ከማዕድናት መካከል የሰው ልጆች ለጌጣ ጌጥ ማዕድናት ልዩ ዋጋና ትርጉም ይሰጣሉ:: ጌጣ ጌጥ ማዕድናት ቀለማቸው ቀልብን የሚስቡ፣ ውስጣዊ ደስታን የሚፈጥሩ በመሆናቸው ተፈላጊነታቸውና ተወዳጅነታቸው ከፍ ያለ ነው:: ሰዎች ይጌጡባቸዋል ይዋቡባቸዋል:: ከፍተኛ ዋጋም ያወጡባቸዋል:: አገሪቷም የተለያዩ ጌጣጌጦችን ማምረት የሚያስችላት የከበሩ ድንጋዮች ባለቤት ናት:: በኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች በርካታ የጌጣ ጌጥ ማዕድናት እንደሚገኙ መረጃዎች ያሳያሉ::
በኢትዮጵያ የጌጣጌጥ ማዕድናት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች እንደሚገኙ መረጃዎች ቢያሳዩም አገሪቱ ከጌጣጌጥ ማዕድናቱ መጠቀም ያለባትን ያህል ተጠቃሚ መሆን ሳትችል ቆይታለች:: የማዕድን ሚኒስትር ኢንጂነር ታከለ ዑማ በቅርቡ የ2014 በጀት ዓመት የ10 ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ባቀረቡበት ወቅት እንደተናገሩት፤ 2317 ኪሎ ግራም ብቻ የጌጣ ጌጥ ማእድናት ናቸው ለውጭ ገበያ የቀረቡት::
አገሪቱ አላት ተብሎ ከሚታሰበው ከፍተኛ የጌጣ ጌጥ ማዕድናት ሀብት አንጻር ለውጭ ገበያ የቀረበው የጌጣ ጌጥ ማዕድናት መጠን እጅግ አነስተኛ ነው:: አገሪቱ ከጌጣ ጌጥ ማዕድናት ተጠቃሚ መሆን ባለባት ልክ ተጠቃሚ እንዳትሆን ካደረጉት ምክንያቶች መካከል በምርት እና በግብይት ስርዓት ላይ የሚታዩ ችግሮች ናቸው::
አገሪቱ ከጌጣ ጌጥ ማዕድናት ተጠቃሚ መሆን ባለባት ልክ ተጠቃሚ እንዳትሆን እንቅፋት ከሆኑት ችግሮች መካከል በተለይም በማዕድናቱ የመንግሥት የዋጋና የደረጃ ተመን እንዲሁም ሌሎች አላስፈላጊ መስፈርቶች ተጠቃሽ ናቸው:: የጌጣ ጌጥ ማዕድናት ግብይት ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መንግሥት የተለያዩ ጥረቶችን እያደረገ ይገኛል::
ከዚሁ ጋር በተያያዘም ሰሞኑን ሚኒስትሩ በማህበራዊ ሚዲያ ገፃቸው ባጋሩት መረጃ፤ የጌጣ ጌጥ ማእድናት የግብይት ሰንሰለትን ለማቃለልና ኢትዮጵያ ከዘርፉ ማግኘት ያለባትን እንድታገኝ ከዚህ በፊት ሥራ ላይ የነበረውን በመንግሥት የዋጋና የደረጃ ተመን እንዲሁም ሌሎች አላስፈላጊ መስፈርቶች ተነስተው የንግድ ሥርዓቱ በገበያ ብቻ የተመራ እንዲሆን ወስነናል ሲሉ አስፍረዋል።
እነዚህ የጌጣ ጌጥ ማእድናት ከዚህ ቀደም የነበረው የመንግሥት ዋጋና የደረጃ ተመን እንዲሁም አላስፈላጊ መስፈርቶች ተነስተው የንግድ ስርዓቱ በገበያ ስርዓት ብቻ የተመራ እንዲሆን መወሰኑ አገሪቱ ከማዕድናቱ ማግኘት ያለባትን ጥቅም ማግኘት እንድትችል ከፍተኛ ፋይዳ እንደሚኖረው የምጣኔ ሀብት ምሁራን ያብራራሉ::
የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አቶ ዳዊት ተሻለ እንደሚሉት የማዕድናት ግብይት በገበያ ስርዓት ብቻ እንዲመራ መወሰኑ ዘርፈ ብዙ ፋይዳ አለው:: የማዕድናት የንግድ ስርዓት በገበያ ብቻ መመራት በጌጣ ጌጥ ማዕድናት ገበያ ተሳታፊዎች መካከል ነፃ ውድድርን ያበረታታል። የገበያ ውድድር ሲኖር በውድድሩ አሸናፊ ሆኖ ለመውጣት የገበያ ተሳታፊዎቹ ቅልጥፍና እና ፈጠራ የታከለበት አሰራር ለመከተል ይገደዳሉ::
የማዕድን ጌጣ ጌጥ ግብይት ላይ መንግሥት ዋጋ እና የደረጃ ተመን በሚያደርግበት ወቅት በዘርፉ የተሰማሩ አካላት ስኬታማነት የሚወሰነው በዘርፉ ተዋናዮች ጥረት ብቻ ሳይሆን፤ በመንግሥት ዋጋ እና ደረጃም የሚወሰን ነው:: በዘርፉ ተዋናዮች ብቻ ስለማይወሰን የዘርፉ ተዋናዮች ያላቸውን ሙሉ አቅም ተጠቅመው እንዳይንቀሳቀሱ እንደሚያደርጋቸው ያነሳሉ::
አሁን ግን የንግድ ስርዓቱ በገበያ ብቻ ሲመራ የዘርፉ ተዋናዮች ስኬታማነት የሚወሰነው በዋናነት በራሳቸው በዘርፉ ተዋናዮች ጥረት ነው:: ቅልጥፍና በታከለበት መንገድ የሚሰሩት ትርፋማ የመሆን እድላቸው ከፍ ያለ ይሆናል:: በገበያው ስኬታማ ለመሆን የተለያዩ ፈጠራ የታከለበትን አሰራሮችን እንዲከተሉ ያነሳሳቸዋል:: ፈጠራ ያልታከለበት አሰራር ተከትለው ውጤታማ ሊሆኑ አይችሉምና::
በዚህም በማዕድን ዘርፍ የተሰማሩ አካላት ብሎም አገሪቱ ተጠቃሚ ይሆናሉ:: አገሪቱ ከዚህ ቀደም መሰል አሰራሮች ባለመዘርጋቱ ተጠቃሚ ሳትሆን የቆየችበትን ዘመን ለማካካስ የሚያስችል ሥራ ለመስራት ያስችላል::
አቶ ዳዊት እንደሚሉት፤ የግብይት ስርዓቱ በገበያ ስርዓት ብቻ የሚመሩ የጌጣ ጌጥ ማዕድናትም በጥንቃቄ ሊለዩ ይገባል ይላሉ:: ሁሉም የጌጣ ጌጥ ማዕድናት ግብይት በገበያ ስርዓት ብቻ እንዲመራ የሚለቀቅ ከሆነ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ አሉታዊ ጫና ሊያሳድር ይችላል:: በአሁኑ ወቅት የአገሪቱ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት የሆኑ ማዕድናት ከመንግሥት ቁጥጥር ውጪ ሊሆን አይገባም::
ለአብነት ያህል ወርቅ ለአገሪቱ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የሚያስገኝ ማዕድን ነው:: የወርቅ ግብይት ግን ከገበያ ስርዓት ውጪ ሊሆን አይችልም:: ምክንያቱም ወርቅ የአገሪቱ የውጭ ምንዛሬ ግኝት መሰረት ነውና:: ወርቅ የመንግሥትን ካዝና ከማሳደግ አልፎ ብዙሃኑን የሚጠቅም ነው:: እንደ ወርቅ ያሉ ምርቶች ግብይት ላይ የመንግሥት ቁጥጥር ተጠናክሮ መቀጠል አለበት::
ከወርቅ ውጭ ያሉ እና እስካሁን ድረስ በሚፈለገው ልክ ጥቅም ላይ ያልዋሉ የጌጣ ጌጥ ማዕድናትም በገበያ ስርዓት ብቻ እንዲመራ በሚደረግበት ወቅት ጥንቃቄዎች ሊደረግ ይገባል:: የጌጣ ጌጦቹ ግብይት በአቅርቦት እና ፍላጎት ብቻ እንዲመራ መደረግ አለበት ምንም አይነት ቁጥጥር ሊኖር አይገባም ማለት እንዳልሆነ ሊታወቅ ይገባል ይላሉ::
እንደ አቶ ዳዊት ማብራሪያ፤ መንግሥት እንደ መንግሥት ገብቶ ከመነገድ እና አላስፈለጊ መሰናክሎችን ከመፍጠር መውጣት አለበት ማለት በዘርፉ ምንም አይነት ቁጥጥር አይኑር ማለት አይደለም:: በገበያ ብቻ እንዲሆን መደረጉ እንደመልካም ነገር የሚወሰድ ሆኖ የመንግሥት ክትትል እና ቁጥጥርም አስፈላጊ ነው:: ነጻ ተብሎ ከመልቀቅ ይልቅ ቁጥጥር የሚያደርግ አካል ሊኖር ይገባል:: በገበያ ብቻ ይመራ ሲባል በአቅርቦትና ፍላጎት ላይ ብቻ ይወሰን ማለት ነው::
ይህ ደግሞ የተለያዩ ህገ ወጥ ሥራዎችን ለሚሰሩ አካላትም በር ሊከፍት ይችላል:: ቁጥጥር ካልተካሄደ በዘርፉ የተሰማሩ ነጋዴዎች ጌጣ ጌጦችን የሸጡበትን የውጭ ምንዛሬ ለህገ ወጥ አላማዎች ሊጠቀሙበት እንደሚችሉ የጠቆሙት አቶ ዳዊት፤ ቁጥጥር ማድረግ ከተቻለ አገሪቱ ተጠቃሚ ልትሆን ትችላለች:: ዝም ብሎ ልቅ የሚደረግ ከሆነ ግን አደገኛ ችግር ይዞ ሊመጣ ይችላል:: በተለይም ከዚህ ዘርፍ ግብይት የሚገኘው ገንዘብ ምን ላይ ይውላል የሚለውን መከታተል አለበት::
ችግሮች ከተከሰቱ በኋላ ከመሯሯጥ ይልቅ ከአሁኑ ሊታሰብበት ይገባል፤ እነዚህን ነገሮችን መቆጣጠር የሚቻለው የሚቆጣጠር አካል ሲኖር ነው የሚሉት አቶ ዳዊት፤ ለዚህም ተቋም ሊኖር ይገባል ይላሉ:: በተለይም አገሪቱ ካለችበት ሁኔታ አንጻር በአግባቡ ቁጥጥር ተደርጎበት ለተገቢው ዓላማ ካልዋለ ለሌላ ዓላማ የመዋል እድሉ ከፍ ያለ ነው::
የማዕድን ዘርፍን ለማሳደግ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መንግሥት እየወሰዳቸው ያሉ እርምጃዎች ዘርፉ ለአገሪቱ ኢኮኖሚ ማበርከት ያለበትን ማበርከት እንዲችል ከፍተኛ እድል የሚፈጥሩ ናቸው:: መንግሥት በጌጣ ጌጥ ማዕድናት የግብይት ስርዓት በገበያ እንዲመራ መተው እንደተጠበቀ ሆኖ የማዕድናቱን የምርት እድገት ሊያሳድጉ የሚችሉ እርምጃዎችን አጠናክሮ መቀጠል አለበት:: በአገሪቱ የከበሩ የጌጣ ጌጥ ማዕድናት ምርትና ግብይት ላይ እየታዩ ያሉ ችግሮች የማዕድናቱ ግብይት በገበያ ስርዓት እንዲመራ በመተው ብቻ የሚፈታ አይደለም:: የግብይት ስርዓቱ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት በዘርፉ የተሰማሩ ባለድርሻ አካላት በጋራ የመስራት ልምዳቸውን ሊያዳብሩ ይገባል::
በዘርፉ የተሰማሩ አካላትን የማበረታታት ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው:: የባህላዊ የጌጣ ጌጥ ማዕድናት አምራቾች ማህበራትን ማጠናከር ወሳኝ ነው:: ማህበራቱ የሚያጋጥማቸው እንቅፋቶችን ለማቃለል መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ መሥራት አለበት::
የዘርፉ ችግር የግብይት ስርዓቱ በገበያ ብቻ እንዲመራ በመተው የሚፈታ አይደለም:: ለዘመናት የተከማቹ ችግሮች ያሉበት ዘርፍ እንደመሆኑ ተጨማሪ እርምጃዎች መወሰድ አለባቸው:: በተለይም በዘርፉ ለተሰማሩ የህብረተሰብ ክፍሎች አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረጉን መቀጠል አለበት:: በዘርፉ ለተሰማሩት አነስተኛ የማምረቻ መሳሪያዎች ከውጭ አገራት የሚገቡበትን አሰራሮች ማመቻቸትን ጨምሮ ሌሎች ድጋፎችን ማድረግ አለበት:: መሰል ድጋፎች በመንግሥት በኩል የማይቀርቡ ከሆነ ዘርፉን በሚፈለገው ደረጃ ለማድረስ አዳጋች ይሆናል::
የጌጣ ጌጥ ማዕድናቱ እሴት ሳይጨመርባቸው ወደ ውጭ አገራት የመላክ ሁኔታ እንዲቀጥል ማድረግ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ የሚያሳድረውን አሉታዊ ተፅዕኖ ከግምት በማስገባት መንግሥት የንግድ ስርዓቱን ከማመቻቸት ባሻገር መንግሥትም አገሪቱ ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን የውጭ ምንዛሬ እንድታገኝ ማዕድናቱ እሴት ተጨምሮባቸው የሚወጡበትን መንገድ ቢያመቻች መልካም ነው::
በጌጣ ጌጥ ማዕድናት ልማት ላይ የሚሰማሩ ፕሮጀክቶች መንግሥት መሸፈን ያልቻለውን በመሸፈን ለበርካታ ሥራ ፈላጊ ወጣቶች የሥራ እድል የመፍጠር አቅም ያላቸው በመሆናቸው ማዕድን በአገርና በመንግሥት አቅም ብቻ ፈልጎ ማግኘት ከባድ በመሆኑ ፕሮጀክቶችን በማፈላለግ ከአጋር አካላት ጋር መሥራት ያስፈልጋል::
ዓለም አቀፍ ድርጅቶች እውቀታቸውን፣ ገንዘባቸውን እና የሥራ ባህላቸውን ይዘው እንዲመጡ እና ኢትዮጵያ ካላት የሰው ኃይልና የተፈጥሮ ሀብት ጋር ለማስተሳሰር በትኩረት መሰራት አለበት::
በተግባር በጌጣ ጌጥ ማእድናት ሥራ ላይ የማይገኙ ግን በህገ ወጥ ሥራዎች ላይ ተሰማርተው ዘርፉን እየጎዱ ያሉ አካላትን ለህግ የማቅረብ ሥራዎች ሊታሰብበት ይገባል:: ህገ ወጥ ማዕድን አዘዋዋሪዎች ላይ የሚወሰዱ ህግ የማስከበር እርምጃዎች መጠናከር አለባቸው:: እርምጃዎቹ በመሰል ህገ ወጥ ተግባራት ላይ የሚሳተፉትን ሊያስተምር የሚችል ሊሆን ይገባል::
አገሪቱ የጌጣ ጌጥ ማእድናትን ወደ ውጭ አገራት በመላክ ተጠቃሚ እንድትሆን ለማስቻል ባለሙያዎችን በስፋት ማብቃት የግድ ነው:: ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎች የማዕድን ዘርፉን የሚመለከቱ የትምህርት ክፍሎች ተከፍተው ማስተማር መጀመራቸው እና የነበሩትን የማጠናከር ሥራ መጀመሩ እንደመልካም ጅምሮ የሚታይ ነው:: መሰል ሥራዎች በሌሎች ዩኒቨርሲቲዎችም ተጠናክሮ መቀጠል አለበት::
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተፈጠሩ ያሉ ምቹ ሁኔታዎችን በመጠቀም በዘርፉ የተሰማሩ አካላት ማዕድናትን በጥሬው (እሴት ሳይጨመርባቸው) ለገበያ ከማቅረብ ይልቅ እሴት ጨምረው ለማቅረብ በትኩረት መስራት አለባቸው:: የጌጣ ጌጥ ማዕድናትን ከመቁረጥ ውጭ ምንም ሳይጨምሩ ለገበያ የማቅረብ ሁኔታ እንዲቆም መደረግ አለበት:: እሴት ተጨምሮባቸው ሲወጡ ለአገርም ሆነ ለማኅበረሰቡ የሚኖራቸው አስተዋጽዖ የጎላ ይሆናል::
የኢትዮጵያን የጌጣ ጌጥ ማእድናት እና ሌሎች የተፈጥሮ ሀብቶች ለዓለም ማስተዋወቅ ሥራ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት ሊሰራ ይገባል:: የጌጣ ጌጥ ማዕድናት ስኬት እውን የሚሆነው በመንግሥት እና በዘርፉ በተሰማሩ አካላት ጥረት ብቻ አይደለም:: ማህበረሰቡም ከፍ ያለ ፋይዳ አለው:: ማህበረሰቡም የሌሎች አገራትን የጌጣ ጌጥ ማዕድናት ከመጠቀም ይልቅ የአገራቸውን የጌጣ ጌጥ ማዕድናት በመጠቀም ለሌሎች አገራት ማስተዋወቅ ይጠበቅባቸዋል::
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን ሰኔ 24/2022