ፔንታጎን በኮንግረሱ አባላትና በዴሞክራቶች ዘንድ ከፍተኛ ተቃውሞ ሲያስተናግድ የቆየውን የፕሬዚዳንት ትራምፕ አወዛጋቢ ዕቅድ ለማስፈጸምና የአሜሪካ ሜክሲኮ ድንበርን ለማጠር የሚውል አንድ ቢሊዮን ዶላር አጸደቀ፡፡
በአሜሪካው የመከላከያ መስሪያ ቤት ፔንታጎን አማካኝነት የሜክሲኮ ድንበርን ለማጠር የጸደቀው አንድ ቢሊዮን ዶላር ወይም 758 ሚሊዮን ዩሮ ፕሬዚዳንት ትራምፕ በኮንግረሱ ውድቅ የተደረገባቸውን የሜክሲኮን ድንበር የማጠር ሃሳብ በኃይል ለማስፈጸም ብሔራዊ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ካወጁ ወዲህ የተገኘ የመጀመሪያው ገንዘብ ነው፡፡
ትራምፕ “ቀውስ” እያሉ የሚጠሩትን የአሜሪካ የደቡብ አዋሳኝ የሜክሲኮ ድንበር ችግር ለመፍታትና ድንበር አቋርጠው ወደ ሀገሬ የሚገቡ ወንጀለኞችን ለመከላከል ብቸኛው መፍትሔ ነው በሚል አጥብቀው ሲከራከሩለት የቆዩትን “አጥር መገንባት” ዕቅድ ለማስፈፀም እስከመጨረሻው ተጉዘዋል፡፡ ተቃዋሚዎቻቸው በበኩላቸው “ራሳቸው የፈበረኩት ቀውስ ነው” እያሉ ያብጠለጥሏቸዋል፡፡
ይሁን እንጂ ተቃዋሚዎቹን ዴሞክራቶችን ጨምሮ ከራሳቸው አባላትና ከኮንግረሱ ሳይቀር ከባድ ተቃውሞ ሲገጥማቸውና ከፍተኛ ትችትን ቢያስተናግዱም፤ የአገሪቱ ኮንግረስ ዕቅዱን ውድቅ ቢያደርግባቸውም ሰውዬው በመጨረሻ በማርያም መንገድም ባይሆን በገብርኤል መንገድ ወደ አሸናፊነት መጥተዋል፡፡
እናም አገራቸው የሠጠቻቸውን የመጨረሻው የወሳኝነት ስልጣን ተጠቅመው ማንኛውንም ዓይነት የተቃውሞ አፍ ለማዘጋትና ዕቅዳቸውን በኃይል ለማስፈጸም እንደ አውሮፓውያኑ ዘመን አቆጣጠር ባለፈው የካቲት 15 ብሔራዊ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ካወጁ በኋላ ከትናንትና ወዲያ የመጀመሪያውን ድላቸውን አስመዝገበዋል፡፡
በዚህም ከእርሳቸው ቀጥሎ በሀገሪቱ ሁለንተናዊ ጉዳዮች ውስጥ ወሳኝ ሚና የሚጫወተውን ኃያሉን የመከላከያ መስሪያ ቤት ፔንታጎንን ከጎናቸው አሰልፈዋል፡፡ የብሔራዊ ደህንነት ስጋት ነው ባሉት የሜክሲኮ ድንበር ላይ አጥር የሚገነቡበትን አንድ ቢሊዮን ዶላርም አስፈቅደዋል፡፡
የአሜሪካ መከላከያ ተጠባባቂ ዋና ጸሃፊ ፓትሪክ ሻናሃን “የአገር ውስጥ ደህንነቱን በመደገፍ ድንበሩን ለማጠር አንድ ቢሊዮን ዶላር እንዲበጀትና ሥራው እንዲጀመር ለሰራዊቱ የምህንድስና ክፍል መምሪያ ትዕዛዝ አስተላልፌያለሁ” ማለታቸውን ቢቢሲ ከፔንታጎን ባገኘው መረጃ አረጋግጫለሁ ብሏል፡፡
“በአደገኛ ዕፅ ምክያንያት የሚከተለውን ቀውስ ለመከላከል የዕፆች መግቢያና መውጫ መተላለፊያ በሆኑ ዓለም አቀፍ የአሜሪካ ድንበሮች ላይ መንገድና አጥሮችን እንድንገነባና መብራቶችን እንድንተክል የፌደራል መንግስቱ ህግ ይፈቅድልናል” የሚለው የፔንታጎን መግለጫ ድርጊቱ የህግ ድጋፍ ያለው መሆኑንም ያትታል፡፡
የዴሞክራቲክ ፓርቲ ሴናተሮች በበኩላቸው “ፔንታጎን ገንዘቡን ማጽደቁን ለፓርላማ ከማቅረቡ በፊት ለጉዳዩ ተገቢ ከሆነ ኮሚቴ ፈቃድ አላገኘም” በማለት የፔንታጎንን ውሳኔ በጽኑ ተቃውመዋል፡፡
ሴናተሮቹ ለፔንታጎን ዋና ጸሃፊ በላኩት ደብዳቤ፤ “የገንዘቡን መተላለፍም ሆነ በጀቱ ያለ ኮንግረሱ ገምጋሚ ኮሚቴ ፈቃድ ሥራ ላይ እንዲውል መወሰኑ እንዲሁም ራሱ መከላከያ ይህን የማድረግ ተገቢው ስልጣን ሳይኖረው ሥራውን በኃላፊነት እንዲይዝ መደረጉ ህግን የተላለፈ ድርጊት በመሆኑ በጥብቅ እንቃወማለን” ማለታቸውን የሲ.ኤን.ኤን ዘገባ ያመለክታል፡፡
ፕሬዚዳንት ትራምፕ የአሜሪካ ሜክሲኮ ድንበር አጥርን ለማስገንባት ኮንግረሱ 5 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር እንዲመድብላቸው ጠይቀው እምቢ ከተባሉ በኋላ ካለፈው የካቲት 15 ጀምሮ አገሪቱ በብሔራዊ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሥር መሆኗ ይታወቃል፡፡
በዴሞክራቶች የበላይነት የታያዘው የአሜሪካ የህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤትም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን “ኢ-ህገ መንግስታዊ ነው” በማለት አዋጁ እንዲነሳ ውሳኔ አሳልፎ የነበረ ሲሆን አስራ ሁለት የሚሆኑ የሪፐብሊካን ሴናተሮችም ከዴሞክራቱ ጋር ወግነው ጉዳዩ በህግ መወሰኛ ምክር ቤት አማካኝነት እልባት እንዲገኝ ውሳኔ ላይ ተደርሶ ነበር፡፡
ሆኖም ፕሬዚዳንት ትራምፕ ድምፅን በድምፅ የመሻር መብታቸውን ተጠቅመው በያዝነው ወር መጀመሪያ ላይ ውሳኔውን ውድቅ ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ዋና ዓላማ የምክር ቤቱን እምቢታ በኃይል ለማገድና በመከላከያ ድጋፍ ዕቅዳቸውን ለማስፈጸም ያለመ ሲሆን አሁን ላይ ፔንታጎን ለአጥሩ ማስገንቢያ አንድ ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ማድረጉ ፕሬዚዳንቱ ሃሳባቸውን ለማሳካት ጫፍ ላይ የደረሱ ይመስላል፡፡
ለሜክሲኮ ድንበር አጥር ግንባታ አንድ ቢሊዮን ዶላር በጀት የፈቀደውን አዲሱን የፕሬዚዳንት ትራምፕና የፔንታጎን ውሳኔ ውድቅ ለማድረግም የሁለቱም ምክር ቤቶች ሁለት ሦስተኛ አብላጫ ድምጽ ያስፈልጋል የሚለው የቢቢሲ ዘገባ ይህም የመሆን ዕድሉ ጠባብ በመሆኑ ድሉ የፕሬዚዳንት ትራምፕ መሆኑን በገደምዳሜው ይደመድማል፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 19/2019
በ ይበል ካሳ