
አዲስ አበባ፡- በምክክር መድረኩ የሚሳተፉ ሁሉ እኔ ምን አተርፋለሁ ሳይሆን ኢትዮጵያ ምን ታተርፋለች፤ ልጆቻችንስ ምን ያተርፋሉ፤ የሚለውን ይዘው ወደአውዱ መምጣት እንደሚገባቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ አሳሰቡ።
የአገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ አባላት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር ትናንት ውይይት አድርገዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ፤ በውይይቱ ላይ እንደገለጹት፤ የአገራዊ ምክክሩ ለልጆቻችን የሚተርፍ ውጤት ያመጣል ተብሎ ይጠበቃል።
በአገራዊ ምክክሩ በአካታችነት እንዲከናወን መንግሥት የበኩሉን ጥረት አድርጓል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የምክክሩ መሳካት በይበልጥ ለቀጣዩ ትውልድ በጎ ነገር የሚያመጣ እንደሚሆን ይታመናል ሲሉ ተናግረዋል።
መንግሥት በኮሚሽኑ ሥራ ጣልቃ የመግባት ምንም ዓይነት ፍላጎት የለውም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ፤ ይልቁንም ለአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ሥራ መሳካት አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።
በነፃነት እንዲከናወን የሚፈለገው የምክክር መድረኩ እንዲሳካ የኮሚሽኑ አባላት ትልቅ አገራዊ ኃላፊነት እንዳለባቸውም ጠቁመዋል። በዚህ ረገድ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በኩል ከሕዝብ ተመርጠው የመጡ በመሆናቸው ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ይወጣሉ ተብሎ ዕምነት ተጥሎባቸዋል ሲሉም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ውስጥ የመጣውን ሁሉ መውቀስ በመለመዱ የወሰንና ማንነት እንዲሁም የዕርቀ-ሰላም ኮሚሽኖች ሥራ አለመሳካቱን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውሰው፤ ኮሚሽኖቹ ያልተሳኩት ሰዎቹ ጥሩ ስላልሆኑ ሳይሆን ተባባሪ ከመሆን ይልቅ የሚጠላለፍና እንቅፋት የሚፈጥር በመብዛቱ ነው ብለዋል። በመሆኑም የምክክር ኮሚሽኑ ሥራ እንዲሳካ ሁሉም ተባባሪ መሆን ይገባዋል ሲሉ አሳስበዋል።
ኮሚሽኑም ከቀድሞዎቹ የእርቀሰላምና የወሰንና ማንነት ኮሚሽኖች ልምድ በመውሰድ ለውጤታማነቱ ይበልጥ ጥረት እንዲያደርግ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ በበኩላቸው፤ የምክክር ኮሚሽኑ የቅድመ ዝግጅት ሥራውን አጠናቆ የዝግጅት ምዕራፍ ላይ መሆኑን አሳውቀዋል።
አገራዊ ምክክሩ የቅድመ-ዝግጅት፣ የዝግጅት፣ የዋናው ምክክር እንዲሁም የትግበራና ክትትል የሚሉ አራት ምዕራፎች እንዳሉት አስታውሰው፤ በዝግጅት ምዕራፉ ለሥራ የሚያስፈልገውን በጀትና ስትራቴጂክ ዕቅድ ዝግጅት አጠናቆ በቅርቡ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለማጸደቅ ጥረት እንደሚደረግ ገልጸዋል።
ባለፉት አራት ወራት በርካታ የቅድመ ዝግጅትና የዝግጅት ሥራዎች መከናወናቸውን ጠቁመው፤ የምክክር ሂደት ፍኖተ ካርታን የማዘጋጀት፣ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን እንዲሁም የምክክሩ ውጤቱን ትግበራ የሚከታተሉ ዘርፎች የማቋቋም ሥራ መከናወኑን አስረድተዋል።
ኮሚሽኑ እስካሁን ከ40 የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ውይይት ማድረጉን ገልጸው፤ በተጨማሪ 13 ፓርቲዎች ጋር በተናጠል ስለ ኮሚሽኑ የሥራ ሂደት ውይይት እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
እንደ ኮሚሽነሩ ገለጻ፤ ኮሚሽኑ ከአምስት ክልሎችና ከአንድ የከተማ መስተዳድር ካቢኔዎችና ኗሪዎች ጋር ውይይት አድርጓል። በዚህም ፓርቲዎችም ሆኑ የክልል ተወካዮች ከኮሚሽኑ ጋር በጋራ ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ኮሚሽኑ በቀጣይም በክልልና በዞን ደረጃዎች ቢሮ ለመክፈት ውጥን እንዳለው ጠቁመው፤ ቢሮዎቹን ሲከፍት ግን የዩኒቨርሲቲዎችንና የሌሎች ተባባሪ ተቋማትን ቢሮ ሊጠቀም እንደሚችል ጠቁመዋል።
የኮሚሽኑ የዝግጅት ምዕራፍ በጥንቃቄ እየተከናወነ መሆኑን በመግለጽ፤ የዝግጅት ምዕራፉ ሲጠናቀቅ የሚጠበቀው የምክክር መድረክ እንደሚከናወን አስረድተዋል።
በዚህም በ2018 ዓ.ም በማያግባቡን ጉዳዮች ላይ ብሔራዊ መግባባት ላይ ደርሰን ለኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ሥርዓት መሠረት እንጥላለን ተብሎ ይጠበቃል ሲሉ ፕሮፌሰር መስፍን ተናግረዋል።
ጌትነት ተስፋማርያም
አዲስ ዘመን ሰኔ 28 /2014