የአብዛኞቻችን የዕውቀት መነሻ “ዕውቀት ይስፋ ድንቁርና ይጥፋ ይህ ነው የኢትዮጵያ ተስፋ” የሚለውን ዓረፍተ ነገር ከአናቷ ባነገበችው የተስፋ ገብረስላሴ ዘብሔረ ቡልጋ የፊደል ገበታ ለመሆኑ ጥርጥር የለኝም። ከ “ሀ እስከ ፐ” ያሉትን ፊደላት ከነዝርያቸው ለያዘችው ካርቶንም የነበረን ጥንቃቄና እንክብካቤ በዋዛ የሚታይ አይደለምና፤ በደረታችን ዕቅፍ ሽጉጥ አድርገናት ከየኔታ እግር ስር ተቀምጠን አነብንበናል።
ታዲያ የፊደል ገበታችን የሆነችውን ያችን ካርቶን አቅፈን ከየኔታ እግር ስር ቁጭ ቁጭ ብለን ፊደል ለይተን፤ መልዕክተን አነብንበን፤ አቦጊዳ ሄውዞ ብለን፤ ከፍ ሲልም ዳዊት ደግመን ይሆናል። ያኔ በአማካይ ሰባት ዓመት ይሆነንና እጆቻችንን በሁለት እግሮቻችን ስር በማሾለክ ጆሮ የመያዝ ፈተና ተፈትነን ጉዞ ወደ አንደኛ ክፍል ይሆናል። በዚህ ሂደት ውስጥ ለቆጠርነው ፊደል ትልቁ ክፍያ ቢበዛ በወር ሁለት ብር ይሆናል።
ዛሬ ዛሬ ግን ልጆቻችን ፊደል ለሚቆጥሩበት የምንጠየቀው ገንዘብ የትየለሌ ከመሆኑም በላይ ለዓመቱ የትምህርት ዘመን የምንጠየቀው የትምህርት መሳሪያዎች ብዛትና ዓይነት አይደለም ሕፃናቱ ተጠቅመውበት ቆጥረውት የማይጨርሱት መሆኑ ሲታሰብ ደግሞ በጣም ያስገርማል። ከዚህም ሌላ ሕፃናቱ ገና በጠዋቱ በሶስት ተኩልና በአራት ዓመት ዕድሜያቸው ወደ ትምህርት ቤት እንዲገቡ ጊዜው ያስገድዳል። ምስጋና ለዘመኑ ቴክኖሎጂ ይግባውና ሕፃናቱም ገና በለጋ ዕድሜያቸው ከአፍ መፍቻ ቋንቋቸው በላይ የፈረንጅ ቋንቋ ይማራሉ።
የሆነ ሆነና ከየኔታ እግር ስር ተቀምጠን ፊደል የቆጠርን እኛ ወላጆችና ከ“ነርሰሪ እስከ ኬጂ ሶስት” ተምረው ወደ አንደኛ ክፍል የገቡት ልጆቻችን የዕውቀት ደረጃችን ሲፈተሽ ነገሩ ሁሉ የተገላቢጦሽ ይሆናል። በመሆኑም የእኛና የልጆቻችን የዕውቀት ደረጃ በዓይነት፣ በብዛትና በጥራት በብዙ ሺህ ኪሎ ሜትሮች ተራርቀን እንገኛለን። ልጆቻችን የሚማሩት ትምህርት መጠኑ ከመብዛቱም በላይ አብዛኛው የውጭ ቋንቋ ላይ መሰረት ያደረገና ምሳሌዎቹ ሁሉ ኢትዮጵያዊ ሽታ የሌላቸው መሆናቸው የብዙ ወላጆች መልስ የሌለው ጥያቄ ሆኖ ቀጥሏል።
ይሁን እንጂ፤ አብዛኛው ወላጅ ያለውን ጥሪት አሟጥጦ ልጁን የግል ትምህርት ቤት ለማስተማር ሲታትር ይታያል። ለዚህም ዋና ምክንያቱ ዘወትር እንደሚሰማው ከእኔ የተሻለ ኑሮ እንዲኖርና፤ በዕውቀት የበለጸገ ትውልድ ሆኖ ዶክተር፤ ኢንጂነር፤ ፓይለትና የመሳሰሉትን በማህበረሰባችን ትልቅ ግምት የሚሰጣቸውን ሙያዎች እንዲቀስምና ከራሱም አልፎ ቤተሰቡንና ሀገሩን እንዲጠቅም ካለው ጥልቅ ስሜትና ጉጉት የተነሳ ነው።
ይሁንና፤ አብዛኛው ወላጅ ለልጆቹ ጥሩ ቦታ መድረስ ባለው ጉጉትና ጥልቅ ስሜት ቀን ከሌት እየተጋ ውጤታማነታቸውን ይጠባበቃል። አንዳንዴ ታዲያ ወላጆች ከአቅም በላይ የሆነ ውጤት ከልጆቹ ይጠብቁና ልጆቹን ላልተገባ የስነልቦና ጫና ሲዳርጓቸው ይታያል። በመሆኑም በርካታ ወጣቶች ቤተሰብ የሚፈልገውን ውጤት ለማምጣትና ቤተሰብ የሚፈልገውን ዓይነት ሰው ሆነው ለመገኘት በሚያደርጉት ትግል ሳይሳካላቸው ቀርተው ከራሳቸውም ከቤተሰብም ሳይሆኑ የቀሩትን ቤት ይቁጠራቸው።
በተቃራኒው ደግሞ፤ አንዳንድ ቤተሰብ ለልጆች የሚገባቸውንና ልካቸው የሆነውን ኃላፊነት እንኳን ባለመስጠት ልጆቹን ሰነፍ፤ ፈሪና በራሳቸው የማይተማመኑ ዜጎች ሲያደርጋቸው ይስተዋላል። በዚህም በርካታ ወጣቶች ሙሉ አቅማቸውን ባለመጠቀምም ይሁን በቸልተኝነት ከሚገባቸው ውጤት በታች ያስመዘግባሉ። ቤተሰብም በእጅጉ ስሜቱ ተነክቶ በልጆቹ ላይ አላስፈላጊ እርምጃ ሲወስድ ይስተዋላል።
በቅርቡ በማህበራዊ ሚዲያ የተሰራጨው አንድ ዜናም ይህንኑ የሚያጠናክር ነው። በቻይናዋ ሉኦያንግ መንደር ቻይናዊቷ ወላጅ ልጇን እኔ የምፈልገውን ውጤት ማምጣት አልቻልክም በማለት መንገድ ላይ ጥላው ትሄዳለች። እናት የ12 ዓመት ታዳጊ ልጇ በአገር አቀፍ ፈተና 95 ከመቶ ያመጣል ብላ የጠበቀችው ቢሆንም፤ ታዳጊው ግን ያቅሙን ያህል ሰርቶ 81 በመቶ ቢያመጣም በውጤቱ ደስተኛ ያልሆነችው እናት ታዳጊውን መንገድ ላይ ጥላው ሄዳለች።
መንገድ ላይ የተጣለው ታዳጊ እናቴ ትመለሳለች ብሎ ሲጠብቅ እናት የውሃ ሽታ ሆና ትቀራለች። በዚህ መሀል ፖሊስ ያገኘውና ስለሁኔታው በአካባቢው የነበሩ ሰዎችን በመጠየቅ ለመረዳት ይሞክራል። በሙከራውም እናት ልጇን ከመኪናዋ ውስጥ እያመነጫጨቀችና እየመታች ካስወጣችው በኋላ መንገድ ላይ ጥላው መኪናዋን አስነስታ እንደሄደች ይረዳል።
ፖሊስ አያይዞም በሲሲቲቪ ካሜራ የነበረውን እንቅስቃሴ በማጣራት ወደ ቤተሰቡ ይደውልና እናቱን አፈላልጎ ያገኛል። ይሁንና ልጇን ጥላ የሄደችው እናት ልጁን ጭራሽ እንደማትፈልገውና የፈለጉትን ቢያደርጉት ግድ እንደማይሰጣት ለፖሊስ አስረግጣ ትናገራለች። ምናልባትም ሊያስቀጣት ሊያሳስራት ቢችል እንኳን ይህንን ሰነፍ ልጇን መልሳ መውሰድ እንደማትፈልግም ጨምራ በመግለፅ ስልኩን ትዘጋለች።
የዚህች ወላጅ ጉዳይ በማህበራዊ የትስስር ገጾች በብዙ ከመሰራጨቱም በላይ በአሁን ወቅት ከተለያዩ አቅጣጫዎች ትችት እየቀረበባት ይገኛል። የቀረበባት ትችትም ታዳጊው ምንም ጥፋት እንደሌለበትና አጥፍቶም ቢሆን እንኳን በትዕግስት መንከባከብና እናት የምትጠብቀውን ሳይሆን ታዳጊው የቻለውን ውጤት እንዲያመጣ መርዳት እንጂ በዚህ መልኩ የወለደችውን ልጅ ሜዳ ላይ መጣል ተገቢ እንዳልሆነ ብዙ እየተባለ ነው።
እንግዲህ አንድ ቤተሰብ አንድ ልጅ ብቻ እንዲወልድ የሚያስገድድ ፖሊሲ ያላት ሀገረ ቻይና ይህን ድርጊት ትፈፅማለች ብሎ ማሰብ ቢከብድም ነገሩ ግን ተከስቷል። በርግጥ በቻይናም ይሁን በማንኛውም ዓለም አገር አቀፍ ፈተናዎች ላይ ጥሩ ውጤት ማምጣት እና አለማምጣት የታዳጊዎችን የወደፊት እንቅስቃሴ ከሚወስኑ ነገሮች መካከል ዋነኛውና የቤተሰብ ቁልፍ ጉዳይ ቢሆንም፤ በዚህ መልኩ ልጆችን መቅጣትና ጎዳና ላይ መጣል ግን ከጤነኛ አስተሳሰብ፤ ያውም ከወላጅ የሚመነጭ አይደለም እያልን ወደ እኛው ጉዳይ እንመለስ።
ወደ እኛ ስንመለስ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ልጅ ሲወልድ በዕቅድ ሳይሆን በስሜት ወይም በአጋጣሚ ይሁን እንጂ ልጆች ከተወለዱ በኋላ ግን ዘወትር እንደምንለው በዕድላቸው ሲያድጉ እናያለን። በርግጥ ኢትዮጵያዊ ወላጅ ለወለደው ልጅ የሚሳሳና ሕይወቱን ሳይቀር አሳልፎ የሚሰጥ እንጂ፤ የትምህርት ውጤትህ ዝቅተኛ ነው ብሎ የአብራኩ ክፋይ የሆነውን ልጁን አውላላ ሜዳ ላይ የሚጥል ማህበረሰብ አይደለም፤ እንዲያውም ከአቅሙ በላይ የሚንከባከብና የሚያስተምር ህዝብ ነው።
በመሆኑም፤ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ወላጅ እሱ ሳይማር ውጤታቸው ምንም ይሁን ምን ልጆቹን የሚያስተምር እንደመሆኑ ለልጆቹ ጥሩ ቦታ መድረስ ያለው ጉጉትና ስሜት ጥልቅ ነው። አሁን አሁን በርካታ ወላጆች ልጆቻቸውን ከአቅማቸው በላይ በሆነ ዋጋ በግል ትምህርት ቤቶች ሲያስተምሩ ይታያሉ። ከነዚህ ወላጆች መካከልም በአካባቢዬ ያስተዋልኳትን አንዲት እናት ላስተዋውቃችሁ።
ወይዘሮ ወርቄ ትባላለች በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ በተለምዶ ጀሞ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የምትኖርና በዛው አካባቢ በጉልት ስራ የምትተዳደር የሁለት ሴት ልጆች እናት ናት። ወርቄ ከስድስተኛ ክፍል የዘለለ የትምህርት ዝግጅት እንደሌላት፤ የልጆቿ አባት በሕይወት እንደሌለና ልጆቿን የምታስተምረውም በአካባቢው በሚገኝ የግል ትምህርት ቤት እንደሆነ ትናገራለች። “ልጆችን ያለአባት ማሳደግና በጉልት ስራ በሚገኝ ገቢ ልጆችን በግል ትምህርት ቤት ማስተማር እንዴት ነው?… አይከበድም?”ብዬ ጠየኳት
“እሱስ በጣም ከባድ ነው ነገር ግን ምንም ምርጫ የለኝም ልጆቼ ተምረው ከእኔ የተሻለ ሕይወት እንዲኖሩ ነው ምኞቴ፤” በማለት መለሰችልኝ። ወርቄ የጉልት ስራዋን የምትከውነው ከክፍያ ነፃ የሆነና ከመንግስት ባገኘችው የመስሪያ ቦታ በመሆኑ ፈጣሪ ይመስገን ትላለች። የአካባቢው ሰውም በብዛት አትክልት ከሷ እንደሚገዛትና ይህም ትልቅ ድጋፍ እንደሆናት ትናገራለች። ወርቄ የምትኖረው በጋራ መኖሪያ ቤቶች ስቱዲዮ ውስጥ ሲሆን፤ የልጆቿን የትምህርት ቤት ክፍያ ጨምሮ ከቤቱ ጋር በወር ከሁለት ሺህ ብር በላይ ወጪ እንዳለባት ትናገራለች።
ወርቄ ብዙ ጊዜ ሌሊት 11፣00 ሰዓት ተነስታ ፒያሳ አትክልት ተራ በመሄድ አቅሟ የፈቀደውን ያህል አትክልት ገዝታ ወደ ሰፈሯ ትመለስና ለልጆቿ ቤት ያፈራውን በማስያዝ ወደ ትምህርት ቤት በመላክ ወደ ጉልት ስራዋ ትመለሳለች። ልጆቿ የሰባትና የአራት ዓመት ዕድሜ ያላቸው በመሆናቸው፤ ከትምህርት ቤት መልስ እዚያው ከእሷው ጋር ጉልት ያመሻሉ። ታድያ በቆይታቸው የተማሩትን በማየት የቤት ስራ ለማሰራት ትጣጣራለች። አንዳንዴም የደንበኞቿን ትብብር በመጠየቅ ልጆቿን ለማስረዳት ትታትራለች።
ወይዘሮ ወርቄ ከፍሎ ከማስተማሩ በላይ የቸገራትና ፈታኝ የሆነባት ነገር፤ ልጆቿ የሚማሩትን ትምህርት ተረድቶ እነሱን ማስረዳትና ይዘውት የሚመጡትን የቤት ስራ ማሰራት መሆኑን ትናገራለች። ለዚህ መፍትሔ ብላ አስጠኚ የቀጠረችላቸው ቢሆንም ክፍያውን ባለመቻል እንዳቆመች በመግለፅ አሁን ግን፤ በጎረቤት ልጆች እገዛ ልጆቿ ቢያንስ የቤት ስራ ሳይሰሩ አይሄዱም ትላለች። ወርቄ ትልቋ ልጅ በጣም በሳል እና ጎበዝ በመሆኗ ትልቅ ተስፋ እንዳላት በልበ ሙሉነት ትናገራለች። ትንሽ ጊዜ ብቻ ነው የምቸገረው፤ ልጆቼ ነገ ከነገ ወዲያ ሁሉንም ነገር ራሳቸውን ችለው ይሰራሉ፤ በትምህርታቸውም ጥሩ ውጤት ያመጣሉ፤ በዚህም ሙሉ እምነት አለኝ ትላለች።
“የምኖረው ለልጆቼ ነው” የምትለው ወርቄ ዛሬ ለልጆቿ የምትከፍለው ውድ ዋጋ ነገ ፍሬ አፍርቶ መልሶ እንደሚከፍላት እምነቷ ነው። እኛም ይህ ህልሟ ዕውን ሆኖ የምታይበት ጊዜ ቅርብ እንዲሆን እንመኛለን። ይሁን እንጂ፤ ከልጆቻችን አቅም በላይ የሆነ ነገር ውጤት መጠበቅ አንድም ልጆችን ወዳልተፈለገ አቅጣጫ ይመራል፤ ሁለትም የተጠበቀው ውጤት ባይመጣ የወላጆች ስሜት ክፉኛ ይጎዳልና ሁሉንም ነገር በልኩና በሚዛኑ ማየት ይገባል እንላለን።
ውድ አንባቢያን እናንተስ? የልጆቻችሁ ውጤት ያማረና የሰመረ እንዲሆን የምታደርጉት ጥረት እንዴት ያለ ይሆን?… ልጆችስ የሚጠበቀውን ውጤት ባያስመዘግቡ ምን ይሰማችሁ ይሆን? መቼም ስሜታችሁ እንደ ቻይናዊት እናት እንደማይሆን እምነቴ ይሁንና መልሳችሁን ለናንተው ልተወው። እኔ አበቃሁ።
አዲስ ዘመን መጋቢት 18/2011