ነዋሪነታቸው በአሜሪካ ቨርጂኒያ ግዛት ነው። ተወልደው ያደጉት እዚሁ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ሲሆን የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን መድኃኒዓለም ትምህርት ቤት ተከታትለዋል። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ ወደ ሱዳን በመሄድ አፍሪካ በተባለ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በጋዜጠኝነት ትምህርት ዘርፍ አግኝተዋል። ወደ አገራቸው ከተመለሱ በኋላም በተለያዩ መንግሥታዊ ተቋማት ተቀጥረው የሠሩት የዛሬው የዘመን እንግዳችን በግል ሥራ ላይ ተሰማርተውም አገራቸውን አገልግለዋል። በተለይም የራሳቸውን የአረብኛ ቋንቋ ኢንስቲትዩት ከፍተው በሥራ አስኪያጅነትና በተለያዩ የአመራር ሥራዎች ላይ ቆይተዋል። በዚህም ሳይወሰኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በፊሎሎጂ ትምህርት ክፍል የማስተርስ ዲግሪያቸውን ይዘዋል።
ካለፉት አስር ዓመታት ወዲህ ደግሞ ኑሯቸውን ሙሉ ለሙሉ አሜሪካ አገር ያደረጉት እኚሁ ሰው በኮምፒዩተር ቴክኖሎጂ ስልጠና በመውሰድ በሙያቸው እየሠሩ ይገኛሉ። ከዚሁ ጎን ለጎንም በአሜሪካ አገር የሚኖሩ ሙስሊም ኢትዮጵያውያንን በማሰባሰብና ለአገራቸው ልማት አዎንታዊ ሚና እንዲጫወቱ ለማድረግ ከፍተኛ ሥራ እየሠሩ የሚገኙ አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ ናቸው። በተለይም በድር ኢትዮጵያ በተባለው እና በሙስሊም ዳያስፖራዎች ከ22 ዓመታት በፊት የተቋቋመውን ተቋም በመቀላቀል በሕዝብ ግንኙነትና በቦርድ አባልነት እያገለገሉ ይገኛሉ።እኛም የዛሬውን የኢድ- አልአድሃ (አረፋ) በዓልን ምክንያት በማድረግ አቶ ቡርሃን አህመድ አህመዲን የዘመን እንግዳችን አድርገናቸዋል።
አዲስ ዘመን፡- ወደአገር የመጡበትን አጋጣሚ እስኪ ያስረዱን?
አቶ ቡርሃን፡- እንደሚታወቀው መንግሥት ያደረገውን አገራዊ ጥሪ ተቀብለን የኢድን በዓል ምክንያት በማድረግ አዲስ አበባ ገብተናል።ሌሎች አባሎቻችንና ደጋፊዎቻችን ቀደም ብለው ነው የገቡት። ትልቅ ኮንቬንሽን አዘጋጅተናል። በነገራችን ላይ በድር ኢትዮጵያ የተመሠረተበትን 22ኛ ዓመት እያከበረ ነው ። ላለፉት 21 ዓመታት ግን በአሜሪካ የተለያዩ ግዛቶችና ካናዳ ነበር ሲዘጋጅ የቆየው። ዘንድሮ ግን አገራዊ ጥሪ ሲደረግልን አገራችን ውስጥ ለማካሄድ ከፍተኛ ደስታና ተስፋ ውስጥ ሆነን ነው ተሰባስበን የመጣነው። አሁንም በመላው ዓለም የሚገኙ አባሎቻችንና ደጋፊዎቻችን ወደ አገር ቤት እየገቡ ይገኛሉ።
የዚህ ትልቅ ኮንቬንሽን ዋነኛ አላማ የሕዝብ ለሕዝብ ትውውቅ ለመፍጠርና እዚህ አገር በጦርነትና በተለያዩ ምክንያቶች የተጎዱና የተፈናቀሉ ወገኖችን ለመደገፍ ነው። በተጨማሪም ኮንቬንሽኑ የቱሪዝምና ኢንቨስትመንት ዘርፉን ለማነቃቃት ትልቅ ዕድል ይፈጥራል ተብሎ ታልሞበት የተዘጋጀ ነው። እንዲሁም ከማኅበረሰቡ ጋር ተዋውቆ በጋራ አገር ለማሳደግ ነው። በተለይ አሁን በአገራችን ያሉት አሳዛኝ ሁኔታዎች፣ ጎሳና ሃይማኖት ተኮር ግጭቶችን ከማኅበረሰባችን ጋር በጋራ በመሆን አንድ ላይ የሚፈታበትን መንገድ ለማየት የታለመ ሰፊ ዓላማ ያለው፣ በርካታ የሥራ እንቅስቃሴ ነው እያደረግን ያለነው።
‹‹ከኢድ እስከ ኢድ›› የበድር ኮንቬንሽን አንዱ አካል ነው። በርካታ ሥራዎች ሲከናወኑ ቆይተዋል። መርሃ ግብሩ ከበዓልም ጋር አብሮ የተገናኘ እንደመሆኑ በዓሉ እንዳለቀ ነው ኮንቬንሽኑ የሚጀምረው። በዚያ መርሃ ግብር ላይ ይዘናቸው ከመጣናቸው ሥራዎች መካከል አንደኛ በጋራ ተገናኝቶ መወያየት ነው። ሃይማኖታዊም፤ አገራዊም በሆኑ ጉዳዮች የተለያዩ ጽሑፎች ይቀርባሉ፤ ውይይቶች ይደረጋሉ።
አዲስ ዘመን፡- በድር ኢትዮጵያ ላለፉት 22 ዓመታት ምን ምን ሥራዎችን አከናውኗል? ከተቋቋመበት ዓላማ አኳያስ ምንዓይነት ውጤቶችን አምጥቷል?
አቶ ቡርሃን፡- በድር ኢትዮጵያ እንዳልኩሽ ከተቋቋመ 22 ዓመታትን ያስቆጠረ ድርጅት ነው። ለአገር አሳቢ በሆኑ ኢትዮጵያውያን የተመሠረተው ይኸው ተቋም ዋነኛ ዓላማው በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያኖንን በማቀራረብ ለአገር አዎንታዊ ሚና መጫወት ነው። በተለይ ሙስሊሙ ማኅበረሰብ ሃይማኖቱንና ባህሉን ጠብቀው እንዲያቆዩ፤ እርስ በእርስ እንዲደጋገፉ፤ አዲሱ ትውልድ ማንነቱንና አገሩን እንዲያውቅና እንዲደግፍ በሚል ሰፋፊ ሥራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል።
በቅርቡ በድር ኢትዮጵያ ከሠራቸው ትላልቅ ሥራዎች መካከል ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አንድ ሚሊዮን 50 ሺ ዶላር ነው ያሰባስብነው። ይህም ብር በተቀመጠለት አካውንት ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ያስገባ ድርጅት በመሆኑ ከመንግሥት አካላት ትልቅ እውቅና ተሰጥቶታል። ምንአልባትም በዋሽንግተን ዲሲ ውስጥ በአንድ ጊዜ ይህንን ያህል ገንዘብ በማሰባሰብ ቀዳሚ ድርጅት እንደሆነም ነው የምረዳው። ከዚህም ባሻገር ኮቪድን ተከትሎ በተፈጠረው የኑሮ ውድነት ማኅበረሰቡን በመደገፍ ትልቅ አስተዋፅኦ ሲያበረክት ቆይቷል። ድርቅ፣ ጎርፍና መፈናቅል ሲከሰት ግንባር ቀደም በመሆን ከዳያስፖራው ማኅበረሰብ ገንዘብ በማሰባሰብ የተጎዱ ወገኖችን ረድቷል። በእነዚህ ዓመታት ከገንዘብ ድጋፉ ባሻገር በአገራችን ላይ የሚደረጉ የውጭ ጫናዎችን ከመታገል አኳያ አሜሪካ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲና ሌሎች የዳያስፖራ ማኅበራት ጋር በመተባበር የተለያዩ ሥራዎችን አከናውኗል።
በነገራችን ላይ በድር ራሱን የቻለ አንድ ድርጅት ሳይሆን በተለያዩ የአሜሪካ ግዛቶች ውስጥ ያሉ የ27 ኮሚኒቴዎችና የካናዳ ሙስሊም ኢትዮጵያን አቅፎ የያዘ ትልቅ ጥላ ነው። ለምሳሌ ፕሬዚዳንታችን ነዋሪነቱ ቨርጅኒያ የሆነና ከሰላም ፋውንዴሽን የተገኘ ነው። የድርጅቱ የበላይ ጠባቂ ደግሞ ዶክተር በርሁን የሚባልና ቴክሳስ ላይ የሚኖር ሰው ነው። የሹራ ካውንስል የምንለው ደግሞ ካናዳ ቶሮንቶ የሚገኘው በሼህ መሃመድ አወል ነው የሚመራው።ስለሆነም በድር ኢትዮጵያ ከተለያዩ ኮሚኒቴዎች የተውጣጣ ትልቅ ድርጅት ነው።
አዲስ ዘመን፡- ዛሬ የአረፋ በዓል እንደመሆኑ እስቲ መለስ ብለው በልጅነት ጊዜዎ በዓልን እንዴት ያከብሩ እንደነበር እና የማይረሱት ገጠመኝ ካለዎት ያስታውሱን?
አቶ ቡርሃን፡- እኔ የተወለድኩትም ሆነ ያደኩት አዲስ አበባ እንደመሆኑ እንደማንኛው የአዲስ አበባ ነዋሪ በዓልን ክርስቲያኑም ሆነ ሙስሊሙ በጋራ ነው የሚከብረው። በልጅነት ጊዜ በተለይ የማልረሳው በዓል ሲመጣ አዲስ ልብስ መልበስና አዲስ ጫማ የምናደርግበት በመሆኑ ከሁሉ በላይ የሚያስደስተኝ ነገር ይሄ ነበር። በተጨማሪም ከአብሮ አደግ ክርስቲያን ጓደኞቼ ጋር ምንም ልዩነት ሳይኖረን አብረን በዓል የምናክብርበት ሁኔታ ዛሬም ድረስ በአዕምሮዬ ከቀሩ መልካም ትውስታዎቼ መካከል በዋናነት የሚጠቀስ ነው።
በመሠረቱ እኛ ባደግንበት ዘመን ጎሳም ሆነ ሃይማኖት ተብሎ የሚፈጠር ልዩነት አልነበረም። የትኛውም በዓል ሲኖር በጋራ አንድ ላይ ሆነን ነው የምናከብረው። ደስታችንም ሆነ ኀዘናችን የጋራ ነው። እርግጥ ከአገር ከወጣን በኋላ በውጭ ያለው ድባብ እዚህ ካለው በጣም የተለየ ነው። በማኅበረሰብ ደረጃ በዓሉን ማክበር ካልተቻለ በስተቀር በአገሪቱ ላይ ኢትዮጵያ እንዳለው ዓይነት ድባብ አይኖርም። እዚህ ግን የነበረው የልጅነት ጊዜያችንን ስናስታውስ በጣም ደስ የሚሉ ነገሮች ነው ያሉት። ለዚያም ነው አሁን ልጆቻችንንም ጭምር ይዘን የመጣነው። ምክንያቱም ልጆቻችን እኛ ያደግንበትን ባህልና ሃይማኖታዊ ሥርዓቱን እንዲያዩና እንዲያውቁት እንፈልጋለን። እርግጥ ባህላቸውን እንዲያውቁ እያንዳንዱ ዳያስፖራ ለልጁ የሚያስተምረውና የሚነግረው ነገር ሊኖር ይችላል። ነገር ግን ከቃል በዘለለ መጥተው ያደግንበትን፤ የተማርንበትን፤ አኗኗራችንም ሁሉንም ነገር አይተው ወደ እነሱ ለማስተላለፍ ትልቅ ዕድል ይፈጥራል።
በአጠቃላይ በዓል ሲመጣ ሁልጊዜም ከጭንቅላቴ የማይጠፋው ሁላችንም ተሰብስበን የምናከብርበት ድባብ ነው – ትልቅ ትዝታዬ። በተለይ በዓሉ ምንም እንኳን ሃይማኖታዊ ቢሆንም ቅሉ ሙስሊም ከክርስቲያኑ ሳይለያይ በጋራ አድምቆ የሚያከብረው፤ ፍቅሩ፣ መከባበሩና መቻቻሉ ይበልጥ የሚታይበት ስለነበር የተለየና የሚናፍቅ ጊዜ ነው። በእርግጥ አሁንም ቢሆን ያ ባህል ሙሉ ለሙሉ አልተሸረሸረም።አብዛኛው ማኅበረሰብ አሁንም ልክ እንደጥንቱ በጋራ ተስማምቶና ተቻችሎ በደስታ እና በኀዘኑ ይደጋገፋል፤ ይረዳዳል።
በተለይ አዲስ አበባ ላይ በዓል ሲመጣ የመረዳዳቱና አብሮ የማክበሩ ባህል አለ። በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ የምናየውና የምንሰማቸው ነገሮች ይህንን ነባር እሴት የሚበርዙ ናቸው። የመቻቻል፤ አብሮ የመሥራትና የመኖር ባህላችንን የሚሸረሽር ችግር በየቀኑ እያጋጠመ ነው። በመሆኑም በአሁኑ ወቅት በተለይ ከሃይማኖት መሪዎች፤ ትላልቅ አባቶች ብዙ ነገር ነው የምንጠብቀው። በጎሳና በሃይማኖት ልዩነት ለመፍጠር የሚደረጉ አሉታዊ እንቅስቃሴዎች ሊቆሙ ይገባል የሚል እምነት አለኝ። እንደበድር ኢትዮጵያም አሁን ያለው ሁኔታ እጅግ የሚያሳስበው በመሆኑ ይህንን ለማስተካከል በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ላይ ሂደቱን ማገዝ እንደሚፈልግ በዚህ አጋጣሚ መግለፅ እወዳለሁ።
አዲስ ዘመን፡- እርስዎ ካደጉበት ማኅበረሰብ አኳያ የተለያዩ ሃይማኖት ተከታዮች መቻቻልና አብሮነት ለአገር የነበረው ፋይዳ ምንድን ነበር ይላሉ? አሁን ላይ የዚህ እሴት መሸርሸር በአገር ላይ ያመጣው ችግርስ እንዴት ይገልፁታል?
አቶ ቡርሃን፡- በነገራችን ላይ በዳያስፖራው ያለው የሃይማኖት ጉባኤ ውስጥ የሙስሊም ማኅበረሰቡን ወክለን እንሳተፋለን። ወደጥያቄሽ ስመጣ በሃይማኖት መቻቻል የመጀመሪያውና ትልቁ ነገር አስተምህሮቻችን ላይ ትንሽ ማየት የሚያስፈልጉን ነገሮች ያሉ ይመስለኛል። አንድ ወጥ የሆነ ነገር መታየት አለበት። ምንአልባት ነገሮች በተለይ ሙስሊሙ ኅብረተሰብ አካባቢ እንደመጅሊስ ተቋማዊ አሠራር ያለመኖሩ ትልቁ ችግራችን ነው ብለን እናምናለን። ተቋም ሲኖር የመቆጣጠሩ ነገር ይኖራል ብዬ አምናለሁ። ምክንያቱም በእምነት ተቋማት ወጥ የሆነ አሠራር ሊዘረጋ የሚቻለው ጠንካራ ተቋም ሲኖር ነው። በክርስትናውም አካባቢ እንደዚሁ አፈንግጠው የሚወጡ ነገሮች እንዳይኖሩ ተቋማት ጠንካራ ክትትል ማድረግ የሚኖርባቸው ይመስለኛል። እነዚህ ተቋሞች በጠንካራ መሠረት ላይ ከተቀመጡ፣ ራሳቸውን ችለው መሥራት ከቻሉ ቢያንስ የምንጠይቀው አካል ይኖራል። አሁን እኮ አንድ ነገር በሚፈጠርበት ጊዜ የሚጠየቅም አካል አለመኖሩ ነው የሚያሳዝነው። እንደእምነት ተቋምም ሆነ መንግሥት ተቋማት እንዲጠናከሩ መሥራት ያስፈልጋል።
በመሠረቱ የትኛውም ሃይማኖት በአስተምሮው ደግና መልካም ነገር ነው የሚያስተምረው ፤ የሚቀበሉት ሰዎች ግን ከሌላ ውጪያዊ ነገሮች ጋር ቀላቅለው ሲያስተምሩ የሚፈጠረው ነገር አሁን የምናየው ነው። ሕፃናትና እናቶች ያለጥፋታቸው እየደረሰባቸው ያለው ጥቃት፤ ሞትና መፈናቀል ስናየው በሌሎች አገራት እያየን ስናዝን የነበረው ዛሬ አገራችን ላይ መከሰቱ በጣም የሚያሳዝን ነው። ነገር ግን ጨርሰን ተስፋ የምንቆርጥበት አይደለም። የማይሻሻል ነገር የለም፤ ግን ሁሉም አካል ኃላፊነት ወስዶ መሥራት መቻል አለበት። የሃይማኖት ተቋማትም፤ መንግሥትም ሆነ ሕዝቡ ኃላፊነት መውሰድ መቻል አለበት። በተለይ መንግሥት ጠንካራና ቆራጥ የሆነ አቋም ወስዶ ሚናውን መወጣት አለበት። ይህንን ሊያደርግ እንደሚችልም እምነቱ ስላለን ነው ከተለያዩ አቅጣጫዎች አሉታዊ ድምፆችን እየሰማን አገራችን ላይ ይህንን ኮንቬንሽን እናዘጋጃለን ብለን ቆርጠን የመጣነው።
ከዚህ በዓል ጋር በተገናኘ ወደዚህ ስንመጣ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ችግር እንደሚፈታ ሙሉ እምነት ተስፋ ይዘን ነው። ከተሠራ ሁሉም ነገር መቀየር ይችላል፤ ለዚህ ደግሞ እኛ ራሳችንን የመፍትሔ አካል በመሆን ልንደግፍ ይገባል የሚል እምነት ነው ያለን። እንዳልኩሽ ግን ስንመጣ ብዙ ጫጫታ ነበር፤ የእኛ ወደዚህ መምጣት በንፁሃን ላይ የሚደረገውን ጭፍጨፋ ማበረታታት እንደሆነ የተናገሩን ሰዎች አሉ፤ እኛ ግን ያንን ሁሉ አልፈንና ተሻግረን፤ ተስፋ ሰንቀን፤ ከሚቀይሩት ጋር አብረን እንቀይራለን የሚል እምነት ይዘን ነው የመጣነው። በአጠቃላይ ያለው ነገር ከባድና አሳዛኝ ቢሆንም ሊቀየር የሚችል ነው የሚል እምነት ነው ያለን።
አዲስ ዘመን፡- ከተቋማቱ ባሻገር በምዕመናኑ
ተቀባይነት ያላቸው የእምነት አባቶች ትውልዱን በማነፅ ረገድ ሚናቸውን ተወጥተዋል ብለው ያምናሉ?
አቶ ቡርሃን፡- ሃይማኖታዊ አስተምህሮች የምንከተለው በዚህ ምድር ብቻ ሳይሆን ከሞት በኋላ ከፈጣሪያችን ጋር ስንገናኝ እሱ የሚሻውን ሠርተን ለማለፍ ነው። ካለፍን በኋላም ጀነት ወይም ገነት መግባት የምንችለው መልካም ሥራ ሠርተን ስናልፍ ነው። የሃይማኖት አባቶችም ያስተምራሉ ተብሎ የሚጠበቀው ይህንኑ ነው። ነገር ግን በተግባር የምናየው ያንን የሚያመጣ ዓይነት አይደለም። እዚህ ምድራዊ ሕይወትን ችላ ብለን ሰማያዊውን እየናፈቅንና እያሰብን እየኖርን አይደለም፤ ከዚያ ይልቅም ምድራዊው ላይ አተኩረን ነው እየኖርን ያለነው። በተለይ የሃይማኖት መሪዎቻችን በዚህ በኩል ጥሩ አርዓያ መሆን ሲገባቸው እዚህ ምድራዊ ነገር ላይ አተኩረዋል። አብዛኞቹ የሃይማኖት መሪዎቻችን የገንዘብም ሆነ የተለያዩ ጥቅማጥቆሞች ላይ እንጂ ትኩረት የሚሰጡት ሃይማኖታዊው የፈጣሪን ተልዕኮ ማስፈጸም ላይ አይደለም ። ‹‹ከልብ የወጣ ነገር ወደ ልብ ይገባል›› እንደሚባለው ከልባቸው ስለማይሠሩ ወደ እኛ ሊደርስ አልቻለም።
ስለሆነም የሃይማኖት አባቶቹ በመጀመሪያ ደረጃ የተቀመጡበትን ቦታ ዋነኛ ተልዕኮ ከፈጣሪ የተሰጠ መሆኑን ቢያውቁት ጥሩ ነው። ባህላችንን በደንብ ማወቅ ያስፈልጋል። የሞራል ልዕልናም ሊኖረን ይገባል። ምክንያቱም ሰውን ሰው የሚያደርገው ይህ በመሆኑ ነው። ከነብያችን መሃመድ ጀምሮ በሰብሃዎቹ ሁሉንም ነገር ሕይወታቸውን ጊዜያቸውንም ሆነ ገንዘባቸውን ለሃይማኖቱ ሰጥተው ነው ያለፉት። አሁን ግን በሃይማኖቱ የመጠቀም ነገር ነው የምናየው። እንዲህ ዓይነት ሁኔታዎች መቀየር አለባቸው፤ አስተማሪዎቻችን የአመለካከት ለውጥ ማምጣት አለባቸው። ሙሉ ለሙሉ ከምድራዊ አስተሳሰብ ወጥተው ሰማያዊውን ከፈጣሪ የተሰጣቸው ተልዕኮ መፈፀም ነው የሚጠበቅባቸው። አስተምህሮው ብቻ ሳይሆን ሰዎቹ ራሳቸው መቀየር ይገባቸዋል። ከልባቸው ካስተማሩ ሕዝባችን የማይቀየርበት ምክንያት የለም። አሁንም ሕዝባችን ጥሩ አስተማሪና መሪ ካገኘ ይቀራል ብዬ ነው የማስበው።
አዲስ ዘመን፡- መንግሥት በሰሜን ኢትዮጵያ ከሁለት ዓመት በላይ የዘለቀው ጦርነት ቆሞ ሕዝቡ ወደ ተረጋጋ ሕይወቱ እንዲመለስ ያደረገው ጥረት በሕወሓት አሻፈረኝ ባይነት ሳይሳካ ቀርቷል። ለመሆኑ በሕወሓት እምቢተኝነት በሕዝቡ ላይ እየደረሰ ያለውን ጉዳት እንዴት ይገልፁታል? ምንስ ሊሠራ ይገባል ይላሉ?
አቶ ቡርሃን፡- እንግዲህ ሠላም ለአንድ አገር የጀርባ አጥንት መሆኑ አያጠያይቅም። እኛ የምንኖርባት አሜሪካ ሠላም ስላላቸው ሁሉ ነገር አላቸው። ምክንያቱም የሁሉ ነገር መሠረቱ ሠላም በመሆኑ ነው። ሠላም ከሌለ አገር አይደለም ትዳርም አይዘልቅም። ሠላም የሚመጣው ግን በአንድ አካል ፍላጎት ብቻ አይደለም። ሁሉም ለሠላም በጋራ መነሳት፤ በጋራ አስቦ መዘጋጀት ሲችል ነው። አሁንም የምናየው በተለይ ባለፉት አራት ዓመታት ከሕወሓት ጋር እየተደረገ ያለው ጦርነት አገሪቱንም ሆነ ሕዝቡን በከፍተኛ ሁኔታ ጎድቷል። ሠላም ከሌለ እናስተዳድረዋለን ብለን የምናስበውን ሕዝብ ራሱ ሊኖር አይችልም። ሠላም ሲኖር ብቻ ነው የምናስተዳድረው ሰው የምናገኘው።
በአሁኑ ሰዓት የትግራይ ሕዝብ በምን ዓይነት ሁኔታ ላይ ይኖራል ብዬ ለማሰብ ራሱ ይከብደኛል። እንኳን ጦርነት መሃል ያለ ሕዝብ ይቅርና በከተማ ውስጥ ሁሉ ነገር ተመቻችቶለት የሚኖር ሰው ራሱ በምንዓይነት የኑሮ ትግል ውስጥ እየኖረ እንደሆነ አያጠያይቅም። እዚያ ያለው ሁኔታ ምንአልባት ከአዕምሮ በላይ ሊሆን ይችላል። እናም ያንን ክልል የሚመሩ ሰዎች ቆም ብለው ቢያስቡት ይሄ ሕዝብ ለምንድን ነው ይሄ ሁሉ ዕዳ ሊሸከም የቻለው ምን ስላጠፋ ነው? ለሕዝብ ሲባል ምንም ነገር ቢሆን ሊተዉ ይገባል። የቱንም ያህል መስዋዕትነት ከፍለው ሕዝቡን ሊታደጉ ይገባል። መንግሥታችንም ለዚያ ሕዝብ ሲባል የተወሰኑ ነገሮችን ከግምት ውስጥ አስገብቶ ቢተወው መልካም ነው። ለመነጋገር ዕድሉን አሁንም መክፈት አለበት። እርግጥ ነው ሕወሓት ጋር ተያይዞ ያለው ችግር ሁሉም ጋር ያለ ቁስል ነው፤ እናውቀዋለን። አንድ ዓመት በጦርነት ውስጥ መኖር ምንአልባም 10 እና 20 ዓመታት ወደኋላ እንድንመለስ ሊያደርገን ይችላል።
የትግራይ ሕዝብ ደግሞ መልካምና አገሩን የሚወድ ሕዝብ ነው። መሪዎቻቸው ልቦና ገዝተው ተረጋግተው ቢያዩት፤ መልሰው መላልሰው ቢፈትሹት፤ ማድረግ የሚገባቸውን ቢያደርጉ፣ ለመፍትሄ የሚሆኑ ሃሳቦችን ቢያመነጩ የተሻለ ነው። በዚህ በኩል የሚመራው አካልም ያንን ታሳቢ በማድረግ ነገሮችን በማቀራረብና ሁኔታዎችን በማየት ችግሮችን ለመፍታት ቢሞክር መልካም ነው። ምክንያቱም በጦርነት ምንም ዓይነት ችግር አይፈታም፤ ሊፈታም አይችልም። እኔም መልዕክት ማስተላለፍ የምፈልገው በተለይ ትግራይን የሚመሩት ሰዎች ቆም ብለው እንዲያስቡ ነው። የሕወሓት ሰዎች የትግራይ ሕዝብን ከኢትዮጵያ ሕዝብ መለየት እንደማይችሉ ተገንዝበው ለሠላም ደጅ መጥናት አለባቸው። ቀድሞ በነበሩ መንግሥታት ብዙ ጦርነቶች ተካሂደው ሕዝቡ ግን አሁንም ድረስ አብሮ ነው ያለው፤ ወደፊትም በጋራ የሚኖር ነው የሚሆነው። ስለዚህ ይህንን ተረድተው ከአፍራሽ ተግባራቸው ሊቆጠቡ ይገባል የሚል አቋም ነው ያለኝ። በዚህ በኩል መንግሥት ለሠላም አንቺ እንዳልሽው ብዙ ጥረት አድርጓል፤ እያደረገም ነው የሚገኘው። ግን ውጤት እንዲመጣ የበለጠ ሊተጋ ይገባል። አለበለዚያ የምንመራውን ሕዝብ አናገኘውም። በዚህ ሁኔታ ከቀጠልን አሁን ካለው በላይ ችግር ውስጥ እንገባለን ብዬ እሰጋለሁ።
አዲስ ዘመን፡- በሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎችም በአሸባሪ ቡድኖች ንፁሃን ላይ የሚደረገው ጭፍጨፋ በምን መልኩ ሊቆም ይገባል ብለው ያምናሉ?
አቶ ቡርሃን፡- በእኔ እምነት ቀደም ብዬ ላነሳሁት ትልቅ ችግር መፍትሄ መስጠት ከቻልን ትናንሾቹ ችግሮች በራሳቸው የሚደርቁ ይመስለኛል። የሚከፈለው መስዋዕትነት ተከፍሎ ያንን ችግር በሠላም መፍታት ከተቻለ እዚህ ያለውም ችግር እልባት ያገኛል። ጦርነትና ግጭት ለማንም የሚበጅ አይደለም። በተለይ በአሁኑ ወቅት ሕዝቡ ዳቦ ማግኘት ባልቻለበት ጊዜ ለጥይት የምናወጣው አብት ሊኖረን አይገባም። ስለዚህ ዋናውን የሕወሓትን ችግር ከፈታን በኋላ ትንንሾቹ እንደሚከስሙ ሙሉ እምነት አለኝ። በዚያ ላይ ዓለምአቀፍ ተፅዕኖ አለ፤ ከግድቡ ጋር ተያይዞ ከግብፅና ከሱዳን ጋር ችግር አለ፤ ከዚያ አልፎ በየቦታው የሚነሱት ግጭቶችና የንፁሃን ጭፍጨፋ አገሪቱን ወደ ከፍተኛ የህልውና ስጋት ውስጥ ነው የሚከቷት።
ከሠላም ማስከበር ሥራው ጎን ለጎን ተቋማትን ማጠናከር ያስፈልጋል። ለምሳሌ የፍትህ ተቋማት ላይ የተጀመሩት የሪፎርም ሥራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል። አሸባሪዎች የሚያዘወትሩባቸው አካባቢዎች ያሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች ራሳቸውን የሚጠብቁበት ሁኔታ ቢመቻች ጥሩ ነው። ምክንያቱም እነዚህ ሰዎች ያልታጠቀ ኅብረተሰብ ላይ ነው ጥቃት እያደረሱ ያሉት። ንፁሃን ላይ ጥቃት እየፈፀሙ ያሉ አካላት ሕዝብን በመጨፍጨፍ በእርግጠኝነት የፖለቲካ ትርፍ እናገኛለን ብለው የሚያስቡ አይመስለኝም። በዚህ አካሄድ ወደሚፈልጉት ስልጣን ሊደርሱም አይችሉም። ለዘላለም በሽፍታነት ለመቀጠል ካልፈለጉ በስተቀር የቋመጧትን ስልጣን ሊያገኙ አይችሉም። ስለዚህ እነዚህን ለመከላከል ደግሞ በመንግሥት ተቋማት ብቻ የማይሆን በመሆኑ ማኅበረሰቡን ማደራጀትና በሚሊሻ መልኩ አጠናክሮ ራሳቸውን እንዲከላከሉ መንገዶች ቢመቻቹ ጥሩ ነው ብዬ አስባለሁ። ራሳቸውን የሚጠብቁበትን መንገድ የበለጠ ማመቻቸቱ ጥሩ ነው። የፀጥታ ኃይሎች በየገጠሩና ጥሻው የሚፈፀመውን የሽፍትነት ተግባር መከላከል አይችሉም።
አዲስ ዘመን፡- ህዳሴ ግድብን ግንባታን ከመደግፍ ጀምሮ በውጭ ኃይሎች እየተደረገ ያለውን ጫና በመከላከል ረገድ በዳያስፖራው በኩል ምን እየተሠራ ነው?
አቶ ቡርሃን፡- አስቀድሜ እንደገለፅኩልሽ በድር ኢትዮጵያ በገንዘብ ደረጃ የተለያዩ ድጋፎችን ሲያደርግ ቆይቷል። ከዚህ ባሻገር ግን ለተለያዩ አረብና ሙስሊም አገራት በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ የጠራ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ሲሠራ ቆይቷል። በዋናነትም እውነታውንና የኢትዮጵያን አቋም የሚያሳይ ጥናት አሜሪካ ለሚገኙ የአረብና ሙስሊም አገራት ኤምባሲዎች እንዲደርሳቸው አድርጓል። ገንዘብ በማሰባሰቡ ሂደትም ቀጣይነት ያለው ሥራ እየሠራ ነው የሚገኘው።
ሦስተኛው ዙር ሙሌት በሐምሌ ወር የሚካሄድ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ እየተደረገ ያለው በርካታ የውጭ ተፅዕኖዎች አሉ። እነዚህን ተፅዕኖዎችን ለመቋቋም እኛም በርካታ ሥራዎችን እንሠራለን። በአሁኑ ወቅት የቀድሞ የውሃ ሚኒስትር ዶክተር ስለሺ በቀለ የአሜሪካ አምባሳደር ሆነው ስለተመደቡ ከእሳቸው ጋር በቅርበት የምንሠራ ነው የሚሆነው። እየተጋገዝን ዓለምአቀፉን ጫና ለመቋቋም የሚያስችሉ ቀጣይ ሥራዎች ይኖሩናል።
ከዚያ ጋር ተያይዞ ሱዳን ትንኮሳ እያደረገች እንደሆነ ይታወቃል፤ ይህ ብቻ ሳይሆን ከሁሉም አቅጣጫ እኛ ላይ ተፅዕኖ ለመፍጠር ጥረት እየተደረገ ነው ያለው። በመሠረቱ ሱዳን የዚህ ግድብ ዋነኛ ተጠቃሚ ትሆናለች ተብሎ ነበር የሚገመተው ነገር ግን የሌሎችን የቤት ሥራ ወስዳ እየሠራች ነው ያለው። አገር ውስጥ ካለው ችግር ጋር ተደማምሮ በከፍተኛ ሁኔታ ኢትዮጵያ ላይ ጫና እያሳረፈ ነው። ቢሆንም ግን ቀደም ሲል እንደተባለው አንድ ከሆንና ከተጋገዝን ተቋቁመን ሦስተኛውን ሙሌት እንደምናከናውንም ሆነ የግድባችንን መጨረሻ እንደምናይ አልጠራጠርም። እንደጀመርነው እንጨርሰዋለን!።
አዲስ ዘመን፡- በመጨረሻ በዓሉን አስመልክቶ ለመላው ሙስሊም ማኅበረሰብ የሚያስተላልፉት መልዕክት ካለ ዕድሉን ልስጥዎት?
አቶ ቡርሃን፡- ዛሬ በዓል እንደመሆኑ ለመላው ሙስሊም ማኅበረሰብ እንኳን ለኢድ- አልአደሃ በዓል አደረሳችሁ ማለት እፈልጋለሁ። መጪው ጊዜ የተሻለ እንዲሆን መልካም ምኞቴን መግለፅ እወዳለሁ። አሁን በአገራችን ያለው ሁኔታ አልፎ በጥሩ ፤ ደስ በሚልና ባልተጨናነቀ ድባብ ተገናኝተን እናከብራለን ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ በአንባቢዎቼና በዝግጅት ክፍሉ ሥም ከልብ አመሰግናለሁ።
አቶ ቡርሃን፡- እኔም ዕድሉን ስለሰጣችሁኝ አመሰግናለሁ።
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ሐምሌ 2 ቀን 2014 ዓ.ም