በሆነ ወቅት ላይ ኢትዮጵያን ከመሩ ጠቅላይ ሚኒስትሮች አንዱ አዲስ አበባ ሰው እጅግ በጣም እየተበራከተባት ፍልሰቱ በርክቶ ተጨናንቃለች፣ ኑሮም በዚሁ ምክንያት እጅግ ተወዶዋልና ይህን ችግር ለመፍታት ምን አስባችኋል? ተብሎ ተጠየቀ አሉ። እናም ለጥያቄው ምላሽ የሰጠው በማይገመት መልሱ ብዙ የሚነገርለት ጠቅላይ ሚንስትር ምን በማለት መለሰ መሰላችሁ። ተውት ኑሮ ከብዶት መልሶ እንዳመጣጡ መውጣቱ አይቀርም። የቻለ ይኖርባታል። ብሏል፤ አሉ። ጎበዝ እኔ አልሰማሁም አሉ ልብ አድርጉ።
ጎበዝ አሉ! እያልን የምንለው ግን እስከመቼ ነው? ለማንኛውም ወደ ወጌ ልመለስና፤ መሪው የተነበየው አልቀረም፤ እኔ ላይ ሆነ። መሀል አዲስ አበባ ኑሮ ከብዷቸው ወደ ዳር ጠጋ ካሉት እኔ አንዱ ሆኛለሁ። ጠዋትና ማታ ከስራ ወደቤት ከቤት ወደ ስራ የምመላለሰው ረጃጅም ሰልፎችን ተሰልፌ ብዙ ግፊያና መረጋገጥን ተካፍዬ በአውቶቡስ ነው።
በሳምንቱ መጀመሪያ ቀን ነው፤ አንደተለመደው ማልጄ ከቤት ወጣሁና በብዙ ትግል አውቶቡስ ተሳፈርኩ። የምጓዘው ረጅም ርቀት በመሆኑ አመቺ ሁኔታ ከተገኘ እዚያው አውቶቡስ ውስጥ ወንበር የማግኘቱን እድል ካገኘሁ ብዙውን ጊዜ ስልኬን በመጎርጎር አልያም በቁዘማ እጓዛለሁ።
በዚህ ቀን ግን መቀመጫ ወንበር ሳይሆን ደህና መቆሚያ እንኳን ማግኘት ቸግሮኝ ነበር። አንዱን ጥግ ይዤ እዳልወድቅ አጠገቤ ያገኘሁትን የወንበር ጠርዝ ይዤ መቆም ግድ አለኝ።
ከቆምኩበት አጠገብ ሁለት (እድሜያቸው ሀምሳዎቹ የተሻገሩ ይመስለኛል) ቆይቼ ከወሬያቸው አንደተረዳሁት ጓደኛሞች ናቸው፤ በመስኮት የሚያዩት እያነሱ ያወጋሉ። እኔም ጥሎብኝ የሰዎች ወሬ የተለየ ከሆነ አልያም ንግግራቸው አንዳች ነገር ያስገኝልኛል ካልኩ ጆሮዬን ጣል አደርጋለሁና ለእነዚህ ሁለት እናቶች ጆሮዬን አዋስኩ።
“ስንት ደረሰ? እንደው ተበድሬም በርከት አድርጌ ሳልገዛ ያሉት ሆኖ 2000 እንዳይገባ ሰጋሁ እኮ” ስለምን እንደሚያወሩ ቀጣዩን ከሌላኛዋ እናት የሰማሁት እንድገምት አደረገኝ። “አሁን እንደው ወጥ ላይ እያስፈራራን እንደ ቅመም ጠብ ካልሆነ መች እንችለዋለን። እኔም ተዘናግቼልሻለሁ አብሯደጌ፤ አሁን ሀምሌ ላይ ነው ከ1000 ወደ ሁለት ሺ ይገባል እያሉ ነው። ወይ ዘመን እንደው የዘይት ዋጋ ከወርቅ ጋር እኩል ሊሆን ነው” ወይ ይሄ አሉ ነገር ሁሉ አበላሸ። ምንም ተጨባጭ ነገር ሳይኖር ባሉ ተሸብረን ባሉ ኑሮን እራሳችን ላይ ሰቅለን በይሆናል መች ድረስ ነው ጎበዝ የምንዘልቀው።
እኔም መታዘቤን እነሱም ወርያቸውን በአሉ እያዋዙ ቀጥለዋል። ወጋቸው የሁላችንም ወቅታዊ መነጋገሪያ የሆነው ኑሮ ነው። ነገር ግን ምን ዋጋ አለው ማስረጃቸው ግምት መረጃቸው “አሉ” መሆኑ ነው እንድታዘባቸው፤ ጆሮዬን እነዚህ እናቶች ላይ እንዲተከል ያደረገው። ”ኑሮ በዚህ ከቀጠለ ም ሊውጠን ነው እታባ” አንዷ ጥያቄም አስተያየትም መሰል ሀረግ ሰነዘረች። ምን ዘይቱ ብቻ ጤፉም በእጥፍ ሊጨምር ነው አሉ፤ ፈረንጆቹ ጦርነት ላይ ስለሆኑ ጤፍም መምጣት አቁሟል አሉ፤ እንጃልን” ሲሉ ግራ ተጋባሁ።
ወገን ጤፍ ወደ ኢትዮጵያ ከመቼ ጀምሮ ነው የሚገባው? የፈረንጆቹ ጦርነት ላይ መሆን የሰሙት እናት እንዴት ጤፍ ኢትዮጵያዊ መሆኑ እዚሁ አገር እንደሚመረት ጠፋቸው። አይ እናት! ይሄን እርሳቸው እንዳሉት አይመጣም አሉ ሲባል ሰምተው መልሰው አሉ እያሉ ይሆናል።
እንደቀልድ የለመድነው ከእኛ ጋር የተጋባ ቃል ሆኗል ‹‹አሉ››። አብዝተን “አሉ” እያልን የምናወራው ወሬ ስለዚያ ጉዳይ ምንም መረጃ የሌለንና የማናውቅ ከሆነ ለምን አሉ ወይም ሲሉ ሰማሁ ብለን እናወራለን። ይህ አሉ ስንቱ ጋር ያልተባለ እንዳስባለ እንጃ። አንድ ጉዳይ አውርተን አውርተን አድማጫችን አሃ ብሎ በጉጉት ሲሰማን ይቆይና የአረፍተ ነገሩ ማሳረጊያ “አሉ” ብለን ማስረጃ እንዳንጠይቅ እንዘጋዋለን።
ውል ያለው መረጃ ሳይኖረን አሉ ብለን የምናወራው ወሬ እኛኑ ያስገምታል። ወገን ለዚያው በዚህ ዘመን ወሬ እየተፈበረከ በሚመረትበት ሰዎች ሌሎችን ለማሳሳት በሚጥሩበት ጊዜ። አሉን እየደጋገምን የወሬያችን ማጣፈጫ ማድረጉ የእውነት ሊያኖረን ፈጽሞ አይችልም። እኛ አንድን ነገር ስንሰማ በጉዳዩ ላይ እርግጠኛ የሆነ መረጃ ልንይዝ ግድ ይለናል። ተሳስተን ለማሳሳት ምን አስቸኮለን። መጀመሪያ እንዲህ ሆነ ወይም እንዲህ ይሆናል ከሚሉት ስለምን አናጣራም:: እንዴት ያለ ማስረጃ ለሌላው እናስተላለፋለን።
ከዚያው ከባስ ውስጥ አልወረድኩም። እነሱም ማውጋታቸው በአሉ ዘንቀው ማውራቱን ቀጥለዋል። “አየሽው መብራቱ ሲያምር! እንዴት ሸጋ አርገውታል ባክሽ” ከሁለቱ አንዷ ወደ መስኮቱ ያሉት ተናገሩ። ይህን ሲሉ አንድ አደባባይ እየዞርን ነበርና አስተያየታቸው ተከትዬ ወደ ውጪ አየሁ። ተመስጌን ነው ከዚህ የሁላችንም ጉዳይ ከሆነው ኑሮ ተሻግረዋል። ጥሩ ነው ወሬ መቀየራቸው ባሉም ቢሆን ስለ ኑሮ ሲወራ ባንሰማ ይሻለን የለ፤ እየኖርነውም ስለሱ እያወራንም የኑሮ መወደድ እንችለዋለን።
ሴትየዋ አደባባዩ በአበባ ተንቆጥቁጦ በመብራት ፈርጦች ደምቆ ነበርና እሱን አይተው ነው። በእርግጥም ከዚያ በፊት አደባባዩን ለሚያውቀው ሰው በዚያ መልክ ቢያየው ሳያጅበው ማለፉ እንጃ። “አዬ ምን ዋጋ አለው፤ ባለፈው እንዲሁ ተተክሎና አምሮበት መንገዱ ሲሰራ ነው አሉ መልሰው የቆፋፈሩት” አዬ ይሄ ወሬ አሁንም “አሉ” አለው። በነገራችን ላይ አደባባዩ እንዳሉት በመንገድ ግንባታ ምክንያት ፈርሶ ሰፍቶ መልሶ ቢሰራም አደባባዩ ግን ልማት የራቀው ነበር። እና እኚህ እናት “አሉ” በቀላቀለ መደምደሚያቸው በፊት ያልነበረውን አልብሰውታል።
እንኳን ባሉ ያላዩትን እርግጠኛ ሆነው መናገር በማይቻልበትና የሚታየው ሌላ እውነታው ከዚያ ፍፁም የራቀ በሚሆንበት ዓለም፤ አሉ ብሎ የእውነት ያልሆነ ያላወቁትን መንዛት ተገቢ አይመስለኝም። ወገን! ዛሬ ላይ ለተለያዩ አላማዎች ውሸት እየተፈበረከ በደቂቃዎች ውስጥ ከአንድ አድማስ ጫፍ ወደሌላው ጫፍ በሚዳረስበት በአሁኑ ወቅት “አሉን” ጨምረንበት የዓለም ውጥንቅጥነት ምን ያህል እንደሚበዛ አሰባችሁት።
በወሬያችን አሉ እያስገባን የማናውቀውን ለሌሎች አሉ ብለን እያስተላለፍን ያልነው ሁሉ የሌለ ሆኖ በሌሎች እንዳያስተዛዝበን መጠሪያችንም “እነ አሉ” እንዳይሆን ያየነውን እንጂ የሰማነውን ሳናጣራ ባንል መልካም ይመስለኛል። ቸር ይግጠመን።
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን ሰኔ 25/2014