ኢትዮጵያ ከምታመርታቸው የግብርና ምርቶች መካከል ቡና እንዲሁም የቅባት እህሎችን ጨምሮ ሌሎችንም ወደ ውጭ አገራት ገበያ በመላክ የውጭ ምንዛሪ ታገኛለች።ይሁን እንጂ ነዳጅን ጨምሮ በአገር ውስጥ ተኪ የሌላቸው የተለያዩ ምርቶችን ደግሞ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ወደ አገር ውስጥ የምታስገባ አገር ናት።በመሆኑም መንግሥት በማንኛውም መንገድ የሚያገኘውን የውጭ ምንዛሪ በአብዛኛው ለነዳጅ ግዢ የሚያውል መሆኑም ይታወቃል።
ኢትዮጵያ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ወደ አገር ውስጥ ከምታስገባቸው ምርቶች መካከል ቀዳሚውን ድርሻ የሚይዘውና ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪን የሚጠይቀው ነዳጅ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በአሁኑ ወቅት የመንግሥትን ኢኮኖሚያዊ አቅም ከመፈታተን ባለፈ ወገቡን እያጎበጠው የመጣ ከፍተኛ ወጪ እንደሆነ ይታመናል።በተለይም በአሁኑ ወቅት መንግሥት በአንድ ወር ውስጥ ብቻ እስከ 12 ቢሊዮን ብር ዕዳ ተሸክሞ ነዳጅን ወደ አገር ውስጥ እያስገባ እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
በኢትዮጵያ ያለው የነዳጅ ምርቶች ዋጋ ከጎረቤት አገራት ጋር ሲነጻጸር አነስተኛ መሆኑን በማንሳት ይህም ምርቱን ለህገ ወጥ ንግድ እንዳጋለጠው፣ በጥቁር ገበያ እንዲቸበቸብና በተለያየ መንገድ ነዳጅ ከአገር ውጭ እንዲወጣ ምክንያት እንደሆነ የነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን የሥራ ኃላፊዎች ገልጸው፤ ለዚህም መንግሥት ለነዳጅ ድጎማ የሚያወጣውን ከፍተኛ ወጪ ለመቀነስ በጥናት የታለመ የነዳጅ ድጎማን እንደ መፍትሔ አስቀምጧል ይላሉ።
ታዲያ መንግሥት መፍትሔ ነው ያለውን የታለመ የነዳጅ ድጎማን ሲያነሳ አሁን ያለውን የኑሮ ውድነት ይበልጥ እንዳያባብሰውና ሌሎች ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ቀውሶች እንዳይፈጠሩ ምን መደረገ አለበት ስንል ላነሳነው ጥያቄ የምጣኔ ሀብት ምሁራን ምላሽ ሰጥተዋል።
ከዓለም አቀፍ የነዳጅ ዋጋ አንጻር ነዳጅ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚሸጥበት ዋጋ እርካሽ መሆኑን የሚናገሩትና ለዚህም መንግሥት በነዳጅ ላይ ሲያደርግ የነበረው ድጎማ ቀላል ግምት የሚሰጠው ባለመሆኑ ሊመሰገን ይገባል›› በማለት ሀሳባቸውን ያካፈሉን የኢኮኖሚክስና የፖለቲካል ሳይንስ ባለሙያ አቶ ወሰንሰገድ አሰፋ ናቸው፡፡
እንደሳቸው ማብራሪያ፤ ምንም እንኳን በአገር ውስጥ ያለው የነዳጅ ዋጋ ከዓለም አቀፉ የነዳጅ ዋጋ ጋር ሲነጻጻር ቅናሽ ቢሆንም ከአገሪቷ የመክፈል አቅም ጋር ሲነጻጸር ግን አሁንም ውድ እንደሆነ ነው።መንግሥት ድጎማውን በሚያነሳበት ጊዜ ደግሞ አሁን ያለው የነዳጅ ዋጋ ውድነት በእጥፍ ሊጨምር ይችላል፡፡
የነዳጅ ዋጋ በእጥፍ በሚጨምርበት ወቅትም ነገሮች እየተካረሩ ይሄዳሉ።በከተሞች አካባቢ በተለይም ከ70 በመቶ በላይ አሽከርካሪዎች በሚገኙበት አዲስ አበባ ከተማ ላይ አሁን ካለው ከትራንስፖርት ዋጋ መናር ባለፈ የአቅርቦት እጥረትም ይታያል።ስለዚህ የነዳጅ ዋጋ ሲጨምር ለትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች ማስተካከያ ካልተደረገላቸው አሽከርካሪዎች አገልግሎት የመስጠት ፍላጎታቸው ይቀንሳል።ከዚህ ባለፈም ሌሎች በዘርፉ የመሳተፍ ፍላጎት ያላቸው ሰዎች የመግባት ዕድላቸው እየጠበበ ይመጣል፡፡
የነዳጅ ዋጋ ሲጨምር ነዳጅ ብቻውን የሚጨምር እንዳልሆነ ያነሱት አቶ ወሰንሰገድ፤ የነዳጅ ጭማሪ የተለያዩ ነገሮች ዋጋ አብሮ እንዲጨምር የማድረግ ትልቅ አቅም እንዳለው ገልጸው፤ ነዳጅ ለማንኛውም እንቅስቃሴ ወሳኝና አስፈላጊ መሆኑን ነው ያነሱት። ስለዚህ ነዳጅ ዋጋው ሲጨምር ሌሎች ምርቶችም በተመሳሳይ ዋጋቸው ይጨምራል፡፡
መንግሥት ይህን ድጎማ ሲያነሳ በተመሳሳይ ምን ላይ ሊያውለው እንዳሰበ ማንሳቱ ተገቢ እንደሆነ የገለጹት አቶ ወሰንሰገድ፤ ለአብነትም አርሶ አደሩን የሚደጉም ከሆነ ምርትና ምርታማነትን በማምጣት የምርት መጠን ከፍ ይላል።ቤቶች ልማት ላይ
ካዋለውም እንዲሁ የቤት ፍላጎትና አቅርቦቱ ሊጣጣም ይችላል።ሌሎች የህብረተሰቡ መሰረታዊ ፍላጎቶች በሆኑ ዘርፎች ላይ ማዋል ከቻለና ምርት ከተትረፈረፈ የኑሮ ውድነቱን ማርገብ ይቻላል።
የነዳጅ ድጎማው መነሳት የትራንስፖርት ዋጋውን ከፍ ቢያደርገውም መንግሥት ድጎማውን አንስቶ ሌሎች መሰረተ ልማቶችን ማሟላት ከቻለ ዜጎች በትራንስፖርት ያጡትን በምግብ ሸቀጦችና በሌሎች ሊያገኙት ይችላሉና ህመሙ ዘልቆ አይሰማቸው ይሆናል።ነገር ግን መንግሥት ‹‹ለነዳጅ የማወጣው ወጪ ከአቅሜ በላይ ስለሆነብኝ ነው›› በማለት ገበያው ላይ ምንም አይነት እንቅስቃሴ ካላደረገ የነዳጅ ዋጋ መጨመር ትልቅ የሆነ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ መናጋትን ይፈጥራል፡፡
ነዳጅ ትልቅ አቅም ያለው መሆኑን በመግለጽ የነዳጅ ዋጋ መጨመር በህብረተሰቡ ላይ ከሚያሳድረው ጫና ባለፈ መንግሥትንም ሊነቀንቅ እንደሚችል ያነሱት አቶ ወሰንሰገድ፤ በተለይም የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማዕከል የሆነችውና ብዙ ተሽከርካሪዎች ያሉባት አዲስ አበባ ከተማ እንደመሆኗ የነዳጁ ጉዳይ በዋናነት አዲስ አበባ ከተማ ባሉት ነዋሪዎች ይበረታል።ከአዲስ አበባ ከተማ የሚነሳው የኑሮ ውድነት ደግሞ በየአካባቢው ይዳረሳል።የትራንስፖርት አገልግሎት እጥረት ሲፈጠር ደግሞ ህገወጥነት ይበራከታል።ይህም ማህበረሰቡን ላልተገባ ወጪ የሚዳርገውና ወደ መማረር ይወስደዋል።
‹‹መንግሥት ድጎማውን ሲያነሳ ተያይዘው ሊሰሩ የሚገባቸውን በርካታ ሥራዎች በመሥራት ህብረተሰቡ የነዳጅ ድጎማው በመነሳቱ የሚሰማው ህመም ዘልቆ እንዳይሰማው ማድረግ ይቻላል›› ያሉት አቶ ወሰንሰገድ፤ ለአብነትም በግብርናው ዘርፍ ኢትዮጵያ ካላት መሬት የታረሰው እጅግ በጣም ትንሹ እንደመሆኑ በዘርፉ ሰፋፊ ሥራዎች እንዲሠሩ በማድረግ ዜጎች በቀላሉ ምግብ ማግኘት እንዲችሉና የምግብ ሸቀጦች ዋጋ እንዲቀንስ በማድረግ ማመጣጠን ይቻላል።ነገር ግን መንግሥት ድጎማውን አነስቶ ዝም ካለ ግን የሚፈጠረው ቀውስ ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኢኮኖሚክስ ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶክተር መንገሻ ያዮ በበኩላቸው በዓለም አቀፍ የነዳጅ ዋጋ መጨመርና በሌሎችም ምክንያቶችም ጭምር መንግሥት በነዳጅ ላይ ያደርግ የነበረውን ድጎማ ለማንሳት መገደዱን ጠቁመው፤ መንግሥት ወደዚህ ውሳኔ የመጣው የተለያዩ ጥናቶችን ታሳቢ በማድረግ እንደሆነ ይናገራሉ።
ዶክተር መንገሻ መንግሥት ይህን እርምጃ ከወሰደ በኋላ ሊመጣ የሚችለውን ችግርና ይህን እርምጃ ባይወስድ ደግሞ የሚኖረውን ጫና አስመልክቶ ጥናት የተደረገ እንደሆነ ያምናሉ።አያይዘውም ምናልባትም ጫናውን መቋቋም የሚቻልበት ሌሎች አማራጮችን መውሰድ አይቻልም ወይ የሚል ጥያቄ በማንሳት፤ ድጎማው ከመነሳቱ ጋር ተያይዞ ሊመጣ የሚችለውን የኑሮ ውድነት ከግምት ውስጥ በማስጋት ሌሎች አማራጮች መታየት የሚገባቸው እንደነበሩ አንስተዋል።
አማራጭ ካሏቸው መካካልም ድጎማውን ለማንሳት ማዘግየትም አንዱ እንደሆነ ነው ያነሱት።ይሁንና መንግሥት ድጎማውን ለማንሳት የተገደደ በመሆኑ የፖሊሲ ለውጥ ማድረግ አለብኝ ብሎ ሲነሳ መወሰድ የሚገባቸው ጥንቃቄዎች አሉ።ምንም እንኳን በአሁን ወቅት ድጎማውን ሙሉ በሙሉ የማያነሳው ቢሆንም የቁጥጥሩ ሁኔታ አደገኛ እንደሆነና ምን ያህል ተዘጋጅቷል የሚለውን ጥያቄ በአግባቡ መመለስ አለበት፡፡
የቁጥጥር አቅማችን ደካማ በሆነበት አሰራር የነዳጅ ድጎማ በሚነሳበት ወቅት በአግባቡ ለማስተናገድ አዳጋች እንደሚሆን የገለጹት ዶክተር መንገሻ፤ ነዳጅ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ሁሉም ዘርፎች የሚጠቀሙበት እንደመሆኑ በእያንዳንዱ የማህበረሰብ ክፍል ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድር እንደሆነ ነው የሚገልፁት።አሁን ባለው ሁኔታም መንግሥት የዋጋ ግሽበቱን ለማረጋጋት የቱንም ያህል እርምጃ ቢወስድም የዋጋ ንረቱን መቆጣጠር አልተቻለም።አሁን ደግሞ የነዳጅ ድጎማውን በሚያነሳበት ወቅት የኑሮ ውድነቱ ይበልጥ ሊባባስና ጫናው የበለጠ ሊሆን ይችላል፡፡
በአገሪቷ አሁን ያለውን ጦርነት ጨምሮ በተለያየ ሁኔታ ህዝቡ ላይ የተፈጠረ ጫና መኖሩን አስታውሰው ‹‹የደነገጠ ማህበረሰብና የደነገጠ ኢኮኖሚ ነው ያለን›› ይላሉ።በደነገጠ ኢኮኖሚና በደነገጠ ማህበረሰብ ላይ ይህን መጨመር ደግሞ ምናልባትም ኢኮኖሚው መቆጣጠር ወደማይቻልበት የኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ እንዳይገባ ያላቸውን ስጋት ገልጸዋል።
ስለዚህ የነዳጅ ድጎማው በሚነሳበት ወቅት የኑሮ ውድነቱ እንዳይባባስ መንግሥት የተለያዩ አማራጮችን በመጠቀም ሙሉ ለሙሉ ማስቀረት ባይችልም የዋጋ ንረቱን መቆጣጠር የሚችልባቸውን መንገዶች በመከተል የተለያዩ እርምጃዎችን መውሰድና መሥራት እንደሚገባው ያነሳሉ።ለአብነትም የገበያ ስርዓቱን የስርጭትና የቁጥጥር ሥራውን አጠናክሮ መቀጠል ካልቻለ የሚወሰደው እርምጃ መልሶ ችግር ፈጣሪ እንዳይሆን ስጋት አለኝ ይላሉ፡፡
የሚመጣው ችግርም ሙሉ ለሙሉ ማጥፋት ባይቻልም መቀነስ የሚቻልበት የፖሊሲ አማራጮችን ማቅረብ ያስፈልጋል።ከዚህ ባለፈ ግን የቁጥጥር ስርዓቱ ጠንካራ መሆን እንዳለበት አሳስበዋል።
መንግሥት ለነዳጅ የሚያወጣው ወጪ ከፍተኛ መጠን ያለው እንደመሆኑ ይህንን ወጪ አስቀርቶ ወደ ሌሎች ዘርፎች በማዋል የሚመጣው ውጤት ቀላል ግምት የሚሰጠው አለመሆኑን ጠቅሰው፤ ምርትና ምርታማነትንም ሆነ ሌሎች መሰረተ ልማቶችን ማምጣት በአጭር ጊዜ ውስጥ ሊከወኑ የማይችሉና ረጅም ጊዜን የሚጠይቁ እንደሆኑ አንስተዋል።ስለዚህ ከነዳጅ ላይ የሚነሳው ድጎማ በግብርናውም ይሁን በሌሎች ዘርፎች አውሎ ከዘርፉ ተጠቃሚ ለመሆን የወደፊት ዕቅድ ይሆን እንጂ የአጭር ጊዜ መፍትሔ ሆኖ የነዳጅ ድጎማ በመነሳቱ ምክንያት የሚከሰተውን የኑሮ ውድነት ያስቀረዋል የሚል ዕምነት የሌላቸው መሆኑን አስረድተዋል፡፡
መንግሥት አሁን ካለበት ጫና በመነሳት በተለይም የውጭ ምንዛሪ እጥረትና ሌሎች ጫናዎችንም ጭምሮ መቋቋም እንዲያስችለው ችግሩን ማካፈል የግድ ሆኖበታል።ይሁንና በድጎማው ተጠቃሚ ያልሆነው አካል ሸክሙን መልሶ ወደ ማህበረሱ ያወርደዋል።ይህን ለመቆጣጠር ደግሞ የቁጥጥር ስርዓቱ የዳበረ ካለመሆኑ ጋር ተያይዞ ችግሩ እንዳይባባስ ያላቸውን ስጋት አስቀምጠው፣ ‹‹መንግሥት የተወሰነውን የህብረተሰብ ክፍል ደጉሜያለሁ በሚል ዝም ማለት የለበትም።ምክንያቱም ሌሎች ላይ የተፈጠረው ጫና መልሶ ዝቅተኛ ኢኮኖሚ ባላቸው የማህበረሰብ ክፍሎች ላይ ሊተላለፍ ስለሚችል ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል›› ብለዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ድጎማ የሚደረግበት መንገድ በራሱ ጥንቃቄ የሚያስፈልገው ስለመሆኑም ያስረዳሉ።እርሳቸው እንደሚሉት፣ የሚደጎሙት አካላት በራሳቸው በህገወጥ መንገድ ላለመጠቀማቸው እርግጠኛ መሆን ስለማይቻል በቂ የሆነ የቁጥጥር ስርዓት መዘርጋት ያስፈልጋል።ከቁጥጥር በተጨማሪም አማራጮችን መጠቀም የግድ ነው።ነዳጅ ከገጠር እስከ ከተማ እያንዳንዱን ዘርፍ የሚያንቀሳቅስ እንደመሆኑ የተለየ ጥንቃቄን ያስፈልገዋል።በነዳጅ ላይ የሚደረገው የፖሊሲ ለውጥም እንደማንኛውም የፖሊሲ ለውጥ መታየት የሌለበት እንደሆነም አስረድተዋል።
በነጻ ገበያ ስርዓት መንግሥት የነዳጅ ድጎማን ለምን አነሳ ብሎ ማለት የማይቻል መሆኑን ጠቅሰው፤ ነገር ግን መንግሥት ሌሎች በርካታ የማህበረሰብ ጥያቄዎችን መመለስ ያለበት ስለመሆኑ ያስረዱት አቶ ወሰንሰገድ፤ በዋናነት ዜጎች በልተው ማደር እንዲችሉ፣ ትራንስፖርት እንዲያገኙና ሌሎች መሰረታዊ ፍላጎቶቻቸውን ማሟላት የሚችሉበትን መንገድ ማመቻቸት የመንግሥት ግዴታ መሆኑን በመግለጽ ሌሎች የማካካሻ አማራጮች ካልተወሰዱ የነዳጅ ድጎማ መነሳቱ የኑሮ ውድነቱን ሊያባብሰው እንደሚችል ነው ያስረዱት፡፡
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ሰኔ 22/2014