ለነዳጅ መቅዳት የሚደረገው ሰልፍ ወርሐዊ ትዕይነት ሆኖ ቆይቷል። በየወሩ የነዳጅ ክለሳ ይደረጋል በሚል ነዳጅ ለመቅዳት የማይሰለፍ ተሽከርካሪ አልነበረም። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ችግሩ ከፍቷል። በአዲስ አበባ ተሽከርካሪዎች ረጃጅም ሰልፎችን ለሰዓታት መሰለፍ ግድ ሆኖባቸዋል። ከማለዳ አንስቶ ምሽት ድረስ ከባጃጅ አንስቶ እስከ ከባድ መኪና ድረስ ለረጅም ሰዓት ይሰለፋሉ።
በአዲስ አበባ ከተማ ሁሉም ስፍራ በሚገኙ ነዳጅ ማደያዎች ረጃጅም የመኪና ሰልፎች በየቀኑ እየታዩ ናቸው። የሰሞን ወይም የወር ሳይሆን የዓመት ቀለባቸውን ሊሸምቱ የተሰለፉ በሚመስል መልኩ ነው መኪኖች ተሰልፈው የሚታዩት።
ሰልፉ ሁሉኑም ዓይነት ተሽከርካሪዎች ያካተተ መሆኑ ደግሞ የሰሞኑን የነዳጅ ወረፋ የተለየ ያደርገዋል። መጀመሪያ ላይ በአብዛኛው ይሰለፉ የነበሩት ናፍጣ የሚጠቀሙ ተሽከርካሪዎች ነበሩ። ወደ ሀገራችን ከሚገባው ነዳጅ 60 በመቶው ናፍጣ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ። የናፍጣ አቅርቦት ሲስተጓጎል ምን ያህል ተሽከርካሪዎችና ሕዝብ ለችግር እንደሚዳረግ ከዚህ በመነሳት መገመት አይከብድም። አሁን አሁን ደግሞ የቤንዚን ተጠቃሚ ተሽከርካሪዎች ተራ ጥበቃውን በብዛት ተቀላቅለውታል። ነዳጅ የጨረሰ ማደያ ጭር ይል ይሆናል እንጂ የተቀሩት ሙሉውን ቀን በተሽከርካሪ ሰልፍ ተጨናንቀዋል።
ተሽከርካሪዎች ረጃጅም ሰልፎችን ይዘው በነዳጅ ማደያዎች ዙሪያ የመኮልኮላቸው ሚስጥር በናፍጣና በቤንዚል እጥረት ቢሆንም፣ እጥረቱ የተከሰተው ሰው ሠራሽ በሆኑ ችግሮች መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ።
በመዲናዋ በሁሉም አቅጣጫዎች ሳምንትን የዘለቀው የነዳጅ እጥረት አሽከርካሪዎች ዕለታዊ ሥራቸውን ማቀላጠፍ እንዳይችሉ እንዳደረጋቸው እየገለጹ ናቸው። ለሥራ ሊውል የሚገባውን ረጅም ጊዜ በነዳጅ ፍለጋና በወረፋ ጥበቃ ለማሳለፍ መገደዳቸውን ያነጋገርናቸው አሽከርካሪዎች ይጠቁማሉ።
ከሁለትና ሶስት ሳምንት አስቀድሞ ናፍጣ መጥፋቱን አሽከርካሪዎቹ ያስታውሳሉ፤ አሁን ደግሞ በአብዛኞቹ የነዳጅ ማደያዎች ውስጥ የቤንዚን እጥረት መከሰቱን ይጠቁማሉ። ቤንዚን አለ ወደተባለበት አካባቢ ሲዘዋወሩ እንደዋሉና አለ በተባለበት ቦታም አሰልቺውን ወረፋ ለመጠበቅ መገደዳቸውን ጠቅሰው፣ ይህም በሥራቸው ላይ የበረታ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደረ መሆኑን ነው የሚናገሩት።
በከተማዋ በተለያዩ አካባቢዎች ቤንዚን ፍለጋ ተዘዋውረው አራት ኪሎ ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት አጠገብ ከሚገኘው ነዳጅ ማደያ መገኘታቸውን ከገለጹልን አሽከርካሪዎች መካከል ወጣት ሄኖክ ግርማ አንዱ ነው።
ከነዳጅ ማደያው በቅርብ ርቀት ተሰልፎ ተራውን እየተጠባበቀ ያገኘነው ሄኖክ፤ የራይድ አሽከርካሪ ነው። ከሰሞኑ በነዳጅ ላይ እየታየ ያለው ችግር በእጅጉ እንዳሳሰበውና ስጋት ላይ እንደጣለው አምርሮ ይናገራል።
ሄኖክ ችግሩ መንግሥት ነዳጅ ላይ ሲያደርግ የነበረውን ድጎማ ከሐምሌ 1 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ ሊያነሳ መሆኑን ተከትሎ ሕገወጦች የፈጠሩት ነው። ችግሩ በተለይም በራይድ አሽከርካሪዎች ላይ ሊብስ እንደሚችል ያለውን ስጋት ገልጾልናል። ራይድ በቀን ገቢ ተቀብሎ የሚሠራ እንደመሆኑ ነዳጅ ለመቅዳት ብቻ በቀን ከአራት ሰዓት በላይ መቆም ሥራውን ፈታኝ ያደርገዋል ይላል።
ሁሉም ነገር ከነዳጅ ጋር የተያያዘ መሆኑን በመጥቀስም ሄኖክ የኑሮ ውድነቱም ይበልጥ እንዳይባባስ ስጋት አድሮበታል፤ ድጎማው ይነሳል በሚል ይህን ያህል እጥረት ከታየ ድጎማው ሲነሳ ደግሞ ችግሩ ምን ያህል ሊባባስ እንደሚችል መገመት ቀላል ነው ሲል ያመለክታል። የሚመለከተው የመንግሥት አካል ያለውን ችግር ከመረዳት ባለፈ የእኛንም እንግልት በልኩ ሊያጤንና አቅርቦቱን በማስተካከል መፍትሔ ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ ነው ብሏል።
ለአራት ሰዓታት ተሰልፈው ከማደያው ግቢ የደረሱት ሌላው አሽከርካሪ ፍቃዱ ከፈተውም የወጣት ሄኖክን ሀሳብ የሚያጠናክር ሀሳብ ይሰነዝራሉ። አቶ ፍቃዱ፤ ቤንዚን ለመቅዳት ለስድስት ሰዓታት ተሰልፈዋል፤ ይህም ከብዙ ሥራቸው ያስተጓጎላቸው መሆኑን ተናግረዋል።ገና ድጎማው ሳይነሳ በዚህ ደረጃ ገበያው ከተረበሸ ድጎማ ሲነሳ ምን ሊፈጠር እንደሚችል በማሰብ ያላቸውን ስጋት ይገልጻሉ።
አቶ ፍቃዱ ችግሩን ለመፍታት መሠራት እንዳለበት አስረድተዋል። መንግሥት በነዳጅ ላይ ሲያደርግ የነበረውን ድጎማ ሊያነሳ ነው ከሚል ስግብግበነት የመጣ ስለመሆኑ መረጃ ያላቸው እንደሆነ ያነሱት አቶ ፍቃዱ፤ ከዚሁ ጋር ተያይዞም ማደያዎቹ በፍጥነት እየቀዱ አለመሆኑን እና መብራት ጠፋ እየተባለም በእጅጉ መጉላላት እንደሚስተዋል ነው ያመለከቱት።
በነዳጅ ግብይት ላይ ፊቱንም በተለይ ወር በቀረበ ቁጥር የዋጋ ክለሳ ይደረጋል በሚል ሕገወጦች አሉታዊ ተጽእኖ ሲያሳደሩ ኖረዋል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ መንግሥት በነዳጅ ላይ ሲያደርግ የቆየውን ድጎማ ከመጪው ሐምሌ ጀምሮ በሂደት እንደሚያነሳ ማሳወቁን ለእዚህም ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ተከትሎ ሕገወጦች የነዳጅ ገበያውን እየረበሹት ይገኛሉ። በነዳጅ አመላላሽ ቦቴዎች፣ በነዳጅ ማደያዎች እንዲሁም በአንዳንድ አሸከርካሪዎች ጭምር በነዳጅ ላይ ሕገወጥ ተግባር እየተፈጸመ ነው።
ነዳጅ አመላላሽ ቦቴዎች በተያዘላቸው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ነዳጁን ማደያዎች ማድረስ ሲገባቸው በየቦታው እያቆሙ ዋጋ እስከሚከለስ ይጠብቃሉ። አንዳንዶቹም ነዳጁን እስከ መሸጥ ይደርሳሉ። በጎረቤት ሀገሮች የነዳጅ ዋጋ በዓለም ገበያ ዋጋ የሚሸጥ መሆኑን ተከትሎ ዋጋው ውድ መሆኑንም ቦቴ አሽከርካሪዎች፣ ባለማደያዎች እና ሕገወጦች ነዳጁን ወደ ጎረቤት ሀገር በኮንትሮባንድ መልክ እያስወጡ ናቸው። አንዳንድ አሽከርካሪዎች ደግሞ የነዳጅ ዋጋ ይወደዳል ወይም የነዳጅ እጥረት ይከሰታል በሚል ነዳጅ በበርሜልና በመሳሰሉት ይደብቃሉ። ይህ ሁሉ የነዳጅ ግብይቱን ችግር ውስጥ ከቶታል።
መንግስት በነዳጅ ግብይቱ ላይ እየተፈጸመ ያለው ሕገወጥ ድርጊት ለመቆጣጠርና ለመከላከል የተለያዩ እርምጃዎችን ሲወሰድ ቆይቷል፤ ይሁንና ችግር እየተባባሰ እንጂ እየተወገደ አልመጣም። አሁን ከአንድ ሳምንት ለተሻገረ ጊዜ የነዳጅ ግብይቱ ቀውስ ውስጥ መግባቱ የሚያመለክተውም እርምጃው ውጤት እያመጣ አለመሆኑን ነው።
የነዳጅ ድጎማ መነሳት የሚጀመርበትን መጪውን ሐምሌ ወር ታሳቢ በማድረግ ለሕገወጥ ድርጊት ያቆበቆቡ አካላት ታይተዋል። በርካታ ነዳጅ የጫኑ ቦቴዎች የጫኑትን ነዳጅ በወቅቱ ማደያዎች ማድረስ ሲገባቸው በየመንገዱ እየተጎተቱ፣ እየተደበቁ ናቸው። ይህ ነው በአሁኑ ወቅት ለተፈጠረው የነዳጅ እጥረት ምክንያት የሆነው። በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የነዳጅ እጥረት የተከሰተው በዚህ ምክንያት ነው። ይህም በሀገሪቱ ያለው የነዳጅ ግብይት ጤናማ እንዳልሆነ በግልጽ የሚያሳይ ነው።
ይህን ተከትሎ መንግሥት አሁን መረር ወዳለ እርምጃ እርምጃ እየገባ ነው። በተለያዩ አካባቢዎች በእዚህ ሕገወጥ ግብይት ውስጥ የተገኙ ቦቴዎች እና ማደያዎች ላይ እርምጃ መውሰድ ተጀምሯል። እርምጃው እንዳለፉት ጌዚያት በማስጠንቀቂያና ማሳሰቢያ ብቻ የሚታለፍ አይደለም። የቁጥጥርና ክትትል ሥራው ተጠናክሮ ቀጥሏል።
መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ በተደረገው የቁጥጥር ሥራም ሰሞኑን 200 የሚደርሱ ነዳጅ የጫኑ ቦቴዎች ከጅቡቲ ተነስተው ወደ አዲስ አበባና ወደ ተለያዩ መዳረሻ ቦታዎቻቸው መድረስ ሲገባቸው ከመንገድ ቀርተው በየጥጋጥጉ መደበቃቸው ታውቋል። ከቀናት በፊት እንዲሁም ከሳምንት ቀድመው በየቦታቸው መድረስ ይገባቸው የነበሩት ነዳጅ የጫኑ ቦቴዎች የጫኑትን ነዳጅ በተላኩበት ማደያ ደርሰው እንዲያራግፉ ትዕዛዝ የተሰጣቸው ሲሆን፣ ተግባራዊ በማያደርጉት ላይም መንግሥት ተገቢውን እርምጃ ለመውሰድ የሚገደድ መሆኑን የነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን ከሰሞኑ አስገንዝቧል።
የነዳጅ እና ኢነርጂ ቁጥጥር ባለስልጣን ነዳጅ ለመቅዳት በማደያዎች የሚታዩ ረጃጅም ሰልፎችን ለማስቀረት በቀን ከ10 ሚሊዮን ሊትር በላይ ነዳጅ ካለፈው እሁድ ጀምሮ ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገባ እየተደረገ መሆኑን ማስታወቁን ፋና ብሮድካስቲንግ ዘገባ ያመለክታል።
በአቅርቦት በኩል ክፍተት እንዳይኖርም ቀድሞ በቀን ይቀርብ ከነበረው 9 ሚሊዮን ሊትር ወደ 10 ሚሊዮን ሊትር ነዳጅ ማሳደጉን የባለስልጣኑ የነዳጅ ስታንዳርድ ጥራት ዳይሬክተር አቶ ለሜሳ ቱሉ ተናግረዋል።
እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፤ ነዳጅ የጫኑ ቦቴ ተሽከርካሪዎች መንገድ ላይ መዘግየት እንዳይፈጠር እና ስርጭቱ ላይ ችግር እንዳይኖር ለማድረግ ኮሚቴ ተዋቅሮ በዘላቂነት ለመፍታት እየተሠራ ነው። ባለፈው ሳምንት እንደ ሀገር 200 ነዳጅ የጫኑ ቦቴዎች ከጂቡቲ ተነስተው 18ቱ ሞጆ ወደብ መድረሳቸውን እና የተቀሩት ላይ አስተዳደራዊ እና ሕጋዊ እርምጃ እንደተወሰዳባቸው አቶ ለሜሳ ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 8 ነዳጅ የጫኑ ቦቴዎች የተቀመጠላቸውን ቀነ ገደብ ባለማክበራቸው ምክንያት ነዳጁን መውረሱን አቶ ለሜሳም ጠቅሰው፣ ሌሎች ክልሎችም ተመሳሳይ እርምጃ እየወሰዱ መሆኑን ተናግረዋል። ትናንት የወጡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ደግሞ በሌሎች ሁለት ቦቴዎች ላይ ተመሳሳይ እርምጃ ተፈጽሟል።
የችግሩን መጠን በፍጥነት ለመቀነስ እንዲያስችል እየተሠራ መሆኑን የገለጹት ኃላፊው÷ በተደረገው ጠንካራ ክትትልና ቁጥጥር ባለፈው እሁድ 39 ነዳጅ የጫኑ ቦቴዎች አዲስ አበባ መድረሳቸውን ጠቁመዋል።
በሌላ የባለስልጣኑ መረጃ በሀገሪቱ የነዳጅ አቅርቦት ችግር የለም። ቢኖር እንኳ ከመጠባበቂያ ክምችት ማውጣት ይቻላል። የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አሕመድ ሰይድ ለፋና ብሮድካስት እንዳሉት፤ አስፈላጊው ነዳጅ ወደ ሀገር ቤት እንዲገባ እየተደረገ ነው። ችግሩ ያለው ከጅቡቲ የሚመጣውን ነዳጅ የሚፈለገው ቦታ አለማድረስ ላይ ነው።በነዳጅ አመላላሽ ቦቴዎች በኩል የመደበቅና የመጎተት ነገር ይታያል።
በነዳጅ ማጓጓዝና ግብይት ላይ የሚሠራ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ እየሠራ መሆኑን አቶ አሕመድ ጠቅሰው፣ በሚደበቁና በሚዘገዩ ቦቴዎች ላይ እርምጃ እየተወሰደ ነው። እርምጃው ነዳጁን ከመውረስ ፈቃድ እስከመንጠቅ የሚደርስ እርምጃ እንደሚወሰድ አስታውቀዋል። የዘገዩ ቦቴዎች መረጃ ለኮማንድ ፖስት እየተላለፈ እርምጃ እንደሚወሰድ አስታውቀዋል። ሕገወጦች በፈጠሩት ችግር አሽከርካሪዎችና መላው ሕዝብ እየተሰቃየ መሆኑን ጠቅሰው፣ ሕዝቡ በቁጥጥርና ክትትል ሥራው አሁንም ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጠይቀዋል።
በነዳጅ ማደያዎች አካባቢም በሙሉ አቅም ያለመሥራት ችግር እንደሚስተዋል ነው ያመለከቱት፤ ይህንንም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ለመፍታት መሥራት አስገንዝበዋል። ቦቴዎች እርምጃዎችን በመፍራት ከተመደቡበት ቦታ ውጪ እያራገፉ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ እርምጃው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው ያረጋገጡት።
መንግሥት አንዱ ተስፋ ያደረገው ዘላቂ መፍትሔ የድጎማው መነሳት መሆኑን ይገልጻል። ነዳጁ በዓለም ዋጋ መሠረት ግብይት ሲፈጸምበት ሕገወጥ ግብይቱ በተለይ የኮንትሮባንድ ንግዱ እንደሚቀር ይጠበቃል።
በአሁኑ ወቅት ሰው ሠራሽ በሆኑ ችግሮች እየተረበሸ ያለውን የነዳጅ ገበያ ለማረጋጋትና ተያይዘው የሚመጡ ችግሮችን ለመቅረፍ በሚል ከሠራቸው ሥራዎች መካከል የግብይት ሥርዓቱን ዘመናዊ ማድረግ አንዱ ነው።
የግብይት ሥርዓቱን በቴክኖሎጂ የታገዘ ጊዜ ቆጣቢና ቀልጣፋ በማድረግ በነዳጅ ዙሪያ እየታየ ያለውን የግብይት ችግር ለመቅረፍም የነዳጅ ድጎማ ክፍያን መፈጸም የሚያስችል መተግበሪያ ከትናንት በስቲያ ይፋ ተደርጓል። የነዳጅ ድጎማው ከሐምሌ ጀምሮ ተግባራዊ ሲደረግ ችግሩ በሂደት እየተፈታ እንደሚሄድ ይታመናል።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ሰኔ 29 /2014