የቀለም እንቦጭ

የእንቦጭ አረም የጣናን ወዝ መጥምጦ በውስጡ የያዛቸውን ፍጥረታት ሕይወት ስጋት ላይ እንደጣለው ሁሉ፣ የቀለም እንቦጭም በትምህርት ሥርዓታችን የዘራው እንክርዳድ ለማህበራዊ መስተጋብራችን ተረፈና “በእውር በቅሎ ቃጭል ተጨምሮን” አስተረተብን። ሙሽት ያነሰው አዲስ ምጣድ እንጀራ እንደሚያኖኩረው ያለ “ቢጎርሱት ከአንጀት ጠብ የማይል፤ ቢጠጡት ጥም የማይቆርጥ፤ ቢለብሱት ከርዛት የማያስጥል ትውልድ በቀለ” እያሉ ከአጥቢያ እስከ ጀንበር መግቢያ የሚኮኑኑ ሰዎችን ስሰማ

ውል አልባ ክስሽን ምነው ማቅለምሽ፤

እንደው በደፈናው ስትቀቢ ከረምሽ።

ብሎ መዝፈን ይከጅለኛል። ስንኙ የተሳፈረበትን የሃሳብ ጀልባ ስንበረብር ከማን ምን አይተን ለማን ምን እናስተምር? የሚል ጥያቄን ቢጭርም የነገሩ ስር ወዲህ ነው። ሀገር በቀል እውቀቶቻችንን ኋላቀር ናቸው ብለን ልጅ ከማይደርስበት አርቀን ቀብረን ከርዳታ ጋር በተቀበልነውና በልካችን ባልተሰፋ ሥርዓተ ትምህርት ስንወላከፍ ጠልፎ ጣለንና የቀለም እንቦጩ በግላጭ ታየ።

“የጎባጣ አሽከር አጎንብሶ ይሄዳል” ነውና የትምህርት ሥርዓታችን ጉድፍ ለባህላችንና ለፖለቲካ ልምምዳችን የማይሽር ቁስል አውርሶት መላ እስኪጠፋን ድረስ ከንፈር ለሚያስነክስ ፀፀት ዳረገን። እናም ባልንጀሬ … “ሁሉን ቢያወሩት ሆድ ባዶ ይቀራል” እንጂ ሀገራችን የተቃኘችበትን ሥርዓተ ትምህርትንስ “ላም እሳትን ወለደች” የሚለው አባባል የሚገልፀው ይመስለኛል።

እንዳንተወው ሀገር የምትቆምበት ምሰሶ ሆነ፣ እንዳንይዘው ማር በእሬት ተለውሶ ጎመዘዘን፤ የቸገረ ነገር… በዚህ ጉዳይ ዙሪያ በአንድ ወቅት ሙዓዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ስለ ትምህርት ፖሊሲያችን የሰጠውን ምክረ ሃሳብ እማኝ መጥቀሱ ሚዛን ይደፋልና በሰላ ልቦና እንስፈረው። ከመንገድ ዳር ድንች የሚሸጡት ሴትዮ ርሃባቸውን ለማስታገስ የተሰለፉትን ተማሪዎች ሲያዩ እናታዊ ኀዘኔታቸው ከገፃቸው እየተነበበ “እንዳይፈጃችሁ ልጆች” አሉና ትኩሱን ድንች ለመጀመሪያው ልጅ ሲያቀብሉት እጁን አራግፎ ለሁለተኛው አሳለፈለት፤ እሱም ቢሆን ከእጁ ሳያቆይ ለሶስተኛው አሻገረለት። ትኩሱ ድንች እንዲህ እንዲህ እያለ ከመጨረሻው ተማሪ ቢደርስም ከሆድ አትግባ ብሎታልና ከመጀመሪያው ልጅ ዘንድ ዞሮ ተመለሰ።

ተማሪዎች ትኩሱን ድንች አብርደው ለመብላት አለመሞከራቸው ምሳሌነቱ ለእኛው ማህበረሰብ ነው። መንግሥት የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል በሚያደርገው ርብርብ ድጋፋችንን ከመስጠት ይልቅ እንደ ግመል ሽንት ወደ ኋላ ማፈግፈጋችን ሳያንስ የትምህርት ሥርዓታችን ያለበትን ችግር እየነቀስን መተቸት እንጂ የበኩላችንን ሃላፊነት ስንወጣ አይስተዋልም። ከያዝነው ሥራ እንዳያናጥቡንና ሲያለቅሱ ለማባበል በሚል ሰበብ ስልካችንን በመስጠትና እድሜያቸውን የማይመጥን የቴሌቭዥን ዝግጅቶችን በማሳየት የልጆቻችንን ናላ የምናዞር ስንት ቤተሰቦች አለን? በመማር ማስተማሩ ሂደትስ ያሉበትን ደረጃ እንከታተል ይሆን?

ከዚህ ጋር ተያይዞ አንድ የኖርዌይ ተወላጅ ወዳጄ ያጫወተችኝን ሀገርና ትውልድ በቀና የትምህርት ሥርዓት የሚሰናሰሉበትን ብልሀት ማንሳቱ አግባብ አለው። ወዳጄ በአቅራቢያዋ ካለው የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለመቀጠር ባመለከተች ጊዜ መምህርነትን ለምን እንደመረጠች ሲጠይቋት “ሁሉም ወላጆቼ መምህራን ስለሆኑ ፈለጋቸውን መልቀቅ አልሻም” ስትል የሰጠቻቸው መልስ አላጠገባቸውምና ህፃናትን ለማስተማር ሁለተኛ ዲግሪ እንደሚያስፈልግ ነግረው አሰናበቷት። ተስፋ ሳትቆርጥ ጽናት ባጎለመሰው ሞራል ማስተርሷን ተማረችና ዳግመኛ ደጃቸውን ጠናች። አሁንም መልሷ ያው ነበር መምህር የመሆን ህልም! የትምህርት ቤቱ ባለቤቶች ግን እንደበፊቱ “ሾላ በድፍኑ” ብለው ሊያልፏት አልፈቀዱም። ይልቁንም ዝንተዓለም ከልቦናዋ የሚከተብ መልዕክት ነገሯት እንጂ።

“ህፃናትን ማስተማር ማለት በሚያልፍ ቀን የማያልፍ የትውልድ ስብራት እንዳይገጥማትና መሠረቱ በፀና አለት ገንብቶ ኖርዌይን ማስቀጠል ነው። እናም አንቺ መምህር የመሆን ፍላጎትሽ ላይ የሀገር ፍቅር አብሲት ጣይበትና ተመልሰሽ ነይ” ሲሉ ደራሽ ውሃ ያመጣውን ጊዜያዊ ስሜቷን አርቀው ሸኟት።

ሕዝቤ ሆይ አየህልኝ?… “ነገርን ከስሩ ውሃን ከጥሩ” እንደሚባለው የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ከፈለግን የትኩረት ክትትላችንን ከህፃናት መጀመር ይኖርብናል፤ አሊያ ግን “ሆድ ከጠገበ እግር ሞኝ ነውና” መድረሻውን አስቦ መነሻውን ያላበጀ የትምህርት ሥርዓት ሄዶ ሄዶ እንደ ህዳር አህያ ማንም ያሻውን የሚጭነው ትውልድ እንዲበቅል ምክንያት ይሆናል።

እርግጥ ነው የመጣንበት ሁነት እንደሚያስረዳው ነጋ ጠባ ጭንቀታችን የከፍተኛ ትምህርት ተቋሞቻችን ናቸው። እውነት እናውራ ከተባለ የሚፈለገውን ያህል የትምህርት ጥራት ዩኒቨርሲቲዎቻችን ውስጥ አለ? ዩኒቨርሲቲዎቻችን ሀገር ተረካቢ ትውልድ እያፈሩ ናቸው?። የፎቶ ኮፒ ቤቶች ከመምህራን የፈተናውን ጥያቄ ገዝተው አዙረው ለተማሪ በውድ ዋጋ ሲሸጡ ያየሁበት አጋጣሚ አለ። የፈተና ጥያቄዎች ከአመት አመት ያው ናቸው። መምህራኑ አማካሪም ፈታኝም ሆነው ሳለ የተማሪውን የመመረቂያ ጹሁፍ ገንዘብ እየተቀበሉ የሚሠሩ መኖራቸው ያደባባይ ሀቅ ነው። ይህ ድርጊታቸው መንፈሱ የዛለና መምህርነት ባጣ ቆይ ሙያ እንደሆነ የሚያምን ትውልድ እንድናፈራ ያደረገው። የዚህን ዳፋ ገና በልጅነት ማለዳ ፊደል ስንቆጥር የማስታውሰውን ለፍርድ እንዲመች ላካፍላችሁ።

የድጎማ መምህራችን “ሀበል ፒዙ ለበል ፒዙ ” እያለ ግራ ግራውን ሲያስተምረን የተመለከተው ርዕሰ መምህራችን እንደወረቀት በነጣ ብሩህ አዕምሮአችን ለምን እንክርዳድ እንደሚዘራ ቢጠይቀው “በ180 ብር ደመዎዝ እየኖርኩ በቀና ልብ ላስተምር አልችልም” አለ የቀነጨረ ትውልድ ለሀገር ውድቀት መንስኤ መሆኑ ግድ ሳይሰጠው። ታዲያ ከዚህ በላይ የቀለም እንቦጭ ምን አለ”?

ሀብታሙ ባንታየሁ

 አዲስ ዘመን ህዳር 21/2017 ዓ.ም

 

 

Recommended For You