የህይወት ውበት ትዝታና ተስፋ ናቸው። ነፍስ በትዝታና በተስፋ መርፌ የተሰፋች ይመስለኛል። ደግሞም ተሰፍታለች፣ ከጠዋት እስከ ማታ የማረምመው አርምሞ የነፍስ ባለቀለም እንጉርጉሮ ከመሆን ሌላ ምን ሊሆን ይችላል? ህይወት ከፊት ትዝታ ከኋላ ተስፋ ባይኖራት ምን እንደምትመስል ሳስብ የሌለ እጨነቃለሁ።
መኝታ ክፍሌ ውስጥ ነኝ..አልጋዬ መከዳ ላይ ቁጭ ብዬ አስባለሁ። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ካጠናቀኩ አስራ አምስት ዓመታት ተቆጠሩ..እንደ እስቅያስ በልጅነት እድሜዬ ላይ አስራ አምስት ዓመታትን ጨመርኩ። በትዝታ የተሰፉ አስራ አምስት የናፍቆት ዓመታት እንደ ጅረት በላዬ ላይ ፈሰሱ። ሰው የዘመን ወንዝ ነው..ነፍስ የጊዜ ውቅያኖስ ናት። በላዬ ላይ የተጫነውን የትዝታ ቀንበር አዝዬ አስራ አምስት ዓመታትን ወደ ኋላዬ አረምማለሁ። የህይወቴ ደማቋ ፊደል መባ ጋ እስክደርስ ድረስ የትዝታ ተጓዥ ነኝ። ነፍሴ ላይ ነግሳ አበሳዬን እስክታስረሳኝ ድረስ እዛና እዚህ እዳክራለሁ። ነፍስ አውቄ ጉርምስና በተሰማኝ ሰሞን የተነካካሁት ከመባ ጋር ነው። መባ ከልጅነት ወደ ጉርምስና በተሸጋገርኩ ማግስት የተዋወኳት ልጅ ናት። ልጅነቴን ሳስብ፣ ጉርምስናዬን ሳስታውስ ቀድማ አእምሮዬ ውስጥ የምትፈጠረው መባ ናት። ዛሬ ላይ ያን ስሜት ማንም አልሰጠኝም። ባሳለፍኳቸው አስራ አምስት ዓመታት ውስጥ ከተለያዩ ቆንጆና ዘመነኛ ሴቶች ጋር ወዳጅነትን ፈጥሬያለሁ እንደ መባ ነፍሴን በደስታ ያቃተተኝ ሴት ግን የለም።
ፍቅር ድሮና ዘንድሮ ሰማይና ምድር ነው። ፍቅር የልብ ሰማይ ነው..ፍቅር የነፍስ ምድር ነው። አምላክ ዙፋኑን የዘረጋው በፍቅር ሰማይ ላይ ነው። በእውነት ምድር ላይ ነው። ያ የፍቅር ሰማይ፣ ያ የእውነት ምድር ልብ ነው። ፍቅር የነፍስ ምድር ነው። በልብ ሰማይ ላይ ከዋክብቶች ደምቀው የሚያበሩት በህይወት ጠዋት ላይ ነው። በህይወት ከሰዐት ላይ ቆሜ ዛሬም ድረስ የማዜመው የማለዳ ዜማዬን ነው። መባ ያለችበትን ያ የጠዋት ድርሳኔን። ትዝ ይለኛል..አስረኛ ክፍል ነበርኩ ለአዲስ ዓመት የተገዛልኝን አዲስ ስኒከር ጫማ ተጫምቼ ወደ ክፍል እገባለሁ። ጫማው ከተገዛልኝ ከጳጉሜ ሶስት ከሩፋኤል ቀን ጀምሮ አይኖቼ ከዛ ነጭ ጫማ ላይ ተነቅለው አያውቁም ነበር። መሬት መሬት እያየሁ ነበር የምሄደው። ከመባ ጋርም የተዋወቅነው በዛ ስኒከር ጫማ ሰበብ ነበር። ያን ቀን ብርቅ የሆነብኝን ጫማዬን እያየሁ ወደ ክፍል ስገባ ከአንዲት ሴት ጋር ተጋጨሁ። ግጭታችን ሀይለኛ ስለነበር ሁለታችንም መሬት ላይ ወደቅን..አወዳደቃችንን ዛሬ ላይ ሳስበው የፍቅር አምላክ እጅ ያለበት ይመስለኛል። ከዛ በኋላም ሆነ ከዛ በፊት ምድር ላይ እንደዛ ተቃቅፈው የሚወድቁ ወንድና ሴት ስለመኖራቸው እጠራጠራለሁ። ብቅ ብቅ ያሉ ጡቶቿን ተንተርሼ ደረቷ ላይ..ራሴን አገኘሁት። አፌ አፏ ላይ እንደተደፋ ያወኩት ዘግይቼ ነበር። ባጋጣሚ ቢሆንም ለመጀመሪያ ጊዜ ከንፈሬ ከሴት ከንፈር ጋር የተሳሳመው በዛ ጫማ ጦስ ነው። እንደምንም ራሴን ከደረትና ከጡቷ ላይ አንስቼ ወደ ክፍል ተንደረደርኩ። ለካ የክፍላችን ተማሪ ነበረች..። እኔም እሷም ዓመቱን ሙሉ በሀፍረት አሳለፍን። ምንም ሳንባባል ዓመቱ አለቀ። ወንድነቴ በመባ ከንፈር ተሟሸ። ከንፈር ምን ምን እንደሚል ለመጀመሪያ ጊዜ ያጣጣምኩት ያኔ ነው እላለሁ። ያ ጫማ..ያ አጋጣሚ..ያ አዲስ ዓመት ሁሌም ይናፍቁኛል። በህይወቴ እንደዛ አይነት አዲስ ዓመት አሳልፌ አላውቅም። ያ አዲስ ዓመት ዛሬም ከነሙሉ ግርማ ሞገሱ ይታወሰኛል።
አስራ አንደኛ ክፍል አብረን ተመደብን፣ በጣም የሚገርመው ደግሞ አስራ ሁለተኛ ክፍልም አንድ ላይ መሆናችን ነው። በዛች የተረገመች አጋጣሚ አፍራ ይሁን እንጃ ሶስት ዓመት አላወራንም። ክፍል ውስጥ ከሁሉም ወንዶች ጋር ስታወራ ከኔ ጋር ብቻ አታወራም። ልቤ የመጀመሪያህ እያለ ያወራኛል። ነፍሴ ሳቋን ትናፍቃለች..ግን ትሸሸኛለች። ዳግም የማንገናኝበት ጊዜ ከፊታችን መጣ። አንድ ማለዳ ልቤ የሆነ ነገር አለኝ..ልቤን አደመጥኩት። ልብ የእውነት ስፍራ እንደሆነ ያን ቀን ነው የተረዳሁት። የልቤን እውነት ይዘው እግሮቼ ወደ አንድ ቦታ መሩኝ..ከዛ በፊት ወደዛ ቦታ ሄጄ አላውቅም ነበር..ዛሬ ለምን እንደሄድኩ የገባኝ መናን በዛ ሰዋራ ስፍራ ብቻዋን ተቀምጣ ሳያት ነበር። ፊት ለፊት ተፋጠጥን..ምን ማለት እንዳለብኝ ግራ ገባኝ። በአእምሮዬ ውስጥ ሁለት ሀሳቦች ተጸነሱ። አንደኛው..ይሄ መባን በተመለከተ በህይወትህ ዳግመኛ የማታገኘው አጋጣሚ ነው አውራት ይለኛል..ሌላኛው ደግሞ ሌላ ይለኛል። ዛሬ ላይ በማላስታውሰው ውስጣዊ ሀይል ተጠጋኋት..እጄ ላይ ደብተር ይዤ ነበር..ዛሬ ክላስ አልገባም ጻፊልኝ ብዬ ደብተሬን ወርውሬላት መልስ እንኳን ሳልጠብቅ ከፊቷ ተሰወርኩ። እንደዛ ቀን ጠዋት ነቅቼ አላውቅም..ነግቶ ደብተሮቼን ለማየት የቸኮልኩትን አቸኳኮል ለምንም ቸኩዬ አላውቅም። ጠዋት ክፍል ስገባ ሳልጠይቃት ደብተሬን አምጥታ ሰጠችኝ..ጽፋልኝ ነበር። አመሰግናለው ሳልላት የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ፈተና ደርሶ ተለያየን።
ከአልጋዬ መከዳ ላይ ሆኜ መባ የጻፈችልኝን እያየሁ ብዙ ቆየሁ። ከደብተሬ ገጽ ላይ ከጽሁፎቿ መሀል አገኛት ይመስል ፈለኳት። ጽሁፏ ያስቃል…መባ ጽሁፍ አትችልም። ከዛ ውበት፣ ከነዛ ጣቶች መሀል እንዲህ አይነት አስጠሊታ ጽሁፍ መውጣቱ ሁሌም ያስደንቀኛል። መባን እያሰብኩ እጄ የገባውን አንዱን ገፅ ሳገላብጥ ሊደበዝዝ ያለ አንድ ስልክ ቁጥር ደብተሬ ገጽ ላይ ተጽፎ አየሁ። ቁጥሩን በደንብ አየሁት አላውቀውም። ላስታውሰው ብዙ ሞከርኩ ግን አልመጣልኝም። ግን አላረፍኩም..ሳላስበው አስባለሁ። ወደ ኋላ አስራ አምስት ዓመት ተራምጄ የክፍል ጓደኞቼን አስሳለሁ። አንዳንዶቹ ታወሱኝ አንዳንዶቹ ግን ጠፉብኝ። መባ ግን ያው እንደ ድሮዋ ዛሬም በነፍሴ ቦታ ላይ አለች። የሆነ ጥርጣሬ አእምሮዬ ውስጥ ሰተት አለ። ስልኩ የመባ መሰለኝ..ደብተሬን ለመጨረሻ ጊዜ ለሰው የሰጠሁት ለእሷ ነበር። ከዛ በኋላ መልቀቂያ ፈተና ስለወሰድን ብዙ አልቆየንም። ስልኩ የመባ ከመሆን ውጪ የማንም እንደማይሆን አእምሮዬ ለመቶኛ ጊዜ ነገረኝ። ግን አእምሮዬን አላመንኩትም..የእሷ ከሆነ በደስታ አብዳለሁ..አለም ይጠበኛል። የእሷ በሆነ ስል ተመኘሁ። ትዝታዬን ተከትሎ ነፍሴ በደስታ ከልቤ ውስጥ ልትወጣ ምንም አልቀራትም ነበር። ስልኩ የመባ ስለመሆኑ እርግጠኛ ሆንኩ። ከአስራ አምስት ዓመት በኋላ የመባን ድምጽ ልሰማው እንደሆነ ሳስብ የተደሰትኩትን መደሰት አትጠይቁኝ።
ከአስራ አምስት ዓመት በኋላ እየተደነኩና እየተገረምኩ ወደ ማላውቀው ስልክ ቁጥር ላይ ደወልኩ። ከነፍሴ ወደ ፊቴ የሚፈስ የሳቅ ጎርፍ ይታየኛል። ምን ማለት እንዳለብኝ እያሰብኩና ከንፈሬን በምላሴ እየላስኩ ጠበኩ..
ልቤ ይደልቃል..
ቀጭን ሞልቃቃ ድምጽ በአይኔ ላይ ያንዣብባል..
ብዙ አልቆየሁም..ጆሮዬ አንድ መርዶ አደመጠ ‹ይህ ቁጥር አይታወቅም፣ እባኮ የጥሪ ማዕከሉን ያናግሩ› የሚል። ቴሌ ቅስሜን ሰበረው..
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ሐምሌ 1/2014