ሰርጋቸውን በቅርቡ ሊያደርጉ እቅድ ያደረጉ ጥንዶች ቀለበት ሊገዙ ከወርቅ ቤቶች በር ላይ ናቸው። አንዱን ቤት አይተው ወደ ሌላኛው፤ ከዚያም ወደ ሌላኛው እያሉ እያማረጡ። የሚገዛው ቀለበት አይነትና የገንዘብ አቅማቸውን ለማስታረቅ ያወጣሉ ያወርዳሉ ደጋግመው ያሰላስላሉ። በመጨረሻም ከውሳኔ ደርሰው ቀለበታቸው ገዙ። ተቸጋግረው የገዙትን ቀለበት ይዘው በታክሲ ተሳፍረው ከሙሽሪት ሰፈር ደረሱ። ሁለቱም ወደ የራሳቸው ቤት ከመግባታቸው በፊት ሻይ ቡና እያሉ መቆየት ፈልገው ወደ አንድ ካፍቴሪያ ጎራ አሉ። እንደተለመደው ፍቅሬ አካላቴ ወዘተ ሲባባሉ ቆይተው ወደየቤታቸው አቀኑ። ቀኑ መሸ፤ የቀለበት መግዢያው ቀንም ያለፈ ሆነ።
ሁለቱም ቤታቸው ሲደርሱ ግን የገዙት ቀለበት እነርሱ ዘንድ አልነበረም። ተደዋወሉ፤ አንተ ጋር ነው፤ አንቺ ጋር ነውም ተባባሉ፤ ከቀልባቸው ሆነው ሲያስቡት ለካንስ ቀለበቱን ታክሲው ውስጥ ጥለውት ወርደዋል። በድንጋጤ ውስጥ ወደቁ፤ በብዙ የገንዘብ እጥረት የገዙት ቀለበት ነበርና ሃዘናቸውን አከፋው። ታክሲውን ለማስታወስ ሞከሩ፤ በጨለማም ወጥተው ይፈልጉትም ጀመር፤ ፍለጋውም ሳይሳካ ቀረ ቀለበቱም መጥፋቱን አምነው ተቀበሉ። ሙሽሪት ስቅስቅ ብላ ስታለቀስ አባት ይመለከቱና የነገሩን ጭራ ለማግኘት ወደ ልጃቸው ጠጋ ይላሉ። ልጃቸውም ሁሉንም ነገር ለአባቷ ትናገራለች፤ አባትም የአባትነት ምክር ሊነግሯት ወደዱና፤ “ልጄ የወርቁ ቀለበት ከአንቺ ዘንድ የለም፤ ነገር ግን የጊዜ ቀለበት አንቺ ጋር አለ። የጊዜ ቀለበት ደግሞ የወርቁን ቀለበት ይገዛዋል።” ሲሉ ምክራቸውን ሰጡ።
አባት በመቀጠልም፤ “ልጄ በጊዜ ቀለበት ውስጥ የሚዘራው መልካም ዘር አለ፤ እንዲሁም ያልተገባውም። በጊዜ ውስጥ ሁሉ ነገር ይዘራል። ጊዜን ገንዘብ ለመስሪያ ማዋል ይቻላል፤ ጊዜን ችግርን ለመፍቻ መጠቀም ይቻላል፤ ጊዜን የተራቡትን ለማብላት ይጠቅማል፤ ጊዜን የተጣሉትን ለማስታረቅ፤ ጊዜን ትምህርት ለመማር፤ ጊዜን የጠፋን ለመፈለግ፤ ጊዜን ከራስ ጋር በጥሞና ለመሆን፤ ጊዜን ትላንትን መርምሮ ትምህርትን ለመውሰድ፤ ጊዜን ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሶ ያሰቡትን ለማድረግ፤ …፤” ወዘተ ብለው የጊዜ ቀለበትን አስረዱ።
እኛም እንላለን በጊዜ ቀለበት ውስጥ መልካምን በመዝራት መልካምን ማጨድ ይቻላል። በጊዜ ውስጥ ክፉን በመዝራት ክፉን ማጨድ ይቻላል። ለነገሮች የደረሰውን ጊዜ አውቆ ነገሮችን በጊዜ ማድረግ አስተውሎትም ነው። ይህን አስተውሎት ማግኘት ይቻል ዘንድ ጠቢብ ሰው በብዙ ይደክማል።
ጊዜን በአግባቡ የሚመረምሩ በዘመናት መካከል ከጊዜ ጋር የታረቀን ተግባር አድርገው ማለፍ ይችላሉ። በዓለማችን ውስጥ በታሪክ መዝገብ ውስጥ ስማቸውን በደማቁ ጽፈው ያለፉ ጀግኖች የጊዜን ቀለበት በአግባቡ የያዙ ናቸው። ከወርቅም ሆነ ከእንቁ ቀለበት በላይ ለጊዜ ቀለበት ቦታን የሰጡ። የጊዜ ቀለበት ራሳችን ለራሳችን የምናጠልቀው ታላቁ ኪዳን ነው፤ ራስን ፈልጎ ራስን በትክክለኛው አቅጣጫ ውስጥ በጊዜ ውስጥ የማራመድ ኪዳን። የእርምጃው መነሻ ደግሞ፤ አንድ!
መነሻው አንድ ነው
የጊዜ ቀለበት መነሻው ሁለት አይደለም፤ አንድ ነው። መነሻው አመታት አይደለም ሽርፍራፊ ሰከንድ ነው። አንድ ብለን መቁጠር ጀመርን። አንድ ብለን መቁጠር ከጀመርንበት ጊዜ አንስቶ ወደ ኋላ በምናብ ብንሄድ ወራቱና ቀናቱ ትዝታ ሆነው ከኋላችን ናቸው። የዘመናችንን ታሪክ ለመስራት የተገለጡ አዳዲስ ቀናት ደግሞ ከፊታችን። በውስጣዊ ሰውነት በአዲስነት ለሚቀበለው ትርጉም የሚሰጥ። የለውጥ መንገድን የራሱ ላደረገ ሰው ትርጉም የሚሰጥ የጊዜ ቀለበት።
በዘመን መለወጫ ወቅቶች በአመቱ ውስጥ ሽልማት የተገባቸውን ለይቶ እውቅና የመስጠት ባህል እየተለመደ ያለ ባህል ሆኗል። በዘርፉ ላይ ጎላ ብለው የወጡና አስተዋጽኦ ያደረጉትን መርጦ የመሸለም ተግባር በአገራችንም በመላው ዓለምም የተለመደ ተግባር ነው። ሰዎች በአደባባይ የሚሸልሟቸው ወደ ደረጃው ከመውጣታቸው በፊት ራሳቸውን የሸለሙ መሆናቸውን አስበን እናውቅ ይሆን? ለራሳችን ከራሳችን በላይ የሚቀርብ ስለሌለ ራሳችንን ለመሸለም ማንም ሊቀድመን አይገባንም ብሎ የሚያምን ሰው የሚያደርገው። ለራስ ትርጉም በመስጠት የሕይወት ቅኝት ውስጥ የሚመዘዝ ሰበዝ።
አዲስ አመትን ለማብሰር የሰፈሩ ልጃገረዶች አበባይሆሽ ይላሉ። በየቤቱ ደጃፍ ሄደው እየቆሙ ዜማቸውን አሰምተው የሚሰጣቸውን እየተቀበሉ ከአንድ ቤት ወደ ሌላ ቤት የሚደረግ፤ ሁሌ የማይደረግ በልጅነት ወራት በጊዜ ቀለበት ውስጥ የሚሆን። ለልጃገረዶቹ ቤት ያፈራው ሲቀርብ እነርሱም በዜማ ምስጋናቸውን ያቀርባሉ። በጊዜ ቀለበት ውስጥ ከአንድ ምእራፍ ወደ ሌላኛው ምእራፍ ለመሸጋገር ቆሞ ማመስገን የተገባ ነው።
በምሥጋና ከአንድ ምዕራፍ ወደ ሌላ
ለምዶብን በአንደበታችን አመሰግናለሁ ከማለት ባሻገር በጊዜ ቀለበት ውስጥ ትላንትን ስንመለከት አስቀድመን ምስጋናን ብንከፍት እጅግ የተሻለ ነው። በአገራችን የትላንት ታሪክ ውስጥ ወቀሳ ይቀድመናል። እከሌ እንዲህ ሆኖ፤ እከሌ እንዲህ አድርጎ ወዘተ እንላለን። ትላንት ላንቀይረው እንዳለፈ ውሃ ነውና ለነገ ትምህርት የሚወሰድበት እንዲሆን በአመስጋኝነት ገጾቹን መመልከት በብዙ ይመከራል።
የምስጋና ባህል አዎንታዊ መንፈስን በመፍጠር ያለው ሚና ከፍተኛ ነው። በእኛ በኢትዮጵያን ዘንድ የምሥጋና ባህላችን ጠንካራ የሚባል አይደለም። በአጠገባችን ምሥጋና የሚገባቸው የበረከቱ ሰዎች ኖረው እንኳን አጠገባችን ሳሉ መመልከት ሳንችል ቀርተን እለተ ሞታቸውን እንጠብቃለን። አንዳችን በአንዳችን ሕይወት ውስጥ ያለን ቦታ ትርጉሙ ትልቅ ነው። ዛሬ ላይ የሆንበትን ቦታ ተመልክተን ወደኋላ ስንመለከት በሕይወታችን ውስጥ ትርጉም ያለው ተጽዕኖቸውን ያሳደሩ መልካም ሰዎችን እናገኛለን።
መልካም ሰዎችን ለማመስገን የሚደፍር ባህል መልካም ሰዎች እንዲበዙ የሚያደርግ ነው። መልካም ሰዎችም የጊዜ ቀለበት ውጤቶች ናቸው። የተዘራው ዘር ለሌላ ለሚዘራ ዘር እንዲሁ የሚቀርብ መሆኑን መረዳትም ይገባናል። አስተውለን ማየት ከቻልን መልካም ሰዎች በዙሪያችን አሉ። መልካም ሰዎች ግን መልካምነታቸውን ማየት የሚቻለው የተከፈተ አይን ስናይ ብቻ ነው።
የለቅሶ ስርዓታችን የሚወስደው ቀንና በለቅሶ ጊዜ የምናወጣው ጥልቅ ሃዘን ምንጩ የሟች መልካምነት ትውስታ ሆኖ ይታያል። ሟችን በጊዜ ቀለበት፤ ነዋሪውም እንዲሁ። አንዳችን በአንዳችን ውስጥ ያለን ቦታ የጨመረ በሆነ ቁጥር የለቅሶ ቀን ትርጉሙ ሌላ ነው። ለአንዳንዱ ለቅሶ መድረስ የሆነውን ግቡን ለመምታት ወደ ለቅሶ ቤት ይሄዳል። ሌላው ከልቡ አዝኖ ሲያጽናናም ይገኛል። ለሃዘንተኛው ግን ጉዳዩ ሌላ ነው። በሕይወት ዘመኑ መልካም ነገር የሆነለትን ሰው ማጣት፤ ጊዜ ሰጥቶ ጊዜ የወሰደውን። በመልካምነት ትዝታው ውስጥ ሆኖ ሃዘኑን ማስተናገድ። ከመልካም ሰው ትዝታ ውስጥ የሚወጣ፤ ጥልቅ ሃዘን።
የማመስገን ሕይወትን አቅጣጫ ስለማስተካከል ስናነሳ ቅደም ተከተሉን ከምንወደው ሰው ማድረጉ ምቾት የማይሰጣችሁ አንባብያን መፈጠራችሁ አይቀርም። ምክንያቱም “እንዴት ከፈጣሪ ቀድሜ ሰውን ስለማመስገን ላስብ” ልትሉ ስለምትችሉ። በእርግጥ አሳማኝ ምክንያት ነው። ነገር ግን በአጠገባችን ያለውን በአካል የምናውቀውን ሰው ሊመሰገን ሲገባው ያላመሰገንን እንዴት በአካል የማናውቀውን ፈጣሪን እናመሰግናለን? ይህን አመክንዮ በልባችን ይዘን ንባባችንን አስተካክለን መቀጠል እንችላለን።
በምሥጋና በጊዜ ቀለበት ውስጥ ከአንድ ሁኔታ ወደሌላው ስንሸጋገር አስቸጋሪው ሰውን በጠንካራ ጎኑ እንዲበረታ ባደረግነው ቁጥር ደካማ ጎኑን እየቀነሰ የመሄድ እድልን ይፈጥራል። አበባየሁሽ ብለው የሄዱ ልጆች በየቤታቸው ያሉትን አስቸጋሪ ሰዎችን አስበው ይህን ቢተገብሩ በቤታቸው ለውጥን ማየት መቻላቸው እሙን ነው። ሂደቱ አስቸጋሪው ሰውን መርዳት ብቻም ሳይሆን የራስን ደስታ የመፍጠር ሂደትም አካል ነውና። በጊዜ ቀለበት ውስጥ በምስጋና በር ውስጥ ያለንበትን ከባቢ የመቀየር። የአዎንታዊ ተጽእኖን ድባብ የመፍጠር። ራሳችን ጋር ባለው ነገር የሌላውን ውስጥ ለመቀየር የሚደረግ ጥረት።
ምሬትን ማስወገድ
በጊዜ ቀለበት ውስጥ የሚጠፋና የሚጎድል ይኖራል። ጥንዶቹ በብዙ ድካም የገዙትን ቀለበት በጠፋባቸው ጊዜ የተፈጠረባቸውን የስሜት መጎዳት ማሰብ ከባድ አይደለም። በጊዜ ቀለበት ውስጥም መውጣትና መውረድ አለ። ደስታችንን በሚነጥቁን አያሌ ምክንያቶች ሰው ብዙ ጊዜ ደስታውን የሚያጣው በራሱ ሳይሆን በሌሎች ነው። በሌባ የተሰረቀ ሰው በሌባው ምክንያት ደስታውን የተነጠቀ መሆኑን ያነሳል። በሕይወቱ ውስጥ መከዳት የገጠመው ሰው እንዲሁ የደስታው መነጠቅ ምክንያት ከዳተኛው ግለሰብ መሆኑን ጠቅሶ ይነሳል። ይህ እይታ እንዴት ስህተት ሊሆን ይችላል? ተብሎ ቢጠየቅ ምላሹ “እንደየትም ሊሆን አይችልም” የሚል ይሆናል።
በተቃራኒው ግን አደገኛው ልማድ መኖሩን መካድ አይቻልም። ሌሎች የደስታችን መደፍረስ ምክንያት ናቸው ብሎ መቀበል ሕይወታችን የተረጋጋና ወጥ የሆነ ድባብ ሳይኖረው ሁልጊዜ በውጫዊ ነገር እንቅስቃሴ ላይ የተመሰረተ እንዲሆን ሊያደርገው ይችላል። ውጫዊው ነገር ሁልጊዜ ተቀያየሪ ነው። በተቀያያሪው ነገር ላይ የሕይወትን መስመር ለመበየን መነሳት አሳሳች የሕይወት አቅጣጫን ያስይዛል። በተቃራኒው ያለው አደገኛው ልማድም ይህ ነው። በውጫዊው ነገር ምሬትን አርግዞ መኖር።
ሕይወትን በውስጣዊ እንጂ በውጫዊው ሁኔታ እንድትመራ መፍቀድ አይገባም የሚለው አተያይ ደጋግሞ ማሰላሰል የሚገባ ነው። አንባቢው በሕይወቴ ተጎዳሁ የሚልባቸውን ክስተቶች ለማሰብ ይሞክር። ምን ያህሉ ከውጫዊ አካል በኩል በመጣ ተጽእኖ የተፈጠረ እንደሆነ ያስባል? ሁሉም የመሆን እድሉ ከፍተኛ ነው። ከጉዳቱ ለመውጣት የተሄደበት ነገር “ውጩን በመቀየር” ወይንስ “ውስጥን በመቀየር” የሚለውን አስከትሎ እንዲሁ ይጠይቅ። ምሬት ውስጥ የሚከርሙ ሰዎች ውስጥን ለመቀየር አንድ እርምጃ መራመድ የከበዳቸው ሆነው ስለሚገኙ።
ምሬትን አስወግዶ በጊዜ ቀለበት ውስጥ አትራፊ ለመሆን የሚተላለፈው መልእክት በውስጣዊ ጥንካሬያችሁ ውጩን ተቆጣጠሩት የሚል ነው። ውጫዊው ነገር በየወቅቱ የሚቀያየር ነው። በመሆኑም የተረጋጋ ሕይወትን ከመምራት የሚከለክለው እርሱ ነው። መፍትሄው ውስጥን መገንባት፤ በተለዋወጭ ውጫዊ ተጽእኖ ውስጥ እየቀዘፈ ወደ መዳረሻው መሄድን ግቡ ያደረገ ጉዞ።
ምሬትን አስወግደው በጊዜ ቀለበት ውስጥ አትራፊ ሆነው የሚወጡ ሰዎች የመሰጠት ቁርጠኝነት፣ ትእግስት፣ ፍቅር፣ ተስፋ፣ ራእይ፣ ማካፈል፣ ወዘተ በውስጣቸው ያሉ ናቸው። በመሰጠት የታነጸ ሰው በዝናብ በቸነፈሩ ውስጥ አልፎ ማሳካት የሚፈልገውን ለማሳከት ስለሚሄድ የውጫዊው አየር መቀያየር ከጉዞው አይመልሰውም። አትሌቶቻችን ለእዚህ ጥሩ ምሳሌ ሊሆኑ ይችላሉ። ትእግስትን የለበሰ ሰው ተስፋ አስቆራጭ የሆኑ ከመስመር የሚያወጡ ጉዳዮች በገጠሙ ልክ እየተጋፈጠ ተጨማሪውን አንድ ቀን በደስታ የሚቀበል በስተመጨረሻ የድል ማለዳውን ከማየት የማይመለስ ነው። ሌሎቹም እሴቶች ድምር ውጤታቸው የተረጋጋ፣ የሚያደርገውን የሚያውቅ፣ አካሄዱ ከዓላማው አንጻር የተቃኘን ሰው ያደርጋሉ።
ምሬት በምሬት ይባዛል። በምሬት ውስጥ ያለን ሰው ለማውጣት መሞከር ተገቢነት አለው፤ ነገር ግን ምሬቱ ተጋብቶብን የጊዜ ቀለበታችን በምሬት የተገመደ እንዲሆን ማድረግ ግን አስፈላጊ አይደለም። ውሏችንን እንደ ህልማችን ማድረግ ተገቢነት ይኖረዋል። ህልሙ እግር ኳስ ተጫዋች የሆነ ሰውና ለእዚያ እየኖረ ያለሰው ውሎውን ተመሳሳይ ራእይ ከሚጋራው ጋር ቢያደርግ ጥቅሙ ለእርሱ መሆኑ እሙን ነው። በተመሳሳይ ሁኔታ ከፈጣሪያችን ጋር ጊዜን ማሳለፍ። ከፈጣሪ ጋር እና አብረውን ካሉ መልካም ሰዎች ጋር ጊዜን በማሳለፍ ረገድ ውስጣችን ውጫዊውን ተጽእኖ ተቋቁሙ ማደግ የሚችልበትን አቅም ያገኛል።
የአልችልም ጠላት መሆን
ጥንዶቹ ቀለበቱን ከእጃቸው ለማጥለቅ የሚችሉትን ሁሉ አደረጉ። በስተመጨረሻ ግን በጊዜ ቀለበት ውስጥ ወደቁ፤ ጥንቃቄ በሚፈልገው ጊዜ ላይ ባለመጠንቀቅ ያሰቡትን ማድረግ ሳይችሉ ቀሩ። እችላለሁ ብሎ መነሳት ለብዙ ሰው ይቸግረዋል፤ ምክንያቱም እችላለሁ በማለት ብቻ የሚሆን ነገር ስለሌለ። የአልችልም ጠላት ለመሆን ራስ ላይ መስራት ስለሚገባ። አዲስ አመት በመጣ ቁጥር በአመቱ ውስጥ ምን ማሳካት እንዳሰብን የመዘርዘር ልማድ ይኖረን ይሆናል። ማሳካት የፈለግነውን ማሳካትን ስናስብ አስቸጋሪ የሚሆኑብንን ነጥቦችም እንዲሁ ልንለያቸው እንሞክራለን። ለለውጥ መነሳትን ስንመርጥ አትችልም የሚለን በአካባቢያችን የሚሰማ ድምጽ እግራችን ላይ የታሰረ ገመድ ሆኖ ልናገኘው እንችላለን።
አትችልም፤ አትችይም የሚለው ድምጽ በበረከተበት ከባቢ ውስጥ እየኖረን በእችላለሁ መንፈስ ለለውጥ የሚነሱት ማግኘት አንችልም። ልጆች ሲያድጉ የሚነገራቸው፤ ታዳጊዎ ብላቴና ከውስጧ የመዘገበችው፤ ወጣቱ ለለውጥ ጊዜውን እንዲጠበቅ የሚጠበቅበት ወዘተ በአልችልም መንፈስ ውስጥ ሆኖ ለመስራት የሚነሳው ሁሉ እየጨነገፈበት ቢቸገር እንዴት ሊገርመን ይችላል።
አለመቻልህን በውስጥህ ከምታመላለስ መቻልህን ለራስህ ንገረ። የጊዜ ቀለበት ውብ ሆኖ የሚታየው በመቻል መንፈስ፤ ለመቻል ተግባራዊ እርምጃን በመራመድ ነውና። በዙሪያህ ያለው ሳር ቅጠሉ ስለመቻል የሚናገረው ድምጽ ጎርናነቱ በዝቶ ጆሮህን እስክትይዝ የሚያደርስ ቢሆንም አሁንም መቻልን አስብ። ቀላል አይደለም ከባድ ነው። የምንኖርበት የድህነት ጥግ ይታወቃል። አልጠራ ያለው የፖለቲካ መንገዳችን የፈጠረው ውጥንቅጡ እንዳለ ነው። የትምህርት ጥራቱ አሽቆልቁሎ ባለዲግሪውና ዲግሪው የሌለው መካከል በእውቀት ላይ ልዩነት የሌለው ሆኖም ይታያል። ሁሉም ነገር አለመቻላችንን እየነገረን ባለንበት ዘመን ውስጥ ስለመቻል ማንሳት እብደትም ሊመስል ይችላል። በጊዜ ቀለበት የለውጥ መንገዱ ውስጥ ግን የመቻል መንፈስ ግን የሚይዘው ቦታ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። የመቻል መንፈስ ለሁላችን እንዲሆንልን ለጊዜ የምንሰጠው ትርጉም ውስጥ ቦታ ይኑረው። በአንድ ወር ውስጥ ይህን ማድረግ እችላለሁ፤ በአመት ውስጥ፤ በሦስት አመት ውስጥ ብሎ ግብን ለማስቀመጥ የመቻል መንፈስ እጅጉኑ ያስፈልገናል።
በምሥጋና፤ ምሬትን በማስወገድ እና እችላለሁ ብሎ በመነሳት የጊዜ ቀለበትን እናጥልቅ። ጊዜ ዳኛ ይባልስ የለ። ጊዜ የንጉሥ ቀለበት ሲሆን።
በአገልጋይ ዮናታን አክሊሉ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 9/2014