መቼም ማህበራዊ ሚዲያ የማያሳየው ጉድ የለም። ለብዙዎች የነጻ ንግግር መብታቸው እንዲከበር ያደረገውን ያህል በዚያኑ ልክ የብዙዎቹ ድብቅ አሉታዊ ባህሪ ጎልቶ እንዲወጣም አድርጓል። ከሁሉ በላይ ግን ጎልቶ እንዲወጣ ያደረገው በሁላችንም ውስጥ የተደበቀውን የአምባገነንነት ባህሪ ነው። ይህን ያልኩት ያለ ምክንያት አይደለም። የሰሞኑን የማህበራዊ ሚዲያ ውይይታችንን አስተውዬ ነው።
ሁላችንም እንደሰማነው አርቲስት አቤል ሙሉጌታ አዲስ ነጠላ ዜማ አውጥቷል። የሙዚቃውን ይዘት አልተነትንም። ነገር ግን ሙዚቃው በዩቱብ ከተለቀቀ በኋላ ከስር ስለሙዚቃው የተሰጡ አስተያየቶችን ያየ ሰው መደንገጡ የማይቀር ነው። ህዝባችን ይሳደበዋል አይገልጸውም። የስድቡ እና የእርግማኑ አይነት እጅን በአፍ ያስጭናል። ልብ አድርጉ መቃወም መብት ነው። በመቃወም እና በመሳደብ መካከል ግን ሰፊ ልዩነት አለ። የብዙዎች ተቃውሞ ሳይሆን ስድብ ነው። ስድቡ ደግሞ አጸያፊ ከመሆኑ የተነሳ ይሄ ስድብ ሀይማኖተኛ ነው ከሚባል ህዝብ የሚወጣ አይመስልም። ያሳፍራል። የበለጠ አሳፋሪው ነገር ደግሞ ድምጻዊውን ሆን ብሎ ለመጉዳት ከዚህ ዓለም በሞት የተለየች ባለቤቱን ታሪክ በስድብነት ሲጠቀሙ መስማት ነው። ይህ ጸያፍ ነው። ይህ ነውር ነው። ይህ ክብረ ነክ ነው።
የሚገርመው ነገር ህዝባችን ስለ ነጻነት ሀሳብን መግለጽ ሲሟገት በጣም ሀይለኛ ነው። ሁሌም መንግስትን የሚተቸው በዚህ ነው። እገሌ ብእር ብቻ ነው የያዘው ፤ ብእር የያዘን ሰው ማሰር ፍርሀት ነው ምናምን ይልሀል። ነገር ግን የመናገር ነጻነትን በመቀማት ከመንግስት ይልቅ ማህበረሰቡ ራሱ ይቀድማል። ሁሉም ሰው የመናገር ነጻነት መከበር አለበት ብሎ የሚያምነው እሱ ሲናገር ወይም እሱ ሊናገር የፈለገውን ሌላ ሰው ሲናገርለት ነው። ከዚያ ውጭ የመናገር ነጻነት እሱ መስማት ለማይፈልገውም ሀሳብ እንደሚሰራ አይገነዘብም ወይም ሆን ብሎ ይክዳል። ይሄ የማህበራዊ ሚዲያ እንቅስቃሴያችን ያጋለጠው ሀቅ ነው።
ዲሞክራሲ በባህሪው ከስር እየተገነባ የሚሄድ እንጂ ከላይ የሚሰጥ አይደለም። እኛ ግን ከቤታችን ያላሳደግነውን ዴሞክራሲ ነው ከመንግስት ቢሮ የምንፈልገው። ቤቱ እየተኮረኮመ ያደገ ሰው ቢሮ ሄዶ በነጻ ሀሳብ የሚያምን ይሆናል ማለት ዘበት ነው። ህዝብ እርስ በርሱ አንዱ ሌላውን በሀሳብ እየሞገተ ሲያድግ ዴሞክራሲ ያብባል አልያ ግን አንዱ ሌላውን እየጠለፈ እና እያሸማቀቀ የሚቀጥል ከሆነ ዴሞክራሲ እንኳን ሊያብብ እንዲያውም ለአምባገነን መንግስት መፈጠር በር ሊከፍት ይችላል።
እርግጥ እንደ ህዝብ ካሉብን ችግሮች መካከል እኛ ሊኖረን የሚገባውን ነገር በሙሉ ከመንግስት መጠበቅ አንዱ ነው። ለምሳሌ ያህል የትምህርት ጥራት እንዲሻሻል እንፈልጋለን። ነገር ግን የልጃችንን ደብተር ለማየት ፤ የቤት ስራ ለማሰራት ፤ ለማስጠናት ፍላጎት የለንም። የትምህርት ጥራት ግን የብዙ ነገር ድምር ውጤት ነው። ካላስጠናን ፤ የቤት ስራ ካላሰራን፤ አጋዥ መጽሀፍትን ካላቀረብን ፤ እንዳይርባቸው ካላደረግን ፤ አእምሯቸው ትምህርት ላይ ብቻ እንዲያተኩር ካላገዝን ፤ ውሏቸውን ካልተከታተልን ልጆች ትምህርት ቤት ውስጥ ብቻ በሚደረግ ስራ ውጤታማ ሊሆኑ አይችሉም። ያን ሳናደርግ ግን ስለ ትምህርት ጥራት ብናወራ ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ የሚለው ተረት በኛ ላይ ይፈጸማል።
ሁላችንም ፍትህ እንዲሰፍን እንፈልጋለን። ፍርድ ቤት እኛ በምናውቃቸው ሰዎች ላይ የሚወስነውን እያንዳንዱን ውሳኔ እንከታተላለን ፤ የፖሊስን ችግር እንነቅሳለን ፤ አቃቤ ህግ ብዙ ችግር እንዳለበት እንዘረዝራለን። እኛ ያለ ጥፋታቸው ታስረዋል ለምንላቸው ሰዎች እንዲህ ስንሟገት ላየን ሰው ስለ ፍትህ ያለን ተቆርቋሪነት በጣም ከፍተኛ ሊመስለው ይችላል። ነገር ግን በዚያው ልክ ባለስልጣን ዘመድ ካለን ተማምነን ኢ ፍትሀዊ ነገር ስናደርግ ቀዳሚዎቹ እኛ ነን። ለፖሊስ እና ለአቃቤ ህግ ጉቦ ሰጥተን ክስ ስናዘጋም ማንም አይበልጠንም። ሌላም ሌላም። እኛ በግላችን ጉዳይ የማናደርገውን ነገር መንግስት ግን ወንጀል ፈጽመዋል በሚላቸው ሰዎች ላይ እንዲፈጽም እንጠብቃለን።
ወደ ቀደመው ጉዳይ እንመለስና አሁንም ስለ አቤል ሙዚቃ እና ስለ ዴሞክራሲ እናውራ። በመሰረቱ ለአንድ ድምጻዊ ምን መዝፈን እንዳለበት መወሰን ያለበት ማነው? ራሱ ድምጻዊው ብቻ አይደለምን፣ መሆን ያለበትም እንደዛ ነው። ድምጻዊው ያሰኘውን ይዘፍናል ፤ ህዝብ የሚጥመውን መርጦ ይሰማል። ድምጻዊው ምን መዝፈን እንዳለበት ማንም ሊነግረው አይገባም ፤ ህዝብም ምን ማድመጥ እንዳለበት ሊወሰንለት አይገባም። ድምጻዊም ምን መዝፈን እንዳለበት እና መቼ መዝፈን እንዳለበት እንወስን ካልን ግን ወደ ሳንሱር ዘመን ተመለስን ማለት ነው። ለመሆኑ አቤል በዘፈነው ሙዚቃ ላይ መንግስት አልጣመኝም ብሎ በቁጣ የተሞላ መግለጫ ቢያወጣ ተቀባይነት አለው የለውም?። ልክ እንደዛው የብዙዎቻችን ስድቦችም ተቀባይነት የላቸውም።
ደግሞ በጣም አስነዋሪ ነገር አንድን ሰው ለሰራው ስራ ቤተሰቡን አብሮ የመውቀስ አዲስ ባህል ነው። ይህ በጣም አስነዋሪ ነው። ልጅን በአባቱ ጥፋት መውቀስ ፤ ሚስትን በባሏ ጉዳይ መተቸት ፤ እህትን በወንድሟ ጉዳይ ማንጓጠጥ በጣም ጸያፍ ልማድ ነው። ይሄ ኢትዮጵያዊ ባህሪ አይደለም። እንኳን በዚህ ዓለም በህይወት የሌለችን ሴት ቀርቶ በህይወት ያለችውንም ቢሆን እሷ በሌለችበት ባላረገችው ጉዳይ ስሟን ማንሳት አስነዋሪ ባህሪ ነው። በአቤል ሙዚቃ ጉዳይ ባለቤቱን ማንሳት የህሊና ቢስነት መገለጫ ነው።
ልብ አርጉ ፤ የምንከራከረው ስለ አቤል ሙሉጌታ አይደለም። የምንከራከረው በህዝብ ደራጃ እያዳበርነው ስለመጣነው አምባገነንነት ነው። ይህ አዲስ ባህል አደገኛ ነው። አምባገነን ህዝብ ዴሞክራሲያዊ መንግስት አይኖረውም። በፌስቡክ ላይ የሌለውን ዴሞክራሲያዊ ውይይት በምክር ቤት ልናገኘው አንችልም። የሰሞኑ ጫጫታ ያመላከተው ነገር ቢኖር ግን እኛ ራሳችን በነጻነት ሀሳብን የመግለጽ መብትን እያፈንን መንግስት ግን እንዲያከብር እና እንዲያስከብር እንደምንፈልግ ነው።
አቤል ገ/ኪዳን
አዲስ ዘመን ሰኔ 27 /2014