
አዲስ አበባ፡- በኢትዮጵያ የተጀመረውን ወሰን ተሻጋሪ የወጣቶች የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ወደ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም በማስፋት ለፓናል አፍሪካኒዝም ንቅናቄ ማጠናከሪያነት እንዲውል መንግሥት በትኩረት እንደሚሰራ የሴቶችና ማሕበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ አስታወቁ።
“በጎነት ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል መሪ ሃሳብ የዘንድሮ ወሰን ተሻጋሪ የክረምት የወጣቶች በጎ ፈቃድ በድሬዳዋ የተጀመረ ሲሆን፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ በሚካሄደው በዚሁ መርሃ ግብር 19 ሚሊዮን ወጣቶች እንደሚሳተፉ ተገልጿል።
በድሬዳዋ ተገኝተው መርሃ ግብሩን ያስጀመሩት ሚኒስትሯ እንዳስታወቁት፤ በወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ ስራ ላይ የተሰማሩ ወጣቶች የሀገሪቱን መሠረታዊ የማሕበራዊ አገልግሎት ችግሮች ለመፍታት እያደረጉት የሚገኙት ተግባራት በውጤት እየታጀበ ይገኛል።
አምና 21 ሚሊዮን ወጣቶች ተሣትፈው 38 ሚሊዮን ለሚሆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች አገልግሎት በመስጠት 40 ቢሊዮን ብር የሚገመት የልማት ስራዎች ማከናወናቸውን አስታውሰዋል።
ወጣቱ ትናንት ለሀገሩ ሉአላዊነት መከበር የከፈለውን መስዋዕትነት ዛሬ ደግሞ የኢትዮጵያን ልማትና ዕድገት ለማረጋገጥ የተቀናጀ ጥረት እያደረገ መሆኑን ነው ሚኒስትሯ የገለጹት።
በሀገር ውስጥ የተጀመረው ወሰን ተሻጋሪ የወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በቀጣዮቹ ዓመታት በማዘመን ከኢትዮጵያ ውጭ ድንበር ተሻግሮ በአፍሪካ ሀገራት እንዲያብብ ትኩረት ተሰጥቶት እንደሚሰራ ጠቁመው፤ ይህ ጥረት የፓና አፍሪካኒዝምን ንቅናቄ ለማጠናከር ያግዛል ብለዋል።
በድሬዳዋ ትናንት በተጀመረው የወሰን ተሻጋሪ የወጣቶች የበጎ ፍቃድ አገልግሎትን ከሚኒስትሯ ጋር ያስጀመሩት የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ሀርቢ ቡህ እንዳሉት፤ የወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች የከተማውን ማሕበራዊ ችግሮች ትርጉም ባለው መንገድ እያቃለሉ ናቸው።
በዘንድሮ መርሃ ግብርም የአረጋውያን ቤት ከማደስ ሌላ የአረንጓዴ አሻራ ሥራን እንደሚያጠናክር ነው ያመለከቱት።
ድሬዳዋ በተጀመረው መርሃ ግብር ከተሳተፉት መካከል ከኦሮሚያ ክልል የመጣው ወጣት ሁሴን መሐመድ ፤ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከልማቱ ባሻገር የርስበርስ ፍቅራቸውን በማጎልበትና ሕብረ-ብሔራዊ አንድነታቸውን በማጠናከር ለሀገር ከፍታ በጋራ እንዲቆሙ ማገዙን ተናግሯል።
ከአማራ ክልል የመጣችው ወጣት ሳምራት ብርሃኑ በበኩሏ፤ በጎ አድራጎትን በተግባር ለማሳየት በመርሃ ግብሩ ላይ እየተሳተፈች መሆኗን ገልጻለች።
በድሬዳዋ የተጀመረው የወሰን ተሻጋሪ የወጣቶች የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ላይ ከመላው ሀገሪቱ ክልሎች እና ከድሬዳዋ የተውጣጡ ወጣቶች ችግኝ በመትከልና የችግረኛ አረጋውያንን ቤቶች የማደስ ሥራ ላይ በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ሰኔ 25 ቀን 2014 ዓ.ም