በዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ጠንካራና ተፎካካሪ ቡድንን ይዘው እንደሚቀርቡ ከሚጠበቁ ሃገራት መካከል አንዷ ኢትዮጵያ መሆኗ ይታወቃል። በዚህ ስፖርት ዝናና ክብርን የተጎናጸፈችው ኢትዮጵያ በዓለም ቻምፒዮናም ሆነ በኦሊምፒክ መድረኮች በርካታ ሜዳሊያዎችን የሰበሰበችው በረጅም ርቀት የመም እንዲሁም የጎዳና ላይ ሩጫዎች ነው። በአንጻሩ በመካከለኛ ርቀት ሩጫዎች ላይ ያላት የስኬት ታሪክ ጥቂት ነው።
በዘንድሮው የኦሪገን የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ኢትዮጵያን የሚወክለው የአትሌቲክስ ብሄራዊ ቡድን ከ800 ሜትር ጀምሮ የሚሳተፍ ሲሆን፤ ይኸውም እአአ በ2013 የሩሲያዋ ሞስኮ አዘጋጅ በነበረችበት የዓለም ቻምፒዮና ባልተጠበቀ መልኩ በአትሌት መሃመድ አማን የወርቅ ሜዳሊያ ሊመዘገብ ችሏል። በወቅቱ ይህ ስኬት አስደናቂ ከመሆኑም ባለፈ ኢትዮጵያዊያን በእነዚህ ርቀቶችም ውጤታማ መሆን እንደሚችሉ ተስፋ ሆኖ ነበር። ይሁንና በብዙ የተጠበቀው የዚህ ርቀት ስኬት በመሃመድም ሆነ በሌላ አትሌት ሊደገም አልቻለም። ተሳትፎውም ቢሆን እዚህ ግባ የሚባል አይደለም።
ሌላኛው የመካከለኛ ርቀት 1ሺ500 ሜትር ሲሆን፤ በዚህ ርቀትም በተመሳሳይ በሁለቱም ጾታ በድምሩ ሶስት ሜዳሊያዎች ብቻ ተመዝግቧል። የመጀመሪያው በወንዶች እአአ 2009 የበርሊን ቻምፒዮና በአትሌት ደረሰ መኮንን የተገኘው የብር ሜዳሊያ ነው። በሴቶችም እአአ በ2015 ቤጂንግ ላይ በገንዘቤ ዲባባ የተመዘገበው የወርቅ ሜዳሊያ እንዲሁም እአአ በ2019 የዶሃው ቻምፒዮና በጉዳፍ ጸጋይ የተገኘው የነሃስ ሜዳሊያ ነው። ከቀናት በኋላ በሚጀመረው በዘንድሮው የኦሪጎን ዓለም ቻምፒዮናም በእነዚህ ርቀቶች ውጤታማ ለመሆን እየተሰራ ነው።
ኢትዮጵያ አትሌቲክስ ብሄራዊ ቡድን መካከለኛ ርቀት አሰልጣኙ ብርሃኑ መኮንን፤ በ17ኛው የኳታር ዶሃ የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ኢትዮጵያ በ800 ሜትር ሴቶች በአንድ አትሌት ብቻ መወከሏን ያስታውሳል። በአንጻሩ በዚህ ቻምፒዮና በዚሁ ርቀት በሴቶች ሶስት በወንዶች ደግሞ ሁለት በጥቅሉ በአምስት አትሌቶች ትካፈላለች። ይህም ትልቅ ለውጥ ነበር።
በዚሁ ርቀት ረጅም ጊዜ የሸፈነው ዝግጅትም ተጠናቆ አትሌቶቹ ከትናንት በስቲያ ወደ ውድድሩ ስፍራ ተሸኝተዋል። ዝግጅቱ የዓመቱን ሶስት ትልልቅ ውድድሮች ታሳቢ ያደረገ ሲሆን፤ እነርሱም የዓለም የቤት ውስጥ ቻምፒዮና፣ ዳይመንድ ሊግ እንዲሁም የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ናቸው። በዕቅዱ መሰረትም አሁን የዝግጅቱ ሶስተኛውን ምዕራፍ ሲካሄድ ቆይቶም ተጠናቋል። ከአሁን በኋላ ያለው ጊዜም አትሌቶችን በስነልቦና የማብቃት ስራ እንደሚሆን አሰልጣኝ ብርሃኑ ተናግሯል። በዚህ ላይም ከአሰልጣኞች ባለፈ ታዋቂው የህክምናና ስነልቦና ባለሙያ ዶክተር ምህረት ደበበ ብሄራዊ ቡድኑ ባረፈበት ስፍራ ተገኝተው ጠቃሚ ስልጠና መሰጠቱን አሰልጣኙ ይገልጻል።
በ1ሺ500 ሜትር ወንዶች በዓለም የቤት ውስጥ ቻምፒዮና የወርቅ ሜዳሊያ ማጥለቅ የቻለው ወጣቱ አትሌት ሳሙኤል ተፈራ በዚህ ውድድርም ውጤታማ እንደሚሆን ከስፖርት ቤተሰቡ ዘንድ ከፍተኛ ግምት አግኝቷል። አትሌቱ በኦስሎ እና ዩጂን ዳይመንድ ሊጎች ከሚታወቅበት ርቀት ባለፈ መሮጡ ይታወሳል። አቅም እንዳለውም ማስመስከር ችሏል። በዚህም የዓለም ቻምፒዮና ተሳትፎው በሌላ ርቀት ይሳተፋል በሚል ቢጠበቅም በ1ሺ500 ሜትር ቡድኑን እንደሚመራ ፌዴሬሽኑ አረጋግጧል። በመሆኑም በአትሌቲክስ ትልቅ በሆነው በዚህ የውድድር መድረክ አትሌቱ የሜዳሊያ ሰንጠረዡ ውስጥ ይገባል የሚል ከፍተኛ ቅድመ ግምት ተሰጥቶታል።
የአትሌቱ አሰልጣኝ የሆነው ብርሃኑ አትሌቱ በርቀቱ ጠንካራ ከሆኑት መካከል የሚመደብ ቢሆንም ተፎካካሪዎቹ ቀላል እንዳልሆኑ ነው የሚገልጸው። ‹‹መካከለኛ ርቀቶች የመላው ዓለም ውድድሮች ናቸው›› የሚለው አሰልጣኙ ለአብነት ያህል በረጅም ርቀቶች በዋናነት ለሜዳሊያ የሚፎካከሩት ሶስቱ የምስራቅ አፍሪካ ሃገራት አትሌቶች ናቸው። በመካከለኛ ርቀት ግን ከሁሉም ዓለማት የተውጣጡ አትሌቶች ውድድሩ የዓለም ቻምፒዮና እንደመሆኑ ከፍተኛ ዝግጅት ያደርጋሉ። የአውስትራሊያ፣ ኖርዌይ፣ እንግሊዝ እና ኬንያ አትሌቶች በተለይ እንደ ስጋት የሚታዩ መሆናቸውንም አሰልጣኙ አልሸሸገም።
ከዚህ አንጻር የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ዝግጅት ሲያደርግ ቆይቷል፤ የቤት ውስጥ ቻምፒዮኑ ሳሙኤልም ከፍተኛ ተፎካካሪ እንደሚሆን ይጠበቃል። የተለያዩ ቴክኒኮችን እንዲሁም የሚያጋጥሙ እድሎችን በመጠቀም ውጤታማ ለመሆን ጥረት እንደሚያደርጉም አሰልጣኙ ተስፋቸውን ገልፀዋል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ሰኞ ሐምሌ 4 ቀን 2014 ዓ.ም