
አዲስ አበባ፡- “የፍትሕ ተቋማት የሙስና ወንጀለኞች ላይ በሚፈለገው ደረጃ አስተማሪ የሆነ የሕግ እርምጃ እየወሰዱ አይደለም” ሲል የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን አስታወቀ። የባከኑና የሸሹ ሀብቶች በሚፈለገው መጠን ማስመለስ እየተቻለ አይደለም ብሏል።
የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ሙስና መከላከል ላይ እየተከናወኑ ስራዎች አስመልክቶ ያዘጋጀው የባለድርሻ አካላት ውይይት ትናንት በአዳማ ከተማ በተጀመረበት ወቅት የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ዶክተር ሳሙኤል ኡርቃቶ እንደገለጹት፤ መንግሥትና አመራሩ ሙስናን ለመከላከል ያላቸው ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት ብዙ የሚቀረው መሆኑን ገልጸዋል።
መረጃና እውቀትን ከማመንጨትና ዜጎች ስለ ሙስና ያላቸውን ንቃተ ሕሊና ከማዳበር አኳያ መገናኛ ብዙሃንን ጨምሮ የዘርፉ ባለድርሻ አካላት የሚጠበቅባቸውን ያክል እየሰሩ እንዳልሆነ ተናግረዋል።
“የፍትህ ተቋማት የሙስና ወንጀለኞች ላይ በሚፈለገው ደረጃ አስተማሪ የሆነ የሕግ እርምጃ እየወሰዱ አይደለም፣ የባከኑና የሸሹ የሕዝብና የመንግሥት ሀብት ከማስመለስ አንፃር በየደረጃው ያሉ የፀረ ሙስና ኮሚሽኖች ብቃትና አቅም ገና ያልዳበረ ነው” ብለዋል ኮሚሽነሩ።
በኮሚሽኑ ሙስና ለመከላከል የሚያስችሉ የማሻሻያ ስራዎች እየተከናወኑ ቢሆንም “የሙሰኞች የማጭበርበር፣ የመረጃና የሕግ እውቀት ሽፋን ያደረገ ሌብነት” መከላከል የሚችሉ ተቋማት ለመፍጠር ገና ብዙ መስራት እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።
በ2007 ዓ.ም የተዘጋጀው ሙስናን የመከላከል ስትራቴጂ ውስብስብና በየጊዜው ተለዋዋጭ የሆኑ የሙስና ወንጀሎች ምላሽ መስጠት ባለመቻሉ ምክንያት አዲስ ስትራቴጂ እየተዘጋጀ እንደሚገኝ ነው ዶክተር ሳሙኤል የገለጹት።
ስትራቴጂውን ለማዘጋጀት የሚያስችሉ ጥናቶች እየተገባደዱ እንደሚገኝና በ2015 ዓ.ም ዝግጅት ስራ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
ጥናቶቹ በትምህርት፣ በገቢዎችና በፍርድ ቤቶች አካባቢ ያለውን ሙስና፣ በትምህርት ማስረጃ ማጭበርበር፣ የመንግሥትን ገቢ ተመሳጥሮ ከግል ጥቅመኞች ጋር ማስቀረትና የፍትህ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ያለውን የሙስና ተጋላጭነት የተመለከቱ ናቸው ብለዋል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግ፣ የፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ እፀገነት መንግሥቱ በበኩላቸው የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ባለፉት ሁለት ዓመታት ሙስናን ከመከላከል አንጻር ተስፋ ሰጪ ጅምር ስራዎች ቢያከናውንም በቂ እንዳልሆነ ገልጸዋል።
ኮሚሽኑ በሥነ ምግባር ግንባታና ትውልድ ቀረጻ ላይ በትኩረት መስራት እንደሚኖርበትና ይሄንንም ተቋማዊ በሆነ መልኩ ማስኬድ እንደሚገባ ተናግረዋል። የመንግስትና የሕዝብ ሀብት ምዝበራ ከመካሄዱ በፊት ቀድሞ የመከላከል ስራ የኮሚሽኑና የባለድርሻ አካላት ቀዳሚ ተግባር መሆን አለበት ብለዋል።
በተለይ የተመዘበሩ ሀብቶች ወደ መንግሥት ካዝና እንዲመለሱ ማድረግ ላይ አሁንም የሚፈለገውን ያህል አልሰራንም ያሉት ሰብሳቢዋ ኮሚሽኑ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት መስራት እንዳለበት አሳስበዋል። ምክር ቤቱም ለኮሚሽኑ አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።
“በምንም መመዘኛ ዜጎች ሕገ-መንግሥታዊ መብታቸው የሆነውን አገልግሎት በገንዘብ መግዛት የለባቸውም” ያሉት ወይዘሮ እፀገነት ችግሩን ከመሰረቱ ለማስወገድ አደረጃጀት፣ አሰራርና ሥርዓት በመዘርጋት ተቋማት በቴክኖሎጂ እንዲመሩ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።
በምክክር መድረኩ የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን “ፀረ-ሙስና” የተሰኘ በወር አንዴ የሚታተም ጋዜጣ ዛሬ በይፋ ማስጀመሩንም ኢዜአ ዘግቧል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ሰኔ 25 ቀን 2014 ዓ.ም