ይህንን ጉዳይ ለማንሳት ያስገደደኝን አጋጣሚ ላስቀድም። ሴት እንደመሆኔ መጠን ወርሐዊ ግዴታዬ ላይ ነበርኩኝና የሴት ንጽሕና መጠበቂያ አዘውትሬ ወደ ምገዛበት ሱቅ ሄድኩኝ ። ኢቭ ሞዴስ ስጠኝ ብዬ መቶ ብር ሰጠሁት እሱም የንጽሕና መጠበቂያውንና መልስ ደግሞ ሰላሳ ብር ሰጠኝ። የእውነት ደነገጥኩ ምክንያቱም ከአንድ ወር በፊት አርባ ብር የገዛሁት ሞዴስ ነው አሁን ሰባ ብር የገባው። ጭማሪው በጣም የተጋነነ ነው። እየተነጫነጭኩም ቢሆን ገዝቼ ተመለስኩ።
በዛ ቅጽበት ግን ወደ ሀሳቤ የመጣው ይህንን ዋጋ መክፈል የማይችሉ ሴቶች አማራጭ ምን ሊሆን ነው የሚለው ነው። ኮንዶም በሽታ ለመከላከል፣ እንዲሁም ያልተፈለገ እርግዝና ለማስወገድ በሚል መንግሥት በነጻ ኅብረተሰቡ እንዲጠቀም አመቻችቷል። በነጻ( ያለ ክፍያ) እየተሰጠው ደግሞ የማይጠቀመው ብዙ ነው ለዚህም ማሳያ የሚሆነው አሁን ላይ ቁጥሩ እየጨመረ ያለው የኤች አይ ቪ እና የአባላዘር በሽታዎች ስርጭት እንዲሁም፣ እርግዝናን የሚያስወርዱ ሴቶች ብሎም ተማሪዎች ቁጥር ነው። የወር አበባ (menstruation) አንዲት ሴት ፈለገችም አልፈለገችም የተፈጥሮ ግዴታዋ በመሆኑ፣ እስከተወሰነ እድሜ ድረስ በየወሩ የምታየው ተፈጥሯዊ ነገር ነው።
ይህን ለመቋቋም ደግሞ የንጽሕና መጠበቂያ ሞዴስ ያስፈልጋታል። ወደ ገጠሩ የሀገራችን ክፍል ይህን የንጽሕና መጠበቂያ ሞዴስ የማግኘት እድል ስለሌላቸው ( ማግኘት ባለመቻላቸው)፣ በኩበት፣ በጨርቅ፣ በቃጫ፣ በፍራሽ ስፖንጅ ( እሱም ከተገኘ ነው) ብቻ ደሙን ለተወሰነ ሰዓት ሊይዝላቸው በሚችል ነገር ሁሉ ለመቋቋም ይሞክራሉ። በዚህ የተነሳ በየወሩ ሴት መሆናቸውን ያማርራሉ ተፈጥሮን ይጠሏታል። በዚህ ጊዜያቸው ላይ ከሰው ይገለላሉ። ወደትምህርት ገበታቸውም አይሄዱም። ቀናቸውን እስኪጨርሱ፣ ለብቻቸው በስቃይ ውስጥ ነው የሚያሳልፉት።
10 ፍሬ የሚይዘው የንጽህና መጠበቂያ ሞዴስ፣ ከስምንት ብር ተነስቶ አሁን ሰባ ብር እየተሸጠ ነው። ጥቂት የወር ገቢ ያለን ሴቶች ቢወደድብንም እየተነጫነጭንም ቢሆን እንገዛለን። የኑሮ ውድነቱ እዚህ ደረጃ ላይ በደረሰበት በአሁኑ ወቅት፣ የቤት ውስጥ ብዙ ኃላፊነት ያለባቸው ሴቶችስ ይህን የመግዛት አቅም ይኖራቸዋል? በከተማ ያሉ የመግዛት አቅም የሌላቸው ሴቶችስ ምን ያደርጋሉ?። ይገዛሉ ወይስ ይተዉታል? ሲተዉትስ ምን አይነት አማራጭ ነው የሚጠቀሙት? የሚለው አሳሳቢ ጉዳይ መሆን አለበት።
በሚጠቀሟቸው አማራጮች ምክንያት ስንቶች ለማህጸን ኢንፌክሽን እና ተያያዥ የማህጸን ሕመሞች እንደተጋለጡ ቤት ይቁጠረው። ሴት ልጅ እናት ናት፣ እህት ናት፣ ሚስት ናት፣ ደግሞም ሴት በሀገር ትመሰላለች። እንደሚታወቀው በሀገራችን ደግሞ ሴት ብዙ ኃላፊነት አለባት ። የቤተሰብ ኃላፊነት ጫናው የሚወድቀው ሴቷ ላይ ነው። በተለይ ደግሞ የቤት እመቤት የሆኑ እናቶች ላይ ጫናው የበረታ ይሆናል። አሁን በሀገራችን ላይ ባለው የኑሮ ውድነት፣ አባወራ ሰርቶ ገንዘብ ቢያመጣም ሴት ግን ገንዘቡን አብቃቅታ ቤተሰቧን መመገብ ማስተዳደር ይጠበቅባታል።
ሴት ልጅ ተፈጥሮ ብቻዋን እንኳን የምታሸክማት ብዙ ኃላፊነቶች አሉባት። ሴት በመሆኗ፣ የሚሰጧት ኃላፊነቶችን የምትቀበለው ገና በትንሽ እድሜዋ ነው። አደግ ስትልማ በተለይ እንደሀገራችን ባሉ ያላደጉ ሀገሮች ላይ ኃላፊነቷ እየበዛ ነው የሚመጣው። ተፈጥሮ ከምትሰጣት ኃላፊነት ባሻገር ማኅበረሰቡ የሚያሸክማት ኃላፊነት አለ። ሲሆን ሲሆን ሴት ላይ የሚበዛውን ጫና ለመቀነስ ብዙ ጥረት ማድረግ፣ በብዙ መልኩ ማበረታታት ሲገባ እንዴት ፈቅዳ ባላመጣችው ነገር በተፈጥሮ ግዴታዋ መኖሯን እንድትጠላ ሴትነቷን እንድታማርር ይፈቀዳል ። ሴት ከፈጣሪ ድንቅ ስጦታ ተደርጎ በተሰጣት ነገር መማረር አይገባትም።
ሴት ልጅ የወር አበባ (menstruation) ማየት ጀመረች ማለት ፍሬያማነቷ ጀመረ ማለት ነው ። ልጅ የመውለድ ጸጋዋ ይጀምራል ማለት ነው። በዚህ ወርሐዊ ግዴታ ውስጥ ካላለፈች ልጅ ማግኘት አትችልም ። ይህ ድንቅ ስጦታ ነው። ይህን የምታሳልፍበትን ጊዜ መጥላት ሳይሆን በፈጣሪ ድንቅ ሥራ መደነቅ ነው የሚገባት። ለዚህ ደግሞ የምትኖርበት ማኅበረሰብ ነገሮችን ሊያመቻችላት እንጂ ነገሮችን ሊያከብድባት አይገባም።
በሚያሳዝን ሁኔታ ወደ ደቡብ ክልል ጂንካ ወረዳ ባሉ ገጠራማ አካባቢዎች ሴት ልጅ የወር አበባዋ ላይ ስትሆን፣ በጣም ትገለላለች ሰው ፊት እንድትቀርብ አይፈለግም። የበለጠ የሚያሳዝነው ደግሞ ይህንን የሚያደርጉት እናቶች ራሳቸው መሆናቸው ነው። እነሱም ያለፉበት የእነሱም የሕይወታቸው አካል ነው፣ ነገር ግን የሴት ልጅ የወር አበባዋ ሰዓት እንደ እርግማን ነው የሚቆጠረው። ተደብቃ እንድታሳልፍ ነው የሚደረገው። እነዚህ ሴቶች የወር አበባ፣ ልጅ ከመውለድ ጋር የሚያያዝ የተፈጥሮ ግዴታ እንደሆነ አይረዱም። ግንዛቤው የላቸውም። እነርሱ ልጆቻቸውን ያገኙት በዚህ ሂደት ውስጥ በማለፍ ነው ብለው አያስቡም።
በነገራችን ላይ በተለያዩ ገጠራማ የሀገራችን ክፍሎች ላይም ተመሳሳይ አመለካከት ያላቸው ማኅበረሰቦች እንዳሉ ለማወቅ ችያለሁ። በሰሜኑ የሀገራችን ክፍልም የዚህ አስተሳሰብ ተጠቂዎች መኖራቸውን በዛ አካባቢ መምህር በነበረበት ወቅት መታዘቡን አንድ ሰው አጫወተኝ። የሚያሳዝነው ነገር ሴቶቹ ልጆች የወር አበባቸው ላይ በሚሆኑበት ወቅት ይጸየፏቸዋል። ከቤተሰብ አባላት ጋር ማዕድ እንዲቀርቡ አይፈቀድላቸውም። ምግብ እንዲያዘጋጁ አይፈለግም ወደ ማዕድ ቤት እንዲገቡ እንኳን አያደርጓቸውም። ለብቻቸው የሚሆኑበት ጎጆም አላቸው። ምን ያህል ራሳቸውን ሊጠሉ እንደሚችሉ ነው የሚያሳየው። ይህ በጣም የሚያሳዝን ነገር ነው። ይህን አመለካከታቸውን የሚቀየር ትምህርት ያስፈልጋቸዋል። ይህን ግንዛቤ ለመፍጠር ደግሞ በገጠራማው የአገራችን ክፍል የሚሠማሩ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎችና ከሴቶች ጋር በተያያዘ የሚሠሩ አካላት ትልቅ ሥራ መሥራት አለባቸው።
የጤና ባለሙያዋ ዶ/ር ኤልሳ ሙሉጌታ በዚህ ጉዳይ ላይ ሀሳባቸውን ሲያካፍሉኝ ፣በተለያዩ አካባቢዎች በተለይ ደግሞ በገጠራማው የአገራችን ክፍል የሚገኙ ሴቶች የንጽህና መጠበቂያ ሞዴስ ማግኘት ስለማይችሉ የተለያዩ ባዕድ ነገሮችን በመጠቀማቸው ምክንያት ለተለያዩ የማህጸን በሽታዎች ተጋላጭ የሚሆኑበት አጋጣሚ ሰፊ እንደሆነ ነግረውኛል። ከዓመታት በፊት ይሠሩበት ወደነበረው በአማራ ክልል አገው ዞን በሚገኝ አንድ የገጠር ሆስፒታል ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ብዙ ሴቶች በማህጸን ኢንፌክሽን፣ በማህጸን ፈንገስ፣ በተለያዩ የማህጸን አለርጂዎች፣ ተጠቅተው ይመጡ እንደነበር አስታውሰዋል።
ወደ ሆስፒታሉ የሚመጡት ሴቶች የንጽሕና መጠበቂያ ማግኘት አይችሉም። በዚህም ሳቢያ ንጹሕ ያልሆነ ስፖንጅ (ስፖንጅ ከተገኘ ነው) በኩበት፤ በአፈር ይጠቀማሉ። መንግሥትና የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ በዚህ ጉዳይ ላይ ተገቢውን ትኩረት መስጠት አለባቸው። ምክንያቱም ሴት ልጅ ሀገር ናት በአንድ አገር ላይ የሴት ልጅ ድርሻ በጣም ጉልህ ነው። ነገር ግን እንክብካቤ ቀርቶ፣ ይህንን የተፈጥሮ ግዴታዋን እንኳን መቋቋም የምትችልበት ነገር ሊመቻችላት ይገባል ብለዋል።
ዶ/ር ኤልሳ አክለውም ወደ ቤተሰቤ አዲስ አበባ በምመጣበት ወቅት የራሴን እንዲሁም ከተለያዩ ሰዎችና ድርጅቶች የሰበሰብኩትን ንጽህና መጠበቂያ ሞዴስ ይዤ ነበር የምመለሰው። ሁሉን ማዳረስ የማይቻል ቢሆንም ወስጄ ለሴት ተማሪዎች ነበር የማከፋፍላቸው። ይሄ ዘላቂ መፍትሔ እንዳልሆነ ባውቅም፣ ጉዳዩ በጣም ያሳስበኝና ያስጨንቀኝ ስለነበር ለጥቂት ግዜ የሚሆናቸውን ይዤላቸው እሄድ ነበር። ከዛ አካባቢ ሥራ ከለቀቅኩ በኋላም ቢሆን ለተወሰነ ግዜ ያህል ከዚህም፣ ከሀገር ውጪ ያሉ ሰዎችም ጭምር እንዲያግዙኝ በማድረግ እያሰባሰብኩ እልክላቸው ነበር። ከዛ በኋላ ግን ከአቅሜ በላይ በመሆኑ ምንም ማድረግ አልቻልኩም ሲሉ ዶ/ር ኤልሳ ባዘነ መንፈስ ውስጥ ሆነው አጫውተውኛል።
በእርግጥም ጉዳዩ በጣም የሚያሳዝን ነው። እነዚህ በገጠር ያሉ ሴቶች እንዴት ጠንካሮች ናቸው ስል አሰብኩ። በከተማ ያለን ሴቶች እንኳን ነገሮች ተመቻችተውልን፣ ቢወደድም የንጽሕና መጠበቂያውን እያገኘን በተፈጥሯዊ ሕመሙ ምክንያት፣ ምን ያህል ከባድ ጊዜ እንደምናሳልፍ አውቃለሁ። የወር አበባ በባህሪው የራሱ ሕመሞች አሉት ራስ ምታት፣ የሆድ ቁርጠት የተለያዩ እንደዚሕ ናቸው ተብለው ሊገለጹ የማይችሉ ስሜቶች አሉት። ታዲያ እነዚህ ሴቶች በዚህ ሕመምና ባልተመቸ ሁኔታ ውስጥ ሆነው፣ የሚያሳልፉትን ስቃይ ማሰቡ በራሱ ከበደኝ። ይህን ጉዳይ ለመረዳት ከወንድ ይልቅ ለሴት ይቀላልና የሴቶች ጉዳይ እና ከሴቶች ጋር በተያያዘ የሚሠሩ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ አካላት በአንክሮ ሊመለከቱትና ችግሩን መፍታት ለሚችለውም አካልም ትኩረት እንዲሰጠው የማድረጉን ኃላፊነት በአግባቡ መወጣት አለባቸው።
አሁን ደግሞ ዋጋው፣ አይደለም በገጠር ያሉት በከተማ ያሉ እህቶች እንኳን መግዛት የማይችሉበት ደረጃ ላይ ደርሷል። በምኖርበት አካባቢ የአትክልት ችርቻሮ በመሸጥ የምትተዳደርን አንዲት እህት ስለ ጉዳዩ ስጠይቃት የነገረችኝን ላካፍላችሁ። ሞዴስ ገዝቼ መጠቀም አቁሜያለሁ። ዋጋው ከእኔ አቅም በላይ ነው። እኔ ደግሞ አንድ እሽግ ብቻ አይበቃኝም ሁለት እሽግ ነው የምጠቀመው። ይህን ለመግዛት ደግሞ አሁን ካለው የኑሮ ውድነት ጋር አቅሜ አይፈቅድም። በመሆኑም ጨርቅ እያጠብኩ መጠቀምን እንደ አማራጭ ወስጄዋለሁ አለችኝ።
በገጠር ካሉ ባእድ ነገር ከሚጠቀሙት በአንጻራዊነት ይሻላል። እሷ ሳሙና እና ውሃ የማግኘት እድል ስላላት፣ የሚመከር ባይሆንም ኩበትና ቃጫ ከመጠቀም ይሻላልና ጨርቅ እያጠበች መጠቀምን አማራጭ አደረገች። ውሃና ሳሙና በበቂ ሁኔታ ማግኘት የማይችሉትስ አማራጫቸው ምንድነው?። ሌሎችም ያነጋገርኳቸው ሴት እህቶች የዋጋው በዚህ ደረጃ መጨመር እንዳስመረራቸው ነገር ግን ግዴታ ስለሆነ እያዘኑም ቢሆን እንደሚገዙ ነግረውኛል።
ከዓመታት በፊት በትግራይ ክልል እያጠቡ ለመጠቀም የሚያስችል የንጽህና መጠበቂያ ሞዴስ የፈጠራ ሥራ የሠራች ሴት ነበረች። ይህም ሌላ የተሻለ አማራጭ ነው። ንጽሕና መጠበቂያው አንድ ጊዜ ገዝተው ለረጅም ጊዜ እያጠቡ በመጠቀም በየወሩ ከሚወጣ ወጪ ሴቶችን የሚገላግል የፈጠራ ሥራ ነበር። ወደተለያዩ አካባቢዎች የመድረስ እድል ባያገኝም። ነገር ግን ሞዴሱን ለመሥራት የሚያስፈልግ ጥሬ እቃ አቅርቦት እጥረት እንዲሁም፣ ምርትን ለማምረት በሚደረገው ሂደት ውስጥ የሚያስፈልጉ ማቴሪያሎች አለማግኘት፣ የካፒታል እጥረት፣ የቦታ ማጣት፣ ምርትን ለማከፋፈል አመቺ ሁኔታ አለመኖር፣ የመሳሰሉ ችግሮች ቢኖሩበትም የተወሰነ ምርት በማምረት ማሳያውን የተወሰነ ቦታ ለማቅረብ የተሞከረበት አጋጣሚ ነበር። ምርቱም በጣም ተፈላጊ ሆኖ ነበር። ነገር ግን ከላይ በጠቀስኳቸው ምክንያቶች እና የሚያግዝ አካልም በማጣት ማምረት መቀጠል አልተቻለም። እነዚህን ነገሮች ማመቻቸትና ምርቱን የማስቀጠል ሥራ ቢሠራ ኖሮ በተወሰነ መልኩ ችግሩን ማቃለል ይቻል ነበር።
ሴት ልጅ ሀገር ናት በሀገር ግንባታ ውስጥ የሴት ልጅ አበርክቶ ትልቅ ነው። አገር ከቤተሰብ ይጀምራል በአንድ ቤተሰብ ውስጥ ደግሞ ቤተሰቡን በማቆም ዙሪያ የሴቷ ሚና እጅግ የጎላ ነው። ጠንካራ ሀገር እንዲኖረን ጠንካራ ቤተሰብ መገንባት አለብን። ጠንካራ ቤተሰብ ለመመሥረት ደግሞ በሁሉም ዙሪያ ጠንካራ ሴት ታስፈልገናለች። ታዲያ ይህቺ ሴት የቤተሰቧ ምሰሶ ሆና እያለ በተፈጥሮ የሚሰጣትን ስጦታ፤ መሠረታዊ ነገሯን መቋቋም የምትችልበት ነገር ማግኘት የተአምር ያህል እንዴት ሩቅ ይሆንባታል።
በመጨረሻም የጉዳዩ ባለቤት እንደሆነችና በጣም እንደሚሰማት አንዲት እንስት ቢደረግ የሚል ሃሳቤን አቅርቤ ልደምድም። እንደ መንግሥትና ባለድርሻ አካላት የጉዳዩን ክብደት ሊገነዘቡት ይገባል ። የሴቶች የንጽሕና መጠበቂያ ሞዴስ ምርቶች ላይ ያለ ታክስ ሊነሳ ይገባዋል። ይህ የተፈጥሮ ግዴታ ነው እንደ መብላት፣ እንደ መጠጣት ለሴት ልጅ ግዴታ ተደርጎ ከፈጣሪ የተሰጣት ነው። ሰላም!
በአክበረት ታደለ
አዲስ ዘመን ሰኔ 28 /2014