የአገር ህልውና በዋናነት ከአገረ መንግስት ጋር የሚተሳሰር ሲሆን፤ በሥሩ የመንግስት ድንበር ማስጠበቅን ጨምሮ የአገር ሰላም እና መረጋጋት እንዲሁም የኢኮኖሚ ዕድገትን ይመለከታል።ነጋድራስ ባይከዳኝ በ1909 ዓ.ም በታተመው ‹‹የመንግስት እና የሕዝብ አስተዳደር›› በተሰኘው መፅሃፋቸው ‹‹ኢትዮጵያ ራሷን በኢኮኖሚ ካልቻለች ነፃ አገር ናት ማለት አይቻልም›› ሲሉ አስፍረዋል።ይህንን ያሉት ከ100 ዓመት በፊት ቢሆንም፤ አንዳንዶች አሁንም ድረስ ያልዳበረ ኢኮኖሚ እና ያልተረጋጋ የዲሞክራሲ ስርዓት በመኖሩ የኢትዮጵያ ህልውና ተጠብቋል፤ ሉዋላዊነቷ ተከብሯል ለማለት አያስደፍርም ሲሉ ይደመጣሉ፡፡
በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ህልውናዋን አስጠብቃ እንደአገር ቆማ ሶስት ሺህ ዓመታትን ያስቆጠረች፤ ሕዝቡም እርስ በእርስ የተጋመደ ወደፊትም የማይነጣጠል መሆኑ ይገለፃል።በተቃራኒው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድን ጨምሮ ሌሎች ምሁራንና ፖለቲከኞች ጥንቃቄ ካልተደረገ አገሪቷ ለመበተን በቋፍ ላይ ስለመሆኗ ይናገራሉ።
በአዲስ ወግ የውይይት መድረክ ላይ በጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ፅህፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትሩ ዶክተር ቢቂላ ሁሬሳ እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ ህልውናዋ አደጋ ላይ ወድቋል።አጣብቂኝ ውስጥ ገብታም ኢትዮጵያውያን አድነዋታል።አባቶች የኢትዮጵያን ሕልውና ለማስጠበቅ ዕልህ አስጨራሽ ትግል አካሒደው ሕይወታቸውን ሰውተው አሁን ላለችበት ደረጃ አድርሰዋታል፡፡
አሁን ደግሞ የውስጥ እና የውጪ ጠላቶች አስበውበት ኢትዮጵያን ለማዳከም ከፍተኛ ፕሮጀክት ቀርፀዋል።ፕሮጀክቱን የቀረፁት ገንዘብ መድበው፣ የሰው ኃይል እና ሌሎች በቂ ዝግጅቶች አድርገው በስፋት እየሰሩበት መሆኑ ግልጽ ነው፤ በመሆኑም መላው ኢትዮጵያውያን ይህንን ተረድተው ከመንግስት ጎን በመሆን በጥንቃቄ የአገርን ሕልውና ማስቀጠል እንደሚኖርባቸው ይመክራሉ።
የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር አቶ ተስፋዬ በልጅጌ በበኩላቸው እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ ፖለቲካ የፅንፈኝነት ሰለባ ሆኗል።ያለመደማመጥ ጫፍ ለጫፍ ቆሞ መጓተት፤ የአፈሙዝ እና የአፈና አስተሳሰብ ለዘመናት ተንሠራፍቶ ቆይቷል።ይህም የአገር ሕልውናን አደጋ ላይ ጥሏል።ይህንን ችግር ለማለፍ በማህበራዊ፣ በፖለቲካው፣ በፀጥታ እና በደህንነት ጉዳይ ላይ አሁንም ትልልቅ ሥራዎች መሠራት አለባቸው።ነገር ግን ከምንም በላይ ገመድ መጓተቱ ቀርቶ በውይይት በማመን፤ የሃሳብ ሽግግር ማምጣት ይገባል ይላሉ።
የኢትዮጵያ ብሮድካስት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ፍሰሃ ይታገሱ፤ ፅንፍ የሆኑ አቋሞችን ለማቀራረብ ውይይት እና ክርክር በመጨረሻም በወሳኝ ጉዳዮች ላይ መግባባት ይገባል ይላሉ።አገር በሶስት ምሶሶዎች ላይ መቆም አለባት።የመጀመሪያው ነፃ ብቃት ያላቸው ተቋማት መኖራቸው ወሳኙ ነው።
የሲቪል ሰርቪስ፣ የዴሞክራሲ ተቋማትም ሆኑ የአገር ደህንነት እና የፀጥታ ተቋማት ጠንካራ መሆን እንደሚጠበቅባቸው አመልክተው፤ በመንግስት እና በሕዝብ መካከል ያለ ስምምነት እና መተማመንም የአገር ህልውናን ለማስቀጠል ወሳኝ ስለመሆኑ ያብራራሉ።
ተቋማት በተገቢው መልኩ አልተገነቡም። በተጨማሪ በታሪክ፣ በሰንደቅ ዓላማ እና በሌሎችም ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ አገራዊ መግባባት የለም።የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታውም ላለፉት ሃምሳ አመታት ቢጀመርም ተመልሶ ወደ ኋላ እየተቀለበሰ አገሪቷ በርካታ ችግሮች ሲገጥሟት ቆይቷል።ለዚህ መፍትሔው መወያየት እና መግባባት የአገር ህልውና ዘላቂነትን ለማረጋገጥ በቀጣይ ትውልድ ላይ መሥራት ይገባል።በውይይት የሚያምን እርስ በእርስ እንደወንድም የሚተያይ፣ የሚዋደድ፣ የሚከባበር እና የሚደጋገፍ ሕዝብ እንዲኖር ከትምህርት ቤት ጀምሮ መሠራት አለበት።
ዴሞክራሲን ለማስፈን አገርን ለማስከበር፣ የአገርን አንድነት ለማስጠበቅ፤ አገርን ከብተና ለመታደግ ብሔራዊ አቅሞች ወሳኝ ናቸው።ብሔራዊ አቅም ሲባል የመጀመሪያው ዲፕሎማሲ ሲሆን ሌላኛው ኢንፎርሜሽን ነው።እንዲሁም ወሳኝ የሆነው ደግሞ ኢኮኖሚው፣ ፀጥታ እና ደሕንነት መሆናቸው ይነገራል።እነዚህ በተገቢው መልኩ መገንባት ብቻ ሳይሆን መጋመድ እና መሬት ላይ መውረድ አለባቸው።
በተለይ ለፀጥታ እና ደህንነት ልዩ ትኩረት መሰጠት አለበት ሲባል፤ መከላከያ የሁሉም ብሔር ብሔረሰቦችን ተዋፅኦ የተረጋገጠበት መሆን እንዳለበት በሕገመንግስቱ አንቀፅ 38 ተቀምጧል።ይህ ብቻ አይደለም፤ መከላከያ በብቃት፣ በጥራት፣ ተወዳዳሪ እና ትውልድ ተሻጋሪ መሆን አለበት።አቅሙ ጦርነት ውስጥም ሆነ ፀጥታን ማስከበር ተግባር ላይ ከመሰማራቱ ቀድሞ የሚፈራበት ደረጃ ላይ መድረስ አለበት።ለዚህ ደግሞ የፀጥታ እና ደህንነት ተቋሙ በተገቢው መልኩ ተዋፅኦን ማዕከል አድርጎ መገንባት እንዳለበት ይገለፃል።ተዋፅኦ መኖር አለበት ሲባል ከብቃት ጋር እንጂ፤ እንዲሁ ለተሳትፎ ብቻ ማካተት ከጥቅሙ ጉዳቱ እንደሚያመዝንም ይገለፃል።ብቃትን መሰረት አድርጎ የሚኖር ተዋፅኦ በየአካባቢው ለሚኖር ግዳጅ አፈፃፀም ትልቅ ጉልበት ከመሆኑም በተጨማሪ፤ ከሕዝብ ጋር ያለው ግንኙነት ጠንካራ እና ሕዝቡ ማንኛውም ፀጥታ አስከባሪም ሆነ መከላከያን የኔ ነው ብሎ እንዲያምን ያደርጋል።
ከፀጥታ እና ደህንነት በተጨማሪ በዋናነት የአገር ህልውናን ለማስቀጠል ወሳኙ ጠንካራ ኢኮኖሚን መገንባት እንደሆነ የሚናገሩት ደግሞ የፕላን እና ልማት ሚኒስትሯ ዶክተር ፍፁም አሰፋ ናቸው።እንደ ዶክተር ፍፁም ገለፃ፤ ኢኮኖሚው ሲነሳ አሁን የዓለም ተፅዕኖ ቀላል አይደለም የዕዳ ጫና እና የሥራ አጥነት ችግሮች በፖሊሲዎች ማሻሻል አስፈላጊ ነው።ፖሊሲዎችን ማሻሻል ማህበራዊ ፍትሕን ለማረጋገጥ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት እና የማክሮ ኢኮኖሚ ማረጋጋት ወሳኝ መሆኑን ያስረዳሉ።
የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ የሥርዓተ ፆታ እኩልነት፣ ድህነት ተኮር ዕርዳታ መስጠት አገርን በማረጋጋት በኩል ወሳኝ ሚና እንደሚጫወቱ በመጠቆም፤ በኢኮኖሚው ላይ መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት እንደተጀማመረው በግብርና ላይ ኢንቨስት ማድረግ እና መሠረተ ልማት በማስፋፋት እኩል ተደራሽነት እና ፍትሃዊነትን ሲረጋገጥ የአገር ሕልውና ጥያቄ ውስጥ የሚገባበት አጋጣሚ እንደማይፈጠር ያመለክታሉ።
የግል ዘርፉ የአጭር ጊዜ ጥቅም ሳይሆን ረዥም ጊዜን ማዕከል አድርጎ አስተማማኝ ሥራዎች ላይ ትኩረት ማድረግ ይኖርበታል ካሉ በኋላ ጊዜያዊ ግንባታዎች እና አጫጭር ስራዎች ላይ ትኩረት ከማድረግ ይልቅ አምራች ኢንዱስትሪው ግብርና ላይ ትኩረት ማድረግ ለአገር ኢኮኖሚ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያለው ስለመሆኑ ያብራራሉ።
ኢኮኖሚውን ማሳደግ እየተፈጠረ እና እየታየ ካለው የውጪ ተፅዕኖ ለመላቀቅ ወሳኝ መሆኑን በማመልከት ለአገር ሕልውና ኢኮኖሚው ላይ አተኩሮ መስራት አማራጭ የማይቀመጥለት ጉዳይ ስለመሆኑም ይናገራሉ።
በቀድሞ ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ በዛብህ ገብረየሱስ በበኩላቸው፤ ለአገር ህልውና ወሳኞቹ ተቋማት ናቸው።አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በሰዎች፣ በአደረጃጀቶች እና በአሰራር ስርዓቶች ተሰናስለው በህግ ተመስርተው ለሕዝብ ካላገለገሉ የአገር ጉዳይ አሳሳቢ እንደሚሆን ያመለክታሉ።በሞያ እና ውል ባልተገባበት የፖለቲካ ፍላጎት መቀላቀል ሳቢያ፤ የመንግስት ሥራ እና ፖለቲካው መቀላቀሉ እንደትልቅ ችግር የሚታይ መሆኑን በማመልከት፤ የአገር እና የሕዝብ ጥቅም ተገቢውን ሥፍራ ሲያጣ ችግር ፈጥሮ አገርን ለአደጋ ሊያጋልጥ የሚችልበት ሁኔታ ስለመኖሩ ያስገነዝባሉ።
የመንግስት ሥራ የሚቋቋመው በህግ ነው።በሕግ ለህዝብ ተገቢ አገልግሎት ይሰጣል።ሕግ ሲተገበር መንግስት ብቻውን አድራጊ ፈጣሪ የሚሆንበት ሁኔታ ቀርቶ ተገልጋይ ሕዝብም የመገልገል መብቱ የሚከበርበት ዕድል ይኖራል።ለዚህ ሰብአዊ ልማት አስፈላጊ ነው።ፍትሃዊነት እና እኩልነት ለማስፈን፤ ህግ በእኩልነት ሁሉም ላይ እንዲተገበር እንዲሁም ማንም ሆነ ማን በህግ ተገቢውን አገልግሎት ያልሰጠ እና ውጤት ያላመጣ ተጠያቂ እንዲሆን ምቹ ሕግ ማውጣትና ያንንም ማስተግበር ሲቻል፤ የአገር ህልውና ማረጋገጥ አዳጋች እንደማይሆን ያመለክታሉ።
በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የዲፕሎማሲ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር አቶ እንዳለ ንጉሴ በበኩላቸው እንደሚናገሩት፤ የአገር ህልውናን ለማረጋገጥ በሕግ መመራት ያስፈልጋል።ጠንካራ ተቋምም ሆነ ኢኮኖሚ መሰረቱ ህግ ነው።የሕጎች ሁሉ የበላይ የሆነውን ሕገ መንግስት ማሻሻል የሚገባም ከሆነ አሻሽሎ እንደየጋራ የቃልኪዳን ሰነድ በመውሰድ በዛ ላይ ተመስርቶ ተቋማትም ሆነ ኢኮኖሚው እንዲሁም ዲፕሎማሲው የሚመራበትን መንገድ መፍጠር ይቻላል።የጋራ በግልፅ የሚታወቅ ሕግ ሳይቀመጥ ተቋማትም ሆነ ዲፕሎማሲው ላይ ትልልቅ ስራዎችን ማከናወን እና መቆጣጠር አዳጋች ስለመሆኑም አመልክተዋል።
ብዙዎች እንደሚያነሱት የሚሰሩት ሥራዎች ውይይት እና መግባባት ላይ መመስረት አለባቸው፤ ተቋማትን ለማስተካከል ብዙ ሥራዎች ቢከናወኑም ሥራው ቀጣይነት እንዲኖረው በጠንካራ የሕግ መሰረት ላይ መመስረት አለበት።እኩል ተጠቃሚነት፣ ኢትዮጵያውያን በአገራቸው የመኖር ነፃነት፣ ዘላቂ ሰላም እና ዕድገት ለማምጣት ግልፅ አሰራር እና ሕግ ማስቀመጥ ያስፈልጋል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕልኸኛ ነው። ፅናት እና ወኔም ያለው ህዝብ ነው። በመሆኑም ይህንን ወኔውን ወደ ሥራ በማምጣት ጠንካራ ኢኮኖሚ እንዲገነባ ማድረግ ይገባል። ነገር ግን ይህንን ማድረግ ካልተቻለ፤ አገርን ከውጪ እርዳታ እና ብድር ተላቃ በሁለት እግሯ እንድትራመድ ማስቻል አዳጋች ይሆናል።እንዲሁም እልሁን በግጭት ማስተንፈስ ላይ ትኩረት ከተደረገ ውጤቱ በተቃራኒው ይሆናል።ነፍስ እየጠፋ አገር እየወደመ የኢትዮጵያን ህልውና ማፅናት አዳጋች ይሆናል።
አገርን እያነደደ ስላለው የጉያ ረመጥ ተቆጭቶ ለልማት መነሳሳት የግድ ነው።ነገር ግን መነሳሳት ጥፋትን በጥፋት ለመመለስ፣ ለበቀልና ነፍስ ለማጥፋት ሳይሆን አገር በመገንባት፤ ህግ ማክበርና ማስከበር ላይ በመትጋት ነው።ምንም እንኳ በዋናነት ህግ ማስከበር የመንግስት ኃላፊነት ቢሆንም፤ የአገር ሕልውና እንዲረጋገጥ በየአካባቢው፤ እያንዳንዱ ግለሰብ ለህግ መከበር ሚናውን መወጣት አለበት።ዜጎች ለኢኮኖሚ ዕድገት የተቻለውን ሚና በመወጣት እና ጠንካራ ሥራ በመስራት የአገርን ህልውና ማስቀጠል ያስፈልጋል።
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ሰኔ 21 ቀን 2014 ዓ.ም