የኦሮሚያ ክልል ለቱሪዝም ከፍተኛ ፋይዳ ባላቸው የባህልና የተፈጥሮ ሀብት የታደለ ነው።በተራራማ ቦታዎች፣ አስደናቂ መልከዓ ምድሮች፣ ከፍታዎች፣ የወንዞች ገደሎች፣ የተፈጥሮ እርጥበታማ ደኖች፣ አስደናቂ ፏፏቴዎች እና የተለያዩ የውሃ አካላት ጨምሮ የቱሪዝም ሀብቶችን የታደለ ክልል ነው።እነዚህን የቱሪዝም ሀብቶችን በማልማት ተጠቃሚ ለመሆን የተሰሩ ስራዎች ዙሪያ የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ ከሆኑት ሁንዴ ከበደ ጋር ያደረግነውን ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው እናቀርባለን።
አዲስ ዘመን፡- በኦሮሚያ ክልል ውስጥ የሚገኙ የቱሪዝም ሀብቶችን በማልማት እና በማስተዋወቅ ረገድ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ምን ይመስላል?
አቶ ሁንዴ፡– የቱሪዝም ኢንዳስትሪ በዓለም ለሰው ከፍተኛ የስራ እድል የሚፈጥር ኢንዱስትሪ ነው። በሀገራችን ግን ለረጅም ጊዜ ይህንን በአግባቡ ሳንጠቀምበት ቆይተናል። ኢትዮጵያ ከፍተኛ የቱሪዝም ሀብት ያላት ነች። ኦሮሚያ ክልል ደግሞ ካሉት ክልሎች አንጻር ከፍተኛ የቱሪዝም ሀብት ያለበት ክልል ነው።ነገር ግን ያንን ሀብት በአግባቡ ልማት ላይ ያላዋልንበት፤ በመንግስትም በኩል ተገቢው ትኩረት ያልተሰጠበት ነበር። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን መንግስት ለቱሪዝም ኢንዱስትሪ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቷል። ይህንን ማረጋገጥ የምንችለው በሀገራችን ታሪክ ውስጥ ይህንን ዘርፍ የሚመራው ተቋም ላለፉት 20 ዓመታት አንድም መዳረሻ ሲያለማ አላየንም። በሶስት ወይም በአራት ዓመታት ውስጥ የለሙትን መዳረሻዎችን ስናይ የሀገራችንን የቱሪዝም ኢንዳስትሪ መቀየር የሚችሉ ናቸው። ለምሳሌ ብንወስድ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ አነሳሽነት በአዲስ አበባ ሸገር ወንዝ ዳር፣ እንጦጦ እና በሌሎች በመሳሰሉት መዳረሻዎች ላይ የፈሰሰው መዋዕለ ንዋይ ስናይ ትልቅ የቱሪም መዳረሻ እንዲፈጠር አድርጓል።
ያ ብቻ አይደለም በክልላችንም የሚገኝ የወንጪ ደንዲ ኢኮቱሪዝም ፕሮጀክት በሀገራችን ከሚሰሩት ሶስት ኢ ኮቱሪዝም ፕሮጀክቶች መካከል ተጠቃሽ ነው።ይህ በመንግስት ደረጃ የሚሰራ ነው።ነገር ግን የባለሃብቱ ተሳትፎም አለበት። ከዚህ አንጻ ስናይ በዚህ በሁለት እና በሶስት ዓመት የተሰጠው ትኩረት በቱሪም ዘርፉ የዛሬ 20 ዓመት ቢሰጠው ኖሮ ሀገራችን ከቱሪዝም ስንት ታገኛለች የሚለውን መገመት አይከብደንም። ከዚህ አንጻ ሲታይ እንደክልላችንም መሰረታዊ የሆኑ ለውጥ እየመጣ ነው። በተለይም የኦሮሚያ ክልል ለረጅም ዓመታት ካለው የቱሪዝም ሀብት አልተጠቀመም። ከፍተኛ የሆነ የቱሪዝም ሀብት እና የባህል ሀብት ያለበት ክልል ነው።ነገር ግን ያ በአግባቡ ስላልለማ ብዙ ችግሮች ስላሉበት በሚፈለገው ደረጃ ታውቆ ወደ ሀብትነት አልተቀየረም።ያንን ችግር ለመቅረፍ የክልላችን መንግስት ትልልቅ ውሳኔዎችን አስተላልፏል።
ያለንን ሀብት ማወቅ እና ሀብቱን ለዓለም እና ለሀገራችን ህዝብ ማሳወቅ አለብን በሚል ትልቅ የማርኬቲንግ እና የፕሮሞሽን ክንፍ የሆነውን የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን መመስረት ተችሏል።ኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን ከተመሰረተ ሁለት ዓመቱ ቢሆንም ነገር ግን በርካታ ስራዎችን ለመስራት ችሏል።ከዚህ በፊት በውስን ማስተዋወቂያ መሳሪያዎች ሲተዋወቅ የነበረውን የክልሉን ሀብት አሁን ቴክኖሎጂው በደረሰበት የሚመጥን መሳሪያዎችን እየተጠቀምን ለዓለም እያስተወወቅን እንገኛለን። ይህ ትልቅ ስራ ነው ብለን መውሰድ ይቻላል። እንደ ቢሮ የኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የፖሊሲ እና ስትራቴጂ አባት ነው። በክልሉ ያለውን የቱሪዝም ሀብት አንቀው የያዙ ችግሮችን የመቅረፍ ስራዎችን እየሰራ ነው። ደንቦችን የማውጣት፣ የህግ ማዕቀፎች የማዘጋጀት ስራዎች ተሰርተዋል።
አዲስ ዘመን፡- ክልሉ ከቱሪዝም ሀብት ተጠቃሚ እንዳይሆን አንቀው የያዙት ችግሮችን ለመቅረፍ የወጡ የህግ ማዕቀፎች የትኞቹ ናቸው?
አቶ ሁንዴ፡– ዘንድሮ የቱሪዝም ዘርፉን ችግር ይፈታሉ ተብለው የታሰቡ ሶስት የህግ ማዕቀፎችን አዘጋጅቷል። አንደኛው የሀገር ውስጥ ቱሪዝምን ለማበረታታት የተቀረጸ ነው። እኛ ትልቅ ሀብት አለን ብለን የምናስበው የሀገር ውስጥ ቱሪዝም ነው።እንደዚያ የምንልበት ምክንያት የኦሮሚያ ክልል በየዓመቱ የሚካበሩ ትላልቅ በዓላት አሉ። ለምሳሌ ብንወስድ የኢሬቻ ፌስትቫል በየዓመቱ በሚሊየኖች የሚቆጠሩ ሰዎች የሚታደሙበት ለመሆን በቅቷል። ከዚህ በፊት በውስን ቦታዎች ይከበር የነበረው የኢሬቻ በዓል ዛሬ በመላው ኦሮሚያ ክልል ይከበራል፡፡
በአዲስ አበባ የሚከበረው ኢሬቻ ሆራ ፊንፊኔ ዘንድሮ ወደ አምስት ሚሊየን የሚጠጉ የሀገር ውስጥ ቱሪስት የተካፈለበት ፌስቲቫል ነው። ይህ ለቱሪዝም ኢንዱስትሪ ትልቅ ጠቃሜታ ነው ያለው። ከኢሬቻ ጋር ተያይዞ በቢሾፍቱም የሚከበር ክብረ በዓል አለ። ይህ ብቻ አይደለም። ክልሉ ትላልቅ የሀይማኖት ተቋማት ጭምር ያሉበት ክልል ነው። በእነዚህ የሃይማኖት ተቋማት በየዓመቱ የሚከበሩ በዓላት በየዓመቱ በርካታ ቱሪስቶች ወደ ክልሉ እንዲመጡ የሚያደርግ ነው። ከዚህ አንጻር ክልላችን ለሀገር ውስጥ ቱሪዝም የተመቸ ክልል ነው። ከውጭ ቱሪስቶች አንጻር ብናየው የውጭ ቱሪስቱ አሁን ላይ በሀገሪቱ ከተፈጠረው ከተለያዩ ችግሮች (ኮሮናና የእርስ በርስ ግጭቶች) ጨምሮ በከፍተኛ ሁኔታ ተቀዛቅዟል። በዚህ ጊዜ እንደ አማራጭ መጠቀም ያለብህ የሀገር ውስጥ ቱሪዝምን ነው። የሀገር ውስጥ ቱሪዝምን በማበረታታት ረገድ ከፍተኛ ስራ ሲሰራ ቆይቷል።
ለዚህ ግን የህግ ማዕቀፍ ማበጀት አለብን ብለን፤ በተለይም የሀገርህን እወቅ ክበብ በሁሉም የመንግስት ተቋማት፣ በሁሉም ትምህርት ቤቶች፣ በሁሉም የክልሉ ወረዳዎች እንዲዋቀር የህግ ማዕቀፍ ለማውጣት ችለናል።ይህ በቀጣይ ወደታች ወርዶ የሚከናወን ይሆናል። ሌላኛው ከመዳረሻ ጋር ተያይዞ የተወሰኑ መዳረሻዎች የክፊያ ስርዓት አላቸው። የክልላችንን የክፊያ ስርዓት ስናይ ችግር አለ። ለምሳሌ የዛሬ አስር ዓመት የመግቢያ ክፊያ የተወሰነለት ዛሬም እዚያው ነው ያለው።ከቱሪዝም ሀብት አንጻር ስናይ ከፍተኛ የቱሪዝም ሀብት ያለበት መዳረሻ ዋጋው አነስተኛ ይሆናል፤ ሀብቱ አነስተኛ የሆነው ደግሞ ክፊያው ከፍተኛ የሆነበት መዳረሻዎች አሉ። እስከ ዛሬ ድረስ በሁለት ብር የሚጎበኙ መዳረሻዎች አሉ። እኝህን ነገር ለመቅረፍ የህግ ማዕቀፍ ማውጣት ስላለብን የክፊያ ስርዓት የክልላችንን መዳረሻዎች ያማከለ፤ መስፈርት ያለው፣ በዚያ መስፈርት ላይ ተመርኩዞ ዋጋ የሚቆርጥ፤ በየሁለት ዓመቱ ዋጋ የሚጨምር፣ እንደአስፈላጊነቱ መቀነስም ካለበት የሚቀንስ አሰራር እንዲኖር ማበጀት ተችሏል፡፡
ከዚህ አንጻር፤ ከዚህ በፊት የነበሩትንም ክፍተቶች ያስተካክላል ብለን እናስባለን። ይህ ብቻ አይደለም፤ ለምሳሌ በርካታ የቱሪዝም ሀብት እያለን የቱሪዝም ሀብቱ ለቱሪዝም መዋል እያለበት ለሌላ ዓላማ የሚውልበት ሁኔታ አለ። ሶስተኛ የህግ ማዕቀፍ የወጠው ይህንን የሚመለከት ነው።በርካታ መስህቦች አሉ፤ ነገር ግን መስህብ ሆነው፤ ፕላን ተዘጋጅቶላቸው አይገኝም።ያንን ነገር ለመቅረፍ የቱሪዝም መዳረሻዎችን እንዴት መልማት እንዳለበት ሳይት ፕላኑን ወደ ባህልና ቱሪዝም ማምጣት ያስፈልጋል፡፡
ያንን ነገር አንድ ላይ ሀብቱን ደግሞ ካዘጋጀን በኋላ እንዴት ለባለሃብት ማስተላለፍ አለብን የሚለው የህግ ማዕቀፍ አዘጋጅተናል። ይህም ያለንን ሀብት ለብክነት እንዳይዳርግ ያደርጋል ማለት ነው። ሆቴል መገንባት ባለበት ቦታ ላይ ፋብሪካ የምትገነባ ከሆነ፤ ፋብሪካ መገንባት ባለበት ቦታ ላይ ሌላ ነገር የሚገነባ ከሆነ ትክክል አይመጣም።ከዚህ በፊት እየሆነ የነበረው ይሄ ነው። ለአብነት ያህል አቢጃታ ሻላ አካባቢ ብናይ ትልቅ የቱሪዝም ሀብት ያለበት ቦታ ነው። እዚያው ጎን በዚያ ሀብት ላይ ጉዳት የሚያደርስ ፋብሪካ አለ።እንዲህ አይነት መሰረታዊ መመሪያዎችን የማውጣት ስራ የኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ በዚህ ዓመት ሲሰራ ነበር። ከዚህ አንጻር አበረታች ውጤቶች አሉ።በርካታ ስራዎች ታቅደው ሲሰሩ ነበር፡፡
አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ወቅት በክልሉ ውስጥ ያለው የቱሪዝም ሁኔታ እንዴት ይገለጻል?
አቶ ሁንዴ፡- በተለይም ከሁለት ዓመት ወዲህ የነበረው የሀገራችንም ሆነ የክልላችን ሁኔታ ለቱሪዝም ምቹ አልነበረም። ከፍተኛ የሆነ ተግዳሮት የገጠመበት ነው። ኮሮና እና ግጭት የቱሪዝም ዘርፉ ተግዳሮት ሆኖ ነው የቆየው። የኮሮና ተፅዕኖ ጋብ ሲል የተከሰተው ግጭት በጥቂቱ ይመጡ የነበሩ ቱሪስቶች ወደ ሀገር እንዳይመጡ አድርጓል። ግጭቱ የሀገሪቱ መልካም ገፅታ አበላሽቷል። አጠቃላይ የሀገሪቱ ገጽታ ላይ የተፈጠረው የገጽታ ችግር ቱሪስት ፍሰት ላይ ተፅዕኖ አሳርፏል።
በክልላችን ብንወስድ ከዞን ዞን ልዩነት ይኑረው እንጂ አንዳንድ የቱሪዝም ሀብት ያለበት ቦታ ላይ አሸባሪ ሸኔ የሚባል ቡድን ባለበት ቦታ ላይ ቱሪስት ሊሄድ አይችልም። ለምሳሌ ቄለም ወለጋ ብንወስድ እንደሀገራችን ብቻ ሳይሆን እንደ አፍሪካ ትልቁ ሀብት ብለን የምንወስደው ብሄራዊ ፓርክ ያለበት ነው። ከአሸባሪው ስጋት የተነሰ ግን አንድም ቱሪስት እየጎበኘው አይደለም።በአንጻራዊነት ከሌሎች ክልሎችም ይሻላል ብለን የምናስበው ከዚህ በፊት በኦሮሚያ ክልል የለሙ መዳረሻዎች አብዛኛዎቹ ከግጭት ቀጣና ስጋት ውጪ ናቸው። ለምሳሌ ቅድም ያልኩህ አሸባሪ ቡድን ባሌ ላይ ታጥቆ አይንቀሳቀስም። ባሌ ደግሞ የክልሉ ትልቁ ሀብት ያለበት እና በአንጻራዊነት የለማና ብዙ ቱሪስቶች የሚሄዱበት ቦታ ነው። ወንጪ ላይም እንደዚያው ነው።ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አንዳንድ ሙከራዎች ግን አሉ፡፡
ከዚያ ውጪ ደቡብ ምዕራብ ኦሮሚያን ብንወስድ የጅማ መስመር ይዘን እስከ ኢሉባቦራ ድረስ ከግጭት ስጋት ውጪ ናቸው። እነዚህ ከፍተኛ ሀብት ያለባቸው እና ቱሪስትም የሚንቀሳቀስባቸው ናቸው። ከዚህ ውጪ የቱሪዝምና ኮንፍረስ ማዕከል የሆነው አዳማ በየጊዜው ከፍተኛ የሆነ ቱሪዝም ኮንፍረንስ የሚካሄድበት ስለሆነ በአንድ በኩል ያለውን መቀዛቀዝ የምናካክስበት ነው። ስለዚህ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በክልላችን ከፍተኛ የሆነ የቱሪዝም መነቃቃትን መፍጠር ችለናል። ይህን ማስቀጠል መቻል አለብን፡፡
አዲስ ዘመን፡-በተገባደደው በጀት ዓመት ምን ያህል ቱሪስቶች ክልሉን ጎበኙ ?
አቶ ሁንዴ፡- እንደ ክልላችን ዘንድሮ ወደ ስምንት ሚሊየን የሀገር ውስጥ ቱሪስት ለማስተናገድ እቅድ ተይዞ፤ ሰባት ነጥብ አምስት ሚሊን የሚሆን የሀገር ውስጥ ቱሪስት ክልላችንን መጎብኘት ችሏል።
አዲስ ዘመን፡- የውጭ ቱሪስቶች ፍሰት ምን ይመስል ነበር?
አቶ ሁንዴ፡– የውጭ ሀገር ቱሪስት ግን ባቀድነው ልክ አልመጣም። ባለን መረጃ መሰረት 98 ሺህ ገደማ የውጭ ቱሪስት ክልላችንን ጎብኝቷል። ለዚህ ደግሞ የዲያስፖራ ጥሪ ከፍተኛ ለውጥ ማምጣት ችሏል። በርካታ ዲያፖራዎች ሀገራችን መጥተዋል፤ እነሱ ደግሞ ክልላችንን እንዲጎበኙ አድርገናል። ይህ ባይኖር ኖሮ ከዚህም በታች ሆን ነበር ማለት ነው። የውስጥም የውጭም ተፅዕኖ ስላለ ቁጥሩ ዝቅ ብሏል።
አዲስ ዘመን፡- የክልሉ የቱሪስት መረጃ አያያዝ እና የቱሪስት ፍሰት መለኪያዎች ምን ያህል ከግድፈቶች የጸዱ ነው ?
አቶ ሁንዴ፡- የቱሪስት ፍሰት መለኪያ መሳሪያ እንደሀገራችንም ብንወስድ የመለኪያ መሳሪያው ደካማ ነው። በአብዛኛው በግምት ላይ የተመሰረተ ነው። በቱሪዝም ዘርፉ ለውጥ ያመጡ ሀገሮች በቀላሉ ስንት ቱሪስት ሀገራቸው እንደገባ፣ እና ስንት የውጭ ሚኒዛሪ እንደወጣ በቀላሉ ያገኛሉ። በእኛ ሀገር ግን እንዲህ አይነት መሳሪያዎች አልተዋወቁም። የውጭ ሀገር የቱሪስት ፍሰት መረጃ አያያዛችን ስናይ የራሱ ችግር አለበት። እኛ ክልል ነን። ኢምግሬሽንን ወይም ኤርፖርትን ጠይቀን መረጃ ማግኘት አንችልም። ከየመዳረሻው የምናገኘው ቁጥር የምንጠቅሰው። ይህ ችግር አለው። ባሌ ውስጥ የሚገኝ መዳረሻ የጎበኘ አንድ ቱሪስት ኢሉባቦር ሄዶ ሊጎበኝ ይችላል። ስለዚህ ሁለት ቦታ ወይም ሶስት ቦታ የመመዝገብ እድሉ ከፍተኛ ነው። እኝህ ግድፈቶች ቢኖሩትም የተሻለ ቁጥር ያለው ቱሪስት መጥቶ ጎብኝቷል ማለት እንችላለን። መዳረሻዎች ላይ ሄደን እንዳየነው የቱሪስት እንቅስቃሴዎች ጀምረዋል። በቀጣይነት ቁጥሩ ይጨምራል ብለን እናስባለን። እስትራቴጂክ የሆነ ፕላን አውጥተን እየሰራን ነው። ከዚህ አንጻር ገቢውም በዚሁ መጠን እያደገ ይመጣል ብለን እናስባለን።
አዲስ ዘመን፡- በዚህ በጀት ዓመት ከቱሪዝሙ ምን ያህል ገቢ ተገኘ?
አቶ ሁንዴ፡- በአጠቃላይ ከሀገር ውስጥም ከውጭም ከመጡ ቱሪስቶች ወደ 3 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር ወደ ክልሉ ኢኮኖሚ ገብቷል።
አዲስ ዘመን፡- እናመሰግናለን።
አቶ ሁንዴ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን ሰኔ 19/2014