
አዲስ አበባ፡- ደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ በተመደበበት የ‹‹ተግባር ተኮር›› ዘርፍ ለአገር ከፍተኛ አበርክቶ ያላቸውን የጥናትና ምርምር ስራዎች እያከናወነ መሆኑን አስታወቀ፡፡
የደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ንጉስ ታደሰ በተለይ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ በጥናት ተለይቶ የተግባር ተኮር ዩኒቨርሲቲ መሆኑ በተወሰኑ የትምህርት ዘርፎች አተኩሮ ጥናትና ምርምር በማካሄድ ውጤታማ ስራ እየሰራ ነው፡፡ እንደ ዶክተር ንጉስ ገለጻ፤ ከዚህ በፊት በሁሉም ዘርፍ ምርምር ይደረጋል፤ ነገር ግን የሰው ኃይልና የገንዘብ እጥረት የሚገጥም በመሆኑ ከመነካካት ያለፈ ውጤት አይመጣም፡፡
ዩኒቨርሲቲው ተግባር ተኮር መሆኑን ተከትሎ የአካባቢውን ችግር ሊቀርፉ የሚችሉ ጥናትና ምርምሮችን በማካሄድ ለአገር የሚጠቅም ስራ እየሰራ ነው ያሉት ዶክተር ንጉስ፤ ሕብረተሰቡ እንዲፈቱለት የፈልጋቸውን ችግሮች በመለየት በጥናት ተደገፈ መፍትሔ እንድንሰጥ አስችሎናል ብለዋል፡፡
እንደ ዶክተር ንጉስ ገለጻ፤ ከማሕበረሰቡ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸው ከጤና፣ ከግብርና፣ ከኢንጂነሪንግና ቴክኖሎጂ ጋር የተገናኙ ጥናቶች በስፋት እያካሄድን ነው ያሉት ዶክተር ንጉስ፤ በጤናው ዘርፍ ሕብረተሰቡ ጋር ያለውን እውቀት በመዘናዊ አሰራር በመደገፍ ተደራሽነቱ አንዲሰፋና የእውቀት ሽግግር እንዲኖር በትኩረት እየተሰራ ነው።
ተግባር ተኮር መሆናችን ከዚህ ቀደም እንደነበረው በብዙ የትምህርት መስክ ጥናት ለማድረግ ከመሞከር በተወሰኑ የትምህርት መስኮች ላይ በትኩረት በመስራት ውጤት ለማምጣት እየረዳን ነው ያሉት ዶክተር ንጉስ፤ እንዲሁም ያለንን ውስን የሰው ኃይልና የገንዘብ ሀብታችንን በሥርዓት ለመጠቀም ከፍተኛ እድል እንደፈጠረላቸው ገልጸዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው የተግባር ተኮር የተባለው አካባቢውና ዓለም አቀፍ ጠቀሜታው ታይቶ ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ በሰሜን ሸዋ ዞን ከፍተኛ የሆነ የኢንቨስትመንት አቅም በመኖሩ በኢንጂነሪን ዘርፍ ከፍተኛ ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
የሚሰጡ ትምህርቶችንም ከ ኢ ን ቨ ስ ት መ ን ት ና ከኢንዱስትሪ ጋር አስተሳስረን የተግባር ትምህርት ለተማሪዎች በመስጠት በተለያዩ መስኮች ኢንቨስት የሚያደርጉ ባለሀብቶችም ተጠቃሚ እየሆኑ ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ ዩኒቨርሲቲው በተግባር ተኮር ዘርፍ ከተመደበ ጊዜ ጀምሮ የአካባቢውን አቅም በጥናትና ምርምር ለይቶ በማጉላት ሕብረተሰቡን ይበልጥ ተጠቃሚ የሚያደርጉ ስራዎችን እንዲሰራ አስችሎታል ብለዋል፡፡
እንደ ፕሬዚዳንቱ ገለጻ፤ ተማሪዎች ተመርቀው ወደ ኢንዱስትሪዎች በሚቀላቀሉበት ጊዜ በቀጥታ ወደ ስራ እንዲገቡ የሚያስችል የተግባር እውቀት እንዲኖራቸው እየተደረገ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ተማሪዎች በተግባር የበለጸጉና ልምድ ያላቸው ሆነው
እንዲወጡ በማድረግ ወደ ስራ ዓለም ሲቀላቀሉ ችግር የሚቀርፉና በራሳቸው መስራት የሚችሉ እንዲሆኑ አስፈላጊው የተግባር ትምህርት እየተሰጠ መሆኑንና አካባቢው የኢንዱስትሪ መንደር በመሆኑ መማር ማስተማሩ ተግባር ተኮር እንዲሆን በዋናነት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ሞገስ ጸጋዬ
አዲስ ዘመን ሰኔ 27/2014