በዛሬው አዲስ ዘመን ድሮ ዓምዳችን በ1958 ዓ.ም የታተሙ ጋዜጦችን ዓይተናል።የመረጥናቸው ዜናዎች በማኅበራዊ ጉዳዮች ማለትም በምግብ መጠጥና ትራንስፖርት ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ናቸው።እነዚህም በዚያ ዘመን በትራንስፖርቱ ረገድ ከታሪፍ ውጪ በማስከፈልና ትርፍ በመጫንና የሚታዩ ችግሮችን የሚያሳዩ ናቸው።
ይህ ችግር አሁንም ድረስ በዘርፉ ከሚስተዋሉ ችግሮች አንዱ ሆኖ ይታያልና በዚያ ዘመን የነበረውን እውነታ ከአሁኑ ጋር ለማነፃፀር እንዲረዳ አቅርበነዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አውቶቡሶች ሥራቸውን አቁመው ዋሉ
በአዲስ አበባ የሚገኙ የአንበሳ የማመላላሻ አውቶቡስ አሠሪዎችና ሠራተኞች መካከል በተፈጠረው አለመግባባት ምክንያት ከትናንት በፊት የኩባንያው ሠራተኞች ሥራቸውን አቁመው ነበር።
የአንበሳ የማመላላሻ አውቶቡስ፤ በትናንትናው ቀን ለሕዝቡ የሚሰጠውን ግልጋሎት በማቋረጡ ምክንያት በአዲስ አበባ ውስጥ የሚገኙ ታክሲዎች ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ አደባባይ እስከ አራት ኪሎ፤ ከዚያም በቅርብ ለሚገመት ርቀት ላለው ሥፍራ ከመደበኛው ሃያ አምስት ሳንቲም የመጓጓዣ ክፍያ ዋጋ ወደ አንድ ብር ከፍ ሲያደርጉት፤ ሩቅ ናቸው ለተባሉ ሥፍራዎች ደግሞ የክፍያው ዋጋ ከብር በላይ ሆኖ ውሏል፡፡
በብዙ የሚቆጠር የአዲስ አበባ ኗሪ ሕዝብ ሠራተኛው፤ ተማሪውና እንዲሁም ነጋዴውም ወደ ተግባሩ ለመሠማራት፤ እንደቀድሞው አውቶቢሱን ሲጠባበቅ ቆይቶ፤ በከተማው ውስጥ የማይዘዋወር መሆኑን ከተረዳ በኋላ፤ የከተማው ታክሲ ነጂዎች የጠየቁትን መክፈል ግድ ሆኖበታል፡፡
በዚሁ በድንገት በተፈጸመ የሥራ ማቆም ምክንያት ኩባንያው በብዙ ሺህ የሚቆጠር የገቢ ኪሣራ የደረሰበት መሆኑ ታወቀ።በአሠሪዎችና በሠራተኞች መካከል የተፈጠረው አለመግባባት አስፈላጊውን ጥናት የሚደረግበት ቢሆንም፤ የአንበሳ የማመላለሻ አውቶቡሶች ሥራቸውን ከቀትር በኋላ ቀጥለዋል፡፡
በአሠሪዎችና በሠራተኞች መካከል የተፈጠረው አለመግባባት ለማስወገድ የሕዝባዊ ኑሮ ዕድገት ሚኒስቴር ርምጃ የወሰደ ሲሆን፤ የመቶ አለቃ ሚካኤል አመዴ በዚሁ ጉዳይ ላይ በሰጡት አጭር ማብራሪያ ‹‹ የሥራው ማቆም በድንገት የተፈጠረ ለመሆኑ ጉዳዩ በመጣራት ላይ ነው›› ብለዋል።
አንበሳ አውቶቡስ አሠሪና ሠራተኞች የኅብረት ሥራ ስምምነት የተፈራረሙት ኅዳር 1 ቀን መሆኑ ይታወሳል።
(ታኅሳስ 5 ቀን 1958 የወጣው አዲስ ዘመን)
የመንጃ ፍቃድ የሌላቸውና ትርፍ የጫኑ ሹፌሮች ተቀጡ
ከኢትዮጵያ ወሬ ምንጭ
ጅማ፤ በጅማ ከተማ ውስጥ ንጋቱ ወልደ ትንሳይ የተባለ ሹፌር ከተፈቀደለት ክብደት በላይ 14 ሰው አሳፍሮ፤ የግል ጥቅምን ብቻ በመሻት የተሳፋሪውን ሕዝብ መብት ሳይጠብቅ ባደረገው ጥፋት በጅማ አውራጃ ፖሊስ ትራፊክ አባሎች ተይዞ ቀርሳ ወረዳ ፍርድ ቤት ከቀረበ በኋላ ጥፋቱ ስለተረጋገጠበት ፶ ብር መቀጫ ከፍሎ ለሁለት ወር መኪና እንዳይነዳ ተበይኖበታል፡፡
እንዲሁም ጌታቸው ተክለማርያም የተባለ ሹፌር ከተፈቀደለት ክብደት በላይ ፱ ሰዎች አሳፍሮ ሲጓዝ በትራፊክ ፖሊስ ተይዞ ጅማ ከተማ ሁለተኛ ወረዳ ፍርድ ቤት ቀርቦ ፵፭ ብር መቀጫ እንዲከፍል ተፈርዶበታል፡፡
ከዚህም ሌላ ጀማል አህመድ የተባለ ሹፌር ከተፈቀደለት ክብደት በላይ ፭ ሰዎች አሳፍሮ ስለተገኘ በትራፊክ ፖሊስ ተይዞ በዚሁ ፍርድ ቤት ከቀረበ በኋላ፤ ጥፋቱ ስለተረጋገጠበት ፳፭ ብር መቀጫ እንዲከፍል የተፈረደበት መሆኑን በደረሰን ጽሁፍ ሊታወቅ ተችሏል።
* * *
ድሬዳዋ፤ በድሬዳዋ ከተማ ውስጥ የትራንስፖርት ሕግ በመተላለፍ የመንጃ ፈቃድ ሳይዙና ከተወሰነላቸው ጭነት በላይ ትርፍ በመጫን ሲዘዋወሩ በመገኘታቸው በትራፊክ ፖሊሶች ተከታታይነት የተያዙት ፯ ሰዎች ወደ ወረዳው ፍርድ ቤት ቀርበው ፫፻፭ ብር መቀጣታቸውን የድሬዳዋ አውራጃ ግዛት ፖሊስ ጽ/ ቤት በሰጠው ዜና ገልጧል፡፡
* * *
ሀገረሕይወት፤ ስሜነህ ተስፋዬ ፪ኛ ሽፈራው በቀለ የተባሉ የከባድ መኪና ሹፌሮች የትራፊክ ደንብ በመተላለፍ ከተፈቀደላቸው በላይ እያንዳንዳቸው አሥር ሰዎች አሳፍረው በመገኘታቸው አንደኛው ፶ ብር ሲቀጣ ሁለተኛው ደግሞ ፵ ብር መቀጫ ከፍሏል።
(ኅዳር 28 ቀን 1958 የወጣው አዲስ ዘመን)
የድሬዳዋ ዳቦ ጋጋሪዎች ስምምነት ፈረሙ
ከኢትዮጵያ ወሬ ምንጭ፡፡
ድሬዳዋ፤ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ስለ ዋጋ መቆጣጠር ድሬዳዋ ከተማ በሚገኘው ቅርንጫፍ መስሪያ ቤት ኅዳር ፲፯ ቀን ስብሰባ ተደርጎ ነበር።የስብሰባውም ዓላማ በከተማው ውስጥ የሚገኙት ዘጠኝ ዳቦ ጋጋሪዎች የሚጋግሩት ዳቦ ኪሎ ግራም ከፍና ዝቅ በማለቱ የተነሳ ሲሆን፤ ዳቦ ጋጋሪዎች በስብሰባው ላይ ተገኝተው በአንድ ዓይነት ኪሎ ግራም እንዲጋግሩ አንድ ስምምነት ፈርመዋል፡፡
(ኅዳር 28 ቀን 1958 የወጣው አዲስ ዘመን)
የመጠጥ ቤቶች ጉዳይ ለፓርላማ ቀረበ
ከኢትዮጵያ ወሬ ምንጭ
የህግ መወሰኛ ምክር ቤት ስለ ሴተኛ አዳሪዎችና መጠጥ ቤቶች መስፋፋት ላይ ከተነጋገረ በኋላ፤ ጉዳዪን አግባብ ያለው የመወሰኛው ምክር ቤት ኮሚቴ ከሕዝባዊ ኑሮ ዕድገት ሚኒስቴር ልዩ ኮሚቴ ጋር እንዲያጠና ትናንት ባደረገው ስብሰባ ወሰነ፡፡
በኢትዮጵያ የሴተኛ አዳሪዎችና እንዲሁም የመጠጥ ቤቶች መስፋፋት የሚያስከትለውን ፕሮብሌም ገልጸው፤ ምክር ቤቱ በጉዳዩ መክሮበት አንድ መፍትሔ እንዲገኝለት በማለት ለምክር ቤቱ ሐሳብ ያቀረቡት የተከበሩ አቶ አመዴ ለማ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አባል ናቸው።
ይኸው ጉዳይ በቀደምትነት የሕዝባዊ ኑሮ ዕድገት ሚኒስቴር ከውጭ አገር ባስመጣቸው ኤክስፐርቶች በመጠናት ላይ መሆኑም ተገልጿል።
(ኅዳር 28 ቀን 1958 የወጣው አዲስ ዘመን)
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን ሰኔ 21/2014