የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን(ዋልያዎቹ) የዓለምን እግር ኳስ በበላይነት የሚመራው ፊፋ በየወሩ በሚያወጣው የሀገራት የእግር ኳስ ደረጃ መሻሻል አሳይተዋል። ዋልያዎቹ ካለፈው ወር የፊፋ የሀገራት የእግር ኳስ ደረጃ ሰንጠረዥ በሁለት እርከን መሻሻል አሳይተው ከነበራቸው 140ኛ ደረጃ ወደ 138ኛ ደረጃ ከፍ ብለዋል። በአፍሪካ የነበራቸው ደረጃም ወደ አርባ አንደኛ ከፍ ሊል ችሏል።
ዋልያዎቹ ከሶስት ሳምንት በፊት በ2023 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ከመጀመሪያዎቹ ሁለት ጨዋታዎች አንዱን ማሸነፋቸው ይታወሳል። ዋልያዎቹ የመጀመሪያውን የማጣሪያ ጨዋታ ከሜዳቸው ውጪ ከማላዊ አቻቸው ጋር አድርገው ሁለት ለአንድ መሸነፋቸው የሚታወስ ሲሆን ሁለተኛውን ጨዋታ እዚያው ማላዊ ላይ በማድረግ የግብጽ አቻቸውን ሁለት ለ ዜሮ ማሸነፋቸው አይዘነጋም። የነዚህ ሁለት ጨዋታዎች ውጤት ለዋልያዎቹ የደረጃ መሻሻል ትልቅ ድርሻ አላቸው። ፊፋ ለየሀገራቱ የሚሰጠው ወርሐዊ የእግር ኳስ ደረጃ ሀገራቱ በወር ውስጥ በሚያደርጉት ጨዋታ እንዲሁም በተጋጣሚያቸው ጥንካሬ ላይ የተመረኮዘ መሆኑ ይታወቃል። በዚህም መሠረት ዋልያዎቹ በአፍሪካ ጠንካራና የተሻለ ደረጃ ያላት ግብጽን ማሸነፋቸው አሁን ከተሰጣቸው ደረጃ የተሻለ የሚያስቀምጣቸው ቢሆንም በአንጻራዊነት ደካማ በሆነችው ማላዊ መሸነፋቸው በወርሐዊ ደረጃቸው ላይ ከዚህ የተሻለ ቦታ እንዳይቀመጡ አድርጓቸዋል።
በተያያዘ በሴቶች ወርሐዊ የፊፋ የደረጃ ሰንጠረዥ የኢትዮጵያ የሴቶች ብሔራዊ ቡድን(ሉሲዎቹ) ከባለፈው ወር ከነበራቸው ደረጃ ቀንሰው ከዓለም 126ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጡ በአፍሪካ አስራ ስምንተኛ ሆነዋል። ሉሲዎቹ ከሶስት ሳምንት በፊት በመካከለኛና ምስራቅ አፍሪካ ዋንጫ(ሴካፋ) ወደ ዩጋንዳ ተጉዘው በሶስተኛነት ማጠናቀቃቸው ይታወሳል።
ያለፉት ሁለት የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች በአህጉሪቱ የእግር ኳስ ደረጃ ላይ የተለያዩ ለውጦችን ፈጥረዋል። ጊኒን በሜዳዋ አንድ ለዜሮ የረታችው የሰባት ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫ አሸናፊዋ ግብጽ በዋልያዎቹ መሸነፏ በአፍሪካ የነበራትን ደረጃ ከቀዳሚዎቹ እንዲንሸራተት አድርጓል። በዚህም ከአፍሪካ ወደ ስድስተኛ ደረጃ ስትወርድ በዓለም አርባኛ ደረጃ ላይ አስቀምጧታል።
የአፍሪካ ዋንጫ ሻምፒዮኗ ሴኔጋል በበኩሏ የአህጉሪቱን የእግር ኳስ ደረጃ በመሪነት ልትቆናጠጥ ችላለች። በዓለም ያላት ደረጃም ወደ አስራ ስምንተኛ ከፍ ብሏል። ሴኔጋልን ጨምሮ በኳታሩ የዓለም ዋንጫ አፍሪካን ከሚወክሉ አምስት ሀገራት አንዷ መሆኗን ያረጋገጠችው ሞሮኮ በዓለም ሃያ ሁለተኛ በአፍሪካ ደግሞ ሁለተኛ የሆነችበትን ደረጃ ማግኘት ችላለች።
ሌላኛዋ የዓለም ዋንጫ ተሳታፊና ያለፈው የአፍሪካ ዋንጫ አዘጋጅ አገር ካሜሩን በወሩ የፊፋ ደረጃ ከተንሸራተቱ የአፍሪካ አገራት አንዷ ብትሆንም ከዓለም ሰላሳ ስምንተኛ ከአፍሪካ አምስተኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችላለች። የፊፋ አረብ ካፕ ንጉሷ አልጄሪያ በበኩሏ ደረጃዋን አሻሽላ ከአፍሪካ ሰባተኛ ከዓለም አርባ አንደኛ መሆን ችላለች። ናይጄሪያ፣ጋናና ደቡብ አፍሪካም ካለፈው ወር ደረጃቸውን ማሻሻል የቻሉ ቁንጮ የአፍሪካ ሀገራት ሆነዋል።
እንደ አጠቃላይ በዓለም ቀዳሚውን የደረጃ ሰንጠረዥ በመያዝ ደቡብ አሜሪካዊቷ የእግር ኳስ ሀገር ብራዚል ባለፈው የነበራትን ደረጃ ሳትለቅ መሪነቱን ይዛለች። ቤልጂየምም በተመሳሳይ የነበረችበትን የሁለተኛነት ደረጃ አስጠብቃ ቀጥላለች። ሌላኛዋ ደቡብ አሜሪካዊት አገር አርጀንቲናም ደረጃዋን አሻሽላ በሶስተኝነት ተቀምጣለች። በአውሮፓ ኔሽንስ ሊግ ደካማ አቋም በማሳየት ያልተጠበቁ ሽንፈቶችን ያስተናገደችው የዓለም ዋንጫ አሸናፊዋ ፈረንሳይ ከዓለም የነበራት ቀዳሚ ደረጃ ባለፉት ወራት እየተንሸራተተ ቢመጣም የአራተኛነት ደረጃን በመያዝ ከመሪዎቹ ብዙ አልራቀችም።
የሴቶቹን እግር ኳስ የአፍሪካ ደረጃ ናይጄሪያ በቀዳሚነት ከመቀመጥ ያገዳት የለም። ናይጄሪያን በመከተልም ካሜሩን፣ደቡብ አፍሪካ፣ጋና፣ኮትዲቯርና ቱኒዚያ ተከታዮቹን ደረጃዎች ይዘው ይገኛሉ። የዓለምን ደረጃ ደግሞ አሜሪካ በቀዳሚነት ትመራዋለች። ስዊድን፣ፈረንሳይ፣ኔዘርላንድስና ጀርመን ደግሞ በቅደም ተከተል እስከ አምስተኛ ያለውን ደረጃ ይዘው ይከተላሉ።
ቦጋለ አበበ