ህንድ ውስጥ የሚገኝ የፋሽን እና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት እንዲሁም በሌሎች አገራት በፋሽን ላይ የተለያዩ ምሁራን ጥናት ሰርተዋል፤ ብያኔዎችንም አስቀምጠዋል። እነዚህ ብያኔዎች ጠቅለል ተደርገው ሲተረጎሙ፤ ፋሽን ማለት በአጭሩ ራስን መግለጽ ማለት ነው።
ራስን መግለጽ ሲባል በአንድ በተወሰነ ጊዜ፣ ቦታ እና ዓውድ ውስጥ እንደሆነ ማብራሪያዎቹ ያሳያሉ። በተወሰነ ጊዜ ውስጥ ሲባል እንግዲህ ፋሽን ዘመን አለው ማለት ነው። ለዚህም ነው ‹‹ፋሽኑ አልፎበታል›› ሲባል የምንሰማው። ‹‹አሁን የመጣ ፋሽን›› ሲባልም እንሰማለን። ስለዚህ ፋሽን በጊዜ የተወሰነ ነው ማለት ነው።
ቦታ ሲባል ደግሞ ከአንድ አገር ሌላ አገር ይለያያል ማለት ነው። እንኳን ከአገር አገር ከአንድ አገር ውስጥ እንኳን ከአካባቢ አካባቢ ይለያያል ማለት ነው። ለምሳሌ ገጠር ውስጥ ወጣት ወንዶችና ሴቶች በተለያየ ጊዜ የተለያየ ፋሽን ያመጣሉ። የልብሱ የስፌት አይነት፣ የጌጣጌጥ አቀማመጥ (ቁልፍ)፣ ጥልፍ፣ ከቦታ ቦታ ይለያያል። የገጠርና የከተማ ይለያያል። ስለዚህ ፋሽን በቦታ የተወሰነ ነው ማለት ነው።
ዓውድ ሲባል ደግሞ አለባበሱ ወይም የፀጉር አሰራሩ ወይም ሌላ የፋሽን አይነት የሚገለጽበት ሁኔታ ማለት ነው። ለምሳሌ ሰርግ ከሆነ እንደየ አካባቢው ሁኔታ ሰርግን የሚገልጽ፣ በከተማ አካባቢ የእራት ግብዣ ወይም ሌላ ጉዳይ ከሆነም እንደዚያው። በአጠቃላይ ሰዎች የሄዱበትን ጉዳይ ይገልጽልኛል ብለው የሚያስቡትን ማለት ነው። ስለዚህ ፋሽን በዓውድ ይወሰናል።
እነዚህን ብያኔዎች ያነሳናቸው ያለምክንያት አይደለም። ኢትዮጵያ የባህል ልብሶቿን ለዓለም ለማስተዋወቅ አርማ(ብራንድ) የማድረግ እንቅስቃሴ ላይ ስለሆነች ነው። ባለፈው ሳምንት ከባህልና ስፖርት ሚኒስቴር በሰማነው ዜና ኢትዮጵያ የባህል ልብሶቿን የመለያ አርማ ልታደርግባቸው ነው።
ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ የአገር ባህል ልብስ ቀን ተከብሯል። በበዓሉ አከባበር ላይ የተገኙት የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የኪነጥበብ የፈጠራ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ናፊሳ አሊማህዲ እንደገለፁት፤ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የአገር ባህል ልብስ በሚገባው ልክ ክብርና እውቅና እንዲሰጠው ሥራዎችን በመሥራት ላይ ይገኛል።
የአገር ባህል ልብስ ቀን ሲከበር ለኢትዮጵያ የባህል አልባሳት ትኩረት መሰጠት እንዳለባቸው በሰፊው ውይይት ተደርጎበታል። ይሄው የባህልና ስፖርት መሥሪያ ቤትም ዘርፉ ላይ ለውጥ ለማምጣት ብዙ ተግባራትን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ በዕለቱ ኃላፊዎቹና ተወያዮቹ ተናግረዋል። ኢትዮጵያን በዓለም አደባባይ የሚያስጠራ የኢትዮጵያ ባህላዊ አልባሳት መለያ አርማ (ሎጎ) በመዘጋጀት ላይ እንደሆነም ሚኒስትር ዴኤታዋ ገልፀዋል።
በዕለቱ እንደተገለጸው፤ የሎጎ ሥራው «የባህል ልብሳችን መድመቂያችን» በሚል የኢትዮጵያን ልብስ መለያ ለማዘጋጀት ታቅዶ የተከወነ ነው። የአገር ባህል ልብሶች ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ፋይዳቸው የጎላ ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ በባህል ልብሶች ኢንዱስትሪ ላይ ያለውን አሉታዊና አወንታዊ ጎኖች መርምሮ ለዘርፉ የተሻለውን መንገድ በመከተል ላይ የተመሠረተ አሠራር መዘርጋቱንም አመላክተዋል። ትውልዱ የባህል ልብሶችን ቀን እየመረጠ ሳይሆን በአብዛኛው ጊዜ እንዲጠቀም ግንዛቤ በመፍጠር ትውልድ መቅረፅ ያስፈልጋልም ተብሏል።
ባለፈው ሳምንት የተከበረው የአገር ባህል ልብስ ቀን «ልብሳችን ለወጣቶቻችን» በሚል መሪ ቃል የተከበረ ሲሆን፤ የባህል ልብስ ቀን አከባበር መርሀ ግብሩን የአዲስ አበባ ወጣቶች ማህበር ከጥፍጥሬ ሁነት አዘጋጅ (ኢቨንት ኦርጋናይዘር) ጋር በትብብር አዘጋጅተውታል። በነገራችን ላይ ጥፍጥሬ ማለት የጥጥ ፍሬ ማለት ነው። በገጠር ጥፍጥሬ እያሉ ነው የሚጠሩት። ጥጥ ደግሞ ሁላችንም እንደምናውቀው ልብስ የሚሰራበት ጥሬ ዕቃ ነው። የሁነት አዘጋጁ ይህን ስያሜ በአገርኛ (ለዚያውም በገጠሩ አጠራር) ማድረጉ ለባህል ያለውን ክብር ያሳያል።
አሁን ወደ ፋሽን ብያኔዎች እንመለስ። ፋሽን ማለት ራስን መግለጽ ነው ብለናል። ስለዚህ ልክ እንደ ባህል ነው ማለት ነው። ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነን ደግሞ የፈረንጅ ተፅዕኖ የሌለባቸው የገጠሩ አገራችን ክፍል ማህበረሰቦች ናቸው። በተለይም ወጣቶች በተለያየ ጊዜ የተለያየ አይነት አለባበስ ይከተላሉ። ወንዶች ቁምጣ ሱሪያቸውን ጉራማይሌ ጌጣጌጥ ያደርጉበታል፣ ቁልፍ ያደርጉበታል። ሴቶችም ቀሚሳቸውን በጥልፍ እና በቁልፍ ያሸበርቁታል።
በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች የተለያዩ የባህል መገለጫዎች አሉ። ምንም እንኳን ፋሽን ሲባል በልብስ ላይ ብቻ ባይወሰንም በአብዛኛው ግን የሚገለጸው በልብስ ነውና የኢትዮጵያ የባህል ልብሶች የራሳቸው መለያ አርማ እንዲኖራቸው መደረጉ ጥሩ ጅማሮ ነው። መለያ አርማው ምን አይነት እንደሆነ፣ የት ላይ እንደሚደረግ ለጊዜው ገና አልተወሰነም። በውይይት ላይ ነው። ሲያልቅ የምናውቀው ይሆናል።
የተለያዩ አገራት በልብሶች ላይ ምልክቶችን ያደርጋሉ። ብዙ ልብሶቻችን ፈረንጅ ሰራሽ ናቸው። የራሳችንን ልብስ እንኳን ብንፈትሽ የእንግሊዘኛ ጽሑፍ ያላቸው ብዙ ልብሶች (በተለይ ቲሸርቶች) ይኖሩናል። የተለያየ መለያ ምልክት ያላቸውም አሉ። ምንም እንኳን አብዛኞቹ ብራንድን የሚያስተዋውቁ ቢሆንም አገራትን የሚያስተዋውቁም አሉ። በየዕቃዎቻቸው ላይ Made in… (በዚህ አገር የተሰራ) የሚል ማንበብ የተለመደ ነው።
ወደ ኢትዮጵያ ስንመጣ ግን ነገሩ ለየት ይላል። ኢትዮጵያ የብዝሃ ብሔር አገር መሆኗ ብቻ ሳይሆን የዕደ ጥበብ አገር መሆኗ ለየት ያደርጋታል። እነዚህ የዕደ ጥበብ ሥራዎች በመላው ዓለም መታወቅ አለባቸው። ለዚህ ደግሞ መለያ አርማ መኖሩ የበለጠ ያስተዋውቀዋል ማለት ነው። የውጭ አገራት ዜጎች የሚያውቁት ጥቂቱን ሊሆን ይችላል። መለያ አርማ ተደረገበት ማለት ግን የየትኛውም የኢትዮጵያ አካባቢ የባህል ልብስ ኢትዮጵያን ይገልጻል ማለት ነው።
ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ያለው የኢትዮጵያ ክፍል ‹‹ኢትዮጵያ›› በሚል መለያ በየሄደበት ይታወቃል ማለት ነው። ኢትዮጵያ የምትባል አገር ምን ያህል ብዝሃ ብሔርና ብዝሃ ጥበብ እንዳለት ለዓለም ይመሰክራል ማለት ነው።
በሌላ በኩል የኢትዮጵያን አልባሳት መለያ አርማ የማድረጉ ጥቅም ደግሞ በሌላ አገራት ተመሳስለው የሚሰሩና በኢትዮጵያ ስም የሚነገድባቸውን የባህል ልብሶች ያስቀራል ማለት ነው። እንደሚታወቀው አሁን አሁን የኢትዮጵያ የጥጥ የባህል አልባሳት እየተፈለጉ ነው። ይህን ተከትሎም በአንዳንድ አገራት አመሳስሎ በመሥራት ሲሸጥ ታይቷል ተብሏል። ስለዚህ የባህል ልብሶቻችን መለያ አርማ ሲኖራቸው በየሄዱበት የኢትዮጵያ መሆናቸውን ይመሰክራሉ ማለት ነው።
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 11/2014