የመኽሩ ወራት የአገራችን አርሶ አደሮች ዘገር የሚጨብጡበት ሳይሆን እርፍ ጨብጠው የዓመት ጉርሳቸውን ለማምረት ደፋ ቀና የሚሉበት ነው። በተለይም የትግራይ አርሶ አደሮች የእርዳታ ስንዴ ጥገኛ ላለመሆን የመኽሩን ወቅት በሥራ የሚያሳልፉበት ሊሆን በተገባ ነበር። የሕወሓት አሸባሪ ቡድን ግን የመኽሩን ወቅት ለጦርነት የመረጠው ይመስላል።
አሸባሪው የሕወሓት ቡድን በዙሪያው ያሉ አርሶአደሮችን ወደ ጦርነት እየመለመለ ለማስገባት ከሚጠቀምበት ስልት አንዱ ረሃብ ነው። አስቀድሞ ረሃብ እንዲፈጠር የተለያዩ አሻጥሮችን ይሠራል። ከአሻጥሩ አንዱ በተቆጣጠራቸው አካባቢዎችና በዙሪያ ገባው ጦርነት በመክፈት ምርት እንዳይመረት ማድረግ ነው። ከዚያም ይህን ያህል ሕዝብ ለረሃብ አደጋ ተጋልጧል እያለ ዓለምአቀፍ እርዳታ መሰብሰብ ነው።
በመቀጠልም በረሃብ ምክንያት ለምኖ የሚያገኘውን ርዳታ (ስንዴም ይሁን ገንዘብ) ቅድመ ሁኔታ እያስቀመጠ ለተጎጂዎች ይቆነጥርላቸዋል። እርዳታ የሚያደርግላቸው በረሃብ አደጋ ውስጥ ላሉት ሁሉ ሳይሆን የእርሱን ዓላማና ትግል ለሚደግፉ ብቻ ነው። ከዚያ በመቀጠል ከረሃብና ከችግር ለመውጣት ታግሎ ነጻ መውጣት አማራጭ የሌለው ጉዳይ እንደሆነ ይሰብካል።
ሰዎች ላለመራብና የራሳቸውንና የቤተሰባቸውን ሕይወት ለማትረፍ ሲሉ የሚቆነጠርላቸውን እርዳታ እየወሰዱ ሳይወዱ በግድ የጉዳዩ አስፈጻሚ ይሆናሉ።
ቡድኑ በበጋው ወራት ከሰበሰበው እርዳታ እየቆነጠረ ለጦርነት የመለመላቸውን ተዋጊዎች አሰልጥኖ በአፋር፣ በአማራና በኤርትራ አዋሳኝ አካባቢዎች በማስፈር ቀጣናውን ውጥረት የነገሰበት አድርጎ መሰንበቱ የሚታወስ ነው። አሁን ደግሞ በአካባቢው ያሉ አርሶ አደሮች አምርተው እንዳይጠቀሙ የመኽሩን ወቅት ጠብቆ የግብርናውን ሥራ ለማስተጓጎል እየተዘጋጀ ይገኛል። ትንኮሳዎችንም እያደረገ ነው።
ሕዝብ በረሃብ አንገቱን እንዲደፋ፣ ችግሮች እንዲባባሱ፣ እንዳይታረስ፣ እንዳይመረት፣ የተፈናቃዮች ቁጥር እንዲጨምር፣ መንግሥት ተፈናቃዮችን በመርዳት እንዲወጠር ለማድረግ አልሞ እየተንቀሳቀሰ ነው። ከዚህ በተጨማሪ በትግራይና በአጎራባች አካባቢዎች የሚኖሩ አርሶ አደሮች እየተለመነ በሚመጸውታቸው እፍኝ የማይሞላ ስንዴ የእርሱ ተገዢ እንዲሆኑ የነደፈው አንድ ስትራቴጂ መሆኑን ከቀደመ ልምዱ መረዳት አይከብድም።
የመንግሥት የልማትና የእድገት ስትራቴጂዎች ግባቸውን እንዳይመቱ ማድረግ ሌላው ዓላማው ነው። ኢትዮጵያ በሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሃግብር ትኩረት ከሰጠቻቸው አምስት የኢኮኖሚ ዘርፎች አንዱ ግብርና ነው። የግብርና ምርትን አስተማማኝና ተከታታይነት ባለው መንገድ ለማሳደግ እቅድ ተይዞ ወደ ሥራ ከተገባ ሁለትና ሶስት ዓመታት ተቆጥረዋል። በነዚህ ዓመታት በምግብ አቅርቦት ራስን ለመቻልና ከዚያም አልፎ የውጭ ምንዛሬ ለማምጣት የሚያስችሉ ስትራቴጂዎች ተነድፈው አበረታች ውጤቶች መ ታየት ጀምረዋል።
ግብርናው ከመኽር ወቅት ሥራ ተላቆ በመስኖ የማምረት ባህል እንዲያዳብር በርካታ ሥራዎች ተሠርተዋል። በተለይም ከውጭ የሚገባውን እና ከፍተኛ ምንዛሬ የሚጠይቀውን ስንዴ ለማስቀረት እየተደረገ ያለው የበጋ መስኖ ልማት ከፍተኛ ውጤት እየታየበት ነው።
27 ዓመት ሀገር ሲያስተዳድር በነበረ ጊዜ የእርዳታ ስንዴን እየለመነ የመመገብ ልክፍት የተጸናወተው አሸባሪው ቡድን ዛሬ ኢትዮጵያ የግብርናውን ምርታማነት ለማሳደግ ያሳየችው ጅምር ምቾት ስላልሰጠው አርሶ አደሩ እንዳያመርት በአንድ እጁ መሳሪያ ይዞ እየተዋጋው ሲሆን ሌላው እጁን ደግሞ እንደለመደው ለስንዴ እርዳታ ወደ ውጭ እየዘረጋው ይገኛል።
ባለፈው ሳምንት የአውሮፓ ሕብረት የአደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽነር ጃኒዝ ሌነርሲስ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድና ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጋር ተወያይተዋል። ወደ መቀሌ ሄደው ከአሸባሪው ቡድን አመራሮችም ጋር ተመሳሳይ ውይይት ማድረጋቸው ይታወሳል።
የውይይቱ ዝርዝር ፍሬ ሃሳብ ባይገለጽም ኮሚሽነር ጃኒዝ ሌነርሲስ በተለይም ወደ ትግራይ ክልል የሚገባው እርዳታ መሻሻል እንደታየበት ተናግረዋል። በቀጣይም የፌዴራል መንግሥቱ የነዳጅ አቅርቦትና የጥሬ ገንዘብ እጥረት እንዲፈታ የበኩሉን ትብብር እንዲያደርግ ለጋዜጠኞች ከሰጡት መግለጫ መረዳት ተችሏል።
ይህ ሲታይ አሸባሪው ሕወሓት የሰላም መንገዶችን ለመከተል የተዘጋጀ ይመስል ነበር። ብዙም ሳይቆይ የአሸባሪው ቡድን ቃል አቀባይ ጌታቸው ረዳ በፌስቡክ ገጹ ካሰፈረው ጽሑፍ መረዳት የቻልነው ኮሚሽነር ጃኒዝ ሌነርሲስ እና ደብረጽዮን ገብረማርያም ገንቢ ውይይት ማድረጋቸውን ነው። ከአንድ ቀን በፊት ደግሞ መድሃኒትና ሌሎች ሰብአዊ እርዳታ ይዘው ወደ ትግራይ የሚበሩ አውሮፕላኖች ትግራይ ምድር ላይ እንዳያርፉ አስጠንቅቋል። ያም ብቻ ሳይሆን በሰሜን ወሎ የተወሰኑ ወረዳዎች ወረራውን በማስፋፋት ልክ እንደከርሞው የእርሻ ወቅቱን በማወክ ላይ ይገኛል።
ቡድኑ ከፌዴራል መንግሥት ጋር የመደራደር ፍላጎት እንዳለው አመራሮቹ በተለያዩ ጊዜያት ከሚያስተላለፉት መልእክት እንረዳለን። ሁኔታው ግን ከማስመሰል የዘለለ አይደለም።
ቡድኑ ሁልጊዜም የሰላም አማራጭን በማጣት ተገዶ ወደ ጦርነት እንደገባ ይናገራል። ፌዴራል መንግሥት በከበባ ውስጥ እንዳስቀመጠው፤ የመሰረተ ልማት አገልግሎት እንዳሳጣው፣ የእርዳታ እህል እንዳይገባ መተላለፊያ በሮች እንደተዘጉበት ይገልጻል። እንዲህ አይነት ዲስኩር የሚያደርገው ደግሞ ምእራባውያንን ለማታለል ብቻ ሳይሆን እራሱን የትግራይ ሕዝብን ጭምር ወደ ጦርነት ማስገባት ሲፈልግ እንደሆነ የቀደመው ልምዱ ይነግረናል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ሰሞኑን ለፓርላማ አባላት ባደረጉት ንግግር መንግሥት እስከ አሁን ድረስ ከአሸባሪው ሕወሓት ጋር ምንም አይነት ድርድር አለመጀመሩን አስረድተው፤ ነገር ግን ችግሮችን በንግግርና በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት መንግሥታቸው ምን ጊዜም ዝግጁ እንደሆነ ተናግረዋል።
የመንግሥት እጆች አሁን ሳይሆን ገና ድሮ በዚህ መጠን ቀውስ ውስጥ ከመገባቱ በፊት ለሰላም የተዘረጉ መሆናቸው በርካታ ማስረጃዎችን ማቅረብ ይቻላል። የሰላም አምባሳደር እናቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች መቀሌ ድረስ በመሄድ ያቀረቡትን የሰላም ጥሪ ማስታወስ ያስፈልጋል።
ጦርነትን ባህላዊ ጨዋታው አድርጎ የሚመለከት ይህ ቡድን የሰላምና የእርቅ ፍላጎት እንዳለው እያስመሰለ ለጦርነት ሲዘጋጅ መክረሙ የሚያስገርመን ላይሆን ይችላል።
እውን አሸባሪው የሕወሓት ቡድን ከመጀመሪያ ጀምሮ የሰላም አማራጭ አጥቶ ነው ወደ ጦርነት የገባው ወይስ በጦርነት የበላይነትን ወስዶ የኢትዮጵያን ሕዝብ ማንበርከክ የሚፈልግ የአምባገነኖች ስብስብ ስለሆነ ነው?
ቡድኑ የተንኮል ፊት አውራሪ፤ የበደል፣ የአሻጥር፣ የግፍና የጭካኔ መምህር ስለመሆኑ አምና እና ካቻአምና በአማራና በአፋር ክልሎች በንጹሃን ዜጎች፣ በእንስሳትና በእጽዋት ላይ ሳይቀር የፈጸማቸውን ግፎች ብቻ ማስታወስ በቂ ነው።
‹‹ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ›› እንዲሉ አሸባሪው ቡድን አሁንም ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የሥነልቦና ዝግጅት ያለው አይመስልም። እንደለመደው ዘንድሮም የመኽሩን ወቅት ለጦርነት መርጦ ትንኮሳዎችን እያደረገ ይገኛል። የተጸናወተው የክፋት መንፈስ ጥሩ ነገር ስለማያሳስበው እንደ ከርሞው ሁሉ ዘንድሮም በዙሪያ ገባው የሚገኙ አርሶ አደሮችን አምርተው እንዳይበሉ ስጋት ደቅኖባቸዋል።
አሸባሪው ቡድን ላለፉት ዓመታት የእርዳታ ስንዴ (የምግብ እህል) ተማጽኖ ሲያደርግ ለሰማው የምግብ እህል እንዳይመረት እንቅፋት ይሆናል ብሎ አያስብም። እያመረቱ ለሕዝቡ መትረፍ ሚችሉት የትግራይ አርሶ አደሮች በልመና ከሚገኝ ስንዴ እፍኝ የማትሞላ ስንቅ እየቋጠረችላቸው እንዲዋጉ አስገድዷቸዋል።
አምና ቃላቸውን ከሰጡ አብዛኛዎቹ ምርኮኞች ያረጋገጥነው ከቤተሰብ አንድ ሰው በጦርነቱ ካልተሳተፈ የእርዳታ ስንዴ የማይሰጠው መሆኑን ነው። አሸባሪው የሕወሓት ቡድን በእርዳታ የሚያገኘውን ስንዴ እንደ አሞሌ ጨው እያላሰ ሰዎችን ወደ ራሱ ለማቅረብ ስለሚጠቀምበት በአካባቢው የምግብ እህል እንዲመረት ፍላጎት እንደሌለው አንዱ ማሳያ ነው። በመሆኑም ይህንን እኩይ ተግባር ለማስቆም ከመንግሥት ጎን መቆም ከሁሉም ሰላምና ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ የሚጠበቅ ይሆናል።
ሜላት ኢያሱ
አዲስ ዘመን ሰኔ 21 ቀን 2014 ዓ.ም