ብርጋዴር ጄኔራል ዋሲሁን ንጋቱ የተወለዱት በቀድሞ የወለጋ ጠቅላይ ግዛት በሆሮ ጉዱሩ አውራጃ በ1933 ዓ.ም.ነበር። የአንደኛ እና የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸው በትውልድ አካባቢያቸው በወለጋ አጠናቅቀዋል። በ1953 ዓ.ም. የሆለታ ገነት የጦር ትምህርት ቤትን ተቀላቅለው ብቁ የመከላከያ ሰራዊት የሚያደርጋቸውን ወታደራዊ ትምህርት ቀስመዋል። ብርጋዴር ጄኔራሉ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር የታንከኛ መሠረታዊ ትምህርት፣ ከፍተኛ የውጊያ መረጃ ትምህርት፣ የአውሮፕላን የአየር ቅኝት፣ የአየር በረራ ጠለፋ፣ ከፍተኛ የታንክ ትምህርት ተምረዋል።
በኢትዮጵያ መከላከያ ሚኒስቴር የቀድሞ ሠራዊት ውስጥ በተለያዩ የጦር ግንባሮችና የጦር ክፍሎች ለ30 ዓመታት ሀገራቸውን በማገልገል ወታደራዊ ግዳጃቸውን በብቃትና በትጋት እና በታማኝነት የተወጡ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንንም ናቸው። በተጨማሪ በወታደር አዛዥነታቸው ዘመን ከሕዝብ ጋር በቅርበት በመሆን በአካባቢ ሠላም ዙሪያ ከሽማግሌዎች ጋር በመነጋገር መረጋጋትን በመፍጠር ይታወቃሉ።
በአማራ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች ፣ በትግራይም ሆነ በሌሎች ክልሎች ተዘዋውረው የወታደር አዛዥ ሆነው አገራቸውን አገልግለዋል። ብርጋዴር ጄኔራል ዋስይሁን የወቅቱን የፀጥታ እና የደህንነት ሁኔታን በተመለከተ፤ በተለይ በጋምቤላም ሆነ በምዕራብ ኦሮሚያ ጊምቢ ወረዳ ስለተፈፀመው ድርጊት ምን ይላሉ? ምን መደረግ አለበት ? በማለት አነጋግረናቸው እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል።
አዲስ ዘመን፡- በኢትዮጵያ ያለውን የፀጥታ እና የደህንነት ሁኔታ በሚመለከት ምን ይላሉ? ጋምቤላም ሆነ ኦሮሚያ ክልል ላይ ስለተፈፀመው ጥቃት ያልዎትን አስተያየት ይግለፁልኝ ?
ብርጋዴር ጀኔራል ዋስይሁን፡– የወቅቱ የኢትዮጵያ የሰላም እጦት ሲነሳ በዋናነት ይነሳል። ሕወሓት በሰላማዊ መንገድ ሁሉን ነገር መፍታት ሲቻል ጦርነት ከፍቷል። መንግሥት ለሰላም የሰጠውን ትኩረት በመናቅ ጦርነት በመክፈቱ ብዙ ጥፋት አስከትሏል። ይህ እጅግ በጣም ያሳዝናል። መንግሥት ፈልጎ ጦርነት ውስጥ አልገባም፤ መንግሥትን ያስገደደው የሽብር ቡድኑ ራሱ ሕወሓት ነው። አሁን ጦርነቱ ከተጀመረ አንድ ዓመት ከስድስት ወር አልፎታል።
ቡድኑ ሀገሪቱን ፈፅሞ አላስፈላጊ ጦርነት ውስጥ የከተታት፤ አቅምን ባለማወቅ እና በእብሪት ነው። በእርግጥ የትግራይ ሕዝብ ተበድሏል ከሚል ቁጭት እና ለትግራይ ሕዝብ ለመከላከል አይደለም። የትግራይ ሕዝብ ተበድሎ ቢሆን እንኳ ጦርነት ለመንግሥትም ሆነ ለተቃዋሚም ለማንም በፍፁም አይጠቅምም። ጦርነት እልቂት ነው። ኢኮኖሚን የሚያወድም ነው። ከጦርነት በፊት ቀድሞ መነጋገር ይሻል ነበር።
በሌላ በኩል በአንዳንድ ቦታዎች ላይ እየተፈፀመ ያለው ጥፋት አሰቃቂ ነው። መንግሥት ሆነ ብሎ ሕዝብን የሚበድል አይመስለኝም። በምዕራብ ኦሮሚያ በጊምቢ ወረዳ የተፈፀመው የሰው ልጅ ካላበደ በስተቀር በገዛ ወገኑ ላይ እንዲህ አይነት ግፍ ይፈፅማል ብሎ ለመገመት የሚያዳግት ነው። ሰውን አልፎ ተርፎ ሕፃናትን መግደል እጅግ በጣም የሚያሳዝን ነው። ሁሉም ሰላምን የሚወድ ኢትዮጵያዊ በሙሉ በዚህ ተግባር ማዘኑ አይቀርም። እኔም እንደሁሉም ኢትዮጵያዊ በዚህ ተግባር እጅግ በጣም አዝኛለሁ። በእኔ እምነት ይህ ድርጊት የተፈፀመው፤ መንግሥት ተከታትሎ በየወቅቱ እርምጃ ባለመውሰዱ ነው፡፡
የወታደር የጥቃት ዒላማዎች አሉ። ከዛ ውጪ የድሃን ቤት ማቃጠል እና ድሃን መግደል ለምን? ተነጋግሮ መግባባት ባይቻል እንኳን ወታደራዊ ዒላማን መጠቀም ሲቻል ሰላማዊ ሰዎችን ዒላማ ማድረግ ትልቅ ጥፋት ነው። ይህ ድርጊት በተደጋጋሚ በኢትዮጵያ ታይቷል። መንግሥት ትዕግስት አድርጓል።ነገር ግን ትዕግስትም ወሰን አለው። የችኮላ ውሳኔ ሳይሆን በተጨባጭ ማስረጃ የተገኘባቸው ላይ መንግሥት የማያዳግም እርምጃ መውሰድ አለበት።
መንግሥት ጥንቃቄ አድርጎ የድርጊቱ ፈፃሚዎች ላይ ተገቢውን እርምጃ መውሰድ ካልቻለ ድርጊቱ ይቀጥላል።
‹‹ትምህርት መስጠት ተገቢ ነው›› ይባላል። አጥፊዎች ቢሆኑም በእርግጥ ትምህርት መስጠት ያስፈልጋል። ነገር ግን ትምህርት ብቻ ሳይሆን ማንኛውም የሰው ልጅ ይፈራል። ሆነ ብሎ ቀይ መስመርን ያለፈ ካለ፤ መንግሥት ማስረጃ አስቀርቦ እርምጃ መውሰድ አለበት። ሻሸመኔ ላይ ተዘቅዝቆ ሰው ተሰቀለ። የሰቀሉት ላይ ምን እርምጃ ተወሰደ? አይታወቅም። በደቡብ በኩል አንድ ሰው ሚስቱን በጭካኔ በጩቤ ገድሏል ተብሎ ሞት እንደተፈረደበት ሰምቻለሁ። ሌሎች ላይም ወንጀል እየፈፀሙ ያሉ ቡድኖች ላይም እርምጃ በወቅቱ መወሰድ አለበት። የተፈረደባቸው ፍርድም ሊታወቅ ይገባል።
ማንም ሰው ከሕግ በላይ ሊሆን አይችልም። መንግሥት ሕግ ሲያስከብር ደግሞ መንግሥት ብቻ ሳይሆን የሃይማኖት መሪዎችም ተገቢውን ትምህርት በመስጠት ግዴታቸውን መወጣት አለባቸው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዳኞችን ሌባ ናቸው ብለዋል። መስረቅ ተገቢ ባይሆንም፤ ግድየለም ብሎ ማለፍ ይቻላል። በዚህ ጊዜ ስርቆትን ማለፍ ይችላል።ሰው በተጨባጭ የገደለ ግን በዛው በገደለበት ቦታ ሕጋዊ እርምጃ ሊወሰድበት ይገባል።ገዳዮች በተቃራኒው እንደሐረር ሰንጋ ታስረው መቀለብ የለባቸውም።በሶስት ምስክሮች ተረጋግጦ፤ በሶስት ዳኞች ተጣርቶ ከተፈረደ፤ እርምጃ መውሰድ የግድ ነው፡፡
በእኔ እምነት ከዚህ በኋላ የመንግሥት ትዕግስት መሰበር አለበት።ሰው የገደለ፤ ሰው ላይ ግፍ የፈፀመ ማንኛውም ሰው ላይ እርምጃ ካልተወሰደ በምንም መልኩ መንግሥትን መደገፍ ያስቸግራል።በጊምቢ በንጹሐን ዜጎች ላይ የተፈፀመው ዘግናኝ ድርጊት የኢትዮጵያን ሕዝብ ያሳዘነ ነው።በትክክል ተጣርቶ ተገቢው እርምጃ መወሰድ አለበት ብዬ አምናለሁ።ይህንንም በተደጋጋሚ እናገራለሁ።
አዲስ ዘመን፡- በምዕራብ ኦሮሚያ ዞን በጊምቢ ወረዳ የተፈፀመውን ጥቃት ሲያስቡ፤ የጋምቤላውም ሆነ ሌላውን ሲያዩ የእነዚህ ጥፋት ፈፃሚዎች ዓላማ እና ፍላጎት ምንድን ነው ብለው ይገምታሉ?
ብርጋዴር ጀኔራል ዋስይሁን፡– በእውነቱ እንደሚመስለኝ እነዚህ ሰዎች እያሉ ያሉት ‹‹ስልጣን እንፈልጋለን ነው፡፡›› ነገር ግን ስልጣን ሰው እየገደሉ የሚገኝ አይደለም።ይሔ ድርጊታቸው ሕዝብንም መንግሥትንም የናቁ መሆኑን የሚያሳይ ነው።‹‹ያለእኛ ለኢትዮጵያ የሚያስብ የለም፤ ትክክለኛ እኛ ብቻ ነን›› ይላሉ።ድርጊታቸው አረመኔያዊ ነው።ይህ አምባገነንነታቸው በሥርዓት በሕግ መስተካከል አለበት።ለኦሮሞ ወደ 47 ዓመታት ታግለናል ያሉት እንኳ አያዋጣንም ብለዋል።ከጦርነትም ሆነ ከሽምቅ ውጊያ ራሳቸውን ወደ ሰላም ጎዳና መርተዋል።
አማራ ምን አደረገ? በአማራ አካባቢ ለብዙ ጊዜ ኖሬያለሁ። አሁን ደግሞ ስልጣን ላይ የወጣው መንግሥት በሕዝብ የተመረጠ ነው። በሰላም መኖር ሲቻል እንዴት ኢትዮጵያዊ ኢትዮጵያዊን ይገድላል? ሸኔም ሆነ ሕወሓት ኢትዮጵያውያን ናቸው።ኢትዮጵያን ለመግዛት የመጣው ጠላት ፋሺስት እንኳን የኢትዮጵያን ሕግ ካከበረ የመኖር መብት አለው። በወለጋ ጠቅላይ ግዛት ውስጥ አማራዎች በመኖራቸው መገደል የለባቸውም። ሕግ እስካከበሩ ድረስ የመኖር መብት አላቸው። ከዚህ ውጣ ብሎ የመግደል ስልጣን ለማንም አልተሰጠም። ይሔ መንግሥትን መናቅ ነው።ማንም ሰው መሞት አይፈልግም። እርምጃ ከተወሰደ ደግሞ መቆጣጠር ይቻላል። ይህንን ማድረጋቸው በትክክል ከተረጋገጠ ደጋግሜ እንደተናገርኩት እርምጃ ሲወሰድ ሌላው ይፈራል።
አማራ ምን አደረገ? አማራ ገዢ መደብ ነበረ ይባላል። ያ አልፏል። አሁን የአማራም ሆነ የኦሮሞ አምባገነን መኖር የለበትም። ሕዝብ የመረጠው መንግሥት ሁሉም እኩል እንዲሆን ማድረግ አለበት። ይህ መቆም የሚችለው ወንጀለኞች ላይ አስተማሪ እርምጃ መውሰድ ሲቻል ነው። በዚህ ከቀጠለ አስቸጋሪ ነው። አሁንም ጥፋት እንደአሸን እየፈላ ነው። መንግሥት በየኬላው ወታደር ማቆም አይችልም።ነገር ግን እንዲህ ዓይነት ነገር እንዳይደረግ መንገር ማስረዳት፤ እንዳይደገም እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል።እኔ ኮር አዛዥ ሆኜ አማራ ክልል ባህርዳር ለብዙ ጊዜ ቆይቻለሁ። እዚህ አትኑር ውጣ ያለኝ የለም።
መንግሥት ለሕወሓትም ሆነ ለሸኔ ለሁሉም የሠላም ጥሪ አቅርቧል። ነገር ግን አልተቀበሉትም። ይህም ቢሆን በተደጋጋሚ እታች ድረስ በመውረድ በሚገባቸው ቋንቋ ሊነገራቸው ይገባል። ስለሰላም መስበክ እና ማስረዳት ያስፈልጋል። ጀግናው የመከላከያ ሠራዊት የሽብር ቡድኑን ሕወሓትን አይቀጡ ቅጣት ቀጥቶ የመጀመሪያውን ዙር ጨርሷል። አሁንም የጦርነት ዝግጅት እያደረጉ መሆኑ እየተነገረ ነው። ነገር ግን ጦርነት አይጠቅምም። ጥፋት ነው። የሚጠቅመው በሰላማዊ መንገድ ችግርን መፍታት ነው። ማስተማር ይጠይቃል። አባገዳዎችን እና ሽማግሌዎችን በመያዝ በየጎሳው በሚገባቸው ቋንቋ ማስተማር የግድ ነው። አሁንም በከተማም ሆነ በገጠር የሰላም ዘመቻ መታወጅ አለበት። እኛም አስራ አንደኛ ክፍል ሆነን ማርክሲስት ሌኒንስት እንማር ነበር። ማንንም በየትኛውም ደረጃ ላይ ያለውን ስለሰላም ማስተማር ይገባል።
አዲስ ዘመን፡- አደረጃጀቶች ላይ ችግር ካለስ መታየት የለበትም? በተለይ ቀድሞ መረጃ ካለ መጠበቅ እና መጠንቀቅ የነበረበት አካል ጥንቃቄ ሊያደርግ አይገባም?
ብርጋዴር ጀኔራል ዋስይሁን፡– ይገባል! ።እዛ አካባቢ ያሉ ታጣቂዎች፣ ልዩ ኃይሎቹም ሆኑ ሌሎቹ ምልክት ካዩ መጠበቅ አለባቸው። ያለበለዚያ ጥቃት ሊደርስ መሆኑ እየታወቀ በቸልተኝነት ድርጊቱ ከተፈፀመ፤ እያወቁ ተገቢውን ጥንቃቄ ያላደረጉትም ጭምር ተጠያቂ መሆን አለባቸው። ቢጠነቀቁ ኖሮ ይህ ሁሉ እልቂት አይደርስም ነበር። እያንዳንዱ ኃላፊነት ያለበት መጠየቅ አለበት።
ድንበር ላይ የሚደረግ ጦርነት ቀላል ነው። የሽምቅ ውጊያ እና የከተማ ውጊያ አስቸጋሪ ነው። ጠላት እና ደጋፊ አይለይም። የጫካ እና የበረሃ ውጊያም ያስቸግራል። የእነኚህም ጥፋት የእርስ በእርስ በመሆኑ እርግጥ ያስቸግራል። ነገር ግን እነዚህ እንደጠላት ጦር መታየት የለባቸውም ፤ ሽፍቶች ናቸው። እንኳን ወገን መሳሪያ ያልያዘ ንፁህ ዜጋ ቀርቶ፤ ጠላት እንኳ እጁን ካወጣ ተማርኬያለሁ ካለ አይገደልም። እነዚህ አጥፊዎች ጠላት እንኳን የማይፈፅመው የንቀት ተግባር በገዛ ወገን ላይ ፈፅመዋል። የሚታየው ቸልተኝነትም ትክክል አይደለም።
ይህንን ድርጊት ፈፃሚዎች እነ ሸኔ አሰልጥነው እና አስተምረው ትምህርት ቤት አስመረቁ ይባላል። ግብር እያስገበሩ እንደሆነም ይነገራል። ይህንን ሁሉ ሲፈፅሙ የሚተባበራቸው መዋቅር አለ ማለት ነው። የኦሮሚያ ግዛት ሰፊ ቢሆንም፤ ይህ ሁሉ ሲሆን እንዴት ዝም ይባላል? ሽፍታን ለመደምሰስ፣ አውሮፕላንም ሆነ መድፍ እንዲሁም ታንክም ሆነ ትልቅ መሣሪያ አያስፈልግም። አሰሳ አድርጎ መርምሮ አጣርቶ ማጠናቀቅ ይቻላል።
ኦሮሞ እንኳን ለራሱ ለኢትዮጵያ የሚሆን የዴሞክራሲ ሥርዓት አለው። አስመሮም ለገሰ የሚባል የሶስተኛ ዲግሪ ተማሪ የገዳ ስርዓት 200 ዓመታትን ፈጅቷል ከሚባለው የአሜሪካ የዴሞክራሲ ሥርዓት የተሻለ መሆኑን አጥንቶ አረጋግጧል። በዚሁ ጥናቱ ሶስተኛ ዲግሪውን አግኝቷል። ሰላም ለማስፈን የኢትዮጵያ ባህል ራሱ ምቹ ነው። ሽምግልና አለ። ፍርድ ይሰጣሉ። ስለዚህ በሀገር ላይ ሰላምን ለማስፈን ያለውን ባህል መጠቀም ይቻላል።
በሌላ በኩል የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሳይቀሩ ከሕግ በላይ አይደሉም፤ አመራርነት በእያንዳንዱ ነጥብ ላይ የራስን ጣቶች መቀሰርን ያስገድዳል።መሪ ስትሆን እያንዳንዱን ነገር መቆጣጠር ይገባል። በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ሆኖ ይህንን አሰቃቂ ድርጊት የሚፈፅሙትን የሚረዳ መኖር የለበትም።
በመንግስት መዋቅር ውስጥ ሆነው ይህንን የሚያደርጉት ምን ለማግኘት ነው? ማንም ቢሆን በኦሮሚያ የኦሮሚያን ባህል ጠብቆ መኖር ይችላል። ኢትዮጵያኖች አሜሪካ ሔደው ይማራሉ፤ ይኖራሉ። እኔም አሜሪካን ሄጄ ሁለት ዩኒቨርስቲዎች ገብቼ ተምሬያለሁ። ውጡ እናንተ የሚል የለም። ኢትዮጵያኖች አሜሪካን እየኖሩ በገዛ አገራቸው ለመኖር እንዴት ይከለከላሉ? ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ወለጋ፣ ሀረር … የትም ቦታ ላይ የመኖር መብት አለው። ነገር ግን የመንግሥት መላላት እና እርምጃ አለመውሰድ ዋጋ እያስከፈለ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ የአማራም ሆነ የኦሮሞ አምባገነን አያስፈልግም። ሁሉም እኩል ነው። ስልጣን የሚገኘው በምርጫ ነው። አማራ የኦሮሞን ጡት ቆርጧል፤ እንዲህ አድርጓል መባል የለበትም። የሚያዋጣን እውነት ድርጊቱ ተፈፅሞ ከሆነ ለታሪክ መተው ይሻላል። ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ ጥናት አጥንተው ኦሮሞ ጎንደርን በመቶ ለሚቆጠሩ ዓመታት መግዛቱን ፅፈዋል። እንደውም ጎንደርን ለ700 ዓመት የኦሮሞ ገዢ አስተዳድሮታል ብለው አጥንተዋል። የኋላውን አስቦ አማራዎች እንዲህ ገዝተውናል ማለት ኋላቀርነት ነው።
ቀደም ሲል የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት የነበሩት ኦቦ ለማ መገርሳ የኋላውን እያሰብን ወደ ፊት መሄድ አንችልም ብለዋል። ያለፈው አልፏል። ያለፈውን ለታሪክ መተው ይኖርብናል። አሁን ያለው አዲስ ሥርዓት እና አዲስ መንግሥት ነው። አዲስ ሥርዓት በመገናኛ ብዙኃን በቃል ብቻ ሳይሆን በተግባር የሚተረጎም መሆን አለበት። ከታች እስከላይ መዋቅሩን ማስተካከል በሁለት ቢላዋ የሚበሉ ጉቦኞች ካሉ መንግሥት ማፅዳት አለበት። የሕወሓት ርዝራዥ የሆኑ ችግር እንዲፈጠር፤ ሰላም እንዳይኖር፤ መንግሥት እርምጃ እንዳይወስድ የሚያደርጉ በሙሉ በትክክል ተጣርተው ከስልጣን መውረድ አለባቸው። ጠቅላይ ሚኒስትሩም ትክክለኛውን ሰው ለትክክለኛ ቦታ እንዲሆን ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል።
የሰው ልጅ በበሽታ፣ በጎርፍ እና በመሬት መንቀጥቀጥ በተፈጥሮ አደጋ ሊሞት ይችላል። ከዛ ውጪ ማንም ሰው ያለሕግ ውሳኔ ሰውን መግደል አይችልም። ይህ መንግሥትን መናቅ ነው።ለዚህ ደግሞ የተናቀው መንግሥት ስልጣን ላይ መሆኑን ማሳየት አለበት። በእርግጥ በመነፅር ወይም በኤክስሬ አጣርቶ አይቶ መሾም አይቻልም። ማንም ሌባ ሊሰበሰብ ይችላል።
ሰላምን የሚያደፈርስ አውቆ የሚያጠፋን ከመምከር እና ከመገሰፅም ያለፈ እርምጃ ያስፈልጋል።ሰላም ከገበያ የሚገዛ አይደለም። በተለይ የተከበረውን የሰውን ልጅ ነፍስ ያጠፋ ተገቢውን ቅጣት ማግኘት አለበት። እንደመንግሥቱ ኃይለማሪያም እና በ1997 በመለስ ዜናዊ ጊዜ በአደባባይ ሰው እንደተገደለው ያለፍርድ መግደል ትክክል አይደለም። ነገር ግን ሕግ ማስከበር ደግሞ የግድ ነው። ብዙ ምሁራን ተናግረዋል። ይህች አገር ያጣችው እና የምትሞተው በምግብ እጦት ሳይሆን በፍትሕ እጦት ነው። መንግሥት ይህንን ሕገወጥነትን ለማስቆም ይሠራል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። ሆነ ብሎ ሰው የገደለ ፤ መግደሉ ከተረጋገጠ ሊተው እና ምሕረት ሊደረግለት አይገባም።
አዲስ ዘመን፡- የፍትሕ መስፈን የሚጠቅመው ማንን ነው? ፍትሕ አለመስፈኑስ የሚጎዳው ማንን ነው?
ብርጋዴር ጀኔራል ዋስይሁን፡– ፍትሕ! ሰው የገደለ ሰው የሕዝብም የመንግሥትም ጠላት ነው። የሶስት ቀን ሕፃን መግደል የሚሰጠው ትርጉም ምንድነው? ይህንን የፈፀመ ሰው እርምጃ ካልተወሰደበት ምንም ዋጋ የለውም። ፍትሕ የለም። የጦር ሜዳ ውጊያ ሌላ ነገር ነው። እንዲህ አይነት ድርጊት መፈፀም ጦርነት አይደለም። ሽፍታነት፣ ጨካኝነት እና አረመኔነት ነው። እነዚህን ማስተማር ያስፈልጋል። እርምጃ እየተወሰደ ነው እየተባለ ነው። ነገር ግን መቀጣጫ እንዲሆኑ ማስቻል ያስፈልጋል። ያለበለዚያ ይኸው ተግባር ይቀጥላል። እንኳን የሰው ልጅ አውሬ በጫካ ውስጥ በሰላም የመኖር ስልጣን አለው። እኛ ሰዎች እንዴት እንገዳደላለን? መንግሥት በፍፁም እነዚህን መማር የለበትም።
የኦሮሞን ባህል ጠንቅቄ አውቃለሁ። ኦሮሞ ኩሩ ሕዝብ ነው። እነአብዲሳ አጋ፣ እነጀነራል ደስታ ገመዳ፣ እነኃይሌ ፊዳን የመሳሰሉ ጀግኖች የወጡት ከኦሮሞ ነው። ኦነግ ሸኔ የእነዚህን ጀግኖች ስም የሚያጠፋ ነው። እነሌንጮ ለታም ሆነ ዲማ ነገዎ ለ47 ዓመታት ሲታገሉ የነበረውን ትተው ፓርላማ ገብተዋል። ሰላም ካልሰፈነ ተጎጂው ሕዝብ ብቻ ሳይሆን መንግስትም ነው።
አዲስ ዘመን፡- ሸኔ ዓላማው እና ፍላጎቱ ምንድን ነው? ከሕወሓት ጋር ግንኙነት እንዳለውም ይታወቃል? የኦሮሞ ሕዝብን እና ወያኔን እንዴት ያዩታል?
ብርጋዴር ጀኔራል ዋስይሁን፡ – የሚገርመው ይሔ ነው።ኦሮሞ ነኝ የሚል እንዴት ከወያኔ ጋር ይገናኛል? ወያኔ እኮ ለ27 ዓመታት ከገዛ በኋላ ያለእኛ ኢትዮጵያን መምራት የሚችል የለም ብሎ በንቀት የሸፈተ ነው።ሸኔዎች ውስጥ የተማሩም አሉ ይባላል።እንዴት ከወያኔ ጋር እንደተባበሩ ግልፅ አይደለም።ድሮም ቢሆን ኦነግን ያባረረው ወያኔ ነው።በወያኔ የሥልጣን ዘመን ብዙ ቄሮዎች መስዋዕት ሆነዋል።እየተሳደዱ ተገድለዋል።ከወያኔ ጋር መተባበር ወያኔን ለመጣል የታገሉትን እና ብዙ ዋጋ የከፈሉትን የብዙ ቄሮዎችን ደም ደመከልብ ማድረግ ነው።
ወያኔ ‹‹ኦሮሞም አማራም ኢትዮጵያን መግዛት የለበትም፤ መግዛት ያለብን እኛ ብቻ ነን›› ብሎ ጦርነት አወጀ።የትግራይ ሕዝብ መቼ ተበደለ? የለውጡ መንግሥት በጀት አልከለከለም።እንደውም ከጦርነቱ በፊት ለማቋቋሚያ በሚል ለሌሎች ክልሎች ያልተሰጠውን ለትግራይ ማቋቋሚያ በማለት ወደ ሁለት መቶ ሚሊዮን ብር ተበጅቶላቸው ነበር። ይህ መንግሥት ምንም አላጠፋም። አሁንም የትግራይን ሕዝብ እየበደሉ ያሉት ራሳቸው ወያኔዎች ናቸው። ታዲያ ለራሳቸው በቅርብ ላለው ሕዝባቸው እንኳ ካልሆኑት ከወያኔዎች ጋር እንዴት ተባብሮ ሕዝብን ያጠቃል? በውጪ ያሉ የሸኔም ሆኖ የወያኔ ደጋፊዎች ድጋፋቸውን ማቆም አለባቸው በእነዚህ ሽፍቶች ኢትዮጵያ እየተጎዳች ነው።
ጦርነትን ከሦስት አስርት ዓመታት በላይ አይቻለሁ። ጦርነት ለማንም አይጠቅምም። እንኳ ኢትዮጵያን ለመሰለች ደሃ አገር ቀርቶ እነዩክሬንና ራሽያዎች ምን እንደሆኑ እየታየ ነው። ዩክሬንን አውቃታለሁ። ነገር ግን እንዲህ ጦርነት አፈራርሷት እንዳልነበረች ሆና ስመለከት በጣም አዝናለሁ። ትምህርት ቤቱም ሆስፒታሉም መሠረተ ልማቱ በሙሉ ወድሟል። አሁን ደግሞ በኢትዮጵያ ጦርነት እንዲኖር ማድረግ በእውነት ትልቅ ጥፋት ነው። በሌላ በኩል እንዲህ ዓይነት ግፍ መፈፀም ኦሮሞን ማዋረድ ነው። በእርግጥ ሸኔ ኦሮሞን አይወክልም። ኦሮሞ ጨዋ እና ኩሩ ሕዝብ ነው። አማራም ጨዋ ሕዝብ ነው። ተዘዋውሬ አይቻለሁ። ባህርዳር ኮረም መቶ ሺህ ጦር እመራ ነበር። አማራም ሆነ ኦሮሞ ሁለቱም ክብራቸውን የሚጠብቁ ጀግኖች ናቸው።
ከአሁን በኋላ መብቃት አለበት። በየትኛውም ቦታ ያጠፋ በሸኔ ስም ሌላው ሳይጎዳ በመዋቅር ውስጥ ያሉትም ቢሆኑ ተጣርተው እርምጃ መወሰድ አለበት። ከዚህ በላይ መተላለቅ አያስፈልግም፤ ኢሕአፓ እና መኢሶን እየተባለ ተተኪ የሌላቸው ትልልቅ ምሑራኖች አልቀዋል።እዚህ ላይ የኦሮሞ ምሑራን መንቃት አለባቸው። ከዚህ በላይ ጦርነት መኖር የለበትም ። በደርግም ጊዜ ጦርነት መፍትሔ አልሆነም። አንበሳ እንኳን ካልተራበ ሰው አይበላም፤ በእጁ ይዳብሳል። የሰው ልጅ በሰላም መኖር ሲችል፤ ችግርም ካለ ተነጋግሮ መፍታት እየተቻለ ጥጋበኛ ጉርባ ሆኖ ሰው ከተፈጀ ትዕግስትም ወሰን አለው። ሃይ መባል አለባቸው።
አዲስ ዘመን፡- መንግሥት አጥፊዎችን ለማስታገስ ምን ዓይነት መንገድን መከተል ይገባል?
ብርጋዴር ጀኔራል ዋስይሁን፡– አንድ የፀጥታ አስከባሪ ካለበት ቦታ ላይ በአስር ኪሎ ሜትር ቅኝት እያደረገ መቆጣጠር ይኖርበታል። የኦሮሚያ አጠቃላይ አስተዳደር ከመንግሥት ጋር ተሰልፎ እነዚህን ኦሮሞን የሚያዋርዱ ሽፍቶችን ማስቆም ይኖርበታል። ሸኔን ማጥፋት ይቻላል። ዝም ከተባለ አደጋ አለው። አልሸባብ ቤተመንግሥት ድረስ እየሔደ መድፍ ይተኩሳል። እነዚህ እዛ ድረስ እንዳይዘልቁ ቀድሞ መቆጣጠር ያስፈልጋል። ሳይንሱን መከላከያ ጠንቅቆ ያውቀዋል፡፡
ሕዝብን ማስረዳት መንገር፤ ከዛ መከታተል በመጨረሻም ማጥፋት የግድ ነው። ሽፍታ፣ ወንበዴ እና አመፀኛ የሚወጣው ከሕዝብ ነው። መልሶ የሚሸሸገው ሕዝብ ውስጥ ነው። ስለዚህ ለሕዝቡ ወንበዴን ማገዝ እንደሌለበት በደንብ ማስረዳት ያስፈልጋል። ሽፍታ ሰው ነው። ጫካ ውስጥ ቅጠል በልቶ አይኖርም። ወደ ሕዝብ ተጠግቶ መብላቱ አይቀርም። ስለዚህ ለሕዝቡ ወንበዴን አትደግፍ ጠቁም ከተባለ በትክክል ማጥፋት ይቻላል።
በየክልሉ የቀድሞ ሠራዊት አለ። መንግሥት የቀድሞ ሠራዊትን በሚገባ መጠቀም አለበት። ሠራዊቱ የተማረ እና ዲሲፕሊን ያለው ነው። በእነርሱ በኩል መቆጣጠርም ይቻላል። እኛ ዕድሜያችን አልፏል። ነገር ግን ዕድሜያቸው ከ60 ዓመት በታች የሆኑ ከ100 ሺህ ያላነሱ የቀድሞ ሠራዊት አባላት አሉ። ደርግ ብሔራዊ ውትድርናን አሰልጥኖናል። በየክልሉም የሰለጠኑ አሉ። የአሁኑ ጀግናው የኢፌዲሪ መከላከያ ሠራዊትም አለ። 140ሺህ ሆኖ እስከ አፍንጫው ታጥቆ የመጣውን ወንበዴ በ50ሺህ ሠራዊት ማባረር ችሏል። ስለዚህ ጋምቤላም ሆነ ኦሮሚያ ላይ ጥፋት የሚፈፅሙትን የቀድሞ ሠራዊት አባላትንም ሆነ አዲሱን ሠራዊት በመጠቀም መቆጣጠር ይቻላል። ዕድሜያቸው ያለፉት ሳይቀሩ ሳይንሱን ማስተማር ይችላሉ። ዋናው ጉዳይ እነርሱ ላይ እርምጃ ለመውሰድ ቁርጠኛ መሆን ነው።
ሌላው በአማራ ክልልም በኩል በፋኖ ስም የሚነግዱ ሕገ ወጦች ስለመኖራቸው እየተነገረ ነው። እነርሱም ላይ ቢሆን ተገቢውን እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል። በተጨባጭ ሆን ብሎ ሰው የገደለ እርምጃ ሊወሰድበት ይገባል። ያለበለዚያ ስርዓት አልበኝነት ይቀጥላል። መከላከያን ሁሉም ቦታ ላይ ማሠማራት ስለማይቻል ቢያንስ በየክልሉ ያለውን የቀድሞ ሠራዊት የውጊያ ልምድ እና ዲስፕሊን ያለው በመሆኑ ሰፈር ጠባቂ ሊያደርጉት ይችላሉ። መደበኛው ሠራዊት ግዳጅ ሲሔድ የቀድሞ ሠራዊት ደግሞ አካባቢውን በመጠበቅ ያግዛል። ይህ ከሆነ ያሉ ችግሮችን ማስወገድ ይቻላል። ፋኖም ሆነ ቄሮ ልዩ ኃይልም ሆነ ሌላ ሥርዓትን አክብረው የመንግሥትን ትዕዛዝ ተቀብለው ለሀገር ሰላም ከቆሙ ሁሉም ነገር ከባድ አይሆንም የሚል እምነት አለኝ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ስለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉ ስም እጅግ አመሰግናለሁ፡፡
ብርጋዴር ጀኔራል ዋስይሁን፡- እኔም በጣም አመሰግናለሁ፡፡
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ሰኔ 20/2014