ታታሪ ናት፤ ደከመኝ ማለትን አታውቅም። በዚህ ጥንካሬዋ የማይወዳት የለም።ገና በልጅነቷ በሰሜን ጎንደር ከቤተሰቦቿ ጋር ስትኖር ከማጀት ወጥታ እየሠራች ቤተሰቧን ለማስተዳደር የምትባዝነዋ ታታሪ ሴት ለትዳር የማይፈልጋት አልነበረም።ከፈላጊዎቿ መካከል ዕድል ቀንቶት ጎሹ አከላት ፈቃድ አገኘ።በደስታ ትዳር መሰረቱ፤ ነገር ግን የሚወዳት ብዙ ነውና ቅናት እያንገበገበው ኑሮን መግፋት ከበዳቸው።
ልጅቷ ታታሪናትና ጥንካሬዋ አቆያቸው።ትዳራችን ከሚበተን ልጅ እንውለድ ብላ አሰበች።ቀናት እና ከአንድም ሁለት ልጆችን ወለዱ።ተፈላጊዋ ልጃገረድ እማወራ ሆነች።ሆኖም ልጆች ወልዳም ጎሹ ቅናቱ አልለቀቀውም።የጎሹ ጭቅጭቅ ስላማረራት አንድ የመፍትሔ ሃሳብ አቀረበች።ቅናቱ እንዲለቀው ‹‹ከሚያውቁን ሰዎች እና ከአካባቢው ብንርቅ ይሻል ይሆናል›› አለች።ወደ ደቡብ ወሎ እንዲሔዱ ጥያቄ አቀረበች።ጎሹ በደስታ ተስማማ።
ወደ ደቡብ ወሎ ሔዱ።እማወራዋ ደቡብ ወሎ ቢሔዱም ንግዷን እያጧጧፈች ተወዳጅነትን አተረፈች።አሁንም ኑሮ ተመሳሳይ ሆነ።እማወራዋ ትታትራለች።ጎሹ በበኩሉ ከሥራ ይልቅ አዕምሮውን የሚያደክመው እርሷን በመከታተል እና በመቅናት መሆኑን ተከትሎ ክፋት እና ተንኮል ልቡን አደነደነው።
ታታሪዋ እማወራ የጎሹ ፀባይ አለመሻሻሉ እያደማት ነው። እርሷ ደክማ እየነገደች በምታመጣው ገንዘብ አንድ እና ሁለት ብቻ ሳይሆን ሶስተኛ ልጅንም ለማሳደግ ተገደደች።በተጨማሪ ደቡብ ወሎ ላይም ኑሯቸው ‹‹ከወንድ ጋር አየሁሽ›› በሚል የጎሹ ጭቅጭቅ እና ንትርክ ትዳራቸው አደጋ ላይ ወደቀ።ትዳር እንዳይበተን ፅኑ ፍላጎት የነበራት ታታሪዋ እማወራ በድጋሚ ትዳሯን ለማዳን ሌላ አካባቢ እንዲሄዱ ወሰነች።ድሬዳዋ ከተማን መኖሪያቸው እንዲያደርጉ ሃሳብ አቀረበች።
የድሬዳዋ ኑሮ
እንደገና መላ ቤተሰቡ አካባቢ ለመቀየር ተገደደ። ድሬዳዋ ገቡ።ሆኖም የጎሹ ሁኔታ ምንም ለውጥ አላመጣም።ለተወሰነ ጊዜ መልካም ይሆንና መልሶ ይቀያየራል።በቅናት ቤቱን በመበጥበጥ ልጆቹን እና ሚስቱን ያውካል።ከመሥራት ይልቅ በወሬ እና በአሉባልታ በመጠመድ እማወራዋን በገባች በወጣች ቁጥር ይነዘንዛል።እማወራዋ ግን እንደተለመደው የእርሱን ጭቅጭቅ ችላ እየተሯሯጠች እየነገደች ልጆቻቸውን ማሳደግ ቀጠለች።
ድሬዳዋ የተለያዩ ቀበሌዎች እና መንደሮች የተለያዩ ነገሮችን በመነገድ ታዋቂነትን አተረፈች።ከሰዎች ጋር ትግባባለች፤ ትሠራለች፤ ትደክማለች።የያዘችው ደግሞ ይባረክላታል።ባለቤቷ እየበጠበጠ አላስቆም አላስቀምጥ ቢላትም፤ በጤና ውላ መግባቷን አመስግና ለልጆቿ ስትል ሁሉን በመቻል ኑሮዋን ገፋች።
ደከመኝ የማትል ታታሪ እና ጠንካራ በመሆኗ በዛው በድሬዳዋ ከተማ ዜሮ ሁለት ጎሮ ተብሎ በሚጠራው ሰፈር ሶስት ልጆቿን ማሳደግ ለእርሷ እጅግ ከባድ አልነበረም።እማወራዋ ብርድ እና ፀሃይ ሳትል ልባሽ ጨርቅ በመሸጥ ልጆቿን ለማስተማር ብትደክምም አልከፋትም።የጎሹ ቅናት እና ጭቅጭቅ ግን ሰላም እየነሳት ጤናዋን እስከማቃወስ ደረሰ።በዚህ መልኩ ከአቶ ጎሹ ጋር 22 ዓመታት አለፉ።ልጆቹ አደጉ ትልቅየዋ 20 ዓመት ሞላት።
የትዳር መበተን
አሁን ታታሪዋ እማወራ የአባወራው ጎሹ ጭቅጭቅ አሰልችቷታል።እርሱ በበኩሉ የእርሷ ተወዳጅነት አሁንም ያንገበግበዋል። እንደጎረምሳ እምቡር እምቡር እያለ ‹‹ዘራፍ ለምን ተደፈርኩ?›› በማለት ቤተሰቡን ያምሳል።ቅናት ጭንቅላቱን ስለተቆጣጠረው የሚናገረውን እና የሚያደርገውን አያውቅም። የአካባቢው ሰው እስከሚታዘበው ቤተ ሰቡን ያሰቃያል።
ልጆች የአባታቸው ክፋት ቢያበሳጫቸውም ምንም ማድረግ አልቻሉም።በዝምታ ይታዘቡታል። ሲሰድባቸው ከማዳመጥ ውጪ የሚሉት ነገር አልነበረም። እናታቸው ለፍታ ባገኘችው ገንዘብ የሚገዛው ቀለብ ለጎሹ በስሎ እና ጣፍጦ ይቀርብለታል።ከእማወራዋ ገንዘብ ነጥቆ ጠጥቶ አምሽቶ ይገባል።ይህን አታድርግ የሚለው የለም።የሚቃወመው ባለመኖሩ በድጋሚ ይበሳጫል።እንደተለመደው እየደነፋ ይሳደባል፤ ካልተደባደብኩ እያለ ሰው ያስቸግራል።እማወራዋ ከእርሱ በተቃራኒው እርሱ ሰነፍ ሲሆን እርሷ ጎበዝ፤ እርሱ ወደ ኋላ ሲል እርሷ ወደ ፊት፤ እርሱ ትዳሩን ለማፍረስ ሲሞክር እርሷ እያባበለች ትዳሯን ለማቃናት በዝምታ ስታልፍ፤ እርሱ ሲቀና እርሷ ስትታገስ ጭራሽ የበታችነት ስሜት እየተሰማው ሌላ ነገር ለመፈፀም ተነሳሳ።
አንድ ነገር አሰበ።2008 ዓ.ም ድሬዳዋ ላይ ክረምቱ አልበረታም።እንደውም አልፎ አልፎ ሙቀት አለ።የድሬዳዋን ሙቀት ትቶ በጨለማው ሃምሌ በክረምቱ ዝናብ አምርሮ በሚዘንብበት ጊዜ ያሰበውን ለመፈፀም ወደ ትውልድ አካባቢው ሰሜን ጎንደር ሔደ።ሚስቱን የሚያስቀናበትን መንገድ አውጠንጥኖ ባሰበው መንገድ በቅናት አሳብዳታለሁ ብሎ ደመደመ።
ለሰዎች የልጆቹን እናት ከፈታ መቆየቱን ነግሮ ሚስት እንዲፈልጉለት አብሮ አደጎቹን ጠየቀ።በክረምት ለማግባት እንደተጣደፈ ጎረምሳ ታታሪዋን ሚስቱን ለማስቀናት ሁለቱም ከሚያውቋቸው ሰዎች የተወለደችውን የአካባቢያቸውን የሰሜን ጎንደር ጉብል በአደባባይ አገባ።ጋብቻውን የፈፀመው በወረሃ ነሐሴ 2008 ዓ.ም ነበር።ዓላማው ሚስቱን ማስቀናት በመሆኑ ብዙም ሳይቆይ ጥቅምት 2009 ዓ.ም አዲስ ሙሽራውን ይዞ ወደ ድሬዳዋ ተመለሰ።
ጎሹ እንዳሰበው አልሆነም።እማወራዋ ትዳሯ መበተኑን፤ ጎሹ አዲስ ሚስት ከሰሜን ጎንደር ማምጣቱን ሰማች።ከመቅናት ይልቅ ‹‹ተገላገልኩ›› ብላ ፈነደቀች።‹‹አንድ አይደለም አስር ሚስት ማግባት ይችላል።የምኖረው በጉልበቴ፤ ልጆቼን የማሳድገው በላቤ ነው ›› አለች።ጎሹ የፈፀመው ድርጊት ምንም አላስከፋትም።ለጎሹ ይሔ ያልተጠበቀ ምላሽ በመሆኑ አለመቅናቷ አበሳጨው።
ብስጭቱ እንደበፊቱ በቅናት እንደሚበሳጭበት ጊዜ ቀለል ያለ አልነበረም።እጅግ በጣም ማሰብ እና መብሰክሰክ ጀመረ።ነገር የሚፈልግበትን መንገድ አስመልክቶ ማውጠንጠን ያዘ።የአሁኑ ትዳር እንደቀደመው ትዳር እንደማይቆይለት ገምቷል። ቀድሞም ያገባው ይዘልቅልኛል ብሎ ሳይሆን ታታሪዋን ቤተሰብ ወዳድዋን ሚስቱን ለማስቀናት አስቦ ነበር።ነገር ግን እንደገመተው አልሆነም፤ ተስፋ ቆረጠ።ዝንጀሮ ገደል አካባቢ ቤት ተከራይቶ ያስቀመጣት አዲሷ ሚስቱ እንደታታሪዋ ሴት የሚበላውን እያቀረበች እንደማትንከባከበው አረጋግጧል።ስለዚህ ወደ ድሮዋ ሚስቱ ለመሔድ ከቤት ወጣ።
አስከፊው ጥቅምት
የጥቅምት ወር ከጀመረ አስር ቀናት አለፉ።ድሬዳዋ ላይ ለሊት ለሊት እንደሌላው አካባቢ ቅዝቃዜው እና ውርጩ የበረታ ባይሆንም በተወሰነ መልኩ የዛን ቀን ቀዝቃዛ ነበረ።ከጠዋት ጸሀይ ጋር ማልዶ የተከሰተው ውርጭ እስከ ቀትር ዘልቋል።ለወትሮ በወበቅ የምታስጨንቀዋ ድሬዳዋ የዛን ቀን አየሯ የመቀዝቀዝ ዝንባሌ ታይቶበታል።በርካቶች ከድሬዳዋ ሙቀትን እንጂ ቅዝቃዜን የማይፈልጉ በመሆናቸው ብዙዎች ቤታቸው ክትት ብለው ውለዋል።የባሰበት ካልሆነ በቀር ብዙሃኑ ከቤት አልወጣም።
ታታሪዋ እማወራ ግን አልተኛችም።አምላኳን ለምና ፀሎቷን አድርጋ ከቤቷ ማልዳ በመውጣት እንደልማዷ ቀን የምትሸጠውን ልባሽ ጨርቅ በለሊት ተጫርታ ገዝታለች።ሲረፋፍድ ደግሞ ቋጠሮዋን ፈታትታ እና የገዛችውን በየፈርጁ ለይታ የምታነጥፈውን አነጣጥፋ፤ የምትሰቅለውን ሰቃቅላ ንግዷን ጀምራለች።
ጎሹ በበኩሉ በጠዋት ነገር ነገር ብሎቷል።በሰላም ቁርስ ከመብላት ይልቅ ከአዲሷ ሚስቱ ጋር ተነታርኳል።የነገር ዛሩን ከአዲሷ ሚስቱ ጋር አረፋፍዶ ካሟሟቀ በኋላ ወደ ታታሪዋ የቀድሞ ሚስቱ አመራ።ከሩቅ አያት።እንደለመደው ቀጥታ ወደ ስድብ አልገባም።ሲጠጋት እርሷ ልብ አላለችውም።ወደ እርሷ ወደምትሰራበት መደብ ተጠግቶ መቆፈሪያ እና ሸራ እንዲሁም ማዳበሪያ እንድትሰጠው ጠየቃት።
የተገላገለችው ጎሹ ንግድ ቦታዋ ላይ መምጣቱ አበሳጭቷታል።የሚፈልገው ዕቃ እርሷ ጋር እንደሌለ ስትገልፅ፤ ጎሹ እንደለመደው ሰበብ አግኝቶ መሳደብ ጀመረ።ከመሳደብ አልፎ ለማዋረድ ሲል አስከፊ ቃላትን ያዥጎደጉደው ጀመር።ምስኪኗ እማወራ መልስ አልሰጠችውም።ይበልጥ ተበሳጨ እርሱ መጥፎ ነገር ሲያደርግ እርሷ ምላሽ አለመስጠቷ ሁልጊዜም እጅግ ያበሳጨዋል።ስድቡን ሲጨርስ ራቅ ብሎ ተቀመጠ።በኋላ ተመልሶ ከገበያው ወጣ።
በጎሹ ድርጊት የተማረረችዋ እማወራ ቀኑን እንደነገሩ አሳልፋ ወደ ቤቷ ለመሔድ ተሰነዳዳች።ጎሹ ተመልሶ መጥቶ ነበር። እርሷ ግን አላየችውም።ምሽቱ እየቀረበ በመሆኑ ትኩረቷን ዕቃዋን በሥርዓት ማስቀመጥ ላይ አድርጋለች።ጎሹ በበኩሉ ድርጊቷን በሙሉ እየተከታተለ ነበር። ወደ ቤቷ ስትሔድ እንዳ ታየው እየተጠነቀቀ ተከተላት። ቤት ስትገባ ተከትሏት ገባ።
በቤት ውስጥ የ20 ዓመቷ የመጀመሪያ ልጃቸው ምግብ አብስላ የእናቷን መምጣት በጉጉት እየተጠባበቀች ነበር።አባቷ ከእናቷ ኋላ ተከትሎ መግባቱ ክፉኛ አስደነገጣት።እማወራዋም ጎሹን ስታይ ፈራችው።ሚስቱን እና የልጆቹን እናት ለመጉዳት ሆነ ብሎ የተዘጋጀው ጎሹ የያዘውን ቢላዋ ሰነዘረ።እጇን ወጋት፤ ለመታገል ስትሞክር በድጋሚ እጇን ወጋት።ከቤት ውስጥ ወጥታ ለማምለጥ ሮጠች ሆኖም የበሩ ደፍ አደናቀፋትና በደረቷ ወደቀች።ጎሹ ተከተለ። ልጃቸው ራሷን መቆጣጠር አቃታት።ኡኡታዋን አቀለ ጠችው።
ጎሹ እማወራዋ እንደወደቀች እላይዋ ላይ ተከመረ።የልጅቷን የድረሱልኝ ከፍተኛ ጩኸት የሰሙ ጎረቤቶች ብቻ ሳይሆኑ በቅርብ የነበሩ ፖሊሶችም ወደ ቤቱ ተንደረደሩ።ሆኖም መድረስ አልቻሉም።ጎሹ ጊዜ አላባከነም በፍጥነት የእማወራዋን ጭንቅላቷን ጎትቶ እንደዶሮ አረዳት።ይህንን ድርጊት ሲፈፅም ፖሊስ አየ።የቅርብ ጎረቤትም ተመለከተ።ሁሉም ተጯጯኸ፤ ሰፈርተኛ ተሰበሰበ፡፡
የታታሪዋ እማወራ ደም በወፍራሙ በቤቱ ደጃፍ ተንጣለለ።አይኗ አይታይም፤ ግንባሯ ከመሬቱ ጋር ተገናኝቷል፤ በደረቷ ተደፍታለች።ልጇ ራሷን መቆጣጠር አቅቷት ተጠግታ እናቷን ለመንካት ፈርታ ጩኸቷን ታቀልጠዋለች። መሬት ላይ ትንከባለላለች። ሰዎች የተፈፀመው ድርጊት ዘግንኗቸዋል። ግማሹ ይንቀጠቀጣል፤ ግማሹ እንባው ይወርዳል። ቀናተኛው ጎሹ፤ አማራጭ የሌለው ጎሹ እጅ ከፍንጅ ተይዟልና እጁን ሰጠ፡፡
የፖሊስ ምርመራ
የወንጀል ድርጊቱ ሲፈፀም በስፍራው የተገኘው ፖሊስ የሟቾችን አስከሬን አነሳ።ተገቢውን ምርመራ አጠናቆ ለጥያቄ የሚሻቸውን ምስክሮች ለየ።ምስክሮቹ በተደጋጋሚ እየቀና አምቧጓሮ ሲፈጥር እንደነበር፤ ክረምት ላይ በቤት እንዳልነበር እና ድርጊቱን በፈፀመበት ማለትም ጥቅምት 10 ቀን 2009 ዓ.ም ጎሹ የታታሪዋ እማወራ የሥራ ቦታ ተገኝቶ ሲሰድባት እንደነበር ገለፁ።አመሻሽ ላይ ከፍተኛ የድረሱልን ጩኸት ሲሰሙ ወደ ቤት መጠጋታቸውን ሆኖም ደጃፍ ላይ ሟችን ጎሹ በቢላዋ ሲያርዳት ማየታቸውን እና በመጨረሻ በግንባሯ ደም ላይ ተደፍታ ፖሊስ አስክሬኑን ማንሳቱን መሰከሩ።
ፖሊስ የሰው ምስክር ብቻ ሳይሆን የህክምና ማስረጃ አቀረበ።በተጨማሪ እጅ ከፍንጅ ድርጊቱን ሲፈፅም የተያዘ መሆኑን በመጥቀስ ክሱን ለፌዴራል ፍርድ ቤት አሟልቶ አቀረበ፡፡
ውሳኔ
ታህሳስ 11 ቀን 2009 ዓ.ም በችሎቱ የተሰየመው የድሬዳዋው ከፍተኛ ፍርድ ቤት በተከሳሽ ጎሹ አከላት ላይ የተከፈተውን ክስ ለማየት ተሰየመ። ዕለቱ ለመጨረሻ ውሳኔ ቀጠሮ የተሰጠበት ቀን ነበር፡፡ ፍርድ ቤቱ ተከሳሹ በፈጸመው ዘግናኝ የሰው መግደል ወንጀል ጥፋተኛ መሆኑን አረጋግጦ እንዲከላከል ዕድል ሰጥቷል፡፡ ተከሳሹ ለፈጸመው ወንጀል መከላከያ እንደሌለው አሳውቋል፡፡ ፍርድ ቤቱ በዕለቱ በሰጠው ውሳኔ ጎሹ አከላት የልጆቹን እናት የሰው ልጅ ላይ ሊፈፀም የማይገባ እጅግ በጣም ዘግናኝ አገዳደል የፈፀመባት በመሆኑ እና አገዳደሉም የግለሰቡን ጭካኔ ስለሚያሳይ ለሌሎችም ትምህርት ይሆናል ብሎ በማሰብ በወንጀል ህጉ አንቀፅ 149 መሠረት በ20 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ሲል ወሰነ፡፡
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 9/2014