
አዲስ አበባ፡- በኦሮሚያ ውስጥ እየተስተዋለ ላለው የሰላምና ጸጥታ ችግሮች ሕዝቦችን በማጋጨት የአገርን ሠላም ማናጋት የቆየ የወያኔ ስትራቴጂ መሆኑን አንጋፋው ፖለቲከኛ ዶክተር ዲማ ነገዎ አስታወቁ። በቡድኑና ተላላኪው በኦሮሚያ ውስጥ እየተፈጸመ ያለውን ድርጊት አውግዘዋል።
ዶክተር ዲማ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት በኦሮሚያ ውስጥ እየተስተዋለ ያለው የሰላምና ጸጥታ ችግሮች ወያኔ ዘርግቶ የተባረረበት የጥፋት ስትራቴጅ ውጤት ነው። የሽብር ቡድኑ ከበስተጀርባ በመሆን ወንድማማቾች መካከል ግጭቶችን በማባባስ ከክልሉ አልፎ በክልሉ የሚኖሩ ብሔር ብሔረሰቦች ችግር እያደረሰ ይገኛል። የሽብር ቡድኑ ተላላኪ ሸኔ በክልሉ ውስጥ በመንቀሳቀስ በሕብረተሰቡ ላይ ግድያና ዘረፋ እያደረሰ ነው።
እንደ ዶክተር ዲማ ገለጻ፤ ወያኔ ለ27 ዓመታት ሥልጣን ላይ በነበረበት ጊዜ ወታደራዊ ኃይሉን በመጠቀም ኦሮሚያን አፍርሶ መዝረፍ ላይ ትኩረት አድርጎ ሰርቷል። በወቅቱ ኦሮሞ ሕዝብን የሚወክል ነጻ ድርጅት እያለ ወያኔ የሚመቸውን ድርጅት በመፍጠር ኦሮሚያን የማጥፋት እኩይ ተግባሩን ፈጽሟል። ለሕዝቡ የሚቆረቆሩ የኦሮሞ ታጋዮችን ከአገር በማባረር የራሱን መዋቅር በተቋማት ውስጥ ዘርግቶ በመቆየቱ ዛሬም የአገርን ሠላም ለማናጋት እየጣረ ነው ።
የኦሮሞ ሕዝብ ከሌሎች ወንድሞቹ ጋር በመሆን በአደረገው ትግል ገዳይና ዘራፊውን ወያኔን ከሥልጣን እንዲባረር አድርገዋል ያሉት ዶክተር ዲማ፤ በተለያዩ ቦታዎች አምልጦ በቀሩ ሴሎቹ ኦሮሚያን በማናጋት ሕዝብ በመንግሥት ላይ እምነት እንዳይኖረው ለማድረግ እየሞከረ ነው ብለዋል።
እንደ ዶክተር ዲማ ገለጻ፤ በኦሮሞ ነጻነት ግንባር ሽፋን የሚንቀሳቀሰው ሸኔ የወያኔን ተልዕኮ በመቀበል ተግባራዊ ከማድረግ ውጭ ሌላ ለኦሮሞ ሕዝብ የሚሆን ዓላማ የለውም። ከበስተጀርባ ያለውን ምስጥር ሳያውቁ ከእነዚህ ኃይሎች ጋር ተሰልፎ ስህተት እንዲፈጽሙ እያደረገ ይገኛል።
ኦሮሚያ ማለት ኢትዮጵያ ማለት ነው ያሉት ዶክተር ዲማ የኦሮሚያን ሠላም ማናጋት የኢትዮጵያን ሠላም ማናጋት ስለሚሆን ሽብር ቡድኑ አንድ ላይ በመሆን የሽብር ድርጊታቸውን እየፈጸሙ ስለሚገኙ በኦሮሚያ ውስጥ የሚከሰቱ ችግሮችን ለብቻ ነጥሎ ማየት ተገቢ አይደለም ብለዋል።
በሰሜኑ ክፍል ጦርነት ከፍቶ ሲሸነፍ መንግሥት ተረጋግቶ ሀገር እንዳይመራ ለማድረግ እኩይ ተግባራትን በተለያዩ ቦታዎች እየፈጸመ ይገኛል ያሉት ዶክተር ዲማ የሽብር ቡድኑ ትልቁ ፍላጎት በሽብር ድርጊት መንግሥት በሕዝቡ ዘንድ ተቀባይነት እንዳይኖረው ለማድረግ በጋምቤላ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ አማራና ኦሮሚያ እኩይ ተግባሩ እየታየ ነው ብለዋል።
መንግሥት እኩይ ሴራውን ለመቀልበስ የጸጥታ ሃይሎችን በማሰማራት ብቻ ሳይሆን አባ ገዳዎች፣ የእምነት አባቶች፣ ከሀገር ሽማግሌዎች ጋር በመሆን ከሕዝብ ጋር በመወያየት ስትራቴጂ መንደፍ ያስፈልጋል ብለዋል።
እንደ ዶክተር ዲማ ገለጻ፤ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የፖለቲካ ችግር እንጂ በሕዝቦች መካከል ችግር የለም። ስለዚህ ሁሉም ነገር በምክክር መፍታት ይቻላል።
መንግሥት የሰሜኑን ክፍል ጦርነት በሠላመዊ መንገድ ለመፍታት መፈለጉ መልካምና ሊደገፍ የሚገባው ነው ያሉት ዶክተር ዲማ፤ ሁሉም ቡድኖች በጦርነት ያጡትን ነገር በሠላማዊ መንገድ ተነጋግረው እንዲያገኙ በር የሚከፍት ውሳኔ በመሆኑ እንዲሳካ እመኛለሁ ብለዋል። የትጥቅ ትግል አማራጭ ያደረጉ ኃይሎችም ይህ መንገድ እንደማያዋጣ ተገንዝበው በሰላማዊ መንገድ ለመታገል ራሳቸውን እንዲያዘጋጁ ጥሪ አቅርበዋል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ሰኔ 25 ቀን 2014 ዓ.ም