የዛሬው ወጋችን በአንድ ስብሰባ ላይ የተንጸባረቁ አስተያየቶችን የሚያስቃኝ ነው። የስብሰባው ተሳታፊዎች በአንድ ከተማ ውስጥ የሚኖሩና ከሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል የተውጣጡ ናቸው። መድረኩን ከሚመሩት ሰዎች አንዱ የስብስባውን ዋና ነጥብ እንዲህ ሲሉ አስተዋወቁ።
‹‹ዛሬ እዚህ የተሰባሰብነው አሳሳቢ እየሆነ በመጣው የሀገራችን ጉዳይ ላይ ሃሳብ እንድንለዋወጥና መፍትሄዎችንም እንድንሰጥ ነው። ›› ሰብሳቢው ገና ይህን ብሎ ሃሳቡን ሳይጨርስ ባሻ ጉርሙ ከተቀመጡበት ብድግ ብለው ‹‹ጎበዝ እንዴት የሀገር ሰላም በሀገር ሰው ይደፈርሳል? እንዴትስ ወገን በወገኑ ላይ ይጨክናል? ኧረ ውርደት ነው፣ ኧረ ታሪካችን ጎደፈ፣ በደንብ እንመካከር ግድየላችሁም፣ ችግሮችን በመነጋገር መፍታት እንችላለን።
ሀገራችን ሽማግሌ ሳታጣ፣ የተማረ ሰው ሳታጣ፣ መሪ ሳታጣ፣ እንዴት በሕግና በሥርዓት መተዳደር ያቅተናል? እኛ እኮ የገዳ ሥርዓት ባለቤቶችና ዴሞክራሲን ለዓለም ያሰተዋወቅን ሕዝቦች ነን። በተባበረ ክንዳችን ዳር ድንበራችንን ያስከበርን የጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ተምሳሌት መሆናችንንም መርሳት የለብንም። በባህል በቋንቋና በደም አንዳችን ከአንዳችን ጋር የተሳሰርን ብዙ ስንሆን አንድ፤ አንድ ስንሆን ብዙ የሆንን ሕዝቦች ነን።››
ባሻ የንግግር ሥርዓትን ባልጠበቀ መንገድ በድንገት ተነስተው ያደረጉት ንግግር ብዙዎችን ያሳቀ ቢሆንም የኋላ ኋላ ግን በሚያነሷቸው ቁም ነገሮች ዕድምተኞቹ ተመሥጠው እያዳመጡ ነው። ባሻ ጉርሙ እልህና ቁጣ የተቀላቀለበት ንግግር ስለሚያደርጉ ቀዩ ፊታቸው እንጆሪ መስሏል፣ ግንባራቸው ላይና አንገታቸው ላይ እንደ አንቴና ጉብ ጉብ ብለው የሚታዩት የደም ሥሮች በተናገሩ ቁጥር ቱግ ቱግ ይላሉ።
አንዳንዴ እያስቆጩ፣ አንዳንዴ እያሳቁ፣ አንዳንዴ እየመከሩ፣ እንዲያም ሲል የሁኔታውን አደገኝነት በምናብ እያሳዩ ንግግራቸውን ቀጥለዋል። በእርግጥ የሚያነሷቸው ሃሳቦች ወቅታዊና አስፈላጊ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን ስሜትንም የሚነኩ ነበሩ። በዚህም አብዛኛው ሰው ንግግራቸውን ወዶታል፤ እንደውም አልፎ አልፎ ያጨበጭብላቸዋል። ‹‹በቃኝ ንግግሬን ጨርሻለሁ። ክቡር ሰብሳቢው ሳይፈቀድልኝ በመናገሬ ይቅርታ ይደረግልኝ። ጉዳዩ ቢኮረኩረኝ ነው፤የሀገሬ ጉዳይ ስለሆነብኝ ነው።›› ብለው ቁጭ አሉ ።
አሁንም ተሰብሳቢው ሞቅ ያለ ጭብጨባ አደረገላቸው። የሚያስገርም ስብሰባ ነበር። መድረኩን የሚመራው ሰው የውይይቱን ነጥቦች በደንብ ሳያብራራ በአንድ አረፍተ ነገር ብቻ ተሳታ ፊዎቹ የየግል አስተያየታቸውን ለመስጠት እየተሸቀዳደሙ ነው። ባሻ በከፈቱት መንገድ አብዛኛዎቹ የንግግር ዕድል እንዲሰጣቸው እጃቸውን አነሱ። ሰብሳቢው እንዲህ ዓይነት የጋለ ተሳትፎ ይኖራል ብለው ባለመገመታቸው በሚያዩት ነገር ግራ የተጋቡ መስለዋል።
ፈራ ተባ እያሉ ‹‹ይቅርታ አንድ ጊዜ ሃሳቤን እንድጨርስ ትተባበሩኛላችሁ? ቅድም ባሻ ማብራሪያዬን ሳልጨርስ ነበር ንግግር የጀመሩት። ›› ይሁን መልካም መልካም አለ አብዛኛውን ተሰብሳቢ። እማማ ጠንፌ ግን መናገር ፈልገዋል። ወትሮም ቢሆን በዕድርና በተለያዩ ቦታዎች ሰዎች ሲሰበሰቡ ከወንዶች ባሻ ጉርሙ ከሴቶች እማማ ጠንፌ ሳይናገሩ ቀርተው አያውቁም። በዚህም ላይ እነዚህ ሁለት ሰዎች በተገናኙበት መድረክ ሁሉ እኔ እበልጥ እኔ እበልጥ በሚል ይናናቃሉ። ባሻ ተናግረው እማማ ጠንፌ ካልተናገሩ የተሸናፊነት ስሜት ይሰማቸዋል።
ስለዚህ እንደ ባሻ ዘው ብሎ ወደ ንግግር ከመግባት ከባሻ በተሻለ የንግግር ሥርዓት አዋቂ ናቸው እንዲባሉ እጃቸውን አውጥተዋል። ባሻን ለማሳጣት ብለው እንጂ በየስብሰባው ሳይፈቀድላቸው በድንገት በመናገር እማማ ጠንፌን የሚስተካከል የለም። ‹‹የተለየ ሃሳብ አለዎት እናታችን?›› አላቸው ሰብሳቢው። ‹‹ልናገር ፈልጌ ነበር፤ እኔ እኮ ሥነ ሥርዓት ይዤ ልናገር ብዬ ነው እንጂ እንደ ባሻ ሳይፈቀድልኝ መናገር አልጠፋኝም ።›› ብለው ባሻን በአሽሙር ነካ አደረጓቸው።
ባሻም በለሆሳስ ድምጽ አጉረመረሙ። እንደው የተናገሩትን በትክክል አዳምጫለሁ ባልልም ‹‹ስምሽን ቄስ ይጥራው አንቺ ቀለብላባ›› ያሏቸው መሰለኝ። ደግነቱ እንኳን እማማ ጠንፌ አልሰሙ እንጂ መድረኩ ወደ ጦርነት ይቀየር ነበር። ‹‹ አንድ ጊዜ የጀመርኩትን ሃሳብ ጨርሼ ብትናገሩ አይሻልም እናታችን ? ›› አሏቸው ሰብሳቢው ።
‹‹ ምነው የኔ ወንድም የሴቶችና የወንዶች እኩልነት በተረጋገጠበት በዚህ ወቅት ዛሬም በወንዶች የበላይነት ታምናለህ እንዴ? ›› ‹‹ኧረ እኔ እንደዛ አላልኩም›› ‹‹ታድያ ምን ማለት ነው ባሻ በድንገት ተነስተው ደማቸውን አፍልተው ሲናገሩ ዝም ብለህ አሁን እኔ ሥነሥርዓት ይዤ ልናገር ስልህ አሻፈረኝ ማለትህ? ጉዳዩን በደንብ ልግለጽላችሁ ብዬ ነው። ኧረ እናውቀዋለን ባሻም እኮ ገብቷቸው ነው የተናገሩት።
ደግሞስ በዚህ ወቅት ስለሀገሩ ጉዳይ የማያውቅ የማይቆጭ የማይብሰከሰክ፣ የማይገረም፣ኧረ እንደውም የማይናደድ ሰው አለ እንዴ ?›› አሉ እማማ ጠንፌ። ተሰብሳቢዎቹ በተለይም ሴቶቹ ‹‹ኧረ ይፈቀድላቸው ግድየለም። ምን ችግር አለው ሰዓቱ ገናነው እሳችው ሲናገሩ አያድሩ።›› እያሉ ተንጫጩ። ሰብሳቢውም የቤቱን አዝማሚያ አይተው እንዲናገሩ ፈቀዱላቸው። እማማ ጠንፌ የድምጽ ማጉያው (ማይኩ) ተሰጣቸው።
አንድ ሁለቴ እኽ፤ እኽ፤ ብለው ጉሮሯቸውን ከጠራረጉ በኋላ ፊታቸውን ወደ ባሻ መለስ አድርገው ‹‹ስለተሰጠኝ ዕድል አመሰግናለሁ›› ብለው ንግራቸውን ቀጠሉ። ‹‹ሀገር እናት ነች፣ ሀገር ቤት ነች፣ ሀገር ፍቅር ነች፣ ሀገር ክብር ነች ሀገር ያለሰው ሰውም ያለ ሀገር አይኖርም።›› አዳራሹ በጭብጨባ ተናወጠ። ‹‹ዛሬ በሀገራችን እያየን ያለነው ለውጥ አብቦ ፍሬ እንዳያፈራ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች መኖራቸውን እናውቃለን፣ በየቦታው ግጭት እንዲፈጠር የሚያደርጉትም እነማን እንደሆኑ አልጠፋንም።
ከሁሉ በላይ ግን በሕዝቦች መካከል ያለመግባባት እንዲፈጠርና ሰዎች በጥርጣሬ እንዲተያዩ የሚደርጉት የብሔረሰባችን ተቆርቋሪ ነን የሚሉ አመራሮች ቆም ብለው እራሳቸውን ቢመለከቱ መልካም ነው። ‹‹እኔን የሚገርመኝ ሁሉም ብሔረሰብ ተበድያለሁ የሚል ነው፤ መበደሌ ትክክል አይደለም ካለ አሁን መልሶ ሌሎችን መበደል ለምን አስፈለገ? ለማንኛውም ክብር ሰብሳቢው ችግሮቻችንን በውይይት እንድንፈታ እንዲህ ዓይነት መድረክ በመዘጋጀቱ አመሰግናለሁ›› ብለው ቁጭ አሉ። እንደገና ተጨበጨበ።
እማማ ጠንፌ ከጭብጨባው በኋላ እንደገና ‹‹ክቡር ሰብሳቢው አንድ የረሳሁት ነገር፤ ምን መሰሎት? የሕዝባችን ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል። ፍቅር ያጣነውና ለእኔ ለእኔ ማለት የጀመርነው ለዚህ ይመስለኛል። መንግሥት በቤተሰብ ምጣኔ ላይ አጠንክሮ እንዲሰራ አመክራለሁ። አመሰግለናለሁ።›› ብለው ተቀመጡ።
የእማማ ጠንፌ ንግግር ታዳሚውን እንዳስደመመ ያስተዋሉት ባሻ የመልስ ምት ለመስጠት ይመስላል ደግመው እጃቸውን አወጡ። ተማሪዎች፣ ነጋዴዎች፣ መምህራን፣ የመንግሥት ሠራተኞች ፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች ሁሉም ዕድምተኞች እጃቸውን አንስተዋል። ሰብሳቢው ግን እጃቸውን ካወጡት ውስጥ ለአንድ ጸጉረ ልውጥ ሰው ዕድል ሰጡ።
ሰውየው ኢትዮጵያዊ ዜግነት ያለው ትውልደ ቻይናዊ ነው። ኢትዮጵያዊት ሚስት አግብቶ በከተማው መኖር ከጀመረ አስርት ዓመታትን አስቆጥሯል። ቻይናዊው በታታሪ ሠራተኝነቱ የሚታወቅና ጥሩ ስም ያለው ቢሆንም እማማ ጠንፌ ግን አይወዱትም። ምክንያቱም ቻይናዊው እነ እማማ ጠንፌ ዕድር እንዲያስገቡት ወትውቶ ከገባ በኋላ ቀብር ላይ ‹‹አልተገኘህም›› ተብሎ በዕድሩ ደንብ መሠረት አንድ ሁለቴ ሲቀጣ ‹‹ አንድ ሰውን ለመቅበር ይህን ያህል ሰው ሥራ ፈትቶ መዋል አለበት ብዬ አላምንም ›› በማለቱ ከእማማ ጠንፌ ጋር ግጭት ፈጥሮ ነበር።
በዚህም ‹‹ወግና ሥርዓታችንን ሊያጠፋብን ነው›› ተብሎ ከዕድር እንዲወጣ ተደርጓል። እማማ ጠንፌ በዋናነት ይህን ሰው የሚጠሉት ግን በመንደራቸው ሽሮ ቤት ከፍቶ ደንበኞቻቸውን ስለወሰደባቸው ነው። ቻይናዊው በኮልታፋ አንደበቱ እማማ ጠንፌ መጨረሻ ላይ የተናገሩትን ሃሳብ በመንቀፍ ንግግሩን ጀመረ ‹‹ሀገራችን ኢትዮጵያ የሕዝቧ ብዛት ችግር ሊፈጥርባት አይችልም ። ›› ገና አንድ ዓረፍተ ነገር እንደተናገረ ቤቱ በጭብጨባ ተናወጠ።
‹‹ የቀድሞዋ ሀገሬ ቻይና ባለ ግዙፍ ኢኮኖሚ እንድትሆን የረዳት የሕዝቦቿ ቁጥር መብዛት ነው። ሕዝቦቿ በመተባበር ችግርን የሚጋፈጡ እንጂ እርስ በእርስ የሚናቆሩ አይደሉም። በመሆኑም ዛሬ ላሉበት ደረጃ ደርሰዋል። ስለዚህ ለወጣቱ ምቹ የሥራ ዕድል መፈጠርና ይህንን ኃይል ወደ ኢኮኖሚ መመንዘር በሚቻልበት መንገድ መነጋገር የሚበጅ ይመስለኛል።
በተረፈ ግን አሁን የሀገራችንን ሰላም ለማደፍረስ የሚደረገው መቅበዝበዝ ከሕዝብ ቁጥር መብዛት የመጣ ሳይሆን ከአመለካከት ያለመጥራት ጋር የተያያዘ ነው። አመሰግናለሁ።›› አሁንም ቤቱ በጭብጨባ ተናወጠ። ከቻይናዊው ንግግር በኋላ እድምተኛው እርስ በእርሱ እየተነጋገረ ለሻይ እረፍት ወጣ ።
አዲስ ዘመን መጋቢት 19/2011
ኢያሱ መሰለ