ንግግሯን እየቀደመ የሚፈሰው ዕንባ በጉንጮቿ ለመውረድ አፍታ አይጠብቅም። ገና ማውራት ስትጀምር ከልብ ይከፋታል። የሚተናነቃትን ሳግ እንደምንም ይዛ መናገር ትጀምራለች። አይሆንላትም። ብዙ ሳትቆይ ፊቷ በዕንባ ይሸፈናል። ብሶት ከብቸኝነት ተዳምሮ ሆደባሻ አድርጓታል። በትካዜ ምርኩዟን ተደግፋ ከቤቷ ደጃፍ ትውላለች። ደጋግማ እያለቀሰች። ዕንባዋን በልብሷ እያበሰች።
ነበርን በነበር …
የልጅነት ዓለሟን በለምለሙ መስክ እየቦረቀች፣በእንሰት ተክሎች ስር እየተጫወተች አሳልፋለች። አምረው ከተሰሩት ጎጆዎች ማልደው የሚወጡት ባልንጀሮቿ የወላጆቻቸውን ትዕዛዝ ይፈጽማሉ። እሷም ብትሆን እንደነሱ ናት። ቤቶቿ ያሏትን ትፈጽማለች፣ የታዘዘችውን ትከውናለች።
ደጁ በርታ የጉራጌ ምድር ያበቀለቻት የ‹‹እንድብር›› ፍሬ ነች። እንድብር ለእሷ የልጅነት ማስታወሻዋ ፣የማንነቷ መሰረት ናት። የ‹‹አቁባር›› ቀበሌና የደጁ ቁርኝት ከውልደቷ ይጀምራል። በዚህች ቀበሌ እሷና ቤተሰቦቿ ክፉ ደጉን አልፈዋል። ደስታን ከመከራ ተጋርተዋል።
የደጁ ቤተሰቦች የእንድብር መሬት ካፈራው በረከት ጋር ዓመታትን ዘልቀዋል። ቡናውን በቅቤ፣ ቆጮውን በአይቤ፣ ቡላውን በወተት ሲሉ መኖራቸው ብርቅ አይደለም። እንድብር በሙሉ እጇ ካኖረችላቸው በረከቶች መቋደስ ለእነሱና ለአካባቢው ነዋሪ የተለመደ ነው። መሬቱ የሰጡትን ያፈራል። የዘሩትን ያሳቅፋል።
በእንድብርና ዙሪያው ያሉ አንዳንዶች ህይወታቸው በገጠር ብቻ አይደለም። አለፍ ብለው ከተማ ይዘልቃሉ። መንገዳቸው የዕለት እንጀራ አያሳጣቸውም። ባሉበት ሰርተው የእጃቸውን ይዘው ይመለሳሉ። ወጣቶቹ ወደፊት ለሚቀልሱት ጎጆ ጥሪት መያዝ፣ገንዘብ መቁጠር ይለምዳሉ። ገጠር ሲመለሱ ለሙሽራቸው ልብስና ጌጥ ያተረፋሉ። ትዳር መስርተው ቤት አሙቀው ከተማ ይመለሳሉ። የእነሱ ህይወት በገጠርና ከተማ ተወስኗል። ከተማ እንጀራ አላቸው። ገጠር ደግሞ ሰፊ ህይወት።
የደጁ እናት ገጠር ሆነው ብዙ አሰቡ። ልጃቸው በዕድሜዋ ገና ልጅ ናት። ያም ሆኖ ለስራ አትሰንፍም። ከተማ ዘልቃ በጉልበቷ ብታድር ለእሷና ለእሳቸው ትጠቅማለች። እናት ለቀናት ከራሳቸው የመከሩትን ጉዳይ ጊዜ ወስደው አሰቡበት። ልክ ነበሩ። አዎ! ትንሽዋ ደጁ አዲስ አበባ ሄዳ ስራ መጀመር አለባት።
ደጁ በአዲስ አበባ ..
የእንድብሯ ደጁ ከአቁባር ሸገር ከገባች ቀናት አልፈዋል። ልጅቷ የከተማው ውበት አስደንቋታል።በእሷ ምድር የማታውቀውን ለውጥ እያስተዋለች መገረም ይዛለች። አዲስ አበባና ደጁ መላመድ እንደጀመሩ ለእሷ ይበጃል የተባለ ስራ መገኘቱን ሰማች።
አሁን ደጁ በጉልበቷ ድካም፣ በላቧ ወዝ የምታድርበት ጊዜ ደርሷል። የሰው ቤት ስራ ተገኝቶላት ተቀጥራለች። በልጅነት አቅሟ የታዘዘችውን እየፈጸመች፣ ደመወዝ ማግኘቷ አስደስቷታል። ስራው ቢከብዳትም አልከፋትም። ወር ጠብቃ የሚሰጣት ገንዘብ ተስፋዋን አለምልሟል። ከገጠር ወጥታ ከተማ መግባቷን ወዳዋለች።
ጥቂት ቆይቶ የደጁ እናት ገጠርን ትተው አዲስ አበባ ገቡ። ይህኔ ብቸኛዋ ደጁ ደስታዋ ጨመረ። ከእንግዲህ ከእናቷ ጉያ አትወጣም። እሳቸውን በቅርብ ይዛ ያሻችውን ትሆናለች። በእናቷ ናፍቆት ለተቸገረችው ታዳጊ አጋጣሚው ቀላል አልሆነም። ጠቅልለው መምጣታቸው ፊቷን አፈካው፣ ነገዋን አደመቀው።
እናትና ልጅ አዲስ አበባ ላይ ናፍቆታቸውን ተወጡ። መለያየትን ዕርም ብለው ካንድ መሆን ሲጀምሩ ደስታቸው ጨመረ።መተሳሰባቸው ከዓይን ገባ። ደጁ እንደጫጩት ወፍ ከስራቸው ገብታ ‹‹እናቴ›› አለቻቸው። እሳቸውም ዓይኗን በስስት እያዩ ‹‹ልጄ ›› ሲሉ ደጋገሙ።
አዲስ አበባ እንደአገርቤት አይደለም። ከጓሮ እሸት አይቆርጡበትም፣ ከማጀት ወተት አይቀዱበትም። የራስ መተዳደሪያ የግል ገቢ ያስፈልጋል። እናትና ልጅ ይህ አልጠፋቸውም። ኑሯቸውን ለመምራት ቤት ተከራይተው ስራን ፈጠሩ። እናት ገበያውን በቆጮ ንግድ ለመዱት። ለደንበኞች ከንጹህ እየመረጡ፣ ጥራት ካለው፣ እያመጡ መሸጥ ጀመሩ። ታማኝነታቸውን ያዩ፣ የእጃቸውን ሲሳይ የለመዱ አጥብቀው ፈለጓቸው።
በንግዱ ወዳጅ ዘመድ ያፈሩት እናት በቆጮ ገበያ ኑሮን ሲገፉ ትንሸዋ ደጁ ቁጭ አላለችም። ከገብስ፣ ከሽንብራና ሱፍ የተዘነቀ ቆሎ በዕንቅብ ይዛ መዞር ጀመረች። ልጅነቷን ያዩ ጥቂቶች ከቆሎዋ እየገዙ፣ ከሳንቲሙ እየሰጡ አበረቷት። ከእጇ የገባውን እየቆጠረች፣ ያተረፈችውን እየቋጠረች ለእናቷ መስጠት ልምዷ ሆነ።
ደጁና እናቷ ከአገር ቤት ርቀው አዲስ አበባ ከከተሙ ጊዜያት ተቆጠሩ።ሁለቱም ስለነገ ያልማሉ። እንደሌሎች ከበረቱ የማይለወጡበት ምክንያት የለም። ስራ ልምዳቸው ከሆነ ኑሯቸው ይቀየራል። ሕይወታቸው ይሻሻላል። በላባቸው ወዝ የሚያድሩት እናትና ልጅ ማልደው ሲለያዩ መልካሙን እየተመኙ ነው። ዳግም ምሽቱን ሲገናኙ ናፍቆታቸው ይለያል። አንዳቸው ለሌላቸው የሚያሳዩት መተሳሰብ ከልብ ይመነጫል።
አንዳንዴ የደጁ እናት ጤና የላቸውም። ደርሶ የሚሰማቸው ህመም ከስራ እያስቀረ ከቤት ያውላቸዋል። ያም ሆኖ ጠንካራዋ ሴት እጅ አይሰጡም። ከበሽታቸው እየታገሉ ኑሯቸውን ይገፋሉ። ህይወታቸውን ይመራሉ። ለልጃቸው ከእሳቸው ሌላ ሰው የለም። እህት ወንድም ይሉትን የማታውቀው ደጁ ከእናቷ ውጭ የቀረበ ዘመድ አታውቅም።
የእናትና ልጁ የህይወት ትግል ቀጥሏል። በልጅነት ጉልበቷ የምትሮጠው ታዳጊ የአቅሟን እየሰራች ትገባለች። እናቷ ግን እንደሷ መሆን የቻሉ አይመስልም። ህመማቸው ብሷል።ከሚሰሩበት ይልቅ ካልጋ የሚውሉበት በርክቷል።
እናት የብቸኛ ልጃቸው ዕጣ ፈንታ ያሳስባቸዋል። እሷን ካገር ቤት አምጥተው ከተማ ማስገባታቸው ዛሬን እያሥጨነቃቸው ነው። ትንሽዋ ደጁ በየቀኑ የምታስተውለው የእናቷ ህመም ጤና ይነሳታል። ሁኔታቸውን እያየች ታስባለች። መዳናቸውን እየናፈቀች በተስፋ ታድራለች።
ስብራት…
በአንድ ማለዳ የተጀመረው ውሎ የደጁን የህይወት መንገድ ሊለውጥ ግድ አለ። ዛሬ ቆሎ ሻጯ ዕንቅቧን ይዛ ከቤት አልወጣችም። የትንሽዋን ልጅ ተስፋ ያጨለመው መርዶ ገና በጠዋቱ ተሰምቷል። ‹‹አለችኝ›› የምትላት እናቷ እስከመጨረሻው ትታት አሸልባለች። ደጁ ይህን እንዳወቀች ውስጧ ተሰብሯል። ቀኗ ጨልሟል። በማያባራ ለቅሶና ሰቀቀን አንገቷን ደፍታ ውላለች።
አሁን ብቸኛዋ ታዳጊ ከማንም ጋር አይደለችም። ዘመድ አዝማድ በሌለበት ህይወትን እንደቀድሞው መቀጠል ከብዷታል። እናቷን ከቀበረች ወዲህ ተስፋ ይሉትን አጥታለች።አሁን ሮጣ የምትመጣበት፣ ከፍታ የምትገባበት ቤት የላትም። ጠዋት ማታ በዕንባ ለምትውለው ትንሽ ልጅ ብዙዎች ውስጣቸው ተነክቷል። ከነዚህ መሀል ነገዋን በጎ ማድረግ የሻቱ ቀርበው አዋይተዋታል። ህይወቷ ብቸኝነት እንዳይውጠው ያሰቡም ካለችበት አውጥው ከእነሱ አኑረዋታል።
ኑሮን በትግል…
ደጁ እናቷን በሞት ካጣች ወዲህ ብርታት ጨምራ መሮጥ ይዛለች። ከእንግዲህ ማንም እንደሌላት አውቃ ራሷን ልትችል ግድ ሆኗል። እናት አባቷ እህት ወንድም አልሰጧትም። የቅርብ ወዳጅና ዘመድ የላትም። ከእዚህ በኋላ የራሷ ብርታት ራሷ ብቻ ነች። ብትወድቅ ፈጥኖ መነሳት፣ ብትታመም በርትታ መቆም ይኖርባታል።
አሁን ደጁ ዕድሜዋ መጨመር ይዟል። የሰውነቷ ለውጥ የመልኳ ፈገግታ ተመልካችን እየሳበ ነው። ይህን ተከትሎ ለትዳር የሚፈልጓት በርክተዋል። ደጁ ወጣትነቷ ከብቸኝነት ተዛምዶ ያስጨንቃታል። ትዳር ብትይዝ ሁሉን እንደምትረሳ ታውቃለች። ‹‹ይቅር›› ብትል ደግሞ ህይወቷ የብቻ ድካም መሆኑ ይገባታል። ደጁ የወጣትነት ስሜ እየፈተናት ብዙ ቆየች። ኮረዳነቷ እያበበ ቁንጅናዋ ሲደምቅ ከአንድ ውሳኔ ደረሰች። ዘወትር ከሚመኟት አጥብቀው ከሚሹዋት መሀል ለአንደኛው ልቧ ወደቀ።
የአገሯ ልጅ ፍቅር ውስጧን አሸፈተው። ሁለቱም ስሜታቸው አንድ ቢሆን ተግባቡ፣ ተዋደዱ። ጥቂት ቆይቶ ጓደኛዋ ደጁን ለትዳር ጠየቃት። አልተግደረደረችም።ያለፈችበትን ፈታኝ መንገድ፣ የከፈለችውን ከባድ ዋጋ አሰበች። ያለውን ልትሆን፣ በወደደው ልትጓዝ ፈቀደች።
ሙሽሪት ልመጂ…
አሁን ደጁ ገጠር ገብታለች። የእሱ ቤተሰቦች የልጃቸውን ሙሽሪት በክብር ተቀብለው የወጉን ከውነዋል። ደጁ ገጠር መግባቷ አላስከፋትም። ትዳር ይዛ ልጆች ወልዳ መኖር ፍላጎቷ ነው። የረሳችው የገጠር ህይወት በትዳር ሲጀመር ጎጆዋን ልታሞቅ የባሏ ሚስት ልትሆን ተዘጋጀች። ደጁ ውሰጧ በደስታ ተሞላ። ትናንት ያጣችውን ባዶነት አሁን በያዘችው የሞቀ ኑሮ ልትሞላ ተፍ ተፍ አለች። ወራትን በጫጉላው የዘለቀው አባወራዋ ተመልሶ አዲስ አበባ ሊሄድ ግድ ሆነ።
ሙሽሪት ደጁ ባሏን ለከተማ አስረክባ የገጠር ኑሮዋን ቀጠለች።ጥቂት ቆይቶ አባወራዋ ከእሱ እንደሚወስዳት ታውቃለች። ለነገው ህይወት ጥሪት መያዝ፣ ገንዘብ መቋጠር አለበት። ይህ እንዲሆን የእሱ ከእሷ መለየት አስፈላጊ ነበር።
ከሶስት ወራት በኋላ አባወራው ሚስቱን ሊወስድ ገጠር ተመለሰ። አሁን ጥንዶቹ አብረው ሊሆኑ ጊዜው ደርሷል። የከተማ ኑሮ አዲስ ላልሆነባት ደጁ አጋጣሚው መልካም ሆነ። ባልና ሚስቱ በአንድ ጣራ ስር ህይወትን መጋራት ኑሮን በወጉ መምራት ያዙ። የመጀመሪያዎቹ ጥቂት ወራት መተሳሰብ፣ መዋደድ የሞላባቸው ድንቅ ጊዚያት ሆኑ።
አዲስ ዓመል…
የደጁ ትዳር ንፋስ እየገባው ነው። አባወራዋ ጠባዩ መለወጥ ይዟል። በወጣ በገባ ቁጥር ሰበብ ፈልጎ ይጣላታል።መጠጥ በቀመሰ ጊዜ ዱላ ያነሳል፣ክፉ ይናገራል፣ሁሌም እያስቀየመ ያስለቅሳታል፣ እያስለቀሰ ይዝትባታል። ደጁ ውጭ እያደረ የሚገባው ባሏን መቋቋም አልሆነላትም። ሱስና ስካሩን ስትችል፣ ዱላና ዛቻው አቃታት።
የፋብሪካ ሰራተኛው ባሏ ጠባይ አልሆንላት ቢል ሽማግሌዎች ሰብስባ ‹‹ፍረዱኝ›› አለች። ባል ለጊዜው በቤተዘመዱ ምክርና ተግሳጽ የተመለሰ መሰለ። ጥቂት ቆይቶ ግን ክፉ አመሉ አገርሽቶ ከሚስቱ ተጋጨ። ደጁ ለኑሮዋ አንዳች የማይረዳት ባሏ ሁኔታ አላዋጣትም። የቻለችውን ያህል ታግላ ልትለየው ወሰነች። እሱም ቢሆን ከእሷ መዝለቅ አልፈለገም።እያመናጨቀ ከቤት አባረራት። የጥንዶቹ ትዳር ዕድሜው ቢያጥር በፍቺ ተደመደመ።
ህይወት እንደገና …
ደጁ ለጥቂት ጊዚያት የቆየችበት ትዳር ጣፋጭና መራራ ሆኖ አለፈ። አሁን እንደገና ህይወትን ልትቀጥል ጉዞ ጀምራለች። ኑሮዋን ለመግፋት የያዘችው አማራጭ ልባሽ ጨርቆችን መሸጥ ሆኗል። ከላይ ከታች በሩጫ የምትውለው የሰልባጅ ነጋዴ ደንበኞችን ለማፍራት፣ የተሻለ ገንዘብ ለመያዝ ትጥራለች። ልብሱን ሸጣ በምታገኘው ገንዘብ የቤት ኪራይ ከፍላ ቤቷን ታሟላለች።
ደጁ በብቸኝነት ህይወትን እየገፋች ነው። በቅርበት የምታገኛቸው እናት አባት፣ እህት ወንድም የሏትም። ስትባትል የምትውለው ሴት አካሏ በድካም ዝሎ ከቤት ትደርሳለች። አንዳንዴ ደግሞ ሰቅዞ የሚይዛት ከባድ ህመም ፈተና ሆኖ ከቤት ያውላታል። ሰርታ እንዳትበላ ሰበብ የሆነባት ህመም ከመንገድ እየጣለ ያሰቃያታል።
ህመሙ እየጸና አቅሟ ሲዳከም ሀኪም ዘንድ ደርሳ ተመረመረች።ሕክምናው ጥቂት ቆይቶ በሽታዋን አሳወቃት፡፤ደጁ ዓመታትን የዘለቀ ዕጢ በማኅፀኗ መኖሩ ታወቀ። ፈጥና መታከም ነበረባት። በቀዶጥገና ችግሯ ሊወገድ ከሆስፒታል አልጋ ያዘች። ህክምናው ተጀመረ። ሀኪሞቹ ሆዷን ከፍተው ዕጢው በበቂ ደረጃ እንዳልተገኘ አስረዷት። ለህመሟ እፎይታን አገኛለሁ ያለችው በሽተኛ ቁስሏን ይዛ ከቤቷ ገባች።ጥቂት አገግማም በቀድሞ ስራዋ መሮጥ ያዘች።
ውሎ አድሮ ጤና የነሳት ህመም ሰላም አልሰጣትም።ተመልሳ ለምርመራ ሆስፒታል ሄደች። ሀኪሞቹ ዕጢው እንዳደገ ነግረው ለቀዶ ጥገና ቀጠሮ ሰጧት። ይሄኔ ደጁ ‹‹እምቢኝ›› ስትል አሻፈረኝ አለች።ህመሟ እያሰቃያት፣ ድካም እያንገላታት ከኑሮ መጋፈጥ ቀጠለች።
አንዳንዴ ህመሙ ሲብስባት ሀኪም ዘንድ ለመሄድ ትነሳለች። መልሳ ህክምናው ሲያስፈራት ትቀራለች።ሁሉን ትታ ጸበል ለመግባት፣ ጸሎት ለመያዝ ውሳኔዋ ይሆናል።ደጁ የሀኪም እጅ ሳታይ፣ ሕክምናን ሳትሞክር አስራሁለት የስቃይ ዓመታትን ቆጠረች። እያደር የባሰባት ህመም ፊት አልሰጣትም።ስራዋ መሀል ከነሸክሟ እየጣለ፣ ከአልጋ እያሰነበተ ፈተናት።
አንድ ቀን…
ብቸኛዋ ደጁ ህይወቷን ለመምራት ኑሮዋን ለመግፋት ስትል የጀመረችውን ንግድ አልተወችም። ‹‹ይቅርብኝ›› ብትል አይዞሽ ባይ ረዳት የላትም። በየጊዜው የሚመላለስባት ህመም እየታገሳት አይደለም። አንድ ቀን ግን ነገሮች ከታሰቡት በላይ ሆኑ። ደጁ የምትሸጠውን ጓዝ እንደያዘች ከአስፓልት ዳር መዘረሯ ግድ ሆነ። የሚያውቋት ተረባርበው ሆስፒታል አደረሷት።
ሀኪሞች ሙሉ ምርመራ አድርገው የህመሟን አይነት ለዩ። በሽታው ዕጢ ሳይሆን ከባድ የነርቭ ችግር መሆኑንም ደረሱበት። ህክምናውን ለመቀጠል በእጇ አንዳች ገንዘብ የሌላት ሴት እውነቱን በሰማች ጊዜ በዕንባ ታጠበች። ለቅሶዋን ያዩ ልበ ደጋጎች ከጎኗ ሊሆኑ ቃል ገቡላት። የቅርብ ሀኪሟ ለእጇ ገንዘብ አስይዞ በመንፈስ አበረታት።
ወገብና እግሮቿን ክፉኛ ያሰራት ህመም እያዳከመ ከቤት ያውላት ይዟል። ጠዋት ማታ እናቷን እያሰበች፣ በብቸኝነቷ የምታነባው ደጁ ሆደባሻነቷ ቀጥሏል። ትናንት የምትሮጥበት አቅሟ በህመም ተፈትኖ ከቤት ሲያውላት ተስፋዋ ጨለመ። ዕቅዷ ሁሉ ከሰመ። የኔ ትለው ቤትና ንብረት የሌላት ህመምተኛ ጠዋት ማታ ለኪራይ ወጪ ተጨነቀች። ሮጥ ብላ የማታመጣው መሆኑ ሲገባት የሰው ፊት ማየቱ፣ ግራ አጋባት። ያዩዋት አዘኑላት፣ዕንባዋን ሊያብሱላት፣ ከጎረሱት ሊያቃምሷት ልባቸው ተከፈተ። ደጁ ግን ‹‹ብወድቅ የሚያነሳኝ፣ ብሞት የሚቀብረኝ የለም››ይሉት ሀሳብ ያዛት።
ደጁ ዛሬ…
እነሆ! ሰላሳ አምስት ዓመታት በዋዛ ተቆጥረዋል። እኛም እህል በረንዳ መሳለሚያ ወደሚባለው አካባቢ ዘልቀናል። ከአንድ ግቢ ገብተን ትንሽዋን ቤት ባንኳኳን ጊዜ ከውስጥ ደከም ያለና ሳል ያፈነው ድምጽ ተቀበለን። አንዲት አቅመደካማ ሴት ምርኩዟን ተደግፋ በሯን ልትከፍትልን ታገለች። የሚያንገዳግዳት የነርቭ ህመም በወጉ አላቆማትም። ደጁ በርታ መሆኗን አወቅን።
እንደምንም ታግላ ከወንበሩ አረፍ አለች።የተጎሳቆለ ፊት፣ዕንባ የሞላቸው ዓይኖች፣ እርዳታን የሚሹ እጆች በገሀድ ተጋፈጡን። ደጁ ገና እንዳየችኝ በትህትና ተርበተበተች። ትኩስ ዕንባዋ በጉንጮቿ ወረዱ። ዛሬ በትግል የከፈተችው ቤት በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ አራት አካባቢ የተሰጣት የቀበሌ ቤት ነው።ቤቱ አስቀድሞ የተጎሳቆለ ቢሆንም ዛሬ በበጎ ፈቃደኞች መልካምነት ተጠግኖ ምቹ እንዲሆን ተደርጓል። ደጁ የቤት ችግሯ ተቀርፏል። አሁን የምታለቅሰው ስለህመሟና ብቸኝነቷ ብቻ ነው።
ትናንት ለመኖር ያደረገችው ትግል ዛሬን ቆይቶ ባይከፍላትም ከነህመሟ ውላ ታድራለች። አሁንም ከጎኗ መልካም ልብ ያላቸው ‹‹አለንሽ›› ይሏታል። ከቀመሱት ዕህል ውሀ አይነፍጓትም። እሷም በሆነባት ብቻ ሳይሆን በሆነላት በጎነት ጭምር ፈጣሪዋን በምስጋና ታከብራለች። ነገን እያሰበች። ዛሬን እየኖረች።
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ሰኔ 25/2014