የዛሬው የ‹‹ፍረዱኝ›› አምድ ዝግጅታችን በመዲናችን አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 በሚገኙት ሁለት የአጸደ ህጻናት ትምህርት ቤቶችን ይመለከታል። አጸደ ህጻናቱ ህጻን ዓለም አጸደ ህጻናት እና አምስት ኪሎ አጸደ ህጻናት በመባል ይታወቃሉ። በአፀደ ሕፃናቱ የሚያስተምሩ መምህራን ለቅሬታቸው መነሻ የሆነውን ምክንያት ይዘው ወደ ዝግጅት ክፍላችን መጥተዋል።
ቅሬታው የተፈጠረው በትምህርት ቤቱ እና በሸማች ህብረት ስራ ማህበር መካከል ሲሆን ‹‹በድል ተፈጽሞብናል›› ሲሉ አቤቱታ ያቀረቡት የህጻን ዓለም አጸደ ህጻናት እና አምስት ኪሎ አጸደ ህጻናት መምህራን ናቸው። ከቅሬታው ጋር ተያይዞም ጉዳዩ የሚመለከታቸውን አካላት ምላሽም አካተን እንደሚከተለው አጠናቅረነዋል።
«በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 የሚገኘው የሸማቾች ህብረት ስራ ማህበር በ2004 ዓ.ም በአደራ ከተረከባቸው ትምህርት ቤቶች አንዱ የሆነው ህጻን ዓለም አጸደ ህጻናት ማስተማሪያ ህንጻ ወደ መጠጥ ቤት በመቀየር ተማሪዎችን ከመበተኑ ባለፈ መምህራንንም ለአልተጋባ እንግልት ዳርጎል። ›› የሚሉት መምህራኑ፤ ይሄው ሸማች ማህበር በአደራ የተረከበውን የአምስት ኪሎ አጸደ ህጻናት የሚያስተምሩ መምህራንን ጥቅማ ጥቅም በመከልከል እና መምህራንን አሰላችቶ ትምህርት ቤቱን ለቀው እንዲሄዱ በማድረግ የትምህርት ቤቱን ህንጻ ላልተገባ ጥቅም ለማዋል በማሰብ በደል ሲፈፅም መቆየቱን በምሬት ይገልጻሉ።
የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍልም ከሰዎች እና ከሰነዶች ያገኛቸውን መረጃዎች ዋቢ በማድረግ የኢትዮጵያ ህዝብ ግራ እና ቀኙን በማየት መፍረድ ይችል ዘንድ የውዝግቡን ክፍል አንድ የምርመራ ሂደት እነሆ ብለናል።
በትምህርት ቤቶቹ አቤቱታ ያቀረቡ መምህራን በርካታ ናቸው። ይሁን እንጂ የሁሉም መምህራን አቤቱታ አንድ አይነት ስለሆነ ህጻን ዓለም እና አምስት ኪሎ አጸደ ህጻናትን የሚወክሉልን ከሁለቱ ትምህርት ቤቶች አንድ አንድ መምህራን ጋር ቃለ ምልልስ አድርገናል።
የመጀመሪያዋ አቤቱታ አቅራቢ መምህርት ዓለም ጌታቸው ይባላሉ። በህጻን ዓለም ትምህርት ቤት ለ30 ዓመታት ያህል መስራታቸውን ይናገራሉ። እንደ መምህርቷ ገለጻ፤ ከ2004 ዓ.ም በፊት ህጻን ዓለም ትምህርት ቤት የሕዝብ ትምህርት ቤት ነበር። ነገር ግን በ2004 ዓ.ም በወጣው መመሪያ መሰረት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሚገኙ እና ሕዝብ ያስተዳድራቸው የነበሩ ትምህርት ቤቶች በመንግስት አስተዳደር ስር እንዲሆኑ ተወሰነ። ይህን ተከትሎ በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 ይገኙ የነበሩ በርካታ የሕዝብ ትምህርት ቤቶች መንግስት እንዲያስተዳድራቸው ወደ መንግስት ትምህርት ቤት ተዘዋወሩ።
ይሁን እንጂ በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 ከሚገኙ የሕዝብ ትምህርት ቤቶች መካከል ህጻን ዓለም አጸደ ህጻናት እና የአምስት ኪሎ አጸደ ህጻናት ወደ መንግሥት ትምህርት ቤት አልተካተቱም፡፡ ይልቁንም ባልታወቀ ምክንያት ለሸማቾች ህብረት ስራ ማህበር በአደራነት ተሰጡ። ትምህርት ቤቶች ለማስተዳደር በአደራ የተቀበለው አካልም ስለሙያው ግንዛቤ የሌላቸው ከመሆናቸው በተጨማሪ እያደር የትምህርት ቤቱ ህልውና ከድጡ ወደ ማጡ እየሆነ መምጣቱን ይናገራሉ።
መምህራኑ በትምህርት ቤቱ መምህራን እና ህጻናት የሚፈጸሙ ሁሉም አስተዳደራዊ በደሎች ከነገ ዛሬ ይሻሻላሉ በማለት በተስፋ እየሰሩ ቢቆዩም፤ የወረዳ 6 የሸማች ማህበር የህጻን ዓለምን አጸደ ህጻናትን ህንጻ ለማደስ በሚል ሰበብ መምህራን ሙሉ ተማሪዎቻቸውን ይዘው ወደ አምስት ኪሎ አጸደ ህጻናት እንዲቀላቀሉ መደረጉን አቤቱታ አቅራቢዋ ያስረዳሉ።
ወደ አምስት ኪሎ አጸደ ህጻናት ተደርበው እንዲሄዱ ሲደረግ የትምህርት ቤቱ ህንጻ የቤቱ እድሳት እስከሚያልቅ ተብለው እንደነበር ያስታውሳሉ። ይሁን እንጂ የህንጻው እድሳት ከተጠናቀቀ በኋላ ወደ ነበሩበት ህጻን ዓለም አጸደ ህጻናት እንዲመለሱ ጥያቄ ቢያቀርቡም ጥያቄያቸው ሰሚ አጥቶ ለዓመታት ትውልድን ሲቀረጽበት የነበረው ትምህርት ቤት ለመጠጥ ቤት አገልግሎት እንዲውል መደረጉን ያብራራሉ።
ሆኖም ግን እስካሁን ድረስ ደመወዝ የሚከፈላቸው በህጻን ዓለም ትምህርት ቤት ስም ነው። ለመከላከያ እና መሰል አገራዊ ግዳጆች መዋጮ የሚያደርጉትም በዚሁ በኩል ነው። ‹‹ሌላው ደግሞ›› ይላሉ መምህርቷ በአንድ ከተማ አስተዳደር ስር እየሰሩ ለመምህራኑ የሚከፈለው ደመወዝ በመንግስት ትምህርት ቤት ከሚሰሩ መምህራን እጅጉን ያነሰ ነው። የመምህራን ጥቅማ ጥቅም የሚባለው ነገር ፈጽሞ እንደማይታሰብ ያስረዳሉ። እንደ መንግስት መምህራን የደመወዝ ጭማሪ እንዲደረግላቸው እና ጥቅማ ጥቅሞቻቸውም እንዲከበሩላቸው በተደጋጋሚ መጠየቀቻውን የሚናገሩት መምህርቷ ፤ ‹‹አትራፊ ስላልሆናችሁ ደመወዝ አይጨምርላችሁም›› የሚል መልስ ከሸማቾች እንደተሰጣቸው ይናገራሉ።
አቤቱታ አቅራቢዋ እንደሚገልጹት፤ በእርሳቸው ደረጃ በመንግስት ትምህርት ቤት የሚያስተምሩ መምህራን የቤት አበል እስከ 3 ሺብር ፣ የትራንስፖርት (ፐብሊክ ሰርቪስ እና የከተማ አውቶብስ ) እንዲሁም ደመወዛቸው ደግሞ ከ10 ሺህ ብር በላይ ሲሆን፤ የእርሳቸው ግን 30 ዓመታትን በማስተማር አሳለፈው በወር ያልተጣራ 3 ሺህ ብር ብቻ እንደሚከፈላቸው ይናገራሉ። ይህም የኑሮ ውድነቱን ያላገናዘበ ከመሆኑም ባሻገር ሞራልም የሚነካ ድርጊት መሆኑን ያስረዳሉ። «በእኛ ላይ እየተፈጸመ ያለውን ግፍ መንግስት እና የኢትዮጵያ ሕዝብ ይመልከተው» ሲሉ ቅሬታቸውን ያቀርባሉ።
ሌላኛዋ በደል ተፈጽሞብናል ሲሉ ለዝግጅት ክፍላችን አቤት ያሉት ደግሞ መምህርት አንጓች ታደሰ ናቸው። በአምስት ኪሎ አጸደ ህጻናት ከአስራ አምስት አመት በላይ እንደሰሩ ይናገራሉ። እንደ መምህርት አንጓች ገለጻ፤ በትምህርት ቤቱ ለበርካታ አመታት ይስሩ እንጂ የሚከፈላቸው ደመወዝ የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ያላገናዘበ እና ሌሎች በደረጃቸው ካሉ መምህራን ከሚያገኙት በእጅጉ ያነሰ ነው። በዚህም እኩል እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ መምህር ማግኘት የነበረባቸውን ደመወዝ እና ጥቅማ ጥቅም ማግኘት አልቻሉም።
በግንቦት ወር 2014 ዓ.ም ጉዳዩ የሚመለከታቸው በክፍለ ከተማው የሚገኙ አመራሮች ትምህርት ቤቱ እንዲጠገን እና የመምህራንም ጥቅማ ጥቅም እንዲከበር በማለት ለአንድ ወር ከአስራ አምስት ቀን ማስጠንቀቂያ ሰጥቷቸው ነበር። ነገር ግን አንድም ሰው የት ደረሰ? ብሎ ያየ አካል ባለመኖሩ ሁሉም ነገር ባለበት እንዳለ መሆኑን አመላክተዋል።
ከአራት አመት በፊት በትምህርት ቤቱ ልጆቻቸውን የሚያስተምሩ ወላጆች የመምህራን ደመወዝ ያንሳቸዋል በሚል አንድ መቶ ሃምሳ ብር ጭማሪ አድርገው ነበር። ነገር ግን የሸማቾች ቦርድ ለመምህራን አንድም ብር ሳይጨምር ቀረ። ሸማቾች ይህን ሊያደርግ የቻለበት ዋናው ምክንያት መምህራን ትምህርት ቤቱ ተሰላችተው ጥለውት እንዲሄዱ እና መምህራን ትምህርት ቤቱን ጥለው ከሄዱ ‹‹መምህራን የሉም›› በሚል ሰበብ ትምህርት ቤቱን ለሌላ አላማ ለማዋል በማሰብ መሆኑን ያስረዳሉ።
የአምስት ኪሎ አጸደ ህጻናት ወደ ሸማቾች ከመዞሩ በፊት በአገር አቀፍ ደረጃ በሞዴልነት የተመረጠ ትምህርት ቤት ነበር የሚሉት መምህርቷ፤ በዚህም ከትምህርት ቤታቸው ተሞክሮ ለመውሰድ ከመላው አገሪቱ የሚገኙ መምህራን ወደ ትምህርት ቤታቸው ይመጡ እንደነበር ያስታውሳሉ። አሁን ላይ ግን ‹‹ጽድቁ ቀርቶ በቅጡ በኮነነኝ›› እንዲሉ በሞዴልነት ተመርጦ ለጉብኝት ሊበቃ ይቅርና የትምህርት ቤቱ እድሳት ተደርጎለት ስለማያውቅ ተማሪዎች በጎርፍ ውስጥ ሆነው ለመማር መገደዳቸውን ይናገራሉ።
ስለሆነም የትምህርት ስራው ጨርሶ ሳይጠፋ ትምህርት ቤቱ ወደ መንግስት መዞር እንዳለበት ያመላክታሉ።
የወላጅ ፣ መምህራን እና ተማሪዎች ህብረት ኮሚቴ ሰብሳቢ ምላሽ
አቶ ወንድወሰን ፍታሌ በአራዳ ክፍለ ከተማ የወረዳ 6 የወላጅ ፣መምህራንና ተማሪዎች ህብረት ኮሚቴ ሰብሳቢ ናቸው። እንደ አቶ ወንድወሰን ገለፃ፤ በህጻን ዓለም የተፈጠረው ችግር ከዘጠኝ ዓመታት በላይ ያስቆጠረ ነው። ጉዳዩ ለበርካታ ዓመታት ሰሚ ጆሮ ባለማግኘቱ ችግሩ እየተባባሰ መጥቶ አሁን ላይ ወላጆችን፣ ተማሪዎችን እና መምህራን ክፉኛ እያስለቀሰ ይገኛል።
ማንኛውም ሰው፣ ማንኛውም ኮሚቴ፣ ማንኛውም አካል የተሰጠውን ስራ በአግባቡ ካልሰራ በህግ ሊጠየቅ እንደሚችል በተለያዩ ጊዜያት በኢትዮጵያ ወንጀለኛ መቅጫ እና የፍታብሄር ህግ ተደንግጓል። አንድ ሰው ወይም አካል በኃላፊነት በተሰጠው ስራ ላይ አፈጻጸሙ ችግር ካለበት፤ የአቅም ማነስ ከታየበት ፤ የተሰጠውን ኃላፊነት ለሰጠው አካል የማስረከብ ግዴታ አለበት።
ይህንን አለማድረግ አይቻለም ይላሉ።
ነገር ግን በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 የሚገኘው የሸማቾች ህብረት የተሰጠውን ኃላፊነት መወጣት አልችል ብሎ በግልጽ እየታየ ለምን ብሎ የሚጠይቀው አካል ስለሌለ ብቻ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሰራ ያለው ተግባር አገርን እና ሕዝብን በከፍተኛ ደረጃ እየጎዳ እንደሚገኝ ያስረዳሉ።
በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በሸማቾች ስር እንዲተዳደሩ የሚያስገድድ አሰራርም ሆነ የህግ አግባብ የለም። ነገር ግን በ2004 ዓ.ም የነበሩ የክፍለ ከተማ እና ወረዳ አመራሮች በማን አለብኝነት ትምህርት ቤቱን ለሸቀጥ ነጋዴ አሳልፈው ሰጡ። እዚህ ላይ በደንብ ማስተዋል የሚገባው በሕዝብ እና በመንግስት ስም የሚሰሩ ብዙ ችግሮች አሉ። እነኚህን ችግሮች እስከመጨረሻው መታገል ያስፈልጋል።
‹‹እኔ የሸማችም አባል ነኝ፤ የወረዳው የወተመህ ሰብሳቢ ነኝ። ሸማች መስራት ያለበትን ለይቶ ከተማ አስተዳደሩ ሊሰጠው ይገባል። የትምህርት ጉዳይ ደግሞ በትምህርት ባለሙያ በአግባቡ ሊመራ ያስፈልጋል።
አሁን ሰዎች እየተጎዱ ነው፤ ትውልድ እያጣን ነው። የትምህርቱ ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ ገብቷል።›› ስለዚህ ጉዳዩ የሚመለከተው አካል ትኩረት ሊሰጠው ይገባል።
መንግስት ያወጣው ፖሊሲ እንደሚያመላክተው አንድም ህጻን እቤቱ መቅረት የለበትም የሚል ነው። ነገር ግን በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 እየሆነ ያለው የእዚህ ተቃራኒ ነው። ወደ ትምህርት ቤት የሄደን ህጻን ትምህርት ቤቱን ነጥቀው ወደ መጠጥ ቤት ቀይረውታል። በዚህም በወረዳው የሚገኙ ህጻናት በአቅራቢያቸው በሚገኝ ትምህርት ቤት ተዝናንተው መማር ሲገባቸው በአንድ ትምህርት ቤት ታጭቀው እና ተጨናንቀው ለመማር ተፈርዶባቸዋል ይላሉ።
ይህን ጉዳይ በሌላ ሚዲያ ለሌላ አካልም በዝርዝር ለማስረዳት መሞከራቸውን ጠቅሰው፤ ነገር ግን ለችግሩ መፍትሄ የሚሰጥ እንደጠፋ እና አሁንም ድረስ እንዳልተፈታ ያስረዳሉ። ለእዚህ ደግሞ ዋናው ምክንያት ምን አልባትም ችግሩን የፈጠሩት ሰዎች አሁንም በተሃድሶ ሰበብ ስልጣን ላይ በመገኘታቸው ነው ይላሉ። ይህም አሁን ላይ ችግሩን ከባድ አድርጎታል። ሆኖም ጉዳዩ እልባት ሳይገኝለት እንደማይቀር ያመለክታሉ።
በእነዚህ ትምህርት ቤቶች የሚገኙት መምህራን ከ14 እስከ 30 እና ከዚያ በላይ ዓመት ያገለገሉ ናቸው። ሆኖም የሚያገኙት ደመወዝ እጅጉን ዝቅተኛ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ኑሮን በአግባቡ ለመግፋት የሚያስችል አቅም አጥተዋል። መምህራን በኑሮ ከመጉዳቱም ባለፈ አንድ አይነት ስራ ከሚሰሩ ሌሎች መምህራን ጋር በእኩል አለመታየታቸው ከፍተኛ የሞራል ስብራት እንዲያጋጥማቸው አድርጓል ይላሉ።
በተለይ ሁለቱን ትምህርት ቤቶች በአደራ እያስተዳደረ የሚገኘው የወረዳ 6 የሸማቾች ማህበር ለመምህራኑ ተገቢውን ክብር መስጠት ባይችል እንኳን ትውልድ የሚቀርጹ መምህራንን ክብር ሊነካ እንደማይገባው አሳስበዋል። የሸማቾች ማህበሩ ኃላፊነቱን ባለመወጣቱ ለምን ብለው የሚጠይቁ መምህራንን ‹‹ነገ ትባረራላችሁ›› የሚል ዛቻና ማስፈራሪያ ይደርስባቸዋል። ትውልድ ይቀርጻሉ ተብሎ ኃላፊነት የተሰጣቸውን አካላት በዚህ መልኩ ማስተናገድ ህግን የጣሰ መሆኑን አቶ ወንደወሰን ያስረዳሉ።
‹‹ልጆቻችንን በቅንነትና በታማኝነት ተረክበው በማስተማር ጊዜያቸውን እየገፉ ያሉ መምህራን ሊመሰገኑ ሲጋባቸው በዚህ መልኩ እየተገፉ ሊሰቃዩ አይጋባም። መንግስት የጉዳዩን አንገብጋቢነት ተመልከቶ በአፋጣኝ ውሳኔ ሊሰጥበት ይገባል›› ይላሉ።
የወረዳ 6 ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ ምላሽ አቶ አበራ አብጊና በአራዳ ክፍለ ከተማ የወረዳ 6 ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ ናቸው። ከላይ በተነሳው የመምህራን ቅሬታ ዙሪያ በሰጡት ምላሽ፤ በወረዳው ያለው የአጸደ ህጻናት ፍላጎት እና ያለው ተደራሽነት አይመጣጠንም።
ይህንንም ተከትሎ በፈረቃ ለማስተማር የተገደዱባቸው ጊዜያት ነበሩ። የትምህርት ቤት እጥረቱን ለመፍታት መንግስት ተጨማሪ አጸደ ህጻናት አስገንብቷል። ከዚህ በተጨማሪ በወረዳው የነበረውን የትምህርት ቤት እጥረት ለማቃለል የአምስት ኪሎ አጸደ ህጻናት የነበሩበትን ክፍተቶች በመሙላት ሲሰሩ ቆይቷል።
የአምስት ኪሎ አጸደ ህጻናት እምቅ ሃብት ያለው ትምህርት ቤት ነው። ነገር ግን ትምህርት ቤቱ ያለውን ሃብት ለመጠቀም የሚያስችል አመራር የለውም። ይህን ተከትሎ ትምህርት ቤቱን ከሚያስተዳድረው ሸማቾች ቦርድ ጋር በመነጋገር ትምህርት ቤቱ ወደ መንግስት ስለሚዞርበት ሁኔታ ለበርካታ ጊዜያት መወያየታቸውን ያስታውሳሉ።
‹‹ህጻን ዓለም የሚባለው ትምህርት ቤት ወደ መጠጥ ቤት ተቀይሯል። የተቀየረበት አግባብ ስህተት ነው። በዚህም የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ከሸማቾች ጋር በነበራቸው ውይይት ትምህርት ቤቱ ወደ መጠጥ ቤት መቀየሩ ስህተት መሆኑን መተማመን ላይ ተደርሷል። በዚህም ትምህርት ቤቱ እስከ ሰኔ 30/ 2014 ዓ.ም ድረስ ወደ ትምህርት ቤት እንዲቀየር አቅጣጫ ተስጥቷል፡። ይህ አቅጣጫ የሰጡት የክፍለ ከተማው ትምህርት ጽህፈት ቤት እና የክፍለ ከተማው ህብረት ስራ ማህበራት እንዲሁም ባህል እና ቱሪዝም በጋራ በመሆን ነበር። ስለዚህ ትምህርት ቤቱን ለመቀበል ሰኔ 30ን እየጠበቅን ነው›› ይላሉ።
ኃላፊውም በበኩላቸው ትምህርት ቤቶቹ ተገቢ ተልዕኳቸውን መፈጸም እንዲችሉ በማድረግ ታሪካዊ ኃላፊነታችንን ለመወጣት አሁን ላይ ሁሉም ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት እርስ በእርሳቸው ሊደጋገፉ ይገባል። አለበለዚያ በታሪክ ተወቃሽ እንሆናለን ሲሉ ይገልጻሉ።
የህጻን ዓለም እና የአምስት ኪሎ አጸደ ህጻናት መምህራን ከዲፕሎማ እስከ ዲግሪ የሚደርስ የትምህርት ዝግጅት ያላቸው እና ለበርካታ አመታት በመምህርነት ያገለገሉ ናቸው። ይሁን እንጂ ተጣርቶ በእጃቸው የሚደርሳቸው ደመወዝ ከአንድ ሺህ አምስት መቶ እስከ ሁለት ሺህ አምስት መቶ ነው። ይህ ደግሞ ልክ እንዳልሆነ ትምህርት ጽህፈት ቤቱ ባደረገው የዳሰሳ ጥናቱ አረጋግጧል። የኑሮ ውድነቱን እና የመምህራን ደረጃ ያላገናዘበ ደመወዝ የመምህራንን ስነ ልቦና ከመጉዳቱ ባሻገር እንደ አገር ለመምህራን የሚሰጠውን ክብር የሚነፍግ እና በትምህርት ጥራት ላይም የራሱ አሉታዊ ተጽዕኖ የሚያሳርፍ አስነዋሪ ተግባር መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል።
በሁለቱ ትምህርት ቤቶች ላይ እየተደረገ ያለው ያልተገባ ስራ በአፋጣኝ እንዲቆም ለማድረግ ጉዳዩ የሚመለከታቸውን አካላት መጠየቃቸውን የሚናገሩት ኃላፊው፤ በክፍለ ከተማ እና በከተማ አስተዳደሩ የሚገኙ የፖለቲካ አመራሮች ጣልቃ ገብተው አስተዳደራዊ መፍትሄ ይሰጡታል የሚል እምነት እንዳላቸው ጠቁመዋል።
ከዚህ በፊት በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 ፋና አጸደ ህጻናት የሚባል ትምህርት ቤት በአመራር ችግር መዘጋቱን እና የህጻን ዓለም ትምህርት ቤት ደግሞ የደረሰበት የሚታወቅ ነው ያሉት ኃላፊው ፤ ከዚህ ቀደም በአገር አቀፍ ደረጃ በሞዴልነት ይጠቀስ የነበረው አምስት ኪሎ አጸደ ህጻናት ትምህርት ቤት አሁን ላይ የትምህርት ጥራት ተቆጣጣሪ ሊዘጋው ጫፍ ደርሷል ሲሉ ይገልጻሉ። ስለሆነም አስቸኳይ መፍትሄ እንደሚያሻው ጠቁመው፤ ይህ ካልሆነ ግን ትምህርት ቤቶቹ እስከመዘጋት የሚያደርስ ለከፋ ችግር ሊጋለጡ እንደሚችሉ አስጠንቅቀዋል።
‹‹ለመምህራን የሚከፈለው ደመወዝ መስተካከል አለበት። ልክ አይደለም። በእነኚህ ትምህርት ቤቶች የሚያስተማሩ መምህራን ኢትዮጵያዊ ዜጎች ናቸው። የሸማቾች ማህበር ውስጥ ካሉ ሰዎች ጋር እኩል ደመወዝ እየተከፈላቸው ነው። ሸቀጥ ከሚሸጥ ሰራተኛ ጋር መምህራንን በእኩል ማስተናገድ በትውልድ ላይ ክፉኛ መፍረድ ነው። ምክንያቱም መምህርነት ተተኪ እና አገር ተረካቢ ትውልድን የሚያፈራ ሙያ ያላቸው በመሆናቸው፤ ይህንንም ጉዳይ ወደ ክፍለ ከተማ እና ከተማ አስተዳደሩ ወስደነዋል›› ሲሉ የወረዳው ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ ይናገራሉ።
በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 የህብረት ስራ ጽህፈት ቤት ምላሽ
ለአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 የህብረት ስራ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ለአቶ አብርሃ ታሪክ በእድሳት ምክንያት ከትምህርት ቤት ወደ መጠጥ ቤት ስለዞረው እንዲሁም በአቅም ማነስ ሊዘጋ ጫፍ ስለደረሰው የአምስት ኪሎ አጸደ ህጻናት ትምህርት ቤት አስመልክቶ ላቀረብነው ጥያቄ በሰጡን ምላሽ፤
የህጻን ዓለም አጸደ ህጻናት ትምህርት ቤት በአዲስ አበባ ከተማ ባህል፣ ኪነጥበብ እና ቱሪዝም ቢሮ በቅርስነት የተመዘገበ ነው። ቅርስ እንደመሆኑ መጠን ቅርስነቱን ጠብቆ እንዲቀጥል እድሳት ተደርጎለታል። ከእድሳት በኋላ ግን ቅርሱን በበላይነት የሚያስተዳደረው አካል በቤቱ ትምህርት እንዳይሰጥበት የሚል ደብዳቤ ለሸማቾች ስለላከ ሸማቾችም ቤቱን ሌሎች አማራጭ ስራዎች ለመጠቀም ተገደደ። ስለሆነም ሸማቾች ለሕዝብ አገልግሎት ከሚሰጥባቸው ዘርፎች አንዱ ወደሆነው አማራጭ የሕዝብ መዝናኛነት ቀይሮታል።
አሁን ላይ የአጸደ ህጻናት ትምህርት ቤት የነበረው ቤት የመጠጥ ቤት መሆኑን በምልከታ አረጋግጠናል። ስለዚህ ምን ይላሉ? የሚል ጥያቄ ያነሳንላቸው ሲሆን፤ ቅርሱን በማይጎዳ መንገድ ቤቱን ለመጠጥ ሽያጭ መጠቀም እንደምንችል ቅርሱን በበላይነት የሚያስተዳደረው አካል ፈቅዶልናል ብለዋል።
ነገር ግን የህጻናት የእውቀት መገብያ ቦታ መጠጥ ቤት መሆን ነበረበት ወይስ አልነበረበትም የሚለው ላይ የአሰራር ክፍተት ሊኖር ይችላል ያሉት ኃላፊው፤ የሸማች ማህበሩ ግን ቤቱ ወደ ትምህርት ቤት ቢቀየር እንደሚፈልግ ጠቁመዋል። ይሁን እንጂ ቤቱን ወደ ትምህርት ቤት መቀየር የሚቻለው ቅርሱን በበላይነት የሚያስተዳደረው አካል ሲፈቅድ ብቻ መሆኑን ያስረዳሉ።
አምስት ኪሎ አጸደ ህጻናት ከዚህ ቀደም በአገር አቀፍ ደረጃ ሞዴል ትምህርት ቤት ተብሎ የተመረጠ እና በአገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት ሳይቀር እውቅና ተሰጥቶት እንደነበር ይታወቃል። ነገር ግን የሸማቾች ቦርድ ትምህርት ቤቱን ማስተዳደር ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ትምህርት ቤቱ ሞዴል መሆን ይቀርና ጣራው እያፈሰሰ እና ጎርፍ እያስገባ ተማሪዎች መማር እስከማይችሉበት ደረጃ ደርሷል።
መምህራንም ተገቢው ጥቅማ ጥቅማጥቅም እያገኙ አልነበረም። በተጨማሪም ሸማቾች የታደሰ ትምህርት ቤት እንኳን ለተገቢው ጥቅም እንዲውል ማድረግ አልቻለም። ይህ ደግሞ ሸማቾች ትምህርት ቤቶችን ማስተዳደር እንዳልቻለ ሁነኛ ማሳያ ነው። ሸማቾች ማስተዳደር ካልቻለ ትምህርት ቤቶችን ለመንግስት የማያስረክበው ለምንድን ነው? ሲል ለቀረበላቸው ጥያቄም እንዲህ ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
‹‹እርግጥ ነው ከዚህ ቀደም የሸማች ማህበሩ ትምህርት ቤቶችን በብቃት ማስተዳደር ላይችል ይችላል። ነገር ከዚህ ቀደም ሲል ማስተዳደር አልቻለም ማለት አሁን ላይ አይችልም ማለት አይደለም። በመሆኑም ትናንት አልቻለም እና አሁን አይችልም ብሎ መደምደም ያስቸግራል›› የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
እንደ ኃላፊው ገለጻ፤ የአምስት ኪሎ አጸደ ህጻናት የእድሳት ችግር አለበት። ጣራው ያፈሳል፤ ሌሎች እድሳቶች ያስፈልጉታል። በዚህ ጉዳይ ላይ ትምህርት ቤቱን ከሚያስተዳደረው የሸማቾች ቦርድ ጋር ውይይቶች ተደርጓል። ኮሚቴም ተቋቁሞ የትኛው ጥገና ያስፈልገዋል? የትኛው ምን የጎደለው ነገር አለው? ብሎ ኮሚቴው አጥንቶ የጓደለውን ለማሟላት ስራዎች ተጀምረዋል። የተጓደሉ ነገሮች ተሟልተው በቀጣይ አመት የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ስራዎች ተጀምረዋል።
መምህራንም የጠየቁትን የመብት ጥያቄ ለመመለስ ኮሚቴ ተቋቁሞ እየተሰራ ነው ያሉት ኃላፊው፤ ተፈጥረው የነበሩትን ችግሮች ለማስተካከል አሁን ላይ ማህበሩ በጥሩ መነሳሳት ላይ ይገኛል። ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየተሰራ ነው ብለዋል።
‹‹የመምህራን ደመወዝ የአገሪቱ አቅም በሚፈቅደው ልክ መከፈል አለበት። ይህ የቢሯችን አሁናዊ አቋም ነው። ከዚህም ባለፈ መስተዳደሩ ለተማሪዎች የፈቀደው ምገባ እና መሟላት ያለባቸው ቁሳቁሶች አሉ። እነኚህን ተማሪዎች እንዲያገኙ እንሰራልን። ነገር ግን በሸማቾች ስር እያሉ ምገባ ማግኘት አይችሉም የሚባል ከሆነ እና ለመምህራንም ማግኘት የነበረባቸው ጥቅማ ጥቅሞች ካልተሟሉ ወዴት መሄድ አለብን? የሚለውን በአጭር ጊዜ እንወስናለን። እኛ ግን ከላይ የተጠቀሱትን ነገሮች ለመቅረፍ እንሰራለን›› ሲሉ ተናግረዋል።
ሌላው የዝግጅት ክፍሉ ያነሳው ጥያቄ ከተወሰኑ ወራት በፊት የወረዳ 6 ትምህርት ጽሀፈት ቤት፣ ትምህርት ቤቱን የሚያስተዳደረው የሸማቾች ቦርድ ፣ ወተመህ በተገኙበት በተያዘ ቃለ ጉባኤ ትምህርት ቤቶችን የሚያስተዳደረው አካል ከአቅም ጋር በተያያዘ ትምህርት ቤቶችን እስከ ሰኔ 30 ቀን 2014 ዓ.ም ድረስ ለወረዳው ትምህርት ጽህፈት ቤት ለማስረከብ ተስማምቶ እንደነበር የወረዳው የትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ ያስረዳሉ። በቃለ ጉባኤ ከተስማማችሁ ለምን እስከዛሬ ትምህርት ቤቱን አላስረከባችሁም ? የሚል ነበር ።
ኃላፊው እንዳስረዱት፤ ስለጉዳዩ በቃል ከመስማት በዘለለ ስለቃለ ጉባኤው የሚያውቁት ነገር የለም። ይሁን እንጂ ትምህርት ቤቶችን የሸማቾች ቦርድ ማስተዳደር ካልቻለ ትምህርት ጽህፈት ቤት ያነሳው ጥያቄ ተገቢነት ያለው ነው። ምክንያቱም ትምህርት ቤቱ ቢሻሻል የሚጠቀሙት የሸማች ማህበሩ አባል ልጆች ናቸው። ሸማች ካልቻለ ወደ መንግስት መዞር አለበት። ነገር ግን በምን መልኩ ከተባለ ህጋዊ መስመሩን ተከትሎ ሊሆን ይገባል ብለዋል።
ተማሪዎች ማግኘት የሚገባቸውን እውቀት የማያገኙ ከሆነ ፣ መምህራን ማግኘት የሚገባቸውን ጥቅም ማስከበር ካልተቻለ፤ ትምህርት ጽህፈት ቤቱ ይቅርና የሸማቾች ማህበርም ለመንግስት እንዲሰጥ ከማንም በፊት ግንባር ቀደም ሆኖ ይሰራል ሲሉ ተናግረዋል።
በቀጣይ ሳምንት ደግሞ ጉዳዩ የሚመለከታቸውን አካላት በማነጋገር የሚሰጡንን ምላሽ እናቀርባለን።
ሙሉቀን ታደገ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 6/2014