባል ይታወቅ የነበረ ቢሆንም፤ በአዋጅ የጸደቀ ስሙ ግን የውጭ ጉዳይ በሚል ነው። ይሁንና ወደእዛ ከመሄዳችን በፊት ይህ የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት የተባለው ተቋም ቀደም ሲል የተለያየ ስያሜዎችን ይዞ እዚህ የደረሰ ነው። በአሁኑ ሰዓት ተቋሙ የውጭ ግንኙነት አገልግሎት ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት እና የስትራቴጂክ ጉዳዮች ኢንስቲትዩት በመባል የሚታወቁ የሁለት ተቋማት ውህድ ሆኖ እየሰራ ያለ ነው። አንደኛው የስትራቴጂያዊ ጉዳዮች ኢንስቲትዩት በመባል ይጠራ የነበረው ተቋም ምርምርና ጥናት ላይ ትኩረት ሲያደርግ የነበረ ነው። ሁለተኛው ደግሞ የውጭ ግንኙነት አገልግሎት ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ደግሞ ስልጠና ላይ ያተኮረ ነበር። የሁለቱ ውህድ የሆነው የውጭ ጉዳዮች ኢንስቲትዩት የምርምርና የስልጠና ስራውን በጥምር የሚሰራ ተቋም ነው። ተጠሪነቱም ለውጭ ጉዳዮች ሚኒስቴር ነው።
ቀደም ሲል የስትራቴጂክ ጉዳዮች ኢንስቲትዩት ጥናትና ምርምሩንም ይጨምር ነበር። አሁን ግን የውስጥ ጉዳዮች ፖሊሲ ጥናት የሚባለው የውስጥ ጉዳዮችን ደግሞ እሱ ይሰራል። ይህ የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት የውጭ ጉዳይ ላይ ብቻ አተኩሮ ምርምር የሚሰራ ተቋም ነው። ኢትዮጵያ ከውጭ አገር ጋር ያላት ግንኙነት ላይ ጥናትና ምርምር ማካሄድ ነው።
ለምሳሌ ጥናትና ምርምሩን የምንሰራው በመጀመሪያ ከቅርብ እንደመሆኑ የአፍሪካ ቀንድ ከሚባሉት በጎረቤት አገሮች ላይ ነው። ከአባይ ተፋሰስ ጉዳይ ጋር በተያያዘ እንዲሁም ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጋር ብሎም ኢጋድንም ጨምሮ የኢትዮጵያ መንግስት ከጎረቤት አገሮች ጋርም ሆነ ከተለያዩ አካላት ጋር ያለው ግንኙነት ምን ይመስላል በሚል እናጠናል። እኛ ትኩረታችን የጎረቤት አገር ይሁን እንጂ በሌሎችም አገሮች ላይ ጥናትና ምርምሩን እናካሂዳለን ማለት ይቻላል። ይሁንና ዋና ትኩረት የምንሰጠው በመጀመሪያ ከጉረቤት አገሮች ጋር ባለን ግንኙነት ላይ ነው። ከዚያም ወደአፍሪካ፣ ወደ መካከለኛው ምስራቅና ወደ ሌሎች የዓለም አገራት ላይ ጥናቱን እንሰራለን።
በእርግጥ እንዳልኩሽ የትኩረት አቅጣጫችን በሆኑት በጎረቤት አገራት ላይ የእርስ በእርስ ግንኙነታችንን የሚያጠናክር ሁኔታ ላይ በምናካሂዳቸው ምርምሮችና ጥናቶች ላይ በመመስረት የምክክር መድረኮች፣ ሲሚናሮችና አውደ ጥናቶችን እናካሂዳለን።
ይህ ተቋም ከዓለም አቀፍ፣ ከአህጉራዊና ከጎረቤት አገራት ጋር ያለንን ግንኙነት ሊያሻሽል የሚችል ሰፊ ምርምርና ጥናት እየሰራ እና የፖሊሲ ምርምር ላይ ጥናት እያደረገ የፖሊሲ አማራጭ ሐሳቦችን የሚያቀርብ ነው፤ ምክርም ይለግሳል። ይህን ሲያደርግ የተለያዩ መድረኮችን እያዘጋጀ ባለድርሻ አካላትን በአግባቡ እያሳተፈ እና ወሳኝ የሆኑ ግብዓቶችን እያካተተ ነው።
ከጥናትና ምርምሩ ባሻገር ደግሞ ሁለተኛው የስልጠና ዘርፍ ነው። የስልጠና ዘርፍ ሲባል ሙያተኞችን ማለትም አታሼዎችን ወይም ዲፕሎማቶችን ማሰልጠን ነው። ሌላኛው የስልጠና ዘርፉ ደግሞ የውስጥ አቅምን የሚገነባ ነው። በዋነኛነት ግን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ፍላጎትን መሰረት አድርጎ በውጭ ግንኙነት ዙሪያ አገልግሎት ሊሰጡ የሚችሉ ብቁ ዲፕሎማቶችን ብሎም ባለሙያዎችን ማፍራት ነው። በጥቅሉ ሁለቱ ተቋማት ተነጣጥለው ይሰሩ የነበረውን ስራ አንድ ላይ በማድረግ የውጭ ጉዳዮች ኢንስቲትዩት እንዲሰራው የተደረገ ስራ ሆኗል ማለት ይቻላል። ይህ ሲሆን ግን ኢንስቲትዩቱ የአገር ውስጥ ስራውን ሌሎች ስላሉ የማይመለከተው ነው። ይህንንም የሰላም ሚኒስቴርና የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት የሚሰሩት ስራ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ተቋሙ ሁለቱን ተቋማት አዋህዶ ወደ አንድ ተቋም የማምጣቱ ዋና ዓላማ ምንድን ነው?
ዶክተር ደሳለኝ፡– በእርግጥ ተቋሙ የሁለት የተለያዩ ተቋማት ውህድ ሆኖ በአዲስ መልክ ዓለም ያለችበትን ነባራዊ ሁኔታ ግምት አስገብቶ ስራውን እንዲሰራ ታስቦ የተቋቋመ ቢሆንም፤ በአዋጅ ደረጃ ጸደቀ እንጂ ደንቡ ገና አልጸደቀም። ይሁንና ስራውን ጀምሯል፤ ዋና ዓላማውም የውጭ ጉዳይ ስትራቴጂውንና ፖሊሲውን መሰረት አድርጎ ምርምርና ጥናትን ማካሄድ ነው። አገራዊ፣ ቀጣናዊና ዓለምአቀፋዊ ስትራቴጂክ ክፍተቶች፣ ስጋቶችና አዝማሚያዎች ላይ የምርምርና የጥናት ተግባራትን ያከናውናል።
ለምሳሌ በቅርቡ የተከሰተውን የዩክሬንና የራሽያን ጦርነት መጥቀስ ይቻላል። እነዚህ አገራት ምንም እንኳ በአህጉራችን የሚገኙ እና ጎረቤታችንም ባይሆኑ የሁለቱ አገራት ወደጦርነት መግባት ለአገራችን ያለው ስጋት ምንድን ነው? የሚያሳድርብንስ ተጽዕኖ ምን ሊሆን ይችላል? የሚለውን ጉዳይ የማጥናት ሙከራ እያደረገ ነው። እንዲህ ሲባል ግን ጥናቱ ይፋ የሚደረገው ለሚመለከተው አካል መሆኑ እሙን ነው። ምክንያቱም የጥናቱን ግኝት ዝም ብሎ ይፋ ማድረግ አይቻልም። አንዱን ደግፎ ሌላውን ማኮሰስም ስለማይቻል ግልጽ ማድረጉ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳት የሚያመዝን ይሆናል። ከዚሁ ጎን ለጎን በጎረቤት አገር ሶማሊያ የተካሄደውን ምርጫ በተመለከተም እንዲሁ ስራ ተሰርቷል። ይህም የጥናት ግኝት ይፋ የሚሆነው ለሚመለከተው አካል ነው።
አዲስ ዘመን፡- የተቋሙ አንድ ተልዕኮ ምርምርና ጥናት በማካሄድ ለሚመለከተው አካል ግብዓት ማቅረብ እንደመሆኑ በዚህ ግብዓት አገሪቱ እየገጠማት ካለው ፈተና ምን ያህል ይታደጋታል ማለት ይቻላል?
ዶክተር ደሳለኝ፡– በእርግጥ በአሁኑ ወቅት እኔም ወደቦታው ከመጣሁ ገና ጥቂት ጊዜ በመሆኑ እንዲህና እንዲያ ነው ብዬ ላልናገር እችል ይሆናል። ተቋሙ የብዙ ባለሙያዎች ስብስብን የያዘ ነው። ይህ ቡድን ደግሞ እንዳልኩሽ ጥናቶችን አጥንቶ ለመንግስት ምክረ ሐሳብ ማቅረብ ጀምሯል። ቡድኑም እንደመንግስት አማካሪ (think tank) ሆኖ እየሰራ ያለ ነው። በተለይ ለመንግስት የፖሊሲ አማራጭ የሚያቀርብ ነው።
እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ በቅኝ ገዢዎች ዘመን ያበረከተችው ትልቅ አስተዋጽኦ አለ፤ በተለይ ደግሞ ከአድዋ ጋር ተያይዞ የነበራት ተቀባይነት እና በአህጉራችን ደረጃ የነበራት ሚና ብሎም ለጎረቤት አገሮች የነበራት አስተዋጽኦ ከፍ ያለ ነበር። ዛሬም ደግሞ ቀደም ሲል በሰላምና ደህንነትም ሆነ በማህበራዊ እና በዲፕሎማሲያ ግንኙነት ላይ የነበራትን ተቀባይነት ማጎልበት ነው።
አዲስ ዘመን፡- ምን ያህል የማማከር አቅም አላችሁ? መንግስትንስ ምን ያህል ትደግፉታላችሁ?
ዶክተር ደሳለኝ፡– በጸጥታ፣ በሰላምና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ላይ በጎረቤት አገሮች ላይ ብቻ ብንሰራ ለምሳሌ በደቡብ ሱዳንና በኢትዮጵያ፤ በሱዳንና በኢትዮጵያ፤ በሱማሊያና በኢትዮጵያ እንዲሁም ኢትዮጵያ ከጅቢቲ፣ ከኬንያ እና ከሌሎችም አገሮች ጋር ሊኖራት የሚገባት ግንኙነት ላይ ብዙ ማትረፍ ይቻላል። የሚሰሩና እየተሰሩ ያሉ ስራዎችም አሉ። ተቋሙ ያለውን አቅም ተጠቅሞ አጥንቶ ያቀረበውን የጥናት ግኝት
መንግስት እንዳስፈላጊነቱ ይጠቀምበታል፤ በመጠቀም ላይም ይገኛል። ብቁ የሆኑ ተመራማሪዎች በመኖራቸውም ጥናቶችን ማካሄድ ጀምረናል። ጅማሬውም ትክክለኛውን መንገድ ይዞ እየተካሄደ ነው። በእርግጥ አንዳንድ ጥናት ስድስት ወራትን ፤ አንዳንዱ ደግሞ ከዚያም በላይ ሊጠይቅ ይችላል።
የሚሰራ ብዙ ስራ አለ፤ በአፍሪካ ቀንድ ብቻ ቢታይ ለምሳሌ ሁለቱ ሱዳኖችን መጥቀስ ቢቻል ለዘመናት ከኢትዮጵያውያኑ ጋር የወንድማማችነትን ያህል የሚታይ ህዝብ ድንበር አካባቢ አለ። በደቡብ ሱዳን በኩል ብትወስጂ እኛና ደቡብ ሱዳን በጋምቤላ በኩል ወንድማማች ህዝቦች ነን። በቤኒሻንጉል በኩልም በተመሳሳይ ከሱዳን ጋር ወንድማማቾች ነን። እንዲሁ ደግሞ በኢትዮጵያ ሱማሌና እና በሱማሊያ መካከል ያለው ትስስር የሚታወቅ ነው።
ይህ አይነቱ መልካም የሆነ ወንድማማችነት እንዲፈጠር የሚደረገው በዚሁ ጥናትና ምርምርም ጭምር ነው። ይህም ኢትዮጵያን ወደ አንድነት ሊያመጣ የሚችልና ሉዓላዊነቷን ጠብቃ እንድትጓዝ የሚያደርግም ነው። ስለዚህ የጎረቤት አገሮች ላይ ብቻ እንኳን ስራዎች ተጠናክረው የሚቀጥሉ ቢሆን መንግስትን በከፍተኛ ደረጃ ልንደግፈው እንችላለን ማለት ነው።
በተለይ አሁን ካለው ነባራዊ ሁኔታ ጋር አገናዝበን የምንሰራው ስራ አገራችንን ይበልጥ ተጠቃሚ የሚያደርጋት ነው። እንደአቅማችን ደግሞ በቀጣይ እንዲሁ በዚህ በአፍሪካ በአንዱ አገር ላይ የሚሰራ ጥናት አለ፤ በተጨማሪም መካከለኛው ምስራቅ፣ ሩቅ ምስራቅና ምዕራብ አገሮች ላይ የሚሰራ ይኖራል። የእኛ ስራ ድጋፍ የሚሆን ጥናት በየጊዜው እንደየአስፈላነቱ እያየን ማቅረብ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ ከሱዳን ጋር ያላት የድንበር ውዝግብ በየጊዜው የሚያገረሽ እንደመሆኑ ቀደም ሲል በተጠናው ጥናት መፍትሄ ያገኘ ነገር ይኖር ይሆን?
ዶክተር ደሳለኝ፡– ያነሳሽው ጥያቄ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ አስቀድሜ እንደጠቀስኩት ይፋ ለሚደረገው አካል ነው ይፋ የሚሆነው፤ ለምሳሌ ያለፈው የጎረቤት አገር የሱማሊያ ምርጫ ለኢትዮጵያ ምን ማለት ነው የሚለው የተጀመረ ጉዳይ አለ፤ ቀጥሎ ደግሞ ኬንያ በቅርብ ምርጫ ታካሂዳለችና ስለምርጫውና የሚካሄደው ምርጫ ደግሞ ለኢትዮጵያ ምን ማለት ነው የሚለው በቀጣይ የሚታይ ጉዳይ ነው። ለእኛ በሚጠቅመን አቅጣጫ ጥናትና ምርምሩን ጀምረነዋል። በተለይ በዚህ በጎረቤታችን ምርጫ ላይ ተመራጩ አካል ኢትዮጵያን እንደምን ያያታል፤ የትኛው ቢመረጥ ነው ለኢትዮጵያ የተሻለ ነገር ያለው የሚለውን ግብዓትና ምክረ ሐሳብ ለመንግስት እናደርሳለን።
ይህን የጥናት ግኝትን ግን ለሚመለከተው አካል እንጂ ቀደም ሲል እንደጠቀስኩት ዝም ብሎ ይፋ ማድረጉ እኛ አገር ትንሽ ከበድ ሊል ይችላል። አንድ ምሳሌ ልጠቅስልሽ እችላለሁ፤ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ የስራ መልቀቂያ ባስገቡበት ወቅት እንዳጋጣሚ ኬንያ በሆነ አጋጣሚ ነበርኩና የጠቅላይ ሚኒስትሩን መልቀቅ ተከትሎ በኬንያ ያለው የመንግስት አማካሪ (think tank) የጠቅላይ ሚኒስትሩ መልቀቅ የሚያመጣው ቀውስ እንዲህና እንዲህ ነው፤ በተለይ ለኬንያ ደግሞ የእርሳቸው መልቀቅ ችግር ነው። እርሳቸው ከደቡብ ክልል የወጡ በመሆናቸው ለኬንያ የራሱ የሆነ ጥቅም ነበረው እያሉ በአደባባይ ይተነትኑ ነበር።
የእርሳቸው ስልጣን መልቀቅ በደቡብ ክልል ቅሬታን ስለሚፈጥር ችግርና መፈናቀል ሊኖር ይችላልና ለእኛም ጦሱ ይተርፈናል፤ ተፈናቃዮች ወደአገራችን ኬንያ ሊገቡ ይችላሉ ሲሉም ይተነትኑ ነበር። ስለቀጣዩ ተመራጭም የነበራቸውን ስጋት በይፋ ይናገሩ ነበር። እንደተሰናባቹ ጠቅላይ ሚኒስትር ቀጣዩም ከደቡብ ክልል ቢሆን ለእነርሱ ተመራጭ እንደነበር በስፋት ሲገልጹ ነበር። በተለያዩ ማህበራዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ ትስስርን በአግባቡ ለማሳለጥ የደቡብ ክልል ከኬንያ ጋር ተመራጭ በመሆኑ ለኬንያ የተሻለ እንደሆነ በስፋት ይገለጹ ነበር።
እንዲህ አይነቱ አካሄድ ደግሞ በእኛ አገር የተለመደ አይደለም። ይህን ያለጥንቃቄ በይፋ የምንተነትን ከሆነ የሚያስከትለብን ጉዳት ይኖራል። በኬንያውያኑ ዘንድ የብሔር ብሔረሰቡ ግጭትና የዴሞክራሲው ችግር እንዳለ ሆኖ ያለው ልምድና ነጻነት ግን የምዕራቡ አይነት ሆኗል። ስለዚህም የመንግስት አማካሪ (think tank) የተባለው አካል በይፋ ወጥቶ ይተነትናል። በእኛ ዘንድ በይፋ ወጥተን ብንተነትንና የሆነ ስህተት ቢፈጠር አገር ከአገር ሊያጋጭ ይችላል። ጥንቃቄው ከዚህም የተነሳ ነው። በጥናትና በምርምር የተገኙ የጥናት ግኝቶችን ለመንግስት በማቅረቡ ረገድ ነው ስራ እየተሰራ ያለው።
አዲስ ዘመን፡- የተቋሙ አንዱ ዓላማ ከሆነው መካከል አማራጭ የፖሊሲ አቅጣጫዎችና ምክረ ሐሳቦች ማቅረብ ነውና በዚህ ላይ በተለይ የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ውስጥ ያስገባ ምን አይነት ስራ እየተሰራ ነው?
ዶክተር ደሳለኝ፡- የተለያዩ ስራዎችን በመስራት ላይ ነው፤ ለምሳሌ አንደኛው ‹‹የብሄራዊ ደህንነት ስትራቴጂ ምንነት አቀራረጽና አስፈላጊነት›› ላይ ያከናወናቸው ተግባራት አሉ። ቀደም ሲል ‹‹የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይና የደህንነት ስትራቴጂ›› የነበረ ሲሆን፣ ይህ የውጭ ጉዳዩንም የአገር ደህንነቱን አጣምሮ የያዘ ነበር። ምንም እንኳ ጥሩ የሚባል ፖሊሲ ቢሆንም የራሱ የሆነ ጉድለት ያለበት ነበር። ይኸውም ኢትዮጵያ ሌሎቹን አገሮች እያየች የነበረው ከውስጥ ወደውጭ ነው። እኛ ወደተለያዩ አገራት እንደምናየው ሁሉ ሌሎቹ አገሮች እኛን እንዴት ያዩናል ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው።
እኛ እየተነተንን የምንሄደው እነርሱ እንዲህ ናቸው እያልን ነው፤ እነርሱስ እኛን እንዴት እያዩን ነው በሚል መገምገም ይጠበቅብናል። ከውስጥ ወደውጭ እንደሚያይ ሁሉ ከውጪም ወደውስጥ ማየት ይጠበቅበታል። ከዚህም የተነሳ ‹‹የኢትዮጵያ ብሔራዊ ደህንት ስትራቴጂ››ን ስናይ ነበር። ይህን ስንሰራ የነበረውም ከሚመለከታቸው ዋና ዋና አካላት ጋር በመሆን ነው። ይህ ስትራቴጂ ባለድርሻዎቹ በርካታ ናቸው።
የኛ ተቋም የስትራቴጂውን አስፈላጊነት ያቀረበው በፖሊሲ የምክክር መድረክ ላይ ነው። ይህም ስትራቴጂ በመንግስትም ታምኖበት ተቀባይነት አግኝቷል። የስትራቴጂው መቀረጽ አስፈላጊነት ላይ አመኔታ የተገኘ ሲሆን፣ ይዘጋጅ የሚለውን አቅጣጫ ግን በመጠበቅ ላይ እንገኛለን። ስትራቴጂው አንድ አቅጣጫ ላይ የሚያይ መሆን የለበትም። ለምሳሌ በአጼ ኃይለስላሴ ዘመነ መንግስት ወደምዕራቡ እንዲሁም በደርግ ዘመነ መንግስት ደግሞ ወደሶሻሊስቱ አገራት ላይ ብቻ ማተኮር የለበትም።
ዋናው የትኛው ኢትዮጵያን ይጠቅማል ብሎ የሚሄድ መሆን አለበትና ማየት ያለበት ከውስጥም ከውጪም ነው። አሁን መንግስት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲን ለብቻው አውጥቷል። ይኸኛው ደግሞ ስላልወጣ ነው ይውጣ እያልን ያለነው። በእርግጥ የመወሰን ስልጣን የመንግስት ነው። ከዚህ ቀጥሎ የተካሄደው ሁለተኛው ‹‹የድንበር (ጠረፍ፣ ወሰን) ደህንነት፣ ቁጥጥርና አስተዳደር አገራዊ ስትራቴጂ›› አስፈላጊነት ነው። ዎርክሾፕ አካሂደናል። በዚህ ዙሪያ ኢትዮጵያ ብዙ ያልተካለሉ የድንበር ችግሮች አሉባት። በሱዳን በኩልም ያሉባት ችግሮች የሚታወቅ ነው። በዚህ ስትራቴጂ ላይ ከግለሰቦች ጀምሮ የተለያዩ ባለድርሻዎች ተሳትፈውበታል።
ለምሳሌ በኢትዮጵያ በጎንደር እና በሱዳን በኩል የተፈጠረው የድንበር ውዝግብ ጉዳዩ የሚመለከታቸው በተለይ ከጎንደር አካባቢ የመጡ አንድ ተወካይ ለመድረኩ በአግባቡ በግልጽ አብራርተዋል፤ ይህ ማለት ስትራቴጂው ያስፈልገናል ስንል መፍትሄውም እዛው ጉዳዩ ባለበት አካባቢ ከሚኖርም ነዋሪ መገኘት እንደሚችል የጠቆመ ነበር። በተመሳሳይ ከቤኒሻንጉል ጉምዝ የመጡ አንድ አባትም እንዲሁ በተመሳሳይ በአካባቢው በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል ስላለው የድንበር ችግር አንስተው በውይይት መፈታት እንዳለበት አመላካች የሆነ መፍትሄ ማስቀመጥ ችለዋል። ከሌላ አካባቢ የመጡ አካላትም በአካባቢያቸው ስላለው የድንበር ውዝግብ በማንሳት በየጊዜው የግጭት መፍትሄ እንዳይሆን አማራጭ መፍትሄ ያሉትን ማንሳት ችለዋል።
በዎርክሾፑ ላይ የተገኙ ባድርሻዎች ስለስትራቴጂው አስፈላጊነት የቀረበላቸው ሐሳብ ላይ ከተወያዩ በኋላ የድንበር ችግሩ መፈታት እንዳበት ስለሚያምኑ የስትራቴጂውን አስፈላጊነት በአጽንዖት ሲገለጹ ነበር። በየውይይቱ የተደረሰበትን ግኝት በየሁለት ሳምንቱ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሪፖርት እናቀርባለን። በእርግጠኝነት መናገር የምንችለው ነገር በቀጣይም የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ መንግስት የስትራቴጂ አስፈላጊነትን ስለማመኑ ጥርጥር ይኖራል ብዬ አላስብም።
በጣም የሚገርመው ደግሞ በተለይ በዚህ ከድንበር ጋር ተያይዞ ከቀረበው ዎርክሾፕ በኋላ ስትራቴጂውን በራሳቸው ፍላጎትና ተነሳሽነት እንስራው ብለው ቢሯችን ድረስ የመጡ ምሁራን መኖራቸው ነው። እንዲያውም አንድ ፕሮፌሰር የተወሰኑ የቡድን አባላት ብቻ ስጡኝና ምንም አይነት ክፍያ ሳትከፍሉኝ ልስራው ሲሉም ጠይቀውናል። በተመሳሳይ ‹‹የብሄራዊ ደህንነት ስትራቴጂ››ን በተመለከተም እንዲሁ ለመስራት ፍላጎት ያሳዩን ምሁራን አሉ። ወደተግባራዊነቱም ሲመጣ በዚህ ጉዳይ መንግስት ስትራቴጂው መሰራት አለበት ብሎ ከወሰነና የእኛን ተቋም ይስራው አሊያም ቀጥሮ ያሰራ የሚል ከሆነ እሱን የምንጠብቅ ይሆናል።
ሌላው ሶስተኛ ደግሞ ቱሪዝም ላይ ከተቋሙ ውጪም ሌላ አካል በመጋበዝ አንድ ጥናት አጥንቶ በጉዳዩ ዙሪያ ዎርክሾፕ አካሂደናል። ይህም ጠንካራ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ፖሊሲና ስትራቴጂ መንደፍን የተመለከተ ነው። እንደሚታወቀው ቱሪዝም ለኢኮኖሚና ለዲፕሎማሲ ተገቢውን አስተዋጽኦ የሚያበረክት ነው። እንዲሁም አገራችንን በየጊዜው የሚፈታተናትን የውጭ ምንዛሬ እጥረት ለመቅረፍም ድርሻው ከፍ ያለ ነው። ጭስ አልባው ኢንዱስትሪ እየተባለ የሚጠራው ይህ ዘርፍ አገራችን በርካታ ሰው ሰራሽም ሆነ ተፈጥሯዊ ቅርስና ሀብት ያላት እንደመሆኑ ሀብታችንን በአግባቡ ለመጠቀም የሚያስችል ስትራቴጂ ማስፈለጉ የሚሰመርበት ጉዳይ ነውና የራሱ የሆነ አካሄድ ሊኖረው ይገባል በሚል በጉዳዩ ላይ ውይይት ተካሂዷል። ሌላውና አራተኛ ደግሞ ከስደተኞችና ከመፈናቀል ጋር ተያይዞ ያዘጋጀነው ወርክሾፕም ተጠቃሽ ነው።
ሁለተኛው የተቋሙ ዋና ዓላማ የሆነው ደግሞ እንደጠቀስኩት ስልጠና ነው፤ ስልጠናውን የምናሰለጥነው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መልምሎ የሚሰጠንን ለዲፕሎማትነት የሚፈለጉትን ጎበዝ የሆኑ ወጣቶችን ነው። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እነዚህን ወጣቶች የሚሰጠን ከራሱ ሰራተኞች መልምሎ ሊሆን ይችላል። ስልጠናው የሚመለከተው አዳዲስ ተመልምለው የመጡትንም ሆነ በስራ ያሉትን የሚያካትት ነው። አዳዲስ ምልምል ዲፕሎማቶች ከሰለጠኑ በኋላ በስራ ገበታ ላይ እንደሚሰማሩ ይታወቃል፤ ይሁንና በስራ ላይ እያሉም እንደየአስፈላጊነቱ ስልጠና የሚውስዱ ይሆናል።
ስልጠናው በእኛ ዜጎች ብቻ የተወሰነ አይደለም፤ በቀጣይ አሰልጥኑልን ብሎ ደቡብ ሱዳን ጠይቆናል። የኛን ተቋም ምርጫቸው ያደረጉት ዲፕሎማቶችን በማሰልጠኑ ረገድ በአንጻራዊነት ከደቡብ ሱዳን ተቋም ይልቅ ልምድ ያለው በመሆኑ ነው። በዚህ ጉዳይ በቀጣይ ስልጠናውን በተመለከተ ልንፈራረም ነው። ይህ ደግሞ ከደቡብ ሱዳን ጋር ያለን ግንኙነት የሚያጠናክር ነው። ምክንያቱም ተቋሙ አሁን በምርምር ዙሪያ የራሱንም አቅም በስልጠና በመገንባት ላይም ይገኛል።
አዲስ ዘመን፡- ብዙዎች አንዳንድ አምባሳደሮች ወደሚሄዱበት አገር ሲላኩ ከአካባቢው ገለል እንዲሉ ስለሚፈልግ ወይም ደግሞ ያኮረፉ ሲሆኑ ነው ይላሉ፤ ከዚህ የተነሳ ስለአምባሳደርነት በቂ ግንዛቤ የሌላቸው በመሆኑ እዛ ሄደው ውጤታማ አይሆኑምና ተቋሙ አዳዲስ ዲፕሎማቶችን ማሰልጠኑ ይህን ችግር ለመቀረፍ ምን ያህል ሚና ይኖረዋል?
ዶክተር ደሳለኝ፡– በእርግጥ እዚህ ላይ ብዙ ለማለት ቢያስቸግርም ወደፊት ግን የሚታየውን ክፍተት የሚሞላ ስራ እየተሰራ እንደሚሄድ ጥርጥር አይኖረውም። በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያ ላይ ብዙዎቹ ማለት በሚያስደፍር መልኩ ጣታቸውን ቀስረውባት ያለች አገር ናት። ከዚህም የተነሳ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እቅድ ይዞ በጥልቀት እየሰራበት ይገኛል። ከዚህም የተነሳ በአሁኑ ሰዓት ለውጥ እየታየ ይገኛል። ኢትዮጵያ በቀጣይም አርዓያ ሆና መቀጠል የሚያስችላትን ስራ መስራት ነው የምትፈልገው። ለዚህ ደግሞ ይህን ስራ የሚመጥን ሰው እየሰለጠነ ነው፤ በእርግጥ ይህን ለማለት ጥናት ማካሄድን የሚጠይቅ ነው።
አዲስ ዘመን፡- አሁን ያለው የኢትዮጵያን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዴት ይገልጹታል?
ዶክተር ደሳለኝ፡– ወደተቋሙ ከመጣሁ ገና ጥቂት ጊዜ ብቻ ያስቆጠርኩ በመሆኑ እንዲህ ነው ብዬ ፈጥኜ ለመናገር እቸገራለሁ። ነገር ግን ጠንካራ ዲፕሎማሲያ ግንኙነት እንዲኖረን ብዙ መስራት ይጠበቅብናል። አንዳንዱ በትጋት ለመስራት እየፈለገ በቂ መረጃ ስለማይኖረው ስልክ ደውሎ መረጃ ስጡን እያለ ይጠይቃል። ምክንያቱም የመስራት ፍላጎት ቢኖረውም መረጃ የሚጠይቀው በጥናት ላይ የተመሰረተ ነገር እያጣ ነው።
አንዳንዱም የበኩሉን ጥረት ያደርጋል፤ ለምሳሌ ቀደም ሲል እንደጠቀስኩት በደቡብ ሱዳን ያሉት የኢትዮጵያ አምባሳደር የደቡብ ሱዳን ዲፕሎማቶችን ኢትዮጵያ እንድታሰለጥን በሁለቱ አገራት መካከል የስምምነት ፊርማ እንዲፈረም የበኩላቸውን ሚና ተውጥዋል። ደቡብ ሱዳን ላይ ምንም እንኳ ማሰልጠኛ ማዕከሉ ቢኖርም የእኛ የተደራጀ በመሆኑ በእኛ እንዲሰለጥኑ ስምምነት ላይ ማድረስ ችለዋል።
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያስ ዲፕሎማቶቿ የተሻለ ስልጠና እንዲያገኙ በሚል ወደሌላ አገር ልካ ታሰለጥናለች?
ዶክተር ደሳለኝ፡– አዎ! አሁን እንዲያውም ወደ ኔዘርላድስ ለመላክ እቅድ አለን። እንዴት ማሰልጠን እንዳለበቸው ሰልጠነው እንዲመጡ የሚላኩ አሉ። እስካሁን ባለው ሂደት አሰልጣኝ የሚሆኑት ልምድ ያላቸው የሚያሰለጥኑት ከዩኒቨርሲቲም ከውጭ ጉዳይም እየመጡ ነው፤ በቀጣይ ግን እኛ ራሳችን ብቁ የሆኑ አሰልጣኞች እንዲኖሩን ስለምንፈልግ ወደውጭ አገራት ሄደው እንዲማሩ እናደርጋለን። ሁሉም ነገር በጥሩ ጅማሮ ላይ ይገኛል ማለት ነው። ይሁንና ተቋሙ ከዚህ የበለጠ ስራ በመስራት መንግስትን የበለጠ ማገዝ የሚጠበቅበት እንደሆነ አምናለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ‹‹የድንበር (ጠረፍ፣ ወሰን) ደህንነት፣ ቁጥጥርና አስተዳደር አገራዊ ስትራቴጂ›› አስፈላጊነት ላይ ዎርክሾፕ ማካሂዳችሁን ጠቅሰዋል፤ ይህ ስትራቴጂ በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል ያለውን የድንበር ጭቅጭቅ መፍታት የሚያስችል ይሆን?
ዶክተር ደሳለኝ፡– አሁን ገና የስትራቴጂው አስፈላጊነት ላይ ነው ውይይት እየተካሄደ ያለው። ቀጥሎ የሚመጣው ስትራቴጂ ነው ይፈታዋል አይፈታውም ሊባል የሚችለው። በመጀመሪያ ግን ራሱ ስትራቴጂው ተሰርቶ መጠናቀቅ ይኖርበታል።
ከዚህ በተጨማሪ በአሁኑ ወቅት ተቋሙ የአስር ዓመት እቅድ ሰርቶ በማጠናቀቅ ላይ ነው። ምክንያቱም ተቋሙ የራሱ የሆነ እቅድ ሊኖረው እንደሚገባ ታምኖበታል፤ ከዚህ ቀደም በአብዛኛው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሚሰጠውን ስራ ነው የሚተገብረው። እሱ ደግሞ ደራሽ ስራ ነው። የሚኖረውም አደረጃጀት ከዚሁ የአስር ዓመት እቅድ ጋር የተናበበ እንዲሆን እየተሰራ ነው። ትልቁ ስራው የፖሊሲ አማራጭን ማቅረብ ነው። ዓላማውም በውጭ ጉዳይ ላይ የልህቀት ማዕከል ሆኖ ማገልገል ነው።
በስልጠናው በኩል ደግሞ በውጭ ግንኙነት አገልግሎት የሙያ ብቃትና ክህሎት ያለው፤ በአህጉራዊና በዓለምአቀፍ ደረጃ በላቀ ሁኔታ ተወዳዳሪ የሆነ ባለሙያንም ማፍራት ተግባሩ ነው። አገራችን በውጭ ግንኙነት ያላትን ተደማጭነትም በአህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ደረጃ የሚያጎለብት ነው።
አዲስ ዘመን፡- ስለሰጡኝ ማብራሪያ ከልብ አመሰግናለሁ።
ዶክተር ደሳለኝ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 11/2014