በቅርቡ በኢትዮጵያ ከደረሰው የቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን አደጋ ጋር ተያይዞ ከሁሉም ቀድማ በቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኖች ላይ እገዳ የጣለችው ትልቋ የቦይንግ ደንበኛ ቻይና 300 ኤር ባስ ጀት አውሮፕላኖችን ለመግዛት መስማማቷ ተሰማ፡፡
ስምምነቱ የተፈረመው ፕሬዚዳንት ሽ ጅፒንግ ለይፋዊ ጉብኝት ሰሞኑን ወደ አውሮፓ ማቅናታቸውን ተከትሎ ነው፡፡ ፕሬዚዳንቱ በአውሮፓ ቆይታቸው ፓሪስን በጎበኙበት ወቅት ሦስት መቶ ኤር ባስ ጀት አውሮፕላኖችን ለመግዛት ከፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሩን ጋር ስምምነት ፈርመዋል፡፡
በዚህም ፕሬዚዳንት ሽ ጅፒንግ 290 ኤ320 ሞዴልና አስር ኤ350 ኤርባስ ጀቶችን፤ በድምሩ ሦስት መቶ የመንገደኛ ጀት አውሮፕላኖችን ከኤር ባስ ኩባንያው ለመግዛት ስምምነት ፈጽመዋል፡፡ በዚህ ወቅት ከፈረንሳዩ አቻቸው ጋር በጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት ፕሬዚዳንት ሽ “ስምምነቱ ቻይና ከፈረንሳይ ብሎም አውሮፓ ጋር ያላትን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግር ነው” ማለታቸውን ሮይተርስ ጽፏል፡፡
የፈረንሳዩ አቻቸው ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሩን በበኩላቸው፤ “የተፈረመው ግዙፍ የአቪየሽን ስምምነት ግንኙነታችን አንድ ርምጃ ወደፊት የሚያራምድና አሁን ላይ ያለንበት ወቅታዊ ሁኔታም በእጅጉ በሚያስደስት ደረጃ ላይ መሆኑን አመላካች ነው” ብለዋል፡፡
ታዋቂው የቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን ስድስት ወራት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በኢንዶንዥያና በኢትዮጵያ ሁለት ከባድ አደጋዎችን ካስተናገደና ቻይናም በሁሉም የቦይንግ አውሮፕላኖች ላይ ዕገዳ በጣለች ማግስት መደረጉ አሜሪካንና ሌሎች የአሜሪካና የምዕራብ አውሮፓ አገራትን አሳስቧል፡ ፡
ምክንያቱም የቻይና ኢኮኖሚ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ በመምጣቱ አገሪቱ በሁሉም ዘርፍ ላይ በዓለም አቀፍ መድረኮች ያላት ተሰሚነት እየጨመረ የመጣ በመሆኑ በአሜሪካና በሌሎች ተቀናቃኞቿ ላይ ስጋት እያሳደረ እንዳለ ቢቢሲ በዘገባው አመላክቷል፡፡
አውሮፓዊው የቦይንግ ተቀናቃኝ ኩባንያ ኤር ባስ በምን ያህል ዋጋ እንደሚሸጣቸው ባይገልፅም በአንድ ጊዜ ሦስት መቶ አውሮፕላኖችን መሸጥ ግዙፍ ስምምነት መሆኑንና ከፍተኛ ገቢ የሚያስገኝ በመሆኑ ለኩባንያው ትልቅ እድል የሚፈጥር እንደሆነ የዘገበው ሲኤንኤን ነው ፡፡
ኩባንያው በአንድ ጊዜ ብዙ ለሚገዙ ደንበኞች የሚሰጠውን ቅናሽ ሳይጨምር ኤር ባስ ለቻይና ለመሸጥ ከተስማማው የሦስት መቶ ኤር ባስ ጀት አውሮፕላኖች ሽያጭ እስከ 35 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ሊያገኝ እንደሚችልም ሲኤንኤን ግምቱን አስቀምጧል፡፡
በዚህም ስምምነቱ በተፈጸመበት ማክሰኞ ዕለት የኤርባስ የአክስዮን ሽያጭ በአንድ ነጥብ አምስት በመቶ ዕድገት አሳይቷል፡፡ በዚህም ቻይና ኤርባስን በመምረጧ ኩባንያው ክብርና ደስታ የተሰማው መሆኑን የዘገበው ደግሞ ኤርኦንላይን ነው፡፡
ኤር ባስን ወክለው ስምምነቱን የፈረሙት የኤርባስ ኩባንያ የኮመርሽያል ኤርክራፍት ፕሬዚዳንት ጉለየም ፎሪ፤ “በቻይና አቭየሽን ኢንዱስትሪ ውስጥ አሻራችን እየተስፋፋ መምጣቱ በቻይና ገበያ ያለንን የረጅም ጊዜ ዕምነትና የቻይናንና የሌሎችንም ደንበኞቻችን ፍላጎት ለማርካት ያለንን ቁርጠኝነት አመላካች ነው” ብለዋል፡፡
እስከ ጥር 2019 መጨረሻ ድረስ 1730 ኤርባስ አውሮፕላኖች በቻይና አየር መንገዶች ውስት አገልግሎት እየሰጡ የሚገኝ ሲሆን በሚቀጥሉት ሃያ ዓመታት ደግሞ አሃዙ ወደ 7400 ከፍ ይላል ተብሎ የእንደሚጠበቅ የኤርባስ የቅርብ ጊዜ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 19/2011
ይበል ካሳ