አገሬ ኢትዮጵያ ሞኝ ነሽ ተላላ፣
የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ
ይህ ግጥም የሕዝብ ስነ ቃል እስከሚመስል ድረስ ይነገራል። በየጋዜጣውና መጽሔቱ ለሀገራቸው ተጋድሎ ያደረጉ ሰዎችን ታሪክ ለመዘከር እንደ መግቢያ ያገለግላል። በመድረኮች በሚደረጉ ንግግሮችም የሀሳብ ማዳበሪያ ተደርጎ ይጠቀሳል። በአጠቃላይ ለሀገራቸው የሠሩትን ለማመስገንና ሀገራቸውን እየዘረፉ ለሆዳቸው ያደሩትን ሸንቆጥ ለማድረግ ብዙዎች ይጠቀሙታል።
የዚህ ግጥም ፀሐፊ ባለቅኔው ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሴ ናቸው። በዚህ ሳምንት እኝህን ባለቅኔ እንዘክራለን። ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት ሰኔ 30 ቀን 1939 ዓ.ም ነው። የሚገርመው ደግሞ ሰኔ 30 በየዓመቱ የሚታወሰው የንባብ ቀን በመባል ነው። የኢትዮጵያ ደራሲያን ማኅበርም ቀኑን በተለያዩ ዝግጅቶች ያከብረዋል። እኝህ ደራሲና ባለቅኔ ልክ በዚህ በንባብ ቀን ነው ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት። የባለቅኔ ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሴን ታሪክና ሥራዎች እናስታውስ።
ዮፍታሔ ንጉሤ ከአባቱ ከቄስ ገበዝ ንጉሤ ወልደኢየሱስና ከእናቱ ከወይዘሮ ማዘንጊያሽ ወልደኄር በ1887 ዓ.ም ጎጃም፣ ደብረ ኤልያስ ውስጥ ተወለደ። ‹‹ዮፍታሔ›› የሚለውን ስም ያወጡለት ታዋቂው የደብረ ኤልያስ ቅኔና የመጻሕፍት ትርጓሜ መምህር የኔታ ገብረ ሥላሴ ነበሩ።
ልጅ የአባቱን ፈለግ መከተል የቆየ ልማድ ነውና ዮፍታሔም በነበረው ወግና ሥርዓት መሠረት የቆየው የቤተሰቡ ታሪክ ይቀጥልና ክብሩንም ይወርስ ዘንድ ለትምህርት ተላከ። በተወለደበት አካባቢ፤ አደላ ንጉሤ ወደተባሉ መምህር ዘንድ በመሄድ ትምህርት ጀመረ። ፊደልን ካጠና በኋላ ደረጃ በደረጃ ንባብን፣ መዝሙረ ዳዊትን፣ የዜማ ትምህርትን፣ ፆመ ድጓን፣ ምዕራፍንና ድጓን ተምሮ አጠናቀቀ። እነዚህን ሲያጠናቅቅ ቅኔ ቤት ገባ። በአካባቢው ታዋቂ የነበሩት መምህር ገብረሥላሴ፤ ዮፍታሔ የዘረፋቸውን ቅኔዎች ደጋግመው ሰምተው፣ በቅኔ ችሎታው ብቁ መሆኑን ተገንዝበውና በደብረ ኤልያስ ሊቃውንት ፊት ‹‹ተቀመጥ በወንበሬ ተናገር በከንፈሬ›› ብለው ችሎታውን መስክረውለት ተመረቀ። ዮፍታሔ የቅኔ ትምህርቱን የጨረሰው ገና በለጋ እድሜው ነበር።
ዮፍታሔ በቅኔና በዜማ ትምህርት ለመምህርነት የሚያበቃ ችሎታ ቢኖረውም ደብረ ኤልያስ ውስጥ ብዙ ሊቃውንት ስለነበሩና እድሜው ትንሽ ስለነበር ጉባዔ ከፍቶ አላስተማረም። ከዚያ ይልቅ በሌሎች ተግባራት ደብሩን አገልግሏል። ገና በወጣትነቱም ለጎልማሶች በሚሰጠው ማዕረግ ‹‹ቀኝ ጌታ›› ለመባል በቅቷል።
ዮፍታሔ በግንቦት ወር 1909 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ ተጓዘ። በወቅቱ ሥራ የሚያገኙት የቤተ ክህነት ትምህርት የተማሩ ሰዎች ስለነበሩና ቀኝ ጌታ ዮፍታሔም የቅኔና የዜማ ሊቅ ስለነበሩ ሥራ ለማግኘት ብዙም አልተቸገሩም ነበር። ሥራ ያገኙትም ቀበና አቦ ቤተክርስቲያን ቢሆንም በሥራው ምክንያት ከሚሠሩበት ደብር አልፎ በአዲስ አበባ ውስጥ ተደናቂ ለመሆን በቁ። በአጭር ጊዜያት ውስጥም ስምና ሥራቸው በመንግሥት ዘንድ ታውቆ ተመስግኖ ለሽልማት በቁ።
ጥር 11 ቀን 1910 ዓ.ም የጥምቀት በዓልን ምክንያት በማድረግ ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ለየአድባራቱ ሽልማት ልከው ነበር፤ ቀኝ ጌታ ዮፍታሔም ከተሸላሚዎቹ መካከል አንዱ ነበሩ።
ባየር በተባለው የፈረንሳይ ኩባንያ ውስጥ ሲሰጥ የነበረው ስልጠና በመቋረጡ ምክንያት በሰኔ ወር 1911 ዓ.ም በሊጋባ ጽሕፈት ቤት ውስጥ ተቀጠሩ። ይህም ከቤተ ክህነት እየራቁ እንዲሄዱ እንዳስገደዳቸው ታሪካቸው ያስረዳል። በ1918 ዓ.ም ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ እና አቶ መላኩ በጎሰው በዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት የአማርኛ መምህር ሆነው ተመደቡ። በወቅቱ የአማርኛ ቋንቋ ማስተማሪያ መጻሕፍት ስላልነበሩ ራሳቸው ማስተማሪያ እያዘጋጁ ያስተምሩ ነበር። ከአማርኛ ቋንቋ መምህርነታቸው በተጨማሪም መዝሙሮችን እየደረሱ ለተማሪዎቻቸው ያስተምሩም ነበር።
የቀኝ ጌታ ዮፍታሔ መዝሙሮች በትምህርት ቤቶች ውስጥ ብቻ ተወስነው አልቀሩም። በየጊዜው እየደረሰ ከሚያሳያቸው ትያትሮች ጋር እያስማማ ለሕዝብ ያቀርባቸው ነበር። ሥራዎቹም ተወዳጅ ነበሩ። ለአብነት ያህል ተማሪዎች ‹‹ወላድ ኢትዮጵያ›› የሚለውን መዝሙር በቀኝ ጌታ ዮፍታሔ መሪነት ሲዘምሩ የሰማቸው ሰው ሁሉ ደስ ተሰኝቶ እንደነበር በብርሃንና ሰላም ጋዜጣ ላይ የታተመ ጽሑፍ ያመለክት ነበር።
‹‹ … ወላድ ኢትዮጵያ ለልጆቿ ብላ፣
እጅግ ሳይጥሩላት ሳይዘሯት አብቅላ፣
ስንዴውን ጠብቃ እንክርዳዱን ነቅላ፣
ስትመግበን አየን በፀሐይ አብቅላ … ››
ይሁን እንጂ በጊዜው ሙዚቃን በኖታ ያስተምሩ በነበሩት ናልቫንድያንና ሙዚቃን በድጓ ያስተምሩ በነበሩት በቀኝ ጌታ ዮፍታሔ መካከል መጠነኛ አለመግባባት እንደነበር ታሪካቸው ያስረዳል። ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ በቤተ ክህነት የዜማ ትምህርት ለመምህርነት የሚያበቃ እውቀት ስለነበረው መዝሙር እየደረሰ ማስተማሩ የሚያስገርም ባይሆንም ትያትር ለመድረስ ምን አበረታታው የሚል ጥያቄ መነሳቱ አይቀርም። የቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤን ታሪክ የሚዘክር መጽሐፍ የፃፈው ገጣሚ፣ ደራሲና ሐያሲ የነበረው ዮሐንስ አድማሱ ሰኔ 23 ቀን 1961 ዓ.ም በታተመው መነን መጽሔት ላይ ‹‹ዮፍታሔን ለማስታወስ ያህል›› በሚል ርዕስ ባሰፈረው ጽሑፍ፣ ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ እንዴት ወደ ትያትር ዓለም እንደገባ በመጠኑ ይጠቁመናል።
‹‹ … ወደ ትያትር ዓለም ያስገባው አንዱ ምክንያት ወደ አዲስ አበባ ከመጣ በኋላ ለአማርኛ መምህርነት መመልመሉ ይመስለኛል። በዚያን ጊዜ ተውኔት የሚጽፉና የሚያሳዩ መምህራንና ተማሪዎች ነበሩ። ትያትር የሚያሳዩትም ብዙውን ጊዜ በትምህርት ቤቶችና በሆቴሎች ውስጥ ነበር። ሌላው ምክንያት ደግሞ የጊዜው ሁኔታ ይመስለኛል። ከ1900 እስከ 1928 ዓ.ም ኢትዮጵያ ብዙ ተፈትናለች። ደራሲያኑም የሕዝቡን ስሜት ለመንካትና ልቦናውን ለማንቃት ዋነኛ መሣሪያ የሆናቸው የዘመኑ መድረክ ሳይሆን አይቀርም …››
ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ በ1927 ዓ.ም የፋሺስት ኢጣሊያ ጦር በምስራቅ ኢትዮጵያ በኩል በከፈተው ጦርነት ለአገራቸው ለኢትዮጵያ ክብር በጀግንነት ሲዋጉ ለተሰውት ለደጃዝማች አፈወርቅ ወልደሰማዕት እና ለፊታውራሪ ዓለማየሁ ጎሹ እንዲህ ብሎ ተቀኝቶላቸዋል …
ዓለማየሁ ጎሹ እንደቀድሞ ካሣ
አጥንቱን ከስክሶ ደሙንም አፍስሶ
ደጃዝማች አፈወርቅ ምድሩን አሳርሶ
አጥንቱን ተከለው በደሙ አለስልሶ ።
የኦጋዴን ዳኛ የኦጋዴን ዳኛ
ደከመው መሰለኝ ተሸፋፍኖ ተኛ!
የሀገር ፍቅር ማኅበር በ1927 ዓ.ም ሲቋቋም የአርበኞችን ስሜት ለማነቃቃት በርካታ መዝሙሮችን አዘጋጅቶ አቅርቧል። ‹‹ጎበዝ አየን››የተሰኘ መጽሐፍም ጽፏል።
የፋሺስት ኢጣሊያ ጦር አዲስ አበባን ከተቆጣጠረ በኋላ በፋሺስቱ ጦር በጥብቅ ይፈለጉ ከነበሩ ግለሰቦች መካከል አንዱ በብዕር ተጋድሎው ሕዝቡን ያነሳሳ የነበረው ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤ ሆነ። የፋሺስት ወታደሮች መኖሪያ ቤቱ ድረስ ሄደው እርሱን ሲያጡት ያገኙትን እቃ ዘርፈው ሄዱ። ይህን ሁኔታም ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ በወቅቱ ለፊታውራሪ ሀብተሚካኤል ታፈሰ በጻፉት ደብዳቤ ላይ አስፍረውታል። ከቀናት በኋላም ከተደበቀበት በመውጣት በወለጋ በኩል ወደ ሱዳን ተሻገረ። በ1929 ዓ.ም ሱዳን ውስጥ ሆኖ ከፃፈው መዝሙር የሚከተሉት ስንኞች ይገኙበታል።
ጎበዛዝቴ ሆይ ወይ ቆነጃጅቴ
ምንኛ ነደደ ተቃጠለ አንጀቴ
እንመለሳለን በአዲሱ ጉልበቴ
እናንተም ከምርኮ እኔም ከስደቴ!
ካርቱም ሞቃታማ ከተማ በመሆኗ ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ በየጊዜው ይታመም ነበር። ከሕመሙ በተጨማሪ የገንዘብ ችግር ስለነበረበት በወቅቱ በስደት እንግሊዝ የነበሩት ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ለመታከሚያ የሚሆን ገንዘብ ልከውለት ነበር። በሰኔ ወር 1919 ዓ.ም ከለንደን በፃፉለት ደብዳቤም እንዲህ ብለውት ነበር።
‹‹ … በሀገራችንና በሕዝባችን ላይ በተደረገባትና በደረሰባት መከራ ምክንያት ተሰደህ መምጣትህንና ካርቱም መግባትህን ሰማን። ጽኑ ሕመም መታመምህን በመስማታችን አዘንን። አሁንም እግዚአብሔር ይማርህ። ስለመታከሚያም የእርዳታ ገንዘብ እንዲላክልህ ስላደረግን እስካሁን ሳይደርስህ አይቀርም …››
ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ካርቱም በነበረበት ወቅት የድርሰት ሥራዎቹንና ደብዳቤዎችን ለንጉሠ ነገሥቱና አብረዋቸው ለሄዱት ባለስልጣናት ይልክ ነበር። ካርቱም በነበረበት ወቅት ከፃፋቸው ድርሰቶች መካከል አንዷ አሁንም ድረስ በበርካታ የትያትር አፍቃሪዎች ዘንድ የምትታወቀውና የምትወደደው ‹‹አፋጀሽኝ›› ናት። ‹‹አፋጀሽኝ›› ኢትዮጵያ እንዴት በጠላት እጅ እንደወደቀችና እንዴትስ እንደዳነች በታመመች ሴት አስመስሎ ያቀረበባት ትያትር ናት። በመታመሟና በመዳኗ መካከል ያለው ድርጊት የወቅቱን የፖለቲካ ሁኔታ ይገልፅ ነበር።
የድርሰት ሥራዎችን ከመሥራት በተጨማሪ ከለንደን የሚመጡ ደብዳቤዎችን እየተቀበለ ለአርበኞች ያደርስ ነበር፤ ከአርበኞች በኩል የተገኘውን የጦርነት ወሬም ወደ ንጉሠ ነገሥቱ ያስተላልፍ ነበር። በጊዜው ወደ ሱዳን ከሚሄዱት ኢትዮጵያውያንና እርሱም በድብቅ ወደ ኢትዮጵያ እየመጣ የተገነዘበውን ሁሉ ተከታትሎ ያሳውቅም ነበር።
የካርቱም ቆይታው ብዙ ችግሮችን ያስተናገደበት እንደነበር ታሪኩ ያስረዳል። በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ላይ በነበረበት ወቅት የፋሺስት ኢጣሊያ ጦር በኢትዮጵያውያን አርበኞች አስደናቂ ትግልና በእንግሊዝ ጦር ድጋፍ እየተሸነፈ በመምጣቱ ንጉሠ ነገሥቱ ከለንደን ወደ ካርቱም ደርሰው ወደ ኢትዮጵያ ለመግባት ዝግጅት ተጀመረ። ንጉሠ ነገሥቱ ወደ ኢትዮጵያ ሲገቡ ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ የጉዞ ማስታወሻቸውን እየፃፈ አብሮ ወደ ኢትዮጵያ ገባ።
ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤ ከስደት ከተመለሰ በኋላ የሰንደቅ ዓላማ መዝሙሮችንና የተለያዩ መወድስ ግጥሞችን ለንጉሠ ነገሥቱ አቅርቧል። ከወቅቱ ሥራዎቹ መካከል ከሁሉም ላቅ ብለው የሚታወቁት ‹‹ደሙን ያፈሰሰ›› እና ‹‹ተጣማጅ አርበኛ›› የተሰኙት መዝሙሮች ናቸው።
‹‹አፋጀሽኝ›› የተባለው የትያትር ሥራው በሕዝቡ ዘንድ በመወደዱ ንጉሠ ነገሥቱ በተገኙበት መስከረም 3 ቀን 1934 ዓ.ም በድጋሚ ታየ። ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ሥራ ሳያገኝ ከአንድ ዓመት በላይ ተቀመጠ። በፋሺስት ወረራ ጊዜ ባንዳ የነበሩ ሳይቀሩ ሥራ አግኝተው እርሱ በመቅረቱ ተናደደ። እንዲህም ሲል ተቀኜ።
ለጌሾ ወቀጣ ማንም ሰው አልመጣ
ለመጠጡ ጊዜ ከየጎሬው ወጣ!
አገሬ ኢትዮጵያ ሞኝ ነሽ ተላላ
የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ!
በማለት ጊዜውን የመዘነ ግጥም ገጥሟል። በትምህርትና ስነ ጥበብ ሚኒስቴር ውስጥ ሥራ ቢሰጠውም ለመሥራት ፈቃደኛ ሳይሆን ቀረ። በዚህ መሐልም ቢሆን የድርሰት ሥራውን ስላላቋረጠ በሐምሌ ወር 1934 ዓ.ም ‹‹እያዩ ማዘን›› የተሰኘውን የትያትር ሥራውን ለመድረክ አበቃ። በጥቅምት ወር 1935 ዓ.ም የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት ሆኖ ተሾመ። ‹‹ዕርበተ ፀሐይ›› የሚል ትያትር ደርሶ የነበረ ቢሆንም ለዕይታ ሳይበቃ ቀርቷል። ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ከስደት ከተመለሰ በኋላ ስምንት መጻሕፍትን እንደፃፈ ቢነገርም ድርሰቶቹን ግን ማግኘት እንዳልተቻለ ተፅፏል። ተቋርጦ የነበረውን የትያትር ሥራ ለማስቀጠል በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት አማካኝነት ማኅበር ሲቋቋም የማኅበሩ መሪ በመሆን አገልግሏል።
ገጣሚ፣ ደራሲና ሃያሲ የነበረው ዮሐንስ አድማሱ የቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤን አጠቃላይ አካላዊና ባሕርያዊ ማንነት ሲገልፅ ‹‹ዮፍታሔ ንጉሤ፣ ብሔረ ነገዱ፣ አገረ ውላዱ፣ ጐጃም፤ ቅኔ የተቀኘበት፣ ድጓና ምስጢር የተማረበት፣ ደብረ ኤልያስ ነበር። ጠይም፣ ረዥም፣ ጠጉረ ሉጫ፣ መልከ መልካም፣ ቀጭን ዠርጋዳ፣ ጣተ መልካም፣ ሽቅርቅር፣ ጥዩፍ፤ ኮከቡ ሚዛን ነፋስ ነበር›› ብሏል። ዮሐንስ አድማሱ ሰኔ 25 ቀን 1961 ዓ.ም በወጣው የመነን መጽሔት ዕትም ላይ ‹‹ተወርዋሪ ኮከብ›› በሚል ርዕስ ስለቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤ ግጥም ጽፏል።
ደራሲ፣ አርበኛ፣ ባለቅኔና መምህር ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤ ሰኔ 30 ቀን 1939 ዓ.ም ሥራቸውን ሲያከናውኑ ውለው ወደ መኝታቸው በሄዱበት እስከወዲያኛው አሸለቡ። የቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤ አፅም ያረፈው በመንበረ ፀባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ነበር። ሰኔ 29 ቀን 2009 ዓ.ም አፅማቸው ከአዲስ አበባ ፀሎተ ፍትሐት ተደርጎለት፣ በርካታ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች በተገኙበት መድረክ ‹‹አፋጀሽኝ›› የተሰኘው የትያትርና ሌሎች ሥራዎቻቸውን የሚዘክር አጭር ትርኢት ቀርቦ ወደ ትውልድ ስፍራቸው ተሸኝቷል። በዚያም በርካታ ሰው በተገኘበት አፅማቸው በክብር አርፏል።
አርበኛ እና ባለቅኔ ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሴ ከሚታወሱባቸው አገራዊ ስሜት ያላቸው ግጥሞች በዚህ እንሰናበት።
አጥንቱን ልልቀመው መቃብር ቆፍሬ
ጎበናን ከሸዋ አሉላን ከትግሬ
አሉላ ሴት ልጁን ጥይት ሲያስተኩስ
ጎበና ሴት ልጁን ሲያስተምር ፈረስ
ሀገሬ ተባብራ ካረገጠች እርካብ
ነገራችን ሁሉ የእንቧይ ካብ የእንቧይ ካብ!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 3 ን 2014 ዓ.ም