በቅርቡ የኢፌዴሪ ባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር ‹‹ክብር ለጥበብ›› በሚል ስያሜ ለሁለተኛ ጊዜ በተለያዩ የጥበብ ዘርፎች አስተዋጽኦ ያደረጉ ከያኒያንን ሸልሟል:: ሽልማቱ ከደረሳቸው ከያኒያን መካከል ደግሞ አንዱ ሀሁ የዳንስ ቡድን ነው:: ይህ የውዝዋዜ ቡድን የተመሰረተው በ2003 ዓ.ም ሲሆን ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ለኢትዮጵያ የውዝዋዜ ጥበብ ላቅ ያለ አስተዋጽኦ ከሚያደርጉ ቡድኖች አንዱ ሆኖ እስከ አሁን ድረስ ዘልቋል:: የዛሬው የዝነኞች ገፅ አምዳችንም በዚህ የውዝዋዜ ቡድን ላይ ያተኮረ ይሆናል::
ሀሁ የተመሰረተው እዚሁ አዲስ አበባ ላይ ነው:: መስራቾቹ ደግሞ ስድስት ወጣቶች ናቸው:: እነሱም በድሉ ኢሳያስ፣ ዳንኤል ምስለ ወርቅ፤ ሀዋርያ አሰፋ፣ ብርሃኑ ተስፋዬ፣ ብሩክ እሱእንዳለ ይባላሉ:: በወቅቱ ገና አፍላ ጎረምሳ የነበሩት እነዚህ ወጣቶች ቡድኑን ከመመስረታቸው በፊት በውዝዋዜ ፍቅር የተለከፉ ነበሩ:: ሁሉም በቴሌቪዥን መስኮት በሚያዩት ፤ ሰፈር ውስጥም ሌሎች በሚያሳዩት ዳንስ የሚደነቁ እና እንደሚመለከቷቸው ዳንሰኞች የመሆን ፍላጎት ነበራቸው:: ለምሳሌ ያህል ሀዋርያ አሰፋ በመጀመሪያ ደረጃ ዘፋኝ የነበረ ሲሆን የ17 ዓመት አፍላ እያለ ጓደኛው በድሉ የሂፕ ሆፕ ልምምድ ሲያደርግ አይቶ ነው ልቡ በውዝዋዜ ፍቅር የተለከፈው:: ብሩክ በበኩሉ የ15 ዓመት ታዳጊ እያለ ጓደኞቹ ኮንሰርት ላይ ሲጨፍሩ አይቶ ነው ወደ ዳንስ የተሳበው:: በድሉ ደግሞ አልታሰብ የተባለ አብሮ አደግ ጓደኛው በትምህርትና ሰፈር ውስጥ ሲጨፍር አይቶ ነው ዳንሰኛ መሆንን የተመኘው:: ሌላኛው የቡድኑ አባል ፍቅሩ መጀመሪያ የሰርከስ አርቲስት የነበረ ሲሆን ከዚያም በ15 ዓመቱ ዳንስ ጀምሮ ነው በዚያው የቀጠለው:: ኤፍሬም በ15 ዓመቱ በታዋቂው ኢትዮጵያዊ ዳንሰኛ አነሳሽነት ነበር ወደዚህ ጥበብ የገባው። በዚህ መልኩ የቡድኑ አባላት ከዳንስ ጋር የተዋወቁ ሲሆን ሚዩዚክ ሜይዴይ ውስጥም በተሰጧቸው በዳንስ ይሳተፉ ነበር::
እነሱ ሚዩዚክ ሜይዴይ በሚሰሩበት ወቅት ደግሞ በኢትዮጵያ የኪነ ጥበብ እና የቴሌቪዥን ዘርፍ አዲስ ክስተት ተፈጥሮ ነበር:: ያ ክስተትም ኢትዮጵያን አይደል ነበር:: ወጣቶቹም በዚህ ውድድር ላይ ለመሳተፍ ፈለጉ:: ያ ፍላጎትም ሀሁ የዳንስ ቡድንን ወለደ:: በ6 ወጣቶች የተመሰረተው ሀሁ በውድድሩ ላይ ተሳተፈ:: በርከት ያሉ ዙሮች ያሉት ይህ ውድድር ወጣቶቹ ተሰጧቸውን እንዲያሳዩ እድል ሲከፍት በመሀል ደግሞ ተጨማሪ ሁለት አባላት ቡድኑን እንዲቀላቀሉም በር ከፈተ:: የተቀላቀሉት ፍቅሩ ደምሴና ኤፍሬም ናስር ነበሩ:: ዲጄ ቢንያም ሽመልስም ዘግይቶ ነበር የተቀላቀለው:: በመጨረሻም ሀሁ የዳንስ ቡድን በኢትዮጵያን አይድል በዳንስ ዘርፍ ሁለተኛ በመሆንም አጠናቀቀ:: በወቅቱ ቡድኑ ሁለተኛ ሆኖ ቢያጠናቅቅም የቡድኑ አባላት እድሜ እና ተሰጥኦ ግን በኢትዮጵያ ህዝብ አይን ውስጥ እንዲገቡ አደረጋቸው::
በወቅቱ ሀሁዎች በውድድሩ ሂደት አዲስ ወግ ይዘው ነበር የቀረቡት:: ያ አዲስ ወግም የኢትዮጵያ ባህላዊ ውዝዋዜ ባህላዊ ሙዚቃን፣ አልባሳት ትውፊትና ታሪክን ከዘመናዊው ጋር በመቀላቀል የተፈጠረ አዲስ ስልት ነበር:: ይህን ስልት በመከተል ወጣቱን ትውልድ እንደ ሂፕ ሆፕ እና ዘመናዊ ውዝዋዜ ባሉ አዳዲስ ተጽእኖዎች ተጠልፎ እንዳይሄድ ለማድረግ ሞክረዋል::
ከዚያ ውድድር በኋላ የሀሁ የከፍታና የዝና ጊዜ በይፋ ተጀመረ:: በየመድረኩ እየተጋበዙ ስራቸውን እንዲያቀርቡ በሮች ተከፈቱላቸው:: በዓለም የኢኮኖሚ ፎረም አመታዊ ስብሰባን ጨምሮ በትልልቅ ዓለም አቀፍ ኮንፈረንሶች ላይ ተገኝተው በመሪዎች ፊት ስራቸውን አቅርበዋል ፤ ተቋማት በሚያዘጋጇቸው ትልልቅ መርሀ ግብሮች ላይ የመድረኩ ማድመቂያ እነሱ ነበሩ ፤ የሙዚቃ ኮንሰርቶች ላይም ከብዙ ታላላቅ ድምጻውያን ጋር ሰርተዋል:: ከነዚህም መካከል ጎሳዬ ተስፋዬ ፤ አቡሽ ዘለቀ ፤ሚኪያስ ቸርነት እና ናቲ ማን ተጠቃሽ ናቸው:: በሙዚቃ ቪዲዮዎች በኩልም ለአቢ ላቀው፤ ሀይሌ ሩትስ እና ሌሎች ድምጻውያን የሙዚቃ ቪዲዮዎች ላይ ውዝዋዜያቸው ተካቷል::
ሀሁዎች በውዝዋዜያቸው ውስጥ አንገብጋቢ የሚባሉ አጀንዳዎችን በማንሳት ትውልዱን ለማንቃት እና ለማስተማር ሞክረዋል:: ካነሷቸው ጉዳዮች መካከል የኤች አይ ቪ ኤድስ ጉዳይ ፤ የሱሰኝነት ጉዳይ ፤ የመጤ ባህል ጉዳይ ተጠቃሽ ናቸው:: አሁንም ቢሆን ዋነኛ አላማቸው ዳንስን ለማህበራዊ ጉዳዮች ማከናወኛ መጠቀም ነው::
በአሁኑ ወቅት ከቡድኑ አባላት የተወሰኑት ከአገር ውጭ ቢሆኑም ቡድኑ ግን ያለውን ሀሳብ ይዞ አሁንም ጉዞውን ቀጥሎ ስራውን እያከናወነ ይገኛል:: በኪነ ጥበብ ውስጥ ብዙ ጊዜ እንደታየው የሙዚቃ ባንዶች፤ የሙዚቃ ቡድኖች እና የዳንስ ቡድኖች የመፍረስ ልማዳቸው ከፍተኛ ሲሆን ሀሁዎች ግን የተወሰነ መንገጫገጭ ቢያጋጥማቸውም አሁንም ቅርጻቸውን ሳይለቁ አብረው እየተጓዙ ነው:: ከነባር አባላት መካከል በኑሮ ምክንያት ከአገር ውጭ ከሆኑት በቀር ግማሹ የቡድኑ አባል አሁንም በቡድኑ ውስጥ በንቃት እየተሳተፈ ይገኛል::
ሀሁ ኢንተርቴይንመት የተሰኘ ተቋም አቋቁመው እንቅስቃሴ እያደረጉ ያሉት እነዚህ ወጣቶች አብዛኞቹ ባለትዳር እና የቤተሰብ አስተዳዳሪ ቢሆኑም በዳንሱ ዙሪያ ብዙ የመስራት እቅድን ይዘው እየተንቀሳቀሱ ነው:: ውዝዋዜን ሲጀምሩ ዋነኛ ችግር የነበረው የልምምድ ቦታ እና መሰል ችግሮች አሁን ቢቀረፉም በተቃራኒው አሁንም ለውዝወዋዜ ሙያ የሚሰጠው አመለካከት አናሳ መሆን ግን ትልቁ ተግዳሮታቸው ሆኖ እንደቀጠለ ነው:: የተሰሩ ስራዎች የሚቀርቡባቸው መድረኮች አለመኖራቸውን የሚናገሩት ሀሁዎች አሁን እነሱ ተቸገረው ያረፉበትን ነገር ሌሎች እንዳይገጥማቸው የሚመለከታቸው አካላት ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ይወተውታሉ::
ከውትወታም ባለፈ በየጊዜው በርካታ ታዳጊዎችን በውዝዋዜው በኩል እያሰለጠኑ ይገኛሉ:: እነሱ ካሰለጠኗቸው ወጣቶች መካከል ቴአትር ቤት የተቀላቀሉ ፤ እንዲሁም የራሳቸውን የዳንስ ቡድን መስርተው እየተንቀሳቀሱ ያሉ ይገኙበታል:: የዳንስ አሰልጣኝ የሆኑም አሉበት:: ወደፊት የዳንስ ትምህርት ቤት ለመክፈትም ይመኛሉ:: ለዚህም ከሚመለከተው የመንግስት አካል ጋር በመሆን ስርዓተ ትምህርት ለመቅረጽ ጥረት እያደረጉ ነው::
ከስራ ውጭ የሀሁ አባላት እስከ ቤተሰብ የዘለቀ ወዳጅነት ያላቸው ሲሆን በእረፍት ጊዘያቸውም አብረው በመጫወት እና መንፈሳዊ ተግባራትን በመፈጸም የሚውሉበት አጋጣሚ ብዙ ነው::
አቤል ገ/ኪዳን
አዲስ ዘመን ሐምሌ 10/2014