ሰሞኑን በየመንገዱ ዳርቻ የእግረኞችና የመኪኖች ሰልፍ በርክቷል። በተለይ ደግሞ መኪኖቹ በሰልፍ ውለው በማደር ቀናትን እያስቆጠሩ ነው። ተሽከርካሪዎቹ ባልተለመደ ሁኔታ መንገዱን ማጨናነቃቸው ያለምክንያት አልሆነም። እረፍት አልባው የነዳጅ ወረፋ በሰውሰራሽ ችግር ተተብትቦ ጊዜን በመቁጠሩ እንጂ።
ዛሬም ግን የራስ ወዳዶቹ እጆች አልተሰበሰቡም። አሁንም በየጥጋጥጉ፣ በየጥሻው ነዳጅን ያህል ጉዳይ በችርቻሮ በመሸቀጥ ራስን ከማክበር ማማ ለማድረሰ በጥድፊያ ላይ ናቸው። የሀምሌ ወር መግባትን ተከትሎ ይጨምራል የተባለው የነዳጅ ዋጋ ስጋት የሆነባቸው አንዳንዶች ዕንቅልፍ ካጡ ሰንብተዋል። ብዙሀን በማንኪያ ይቀምሱት በቸገራቸው አጋጣሚ እነሱ በአካፋ ዝቀነው እንሙት ማለታቸው እያስገረመን ነው።
በዓለማችን በየዕለቱ የምንሰማቸው ኢኮኖሚያዊ ጫናዎች የእኛን መሰል አገራት አቅም መፈታተናቸው አይቀሬ ሆኗል። ሁሌም እንደሚስተዋለው በልጽገናል የሚሉት አገራት ለሚገጥማቸው ወቅታዊ የዋጋ ግሽበት እምብዛም ሲንገዳገዱ አይስተዋልም። አስቀድመው ራሳቸውን በኢኮኖሚው አሳድገዋልና መላና መፍትሄው በእጃቸው ነው።
ይህ አይነቱ የኢኮኖሚ ተጽዕኖ በተለይ ወደ አፍሪካውያን ባነጣጠረ ጊዜ ጫናውን ከበድ ያደርገዋል። በተለይ የሰማይ ደመናን ተስፋ አድርጎ ለሚያድርና ያደጉ አገራትን ምንዳ ለሚናፍቅ ህዝብ ደግሞ አጋጣሚው በርካታ ችግሮችን ይመዛል። ኢኮኖሚው በድንገት ሸብረክ ባለ ጊዜ ህይወት ትርጉም ታጣለች። ችግር ፣ርሀብ ስደትና መፈናቀል ይበዛል። እንዲህ መሆኑም ችግሩን በተናጠል ብቻ አይወስነውም። በሀገርና ህዝብ ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ የከፋ ያደርገዋል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚከሰተው ኢኮኖሚያዊ ጫና ሁሌም ህይወቱን ከእጅ ወደአፍ ላደረገው ለፍቶ አዳሪ ፈተና እንደሆነ ነው። ይህ ብቻ አይደለም። አጋጣሚውን ተከትሎ በሚኖረው ሰውሰራሽና የኢኮኖሚ አሻጥር የመጀመሪያው ተጠቂ ሰፊው የህብረተሰብ ክፍል ይሆናል።
ሁሌም የዋጋ ጭማሪ ወሬ ሽው ባለ ቁጥር ለትርፍ ብቻ የሚቆሙ ስግብግቦች የመጋዘኖቻቸውን ሆድ ባሻቸው ሞልተው ‹‹ጆሮ ዳባ ልበስ›› ማለታቸው ተለምዷል። እነዚህ ራስ ወዳዶች ገንዘብ ይሉትን ጥቅም አስካዩ ድረስ የሌላው መቆምና መውደቅ ችግራቸው ሆኖ አያውቅም። ባላቸው ላይ እየከዘኑ፣በደበቁት ቁልል እየጨመሩ በር ዘግተው ይስቃሉ።
ሁሌም ገበያውን በትርፍ ለመቆጣጠር የሚተጉ ወቅታዊ ስግብግቦች ቀን ጠብቀው የደበቁትን ይመዛሉ። እነሱ በወሰኑት ዋጋ ገበያውን ተቆጣጠርውም ተፈላጊነታቸውን ያበዛሉ። ይህ አይነቱ እውነት የከፋ በትሩን የሚያሳርፈው አሁንም ኑሮውን ሊሞላ በሚሮጠው ህብረተሰብ ትከሻ ላይ ይሆናል።
አብዛኛው ተጠቃሚ የሚፈልገውን ጠይቆ ‹‹የለም›› በተባለ ቁጥር የእጁን አራግፎ ከአትራፊዎች መደርደሪያ መቃረሙ የተለመደ ነው። እነሱ በየአጋጣሚው አንዳሻቸው የሚያዙበትን ሸማች ጊዜና ወቅት እየጠበቁ ሲበዘብዙት ኖረዋል። ፡ድርጊታቸውን ተከትሎ የሚወሰደው እርምጃ ጠንካራና አስተማሪ ያለመሆኑም ችግሩ ስር እንዲሰድና እንዲስፋፋ ሲያመቻች ቆይቷል።
ወደቀደመው ጉዳዬ ልመለስ፡፤ወደሰሞኑ የነዳጅ ገበያ ሁኔታ። የዘንድሮ የሀምሌ ወር አመጣጥ ያላማራቸው አንዳንድ ህገወጦች ወሩን በክረምትነቱ ብቻ የተቀበሉት አይመስልም። በዚህ ወር መግቢያ ላይ ይተገበራል የተባለውን የነዳጅ ዋጋ ማስተካከያና ድጎማ ተከትሎ ገበያውን ለመቆጣጠር ዓይን ያወጣ ድርጊት መ ፈጸም ጀምረዋል።
ያለአግባብ የሚገኝ ትርፍን ለማግበስበስ ያሰቡ አንዳድ ህገወጦች በአደራ የተቀበሉትን የነዳጅ ሀብት በየጫካው ደብቀው ለሽያጭ ጭምር እያዋሉት መሆኑ ተደርሶባቸዋል። መንግስት እስከዛሬ ከነበረው ያነሰ የነዳጅ አቅርቦት አለመኖሩን ቢያረጋግጥም ድርጊቱ ግን ቀደም ሲል ይገባ የነበረው ምርት እንዲቀንስና ከፍተኛ የነዳጅ እጥረት እንዲከሰት ምክንያት ሆኗል፤
ከሰሞኑ የነዳጅና ኢነርጂ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው መነሻቸውን ከጂቡቲ ያደረጉና አዲስ አበባ መድረስ የነበረባቸው 200 ነዳጅ ጫኝ ቦቴዎች በተለያዩ ጫካና መንደሮች ተደብቀው ተገኝተዋል። ይህን አግባብ ያልሆነ ድርጊት ሲፈጽሙ ከተገኙት መሀልም እስካሁን ስምንት የነዳጅ የጫኑ ቦቴዎች ለመንግስት ገቢ እንዲሆኑ ተደርጓል።
ከአዋሽ እስከሞጆ ባሉ መስመሮች በየጥሻው ተደብቀው የሚገኙትን የነዳጅ ቦቴዎች ለመቆጣጠርም አሳሽ ግብረሀይል ተደራጅቷል። ነዳጅ ማራገፊያ ቀናቸውን የተላለፉትን በመለየትም እርምጃ የመውሰዱ ሂደት ተጠናክሯል። ችግሩ ግን በዚህ ብቻ የሚቆም አይመስልም። በአሁኑ ጊዜ ወደሰሜን ኢትዮጵያ በተለይም ወደ ወልዲያና ቆቦ አካባቢዎች በህገወጥ መልኩ ነዳጅ እየተዘዋወረ ይገኛል።
ህገወጥ ድርጊቱን ተከትሎ ወልዲያ ከተማ ላይ ነዳጁን የሚያጓጉዙ ግለሰቦች ተይዘዋል። በአፋር ክልል በኩልም ወደትግራይ ሊገባ የነበረ ከአምስትሺህ ሊትር በላይ ነዳጅ በቁጥጥር ስር ውሏል። በዚህ ብቻ ያልተቋጨው ህገወጥነት ግን በዋግህምራና ሰሜን ጎንደር አካባቢዎች ተዛምቶ ቆይቷል ።
ነዳጁ ለሽያጭ የሚውለው በበርሜሎች እየተቀዳና እየታሸገ ሲሆን የንግድ ሂደቱም በከፍተኛ ደረጃ እንደሚከናወን ታውቋል። አሁን የትራንስፖርትና ሎጅስቲክ ሚኒስቴር በነዳጅ አመላላሽ ተሸከርካሪዎች ላይ የእንቅስቃሴ መቆጠጠሪያ /ጂፒኤስ/ ለመግጠም ዝግጅት በማድረግ ላይ መሆኑን እያስታወቀ ነው። ይህ አስገዳጅ የሆነ አሰራር አስኪተገበር ግን አስቸኳይና የማያዳግም እርምጃ ሊኖር ይገባል።
ሰሞነኛውን የነዳጅ እጥረት ተከትሎ በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ የነዳጅ ማደያዎች በሙሉ አቅማቸው እየሰሩ አይደለም። ይህን ችግር ከስሩ ለማጥራትም የክትትልና ቁጥጥር ስርዓት ሊዘረጋ ይገባል። ዕለታዊ መረጃዎች እንደሚጠቆሙት ነዳጅ አራግፈው የቆሙ ቦቴዎች ተመልሰው ወደጀቡቲ የመሄድ ፍላጎት እየታየባቸው አይደለም።
ከጅቡቲ ወደ አዲስ አበባ መግባት የሚገባቸው አንዳንድ ቦቴዎችም ነዳጁን በመዳረሻ ከተሞች እያረገፉት ይገኛል። ይህ ከመወረስና ከተጠያቂነት ለመዳን የሚደረግ ሽሽትም ለችግሩ ስፋት አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው።
በመንግስት በኩል ተደጋግሞ እንደሚነገረው በሀገሪቱ የነዳጅ አቅርቦት ይሉት ችግር የለም። እንዲህ በመሆኑም ተጨማሪ ነዳጅ ማስገባቱ አስፈላጊ አልሆነም። አሁንም ግን ከጅቡቲ አዲስ አበባ መድረስ የሚገባው የነዳጅ ሀብት በአግባቡ እየተጓጓዘ አይደለም።
ነዳጅ ለአንድ አገር የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ከፍተኛውን ድርሻ የሚሸፍን አንቀሳቃሽ ሞተር መሆኑ ይታወቃል። በነዳጅ አምራችነታቸው የሚታወቁ አገራትም ከራሳቸው አልፎ በመላው ዓለም በሚያውሉት ሽያጭ በእጅጉ ሀብታምና ተጠቃሚ መሆን ችለዋል።
በሀገራችንም መንግስት ለነዳጅ ገበያ በዓመት አስከ ሶስት ቢሊየን ዶላር ወጪ ያደርጋል። በየቀኑም ከሁለት ነጥብ ሰባት እስከ ሶስት ሚሊየን ሊትር ነዳጅን ያሰራጫል። ከተለያዩ ኩባንያዎች ጋር በሚደረግ የውል ሰምምነት ምርቱ በተገቢው መስመር ተደራሽ የሚሆንበት አሰራር ሲተገበር ቆይቷል።
የሰሞኑ የነዳጅ እጥረት የመስሪያቤቶችን አቅም በእጅጉ ተፈታትኗል። መስራት የሚገባው ሀይል ሰአታትን ለወረፋ በመስጠት ለኪሳራ እየተዳረገ ነው። ሰራተኛው በሰአቱ ፤ለስራው እየደረሰ አይደለም። በሀገሪቱ የትራንስፖርት ዝውውር ላይ ተጽዕኖው አጥልቷል።
ይህ ብቻ አይደለም። የሐምሌ ወርን ከነዳጅ ትርፍ ጋር ሊቀበሉት የቋመጡ ስግብግቦች የፈጠሩት ማህበራዊና ኤኮኖሚያዊ ጫና ከኑሮ ውድነቱ ተዳምሮ ችግሩን አጉልቶታል። የህብረተሰቡን ጓዳ በማራቆት አቅምን ለመፈተን የሚኖረው ድርሻም ቀላል ሚዛን ላይ የሚቀመጥ አይሆንም።
ለዚህ አይነቱ ኤኮኖሚያዊ ራስ ምታት አስቸኳይ መፍትሄ በማበጀት የወረቀት ላይ ህጎች በተግባር ሊተረጉሙ፤ በጥቂት ግለሰቦች ፍላጎትና ቅጥ ያጣ ስግብግብነት የተፈጠረው ችግርም በ‹‹ነበር›› ሊታለፍ፣ በ‹‹ይቅርታ›› ሊረሳ አይገባም።
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ሰኔ 30/2014