የኢትዮጵያ መንግስት የቱሪዝም ዘርፍን ከማህበራዊ ጉዳይ አውጥቶ ወሳኝ ወደሆነው ቁልፍ ኢኮኖሚያዊ ግቦችን ማሳካት ከሚችሉ ግንባር ቀደም ዘርፎች ውስጥ አካቶታል። በዚህም የቱሪዝም ልማት፣ ፕሮሞሽንና መሰል ጉዳዮችን በትኩረት በመስራት ከዘርፉ የሚገኘውን የላቀ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለማስጠበቅ እንደሚሰራ ግልፅ አድርጓል። ለዚህ እቅድ መሳካት ወሳኝ ከሆኑ ጉዳዮች መካከል ደግሞ የዘርፉን የአገልግሎት አሰጣጥ ሂደት ማዘመን አንዱና ዋነኛው ነው።
በቱሪዝም ዘርፍ ላይ ሙያቸውን ያዳበሩ ምሁራን “ቱሪዝም ከአንድ ቦታ ወደሌላ ስፍራ የሚደረግ እንቅስቃሴ ነው” ይላሉ። በዚህ ሂደት ውስጥ ጉዞውን የሚያደርገው ግለሰብም ይሁን ቡድን ከቋሚ መኖሪያው ለአጭር ጊዜ አሊያም ረዘም ላለ ቆይታ ይንቀሳቀሳል ማለት ነው። ከዚህ ውስጥ ደግሞ የመስህብ ስፍራን ለመመልከት እንዲሁም ታሪካዊ፣ ተፈጥሯዊና የዓለም ቅርስ መገኛዎችን ለመጎብኘት የሚደረገው ጉዞ በዋነኝነት ይጠቀሳል። ይህ ደግሞ በመዳረሻው ለሚገኘው አገር፣ ዜጎች እንዲሁም በአገልግሎት ዘርፍ ላይ ለተሰማሩ አካላት ኢኮኖሚያዊ አቅምን የሚፈጥር ከመሆኑም በላይ የአገር ገፅታን ለመገንባት ጠቀሜታ እንደሚኖረው ያብራራሉ።
በዚህ ሂደት ውስጥ የተሟላና አርኪ የአገልግሎት ዘርፍ ያላቸው፣ ብቁ ባለሙያና ስነ ምግባርን (የአገልጋይነት ባህሪ) የተላበሰ የሰው ኃይልና ዘመናዊ አሰራር የዘረጉ አገራት ጎብኚዎች ቆይታቸውን አራዝመው ገንዘባቸውን በበቂ ሁኔታ አውጥተው ተጠቃሚ እንዲሆኑ እድሉን ይከፍታሉ። በዚህም ምጣኔ ሃብታቸው እንዲያድግና ዜጎቻቸው በሚፈጠረው የስራ እድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያደርጋሉ።
ኢትዮጵያም ከዚህ መሰል እድል ተጠቃሚ ለመሆንና የቱሪዝም ዘርፉን ግንባር ቀደም ዘርፍ አድርጋ አስቀምጣለች። በተለይ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ አንዱና ዋንኛው ግብ በዚህ ዘርፍ ላይ የሚያጠነጥን ነው። ከሰነዱ መረዳት እንደምንችለው ቱሪዝምን ተወዳዳሪ ለማድረግ የዲጂታል አሰራር መዝርጋት ያስፈልጋል። ይህንን ለማድረግ ሶስት መልካም አጋጣሚዎች መለየታቸውንም ያመለክታል። የመጀመሪያው የቱሪዝም ዲጂታላይዛሽን ግብረ ኃይል በማቋቋም የቱሪዝም ኢንዱስትሪውን ዲጂታላይዝ ማድረግ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ የዲጂታል የገበያ ስርዓትን በማበጀት የቱሪስት ፍሰትን እና የቆይታ እና ተሳትፎ መጠኑን ማሻሻል ነው፡፡ ሶስተኛው ደግሞ በቱሪዝም ዘርፍ የተሰማሩ አነስተኛ ኢንተርፕራይዞችን የዲጂታል አገልግሎት እንዲሰጡ አቅም መገንባት ነው፡፡
ይህ የሚያመለክተን ዘመኑን የዋጀ የቱሪዝም አገልግሎት ዘርፍ ለመዘርጋት ስልት መነደፉን ሲሆን፣ ወደዚያ ግብ ለመድረስ ደግሞ አያሌ ተግባራት ከፊት ለፊታችን እንደሚገኙ ነው። ለመሆኑ የአገልግሎት ዘርፉን አዘምኖ፣ ከከፍተኛ የቱሪስት ፍሰት የሚገኘውን ኢኮኖሚያዊ አቅም አሳድጎና ቱሪስቶች የቆይታ ጊዜያቸውን አራዝመው ፈሰስ እንዲያደርጉ የሚያስችል ምን ስልት መከተል ይኖርብናል? ለሚለው ጥያቄ የዝግጅት ክፍላችን በቅርቡ በቱሪዝም ዘርፉ ላይ በተካሄደ አንድ መድረክ ላይ የመወያያ ፅሁፍ ያቀረቡ የሆቴልና ቱሪዝም ኢንስቲቱዩት የቱሪዝም ባለሙያና መምህር የአቶ ማሩ እማኙን ሃሳብ ከዚህ እንደሚከተለው ያቀርባል።
አቶ ማሩ የዓለም የቱሪዝም ድርጅት (ደብሊው ቲኦ) “ቱሪዝም የሰዎች እንቅስቃሴ ነው” በሚል ቱሪዝምን ይተረጉመዋል በማለት ስለ አገልግሎት አሰጣጥና መሰል የቱሪዝም ፅንሰ ሃሳቦች ከመግባታችን አስቀድመን በቅጡ ትርጉሙን ልንረዳው ይገባል በማለት ያስረዱናል። በዚህ ሂደት ውስጥ ጎብኚዎች ከተለመደው ስፍራቸው አዲስ ወደሆነው ሲንቀሳቀሱ የተለያዩ ልምዶችንና መዝናናቶችን እንደሚሹ ይናገራሉ። በዚህ ሂደት ላይ አገልግሎት ዘርፉ እንደሚገባና ከጎብኚዎች አሊያም ቱሪስቶች ጋር መስተጋብር የሚፈጥር እንደሆነ ይናገራሉ።
“ጎብኚዎች ከአካባቢያቸው ራቅ ያለ ቦታ ሲጓዙ የሚጠብቁትና የሚፈልጉት የአገልግሎት አይነት አለ” የሚሉት አቶ ማሩ፣ ይህንን ፍላጎታቸውን በተገቢው መንገድ የምንሰጣቸው ከሆነ ደስተኞችና ቆይታቸውን የማራዘም ፍላጎት አሊያም ደግሞ በድጋሚ የመምጣት፤ ከዚያም አለፍ ሲል ወደመጡበት ስፍራ ሲመለሱ መልካም ገፅታን ለመገንባት ፍቃደኛ እንደሚሆኑ ያመለክታሉ። በዚህ ምክንያት የአገልግሎት ዘርፎቹ አስፈላጊውን ሁሉ ማድረግ እንደሚገባቸው ይመክራሉ።
እንደ አቶ ማሩ ገለጻ፤ ቱሪስቶች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ቆይታቸውን አጠናቀው በሚመለሱበት ጊዜ በፎቶ፣ በተንቀሳቃሽ ምስል እንዲሁም ትውስታቸውን ይዘው ይመለሳሉ፤ ለኢትዮጵያም ሆነ በውስጧ ለሚኖሩት ዜጎች ጎብኚዎች መልካም ስምና አድናቆትን ይዘው እንዲመለሱ አገልግሎት ዘርፉ የበኩሉን ድርሻ መወጣት ይኖርበታል።
በተለይ ቱሪዝም ሲታሰብ መሰረታዊና ግንባር ቀደም የአገልግሎት ዘርፍ የሆነው አንዱ “የትራንስፖርት ዘርፍ” መሆኑን የሚጠቅሱት አቶ ማሩ፣ በዚህ ዙሪያ ራሱን የቻለ የተደራጀ ነገር መኖር እንዳለበት ይገልፃሉ። ሌላው ጎብኚዎች ስለሚገኙበት አንድ መዳረሻ ስፍራ ራሱን የቻለ ምስል ከሳችና እውቀትን የሚያስጨብጥ የተቀናጀና የተናበበ አሰራር ሊኖር እንደሚገባም ይጠቁማሉ። ይህ እንዲሆን አገልግሎት ሰጪዎች ወጥ አሰራር ሊኖራቸው እንደሚገባ ይናገራሉ። ለምሳሌ ያህልም አዲስ አበባ ውስጥ የሚገኙ ታሪካዊ፣ ተፈጥሯዊ፣ ሰው ሰራሽና ሌሎች ቅርሶችን በተመለከተ ጎብኚዎች ተመሳሳይ መረጃን ማግኘት እንደሚገባቸውን ነው በምክረ ሃሳባቸው ላይ የሚያነሱት።
“ቱሪስቶች ረጅም ቆይታ ሳያደርጉ መዳረሻቸው ሌላ አገር ሆኖ ትራንዚት ሲያደርጉ ለአጭር ጊዜ ቆይታ ጉብኝት ሊያደርጉ ይችላሉ” የሚሉት የቱሪዝም ባለሙያውና መምህሩ፣ በተለይ አዲስ አበባን እንደ ትራንዚት ሊጠቀሙ የሚችሉ በርካታ ቱሪስቶች መኖራቸውን ነው የሚያመለክቱት። በዚህ ጊዜ የሚኖራቸውን ከ6 እስከ 72 ሰዓት የሚደርስ የአጭር ጊዜ ቆይታ በተጨናነቀ ኤርፖርት ወይም አልጋ ክፍል ውስጥ ከሚያሳልፉ በዋና ከተማዋ የሚገኙ የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራዎች ላይ እንዲያደርጉ የሚያበረታታቸው ልዩ ልዩ የአገልግሎት አማራጮች መኖር እንዳለባቸውም ይመክራሉ።
በአሁኑ ወቅት መንግስት በአዲስ አበባ የጀመራቸውና ሰርቶ ያጠናቀቃቸው ሜጋ የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራዎችን በቀላሉ እንዲመለከቱ እድሉን ማመቻቸት እንደሚያስፈልግ ነው የሚገልፁት። ይህን ለማድረግ ምቹ የትራንስፖርት አማራጭና የተደራጀ መረጃን ማሰናዳት እንደሚገባ ይናገራሉ። ይህን ማድረግ ከተቻለ ትራንዚት የሚያደርጉት ቱሪስቶች ዶላራቸውን አውጥተው እንዲሄዱ ጥሩ መንገድ ይከፍታል ይላሉ።
“ቱሪዝም በዋናነት እና በመጨረሻ ዋና ግብነት የሚያስቀምጠው ዘርፉን ተጠቅሞ እንዴት ለዜጎች የስራ እድል መፍጠር ይቻላል የሚል ፅንሰ ሃሳብ ላይ የሚያጠነጥን ነው” የሚሉት መምህሩ፤ ቀደም ሲል ዘርፉ በማህበራዊ ዘርፍ ላይ የተካተተ እንደነበር ያስታውሳሉ፤ አሁን ግን ከስራ ፈጠራና ከሚያበረክተው ምጣኔ ሃብታዊ አስተዋጽኦ አንፃር ተቃኝቶ ወደ ኢኮኖሚ ዘርፍ እንደተካተተ ይናገራሉ። በዋነኝነት ግን ሰፊ የስራ እድል መፍጠሩ በመንግስት ቁልፍ የኢኮኖሚ ዘርፎች ውስጥ እንዲገባ እንዳስቻለው ነው የሚያስረዱት። በዋናነት በዘርፉ የስራ እድል ፈጥሮ ስኬታማ የአገልግሎት ዘርፍ እንዲኖር ለማስቻል እንደሚሰራ ይጠቁማሉ። ታዲያ ይህንን እድል በሚገባ መጠቀምና በኢትዮጵያ ልዩ ልዩ ክፍሎች የሚገኙ መዳረሻ ስፍራዎችን በተገቢው ተገንዝቦ ወደ እድል መቀየር እንደሚያስፈልግ ያሳስባሉ።
“ቱሪዝም ሲታሰብ ሶስት መሰረታዊ ነገሮች አሉ” የሚሉት መምህር ማሩ፣ አንደኛው መስህቡና መዳረሻ ስፍራው መኖሩ ሲሆን፣ ሁለተኛውና ትልቁ ነገር ወደዚያ ሰፍራ ለመሄድ የሚያስችል የተመቻቸ የትራንስፖርት አማራጭ መኖር ነው ይላሉ። ሶስተኛው ደግሞ የተለያዩ የምግብ፣ የመዝናኛ እንዲሁም ልዩ ልዩ የግብይትና የአገልግሎት መስጫ ስፍራዎች መኖር መሆኑን ይጠቁማሉ።
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ እነዚህ ሶስት መሰረታዊ ጉዳዮች ሲሟሉና ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት ሲችሉ ቱሪስቱ በሚፈልገው አግባብ መስተናገድ ይችላል። የአገልግሎት ዘርፉ ጥራትና ውጤታማነትም የጎብኚውን የመቆየት እና ጉብኝቱን የማራዘም ፍላጎቱን በእጅጉ ይጨምረዋል። ይህ ሲሆን የተሻለ የገንዘብ ፍሰት ከመፍጠር ባለፈ ሰፊ የስራ እድልም ይፈጠራል።
እንደ መውጫ
በርካታ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፤ ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ አገር ነች። ኢትዮጵያ ከ3 ሚሊዮን ዓመታት በላይ እድሜ ያስቆጠረው “የሉሲ” ወይም ድንቅነሽ አፅም መገኛ ናት፡፡ የአረቢካ ቡና ዝርያ መገኛም ነች። የዓለማችን ረጅሙ ወንዝ ጥቁር አባይም የሚገኘው በኢትዮጵያ ነው። የኤርታሌ የእሳተ ገሞራ ሐይቅና የዓለማችን እጅግ ረባዳና ሞቃት ስፍራ ዳሎልም የሚገኙት በኢትዮጵያ ነው። ይህ ብቻ አይደለም። ኢትዮጵያ የንግስት ሳባ አገር ነች፣ የሙሴ ጽላትም በኢትዮጵያ ይገኛል ተብሎ ይታመናል፤ በአክሱም ፅዮን ቤተክርስቲያን። ከእነዚህ ሌላ ለመዝናናት አመቺ የሆኑ በርካታ የስምጥ ሸለቆ ሐይቆችና ፍል ውኃዎች፣ እንዲሁም የዱር እንስሳት ፓርኮችና መጠበቂያዎች ይገኛሉ።
ኢትዮጵያ በርካታ ተፈጥሯዊ፣ ታሪካዊ፤ ሰው ሰራሽና ባህላዊ ቅርሶችን በዩኔሰኮ በማስመዝገብ በአፍሪካ ቀዳሚዋ አገር ለመሆን በቅታለች። በተፈጥሯዊ፣ ታሪካዊና ባህላዊ ቅርሶች የበለፀገች፤ የቱሪስት መስህብ ያላትና እነዚህንም ቅርሶች በዩኔስኮ መዝገብ በብዛት በማስመዝገብ ከአፍሪካ አገራት ቀዳሚዋ ብትሆንም፣ የአገሪቱ የቱሪዝም ዘርፍ ግን የሚፈለገውን ያህል ወይም የሚገባውን ያህል አላደገም።
ለዚህ እንደ ዋንኛ ምክንያት የሚጠቀሰው ዛሬ በስፋት ያነሳነው የአገልግሎት ዘርፉ በተገቢው አለመዘመን ሲሆን፣ በልዩ ልዩ የቱሪዝም ዘርፉ ተሰማርተው የሚገኙት አገልግሎት ሰጪዎች የስነ ምግባር፣ የእውቀትና መሰል ቱሪስቱ የሚፈልገው የአገልጋይነት ባህሪያት መላበስ ባለመቻላቸው እንደሆነ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ መንግስት የቱሪዝም ዘርፉ የኢትዮጵያ የጀርባ አጥንት እንደሆነ በማመን ልዩ ትኩረት መስጠቱን ነግሮናል። በተግባር ሰፋፊ ልማቶችን፣ ፕሮጀክቶችን እያከናወነ መሆኑን የሚያመላክቱ መረጃዎችን መጥቀስ ይቻላል። ይሄን መልካም አጋጣሚ መጠቀም ከምንም ነገር በላይ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል። በተለይ በግሉ ዘርፍ የተሰማሩ ባለሃብቶች በቱሪዝም ሆስፒታሊቲ ዘርፍ፣ በፕሮሞሽንና የገበያ ልማት ብሎም በአስጎብኚ ድርጅቶች ውስጥ በቀጥታ ሊሳተፉ ይገባል። የዚህ ድምር ውጤት ደግሞ “ምድረ ቀደምት” አገራችንን ለመላው ዓለም ከፍ አድርጎ ማስተዋወቅ እንዲቻል ከማድረጉም ባለፈ ኢኮኖሚያዊ ትርፉ ለአገር እድገት ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት ጥርጥር አይኖረውም።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 10 ቀን 2014 ዓ.ም