
አዲስ አበባ፡- ሸማቹ ሕብረተሰብ መንግሥት ዋጋ እንዲያረጋጋለት ከመጠበቅ ይልቅ የተወደደበትን ምርት ራሱ በማምረት በኢኮኖሚው መሪ ተዋናይ ሊሆን እንደሚገባ የኢኮኖሚ ባለሙያና አማካሪው አቶ ጌታቸው አስፋው አስታወቁ።
የኢኮኖሚ አማካሪው አቶ ጌታቸው አስፋው ለአዲስ ዘመን እንዳስታወቁት፤ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የዋጋ ንረት ማረጋጋትና ዘላቂ መፍትሔ ማምጣት የሚቻለው ሸማቹ ሕብረተሰብ ራሱ የተወደደበትን ምርት በማምረት በኢኮኖሚው መሪ ተዋናይ ሲሆን ነው።
‹‹ብዙዎቻችንን ከደርግ ዘመን ጀምሮ የያዝነው ከመንግሥት ጠባቂነት አስተሳሰብ መውጣት
አልቻልንም። ሥራ መንግሥት ይሰጠኛል፤ ሁሉንም ነገር መንግሥት ያቀርብልኛል ብለን ነው እየኖርን ያለነው። ማግኘትና ማጣታችንን መንግሥትን ከመጠበቅ ጋር አያይዘነዋል›› በማለት አስረድተዋል። ይሁንና አሁን ላይ እየጨመረ ካለው የሕዝብ ቁጥርና የዋጋ ንረት አንፃር መንግሥት ሁሉንም ችግር እንዲፈታው መጠበቅ ችግሩን ከማባባስ ባለፈ ውጤት እንደማያመጣ አመልክተዋል።
በተለይ ሀገሪቱ የምትከተለው ነፃ ኢኮኖሚ ሥርዓት አኳያ መንግሥት ሁሉም ነገር ውስጥ እየገባ ችግር መፍታት እንደማይችል ያነሱት አቶ ጌታቸው በመሆኑም የገበያ ሥርዓቱን ዋነኛ ተዋናይ ሸማቹ እንደመሆኑ ገበያው ላይ የመወሰን መብቱን በመጠቀም የዋጋ ንረቱን ማስተካከል የሚገባው መሆኑን አስገንዝበዋል። ‹‹በነፃ ኢኮኖሚ ሥርዓት ዋነኛ አዛዥ ሸማች ነው፤ አምራቹ ሸማቹ የሚፈልገውን ምርትና መጠን ልክ ነው የሚያመርተው ፤ የመንግሥት ሚና ሁለቱን አካላት ማገዝ ነው። በእኛ ሀገር ግን ሸማቹም ሆነ አምራቹ መንግሥት ላይ ጥገኛ ሆነዋል፤ በተለይ ሸማቹ አዛዥ መሆን ሲገባው ለማኝ ሆኗል›› ብለዋል።
አክለውም ‹‹ሸማቹ መንግሥት ተቆጣጥሮ ዘይቱንም ሆነ ዱቄቱን እንዲያቀርብለት ይፈልጋል፤ አምራቹም መንግሥት መሬት እንዲሰጠው፤ ግብር እንዲቀንስለትና ብድር አመቻችቶለት ነው መስራት የሚፈልገው። በዚህ ሁኔታ ከቀጠለ አምራቹም ሆነ ሸማቹ ከመንግሥት ጥገኝነት መውጣት አይችልም›› በማለት ተናግረዋል።
እንደ አቶ ጌታቸው ማብራሪያ፤ የነፃ ኢኮኖሚ የሚገነባው በዋናነት በአምራችና በሸማቹ ነው። በኢትዮጵያ አሁን ባለው ሁኔታ ነጋዴው ገበያውን ተቆጣጥሮ በመያዝ የመሪነት ሚና ያለውን ሸማች በገዛ ገንዘቡ ባይተዋርና ለማኝ አድርጎታል። በተጨማሪም የአምራቹ ቁጥርም ሆነ የሚመረተውም ምርት አነስተኛ መሆኑ ነጋዴው እንዳሻው ዋጋ እንዲተምንና ተወዳዳሪነት ባለመኖሩም ብቸኛ ተጠቃሚ እንዳይሆን ምክንያት ሆኗል።
‹‹ከዛሬ አምስት ዓመት በፊት እንቁላል ሁለት ብር ነበር፤ ዛሬ 12 ብር የገባው ዶሮ ጠፍቶ ሳይሆን አምራች ሕብረተሰብ መፍጠር ባለመቻላችን ነው። ከዚያ ይልቅ ነጋዴው ዋጋ እያስወደደ አየር በአየር እንዲከብር ነው ያመቻቸንለት›› በማለት አመልክተዋል። ከዚህ ጋር ተያይዞ በመንግሥት በኩል የፖሊሲ አቅጣጫውን ማስተካከል እንደሚገባ አቶ ጌታቸው አስገንዝበዋል። መሻሻል ከሚገባቸው ጉዳዮች መካከል አብነት አድርገውም ‹‹ገበያው ውስጥ ከምርቱ በላይ የሆነ ጥሬ ገንዘብ እንዲገባ የሚደረግበት ሁኔታ በመኖሩ የእቃዎች ዋጋ እንዲወደድ ምክንያቱት ሆኗል፤ በመሆኑም ገበያውን ማረጋጋት ከተፈለገ መንግሥት ምርት ለማገበያየት የሚያስችል ያህል ብቻ መግባቱን ሊቆጣጠር ይገባል፤ ከዚህ አኳያ ያለውን የፖሊሲ አቅጣጫ መፈተሽ ይጠበቅበታል›› ብለዋል።
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ሰኔ 25 ቀን 2014 ዓ.ም