የክረምቱ አገባብ አስደስቶናል፤ ከብዶናልም፡፡ ደስታው ፈጣሪ ራርቶልን በቂ “ሰማያዊ ጠል” አግኝተን ተፈጥሮና ፍጡራን በጋራ መፈንደቃችን ሲሆን፤ በርካታ አካባቢዎች በጭጋግ ተሸፍነው እስከ እኩለ ቀን ድረስ መዋላቸው ደግሞ ክረምቱን ትንሽ ጠነን ሳያደርግብን እንዳልቀረ በብርዱ ማንቀጥቀጥ እየመዘንነው ነው፡፡
እትት እያሰኘ ወፍራም አልባሳት እንድንለብስ ያስገደደንን የክረምቱ መግቢያ ብርድ “አጥንት ዘልቆ ይገባል” በማለት መግለጽ የጀመርነው ሰኔ ጣጣውን ጨርሶ ከሐምሌ ወር ጋር ርክክቡን ለመፈጸም ቀናት ሲቀሩት እንደነበር የሚዘነጋ አይደለም፡፡ “ቀድሞ የገባ ክረምት ለእሸት” እንዲሉ የሰኔና የሐምሌ ባህርይ መለዋወጥ እጅግም አላስከፋንም፡፡
ለዘመናት ተጣብቶን የኖረው የድርቅ መርገምት እንደለመደው ድንገት አድፍጦ በመከሰት በአገራችን የበጋ ወራት ያደረሰው የጉዳት ጠባሳ ገና ስላልጠገገ፤ “ዝናቡና ብርዱ በረታብን” እያልን ማማረራችንን ፈጣሪ እንደ አፍ ወለምታ እንዲቆጥርልን እንጂ የምር አድርጎት ባይቀጣን እንወዳለን፡፡ አንዳንድ ውለታ አስታዋሽ ዜጎች ለተያያዝነው መልካምና ተመጣጣኝ የዝናብ ወቅት ለሦስት ተከታታይ ዓመታት ለተተገበረው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር “ገለታ” ሲያቀርቡ እያደመጥን ነው፡፡ ጸሐፊውም ከአመስጋኞቹ ጋር ይተባበራል፡፡
የክረምቱን መግባት ተከትሎ “ችግኝ ተከላ” የሚለው ሀረግ ወትሯዊ የዜጎች ሁሉ የተለመደ መግባቢያ ወደ መሆን ደረጃ ከፍ ማለቱ ትልቅ የባህል ለውጥ ውጤት እንደሆነ የሚያከራክር አይደለም፡፡ የአረንጓዴ አሻራ ትሩፋት ወጣኙ፣ ጎትጓቹ፣ ቀዳሚ አስተባባሪውና ተግባሪው ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችንን ከወንበራችን ከፍ ብለን ብናመሰግናቸው ይገባቸዋል ባይ ነን፡፡
መቼም ግራ ገቡ ዲሞክራሲያችን በአመለካከታችን ግራና ቀኝ እንድንረግጥ አንዴ አወፍፎናልና “ምሥጋናው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አይገባም!” በማለት የፖለቲካ አክርማ የሚሰነጥቁና “አመስጋኞችን” የሚኮንኑ ዜጎች የሚኖሩም ከሆነ መሟገቻ ሃሳባቸውን ብናደምጥላቸው ክፋት የለውም፡፡
አብዛኛው የማሕበረሰብ ክፍል አባላት በተባበረ ድምጽ በጎነትን አመስገኖ ክፋትን ለመኮነን ለምን አቅም እንዳጣና ሞራሉ እንደወደቀ ተመራማሪዎች ጥናት አድርገው ችግሩንና የመፈወሻውን ዘዴ ቢያመላክቱን አንጠላም፡፡ ያለበለዚያ በዚህ የተሳከረ የማሕበራዊ ሚዲያ ሜዳ እየፈነጩ የኅሊናቸውን ጨርቅ ጥለው ያበዱ ውሱን ዜጎች ወደ ቀልብያቸው ተመልሰው ካልተፈወሱ በስተቀር ነገም ለከፋ ጭጋግ ተጋላጭ መሆናችን አይቀርም፡፡ መመሰጋገን፣ መደናነቅ፣ መከባበር ወደፊት የታሪካችን አካል እንጂ የኑሯችን መገለጫዎች ከመሆን እንዳይደበዝዙ ስጋት ገብቶናል፡፡
አነሳሳችን ስለ ክረምቱ ጭጋግና ስለሚያለመልመን ጠል ጫን ብለን በዝርዝር ለመተረክ አይደለም፡፡ ይልቁንስ “ጭጋግና ጠል” የሚለው አባባል ወቅታዊውን የዕለት ተዕለት አኗኗራችንን በሚገባ ይገልጽልን ስለመሰለን ሀረጉን የተዋስነው ለተመሳስሎ እንዲረዳን ነው፡፡ በእነዚህ ሁለት የተፈጥሮ ክስተቶች አማካይነት የየግላችንን ፈተና ብቻ ሳይሆን የአሁናዊ አገራዊ ኑሯችን መልክ ብንፈትሽበት ጥሩ ገላጭ ይሆናል ብለን በማመን ጭምር ነው፡፡
ጭጋግ በደቃቅ የውሃ ነጠብጣብ ወይንም በብናኝ ቁሶች አለያም በአቧራዎች የተሞላ ሲሆን ለአደጋ የማጋለጥ አቅሙም ከፍ ያለ ነው፡፡ ሰሞኑን እንኳን በተለይ ማለዳ ማለዳ አዲስ አበባን እንደ ብርድ ልብስ እየሸፈና ያለው ጭጋግ ለብዙ ትራፊክ ነክ አደጋዎች መንስዔ ሲሆን ደጋግመን አስተውለናል፡፡
በአየር በረራ ላይም ከፍተኛ ተጽእኖ አሳድሮ ጥቂት የማይባሉ አውሮፕላኖቻችን ሳይቀሩ የግድ ስለሆነባቸው በጎረቤት አገራት የአየር መንገድ ተርሚኖሎች እስከ ማለፍ የደረሱ መሆናቸውን ከዜናዎች ተከታትለናል፡፡ በሰማያዊ ጠል የመሰልነው የዝናብ በረከት የመወደዱን ያህል የጭጋግ ክስተትም ባይኖር እያልን መመኘታችን ስለዚሁ ነው፡፡
በጠል የሚመሰሉና እንደ በረከት ሊቆጠሩ የሚገባቸው አገራዊ ስኬቶች፤
የአገራችን ርእይ በእጅጉ የሚያማልል ነው፡፡ “ሃሴት እያደረግንና” በሃሌሉያ ዝማሬ እያደነቅናቸው ያሉት የተጠናቀቁና በመጠናቀቅ ላይ ያሉ የልማት ጅምሮች እንኳንስ ለእኛ ለባለጉዳዮቹ ዜጎች ቀርቶ ለባእዳንም ቢሆን “በመጎምዠት ምራቅ የሚያስውጡ” መሆናቸው አልጠፋንም፡፡ ሰሞኑን ብስራቱ ሊናኝ ቋፍ ላይ የደረሰውን የሦስተኛ ዙር የህዳሴ ግድባችንን የውሃ ሙሌት እንደ አንድ “ጠል” ወይንም በረከት የምንቆጥረው የዘመናችን ትውልድ አሻራ ያረፈበት ታላቅ ስኬት ስለሆነ ነው፡፡
በገበታ ለአገር ፕሮጀክት እየተፋጠኑ ያሉት ፕሮጀክቶች ከጥቂት ዓመታት በኋላ ተጠናቀው ወደ ስራ ሲገቡ አስተዋሽ አጥተው ሲያንጎላጅጁ የከረሙት አካባቢዎች ምን ሊመስሉ እንደሚችሉ ማሰብ በራሱ ውስጥን ያረሰርሳል፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ “ከስንዴ ለማኝነት ወደ ስንዴ ላኪነት እንሸጋገራለን” የሚለው እቅድ ወደ ተግባር ሊለወጥ ጫፍ ላይ መድረሱን ከእኛዎቹ ብቻ ሳይሆን ከባእዳን አፍ ጭምር “ተግባራዊ እንደሚሆን” ማረጋገጫውን ስንሰማ ውስጣችንን አንዳች ልዩ የደስታ ስሜት ሲወረን ይታወቀናል፡፡
በዘርፈ ብዙ የማዲያት ደዌ የጠወለገው የአዲስ አበባ መልኳ በተለያዩ መገለጫዎች እየወዛ መሆኑን በድፍረት ባንገልጽ ኩነኔው እንኳን ቢቀር በውስጥ ኅሊናችን መገሰጻችን ግን አይቀርም፡፡ ከድህነት ወለል በታች እንዲማቅቁ የተፈረደባቸው ዜጎች ከዝናብና ከብርድ የማያስጥላቸውና ለወጉ ያህል ብቻ ቤት እየተባለ የሚጠቀሰው ደሳሳ ጎጇቸው እየፈረሰ ወደ ተሻለ መኖሪያ ሲሸጋገሩ መመልከት ኑሮውን ላልቀመስነው ለብዙዎቻችን ተራ ጉዳይ ቢመስልም የመከራውን ገፈት ሲጎነጩ ለኖሩት ግፉዓን ግን እንደ ዳግም ልደት መቆጠሩ ከልባችን ጠልቆ ባናመሰግን ኃጢያቱ ለእኛ በረከቱ ለእነርሱ መሆኑ አይቀርም፡፡
“በጠል” የሚመሰሉ እነዚህና መሰል በርካታ አገራዊ ስኬቶችንና ተስፋዎችን ባሰብን ቁጥር የዛሬያችን ጭጋግ ከብዶ ግራ እያጋባ ቢያንገዳግደንም ነገ አንዳች የብርሃን ጨረር እንደሚፈነጥቅና ጭለማችን እንደሚገፈፍ ማረጋገጫ ስለሚሆነን በእፎይታ መተንፈሳችን አይቀርም።
ፈራን! ለምን ፈራችሁ አትበሉን!?
ከላይ የተዘረዘሩ መሰል ደስታዎችን አጣጥመን ባጨበጨብንላቸው አገራዊ ስኬቶች ገና ፈንድቀን ሳንጨርስ እያጋጠሙን ያሉት በጭጋግ የሚመሰሉ መከራዎቻችን ፍርሃት ላይ እየጣሉን እንደሚያንዘፈዝፉን ባንገልጽ አይበጅም፡፡ ስለዚህም ውስጣችንን ብርድ ብርድ እያለው መንቀጥቀጡ የዘወትር ተግባራችን እስኪሆን ድረስ ለምን መከራችን እንደከበደ ምክንያቱን ለማወቅ ግራ ተጋብተናል፡፡ “ለምን ፈራችሁ?” ተብለን እንደማንሞገት ተስፋ እናደርጋለን፡፡ ምክንያቱም በምናያቸውና በምንሰማቸው ብቻ ሳይሆን እየገጠሙን ያሉ እጅግ ውስብስብ ችግሮች ሲበዙብንና ሲበረቱብን ዛሬያችንንም ሆነ ነጋችንን ከመጠራጠር ውጭ ምን አማራጭ ይኖረናል፡፡
አንዳንድ ጥናቶች ከሰው ልጆች፣ ከእንስሳትም ሆነ ከማንኛውም ቁስ የሚወጣው ድምጽ እስከ ምጽዓት ቀን ድረስ በከባቢ አየር ላይ እየተንሳፈፈ (Hovering) ይኖራል እንጂ “ብን ብሎ እንደ ደመና አይጠፋም” በማለት በሳይንሳዊ ግኝታቸው ሲያስገርሙን ባጅተዋል፡፡ የውስብስቡን ሳይንስ ግኝትና ትንተና በአግባቡ ለማሳየት የጸሐፊው እውቀት አናሳ ስለሆነ በእንዴታው ላይ እጅግም ዝርዝር ማብራሪያ ለመስጠት አይዳፈርም፡፡
ሳይንሱ እውነቱን ከሆነና ድምጻችን በኖ የማይጠፋ ከሆነ “የአገራችንን አየር እንደ ጭጋግ የሞላውና የወረረው ድምጽ የበረከት ነው ወይንስ የእርግማን?” ብለን ብንጠይቅ ከመራቀቅ ሊቆጠር፣ ከተስፋ መቁረጥ ጋርም ሊያያዝ አይገባም፡፡ አንደ ማጋነን አይቆጠር እንጂ የአገራችንን ዳመና የሞላውና ከጭጋጉ ጋር ተዳምሮ እንደ ዳፍንት ቁልቁል የተጫነን አንዳች እርግማን ሳይኖርብን እንደማይቀር እንጠረጥራለን፡፡ አየራችን ተበክሏል፡ ፡ ዳመናችን ጠቁሯል፡፡ እንዴታው ግራ ቢያጋባንም ልንፈወስና ልንፈታ ግን ግድ ይለናል፡፡
ግፈኞች ከፈጸሙት የጦር ሜዳ እልቂትና ውድመት ገና አላገገምንም፡፡ ማገገም ብቻም ሳይሆን ወደፊት ለአገሪቱ የሚተርፈውን መዘዝ ለመተንበይ እየተቸገርን ብንፈራም ሊፈረድብን አይገባም፡፡ በተለየ ሁኔታ ግን ሰሞኑን በግላጭ የምንሰማውና በተግባርም የምንመለከታቸው አንዳንድ ዘግናንኝና ሰቅጣጭ የውንብድናና የዘረፋ ድርጊቶች ከማሳፈርም አልፈው አገርን አንገት ያስደፉ እንደሆኑ ለመረዳት ብዙ ምርምር አይጠይቅም፡፡
በቅርብ ሳምንታት ውስጥ በነዳጅ አቅርቦት ላይ የተፈጸመውን የኅሊና ቢሶች ተግባር “ጉድ! ጉድ! እንደምን የነዳጅ ቦቴ ከነተሳቢው ቁጥቋጦ ውስጥ ለመደበቅ ይሞከራል? ተደብቆስ እስከመቼ ይቆያል? ይደበቅ እንኳን ቢባልስ ከሰው ዓይን መሰወር ይቻል እንደሆን እንጂ እንዴት ከኢትዮጵያ ከራሷ ይሰወራል?” እየተባባልን ስንተክዝና ስንቆዝም መክረማችን አይዘነጋም፡፡
“ክፉ ቀን አያምጣብን እንጂ ቢመጣ ዛሬ ቦቴ ከነተሳቢው የደበቁ ነገ በደበቁት ነዳጅ አገር ለማቃጠል የማያመነቱ ስግብግቦች ምን ያደርጉን ይሆን?” የሚለውን ጥያቄ ገና ጠይቀን መልስ ሳናገኝ ሰሞኑን የተፈጠሩት የከፉ ክስተቶች ይበልጥ በፍርሃት መናጣችንን መሸሸግ አይቻልም፡፡
ለስደተኞች፣ ለተፈናቃዮች፣ ከጦርነት እሳት በተአምር አምልጠው ነፍሳቸው ለተረፈችውና ጊዜ ከድቷቸው የወገኖቻቸውን እርጥባንና የመንግሥትን እጅ ነጋ ጠባ እየተጠባበቁ በመከራ ውስጥ ካሉ ዜጎች አፍ የእርዳታ እህላቸው ተሸጦ በጥቂት ስግብግብ ግለሰቦችና ቡድኖች አገር ስትራቆት መስማት እንኳን ለእኛ ለመከረኞቹ ዜጎች ቀርቶ ለረጂዎቻችንና ለልማት አጋሮቻችን ሳይቀር እንቆቅልሽ እንደሚሆን አይጠረጠርም፡፡
ለካስ አንዳንድ ሰው ልብስ ለብሶ በሰው መሃል የሚመላለሰው “በሰብዓዊነት ክብር” ሳይሆን በአውሬ ፍጥረቱ ነው ብለን እስከ ማመን ደርሰናል፡፡ እኒህን መሰል የሙት ኅሊና ባለቤቶችና የግፍ ብልቃጦች (Lords of poverty እንዲሉ) የክፋትና የጭካኔ ጥግ ስንሰማ ብንፈራ ይፈረድብናል? “አትፍሩ” ተብለን ብንጽናናስ በርግጡ መንፈሳችን ያርፍልናል?
በጋራ ቤቶች እጣ አወጣጥ ላይ የተፈጸመውን “በመዋቅር የተውጠነጠነ ወንብድናና የወንበዴዎች ትራዤዲ” እያየንና እየሰማን ፍርሃት ቢያርደንስ ያስወቅሰናል? የገበያውን እብደት፣ የአገራዊ ኢኮኖሚውን ሕመም፣ በፍትሕ ሥርዓቱ ውስጥ ከራሳቸውም፣ ከሰዎችም፣ ከፈጣሪም፣ ከማሉለት ሥነ ምግባርም ጋር በተጣሉ አንዳንድ ራስ ወዳድ የፍትሕ ሥርዓቱ ቤትኞች እየተፈጸሙ ያሉትን እርኩሰቶች ስንሰማ ፍርሃት ብቻ ሳይሆን “ኤሌሄ! ኤሎሄ!” እያልን ወደ ፈጣሪ ብንጮኽ “አምላክ አርፎ ይኑርበት አትረብሹት?” ተብለን በሃይማኖት አባቶች ልንወገዝ ይገባል? በጭራሽ ሊታሰብ አይገባም፡፡
ቀስ በቀስ እየተጋለጡ ያሉት በአገርና በሕዝብ ላይ የተፈጸሙት የዛሬዎቹ በደሎች ትናንት ምን ሲሰራ እንደኖረ ፍንጭ ስለሚሰጡ የምንፈራው ለዛሬ ብቻ ሳይሆን ለትናንቱና ለነገውም ጭምር ነው፡፡ ፈራን፣ ተፈራራን፣ አስፈራን እኮ ምን እንበል? ምንስ እንሁን!? ኢትዮጵያ ሆይ እግዜር ያጽናሽ!
በ(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን ሐምሌ 9/2014