
አዲስ አበባ፡- በጋምቤላ ክልል በዘንድሮው የአረንጓዴ ልማት አሻራ ከሚተከሉ ችግኞች መካከል ሰማንያ አምስት በመቶዎቹ ለምግብነት የሚውሉ እንደሆነ የክልሉ ግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ አስታወቀ።
የክልሉ ግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ አጃክ ኡቻላ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንዳስታወቁት በ2011 ዓ.ም በሀገር አቀፍና በክልል ደረጃ የተጀመረው የአረንጓዴ ልማት አሻራ መርሃ ግብር 15 ነጥብ 1 ሚሊዮን ችግኞች ላይ የክብካቤ ሥራ በመሰራቱ በርካታ ችግኞች መጽደቅ ችለዋል።
በ2013 ዓ.ም የአረንጓዴ ልማት አሻራ መርሃ ግብር በክልሉ በተሰራው ሰፊ ስራ ከሰባት ነጥብ አራት ሚሊዮን በላይ ችግኞች የተተከሉ መሆኑንም ኃላፊው አመልክተዋል።
በየአመቱ በአረንጓዴ ልማት አሻራ መርሃ ግብር አማካኝነት የሚተከሉ ችግኞች የአካባቢውን ሥነ ምህዳር ከማስተካከል አንፃር ጉልህ ድርሻ አላቸው ያሉት ኃላፊው፣ የተፈጥሮን ሚዛን ከመጠበቅ ባሻገር ለምግብነት አገልግሎት በማዋልና የአካባቢውን ወጣት የስራ እድል ከመፍጠር አኳያ ጉልህ ሚና አላቸው ብለዋል።
የጋምቤላ ክልል በተፈጥሮ ሀብቱ በተለይም በበርካታ ወንዞችና ተፋሰሶች የታወቀ ቢሆንም በየጊዜው በተለያዩ
ምክንያቶች የአካባቢው ደንና የተፈጥሮ ሀብቶች ላይ የሚደርሰውን መመናመን ለመከላከል ይህ የአረንጓዴ ልማት አሻራ ተግባር አስፈላጊ መሆኑን አስታውቀዋል።
ለዚህ ተግባራዊነት ቢሮው ትኩረት አድርጎ እየሰራ በመምጣቱ በ2013 ዓ.ም ከተተከሉ ከሰባት ነጥብ አራት ሚሊዮን በላይ ችግኞች መካከል ሰማንያ በመቶዎቹ መጽደቃቸውን አቶ አጃክ ኡቻላ ተናግረዋል።
በዘንድሮው የአረንጓዴ ልማት አሻራ መርሃ ግብርም ከስድስት ነጥብ አምስት ሚሊዮን በላይ ችግኝ ለመትከል የታቀደ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 85 በመቶ የሚሆነው ችግኝ ለምግብነት የሚውል መሆኑን ጠቅሰዋል።
በክልል ደረጃ የአረንጓዴ ልማት አሻራ መርሃ ግብር ሰኔ 26/2014 ዓ.ም የሚጀመር መሆኑን የተናገሩት ኃላፊው፣ በክልሉ 88 በሚደርሱ ችግኝ ጣቢያዎች የሚገኙት ችግኞች ለተክል የተዘጋጁ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በአካባቢው ሞቃታማ አየር ፀባይ ምክንያት በየአመቱ የሚቃጠለውን ዛፍና ችግኝ ለመተካት በሚደረገው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ማሕበረሰቡ በነቂስ እንዲሳተፍና ለስኬታማነቱ የድርሻውን እንዲወጣ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ማሕበረሰቡ እንዲሁም ተቋማት በየወቅቱ በዘመቻ መልክ እየወጡ ችግኝ መትከል ብቻውን ግብ እንዳልሆነ በመረዳት ችግኝ ከተተከለ በኋላ የመንከባከለብ ኃላፊነት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
በግንዛቤ እጦት ምክንያት የተተከለ ችግኝ የመንከባከብ ተግባር አናሳ መሆኑን ያወሱት የግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊው አቶ አጃክ ኡቻላ፣ ማሕበረሰቡ የባለቤትነት ስሜት እንዲኖረውና ከተተከለው ችግኝ ተጠቃሚ እንዲሆን በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ፍቃዱ ዴሬሳ
አዲስ ዘመን ሰኔ 25 ቀን 2014 ዓ.ም