ትናንትና…
ዝነኛ ነበረች። ድንቅ ውበት፣ ማራኪ አለባበስ መለያዋ የሆነ ። ስለእሷ የሚያደንቁ፣ ስለማንነቷ የሚያወጉ በርካቶች ስሟን አንስተው አይጠግቡም። በየጊዜው እየቀያየረች የምትይዛቸው መኪኖች ዘመናዊነቷን ሲመሰክሩ ቆይተዋል። ቀበጥ ነች። መዝናናት፣ መጫወት ያስደስታታል።
በከተማው በተሰማራችባችው ሥራዎች የሚለይዋት ሁሉ ሲያደንቋት፣ ኖረዋል። የትናንት አስተዳደጓን የሚያውቁ ብርታት ጥንካሬዋን እያወጉ በምሳሌ ያነሷታል። ቁንጅናዋ ውሎ አድሮ ባመጣላት ሲሳይ ከራሷ አልፋ አካባቢዋን አስጠርታለች። ይህ የትናንትናው ውብ ታሪኳ ነው።
ወደኋላ ያለፉ ጣፋጭና መራራ ዓመታትን ዛሬ ላይ ቆማ በትዝታ ታስባቸዋለች። በእነዚህ ጊዜያት በሻካራና ምቹ መንገዶች ተራምዳለች። በሳቅና ፈገግታ፣ በለቅሶና ችግር አልፋለች። በእሷ ሕይወት ጨለማና ብርሀን፣ ኀዘንና ደስታ ብርቅ ሆነው አያውቁም። በሌላው ትናንቷ በደመቁ ፈገግታዎችና በማያባሩ ለቅሶዎች መሀል ተመላልሳለች። አብነት ሀይሉ።
ዓመታትን ወደኋላ…
የልጅነት ሕይወቷን ስታነሳ ያሳለፈችው ፈተና ትውሰ ይላታል። እሷ ችግር ይሉት ጉዳይ በሁሉም ዘንድ መኖሩን ታምናለች። ወደራሷ ስትመለስ ግን የእሷ ከሌሎች ሁሉ እንደሚለይ ይሰማታል። ገና በጠዋቱ አባቷ በሞት ሲለዩ እሷና ሁለት ወንድሞቿ ለምግብ ብቻ የደረሱ ሕፃናት ነበሩ። እንዲህ መሆኑ ፈተና የሆነው ለቤት እመቤቲቱ እናት ብቻ አልሆነም። ለቤቱ የመጀመሪያ ልጅ ለሆነችው ለዛኔዋ እምቦቃቅላ ለአብነት ጭምር እንጂ።
አብነት ሃዋሳ ወልዳ ያሳደገቻት የደቡብ ፍሬ ነች። የአባቷን መሞት ተከትሎ የኑሮ ጫናን የተሸከመችው ገና በልጅነት ዕድሜዋ ነበር። እኩዮቿ ደብተር ይዘው ትምህርት ቤት ሲሄዱ ዕጣ ፈንታዋ የቤተሰቡን ኑሮን ለማቅናት ሸክሙን መቀበል ሆነ። ለቤቱ የመጀመሪያ ልጅ መሆኗ ኃላፊነትን ለመቀበል ከፊት አስቀደማት። የልጅነት ጫንቃዋ ሁሉን ሊሸከም ‹‹በቃኝ›› አላለም። በሰባት ዓመት ዕድሜዋ ለሥራ ከመንገድ ወጣች። ሸንኮራ እየሸጠች፣ እየተላከች፡ ሳንቲም ማግኘት ጀመረች። የምታገኘው ጥቂት ገቢ ለእናቷና ለወንድሞቿ በቂ አልነበረም። ይህኔ ትንሽዬዋ አብነት ከሀዋሳ ትልቁ ገበያ እየዞረች ለገበያተኞች ዕቃ መሸከም፣ ያዘች።
ዛሬ ስታስበው በዓይኖቿ ውሀ እስኪሞላ የምትቸገርባቸው ክፉ ትውስታዎች የዚያን ዘመን ጥቁር አሻራዎች ሆነው አልፈዋል። ትንሽዋ አብነት እንደአባት የምታየው፣ እንደታላቅ የምታማክረው የልብ ሰው ከጎኗ አልነበረም። በብቸኝነት እየተብሰለሰለች የቤተሰቦቿን ብርሀን ልታደምቅ ዕድሜ ጉልበቷን ገበረች።
የዛኔ ልጅነቷ ከሴትነቷ ተዳምሮ ብዙ ፈትኗታል። ከማንም በላይ ክብር የምትሰጠው የእንጀራ አባቷ ግን ለእሷ ክፉ አልነበረም። መልካም መንገዶችን እያመላከተ እንዳትውድቅ ደግፏታል። ዛሬን ቆማ እንድትራመድ ከጎኗ ሆኖ ‹‹ አይዞሽ›› ብሏታል ። ስለሱ ያላት ምስጋና ዛሬም ድረስ ሙሉ ነው።
ጠዋት ማታ በሥራ የምትባትለው ሕፃን በዕድሜዋ ስለሚገባት የመማር ዕድል አስባ አታውቅም። በለጋነት ዕድሜዋ ቤተሰቦቿን ለማኖር በድካም ባዘነች። አጋጣሚ ሆነና ከሰባት ዓመቷ በኋላ እንደእኩዮቿ ‹‹ሀሁ… ›› ልትል ፣ ቀለም ልትቆጥር መንገዱን አገኘች። ይህ ዕድል ግን በቀላሉ የተገኘ አልነበረም።
አብነት በአካባቢው ከሚገኝ የካቶሊኮች ትምህርትቤት የገባችው ጉልበቷን ጭምር በመገበር ነበር። ውሎዋን የትምህርት ቤቱን ክፍሎች እያጸዳች የማታ ለመማር ከአንደኛ ክፍል ጀመረች። የዛኔ እንደእኩዮቿ የሆነች ቢመስላት ልቧ በደስታ ዘለለ። ሁኔታው ግን እንዳሰበችው ቀላል አልሆነም። የቀን ድካሟ በዕንቅልፍ እየረታት ተቸገረች። አብነት ከምትማረው የምታንቀላፋበት ጊዜ እየበዛ ተቸገረች።
ቀን በጽዳትና በመላላክ የምትውለው ታዳጊ ምሽቱን ከነድካሟ ደብተር ይዛ ፊደል ቆጠረች። እስከ አምስተኛ ክፍል በጥንካሬ ተጉዛም ቀለም ለየች፣ ዕውቀት ጨበጠች። እነዚህ ጊዜያት ለብርቱዋ ታዳጊ ምቹ አልነበሩም። እርምጃዎቿ ሁሉ የችግር መሰላሎች ሆነው በእጅጉ ፈተኗት። ስድስተኛን ተሻግራ እስከ ስምንተኛ ተማረች። በኋላም እስከ ሁለተኛ ደረጃ በታቦር ትምህርት ቤት ዘለቀች።
በኮምቦኒ ትምህርትቤት ያሉ ተማሪዎች የኑሮ ደረጃ አንድ አልነበረም። የድሀና የሀብታም ቤተሰብ ልጆች በአንድ ይውላሉ። ያለክፍያ ከሚማሩት ተማሪዎች አንዷ የሆነችው አብነት ከማታ ትምህርት ወደቀን ተመልሳ ባልንጀሮቿን መሰለች። ይህኔ ረጅሟና ቀጫጫዋ ተማሪ ከሌሎች ተለይታ ከዓይን ገባች። ቁመቷን ያዩ፣ አረማመዷን የገመገሙ ብዙዎች አሻግረው በጎ ተመኙላት።
በተለይ የትምህርት ቤቱ ፈረንጆች በመለሎዋ አብነት ጀርባ መልካም ነገር አሰቡ። ሞዴል እንድትሆን፣ የፋሽን ኢንዱስትሪውን እንድትቀላቀል መካከሯት። አብነት በየቀኑ በምትሰማው በጎ ሀሳብ ልቧ ተነሳሳ፣ ብዙዎች እሷን እያሰቡ የሚነግሯት የሞዴልነት ዓለም ውስጧን ገዛው። ደግማ ደጋግማ አሰበችበት። ፍላጎቷ ከሌሎች ተዳምሮ አዲስ አበባ አደረሳት።
አብነት በሸገር …
ለአገሩ ባዳ፣ ለከተማው እንግዳ ለሆነችው ወጣት የአዲስ አበባ ሕይወት ቀላል አልነበረም። በውስጧ ጽኑ ፍላጎት ብቻ ለሰነቀችው የፋሽን አፍቃሪ በዋዛ ኢንዱስትሪውን መቀላቀል አልጋ በአልጋ አልሆነም። ለትራንስፖርት ተቸገረች፣ በአልባሳትና በጫማዎች እጥረት ተፈተነች። ከሌሎች እኩል ለመወዳደር ብትቸገርም እጅ አልሰጠችም። ጎዶሎውን በዘዴ እየሞላች ከሞዴሎች ተርታ ተሰለፈች።
የአብነት መንገድ ከባድና ትግል የበዛበት ነበር። ያም ሆኖ ሙከራዋ በጥረት ተሳካ። በቆይታዋ የሚያስፈልገውን ሙያ ዘግና ወደ ሀዋሳ ተመለሰች። እጇን ዘርግታ በተቀበለቻት የትውልድ አገሯ የያዘችውን ዕውቀት በወጉ ልትመነዝር ዕድል ተቸራት ።
በከተማዋ በተካሄደው የቁንጅና ውድድር መድረኩን ናኘችበት። በርካቶች በተወዳደሩበት የሚስ ሀዋሳ ቁንጅና ውድድር ዓይን አዋጅ የሆነባቸው ተመልካቾች አንዷን ቆንጆ ከሌላዋ ሊለዩ ተቸገሩ። የተወዳዳሪዎቹን ውበትና የአንደበታቸውን ቃላትም ሊያመዛዝኑት ጨነቃቸው። ከሁሉም ግን ቁመተ ሎጋዋ፣ መልከ ቀናዋ አብነት የበርካቶችን ቀልብ ገዛች። ዓይኖች ሁሉ በእሷ ላይ አተኮሩ፣ እርምጃዋና፣ ንግግሯ ከሌሎች ተለይቶ ጎላ።
ጥቂት ቆይቶ ዳኞች የተወዳዳሪዎቹን ውጤት አሳወቁ። ወጣቷ ሞዴል አብነት ሀይሉ የውድድሩን የአሸናፊነት አክሊል ከራሷ ላይ ደፋች። ዕልፎች በ‹‹ይገባታል›› አድምቀው አጨበጨቡ። በርካቶች በአድናቆት እጃቸውን ከአፋቸው ጫኑ።
የዘመኑ ‹‹ሚስ ሀዋሳ›› ከውበቷ ጀርባ ማንነቷ አነጋገረ። ምስኪን ድሀ፣ ለእግሯ ጫማ ያልነበራት፣ በሳር ፍራሽ የተኛች፣ በበርካታ ችግሮች የተመላለሰች መሆኗ አስደነቀ። ታሪኳን የሰሙ ሁሉ በከፍታ አከበሯት፣ ቆመው በድምቀት አጨበጨቡላት። እንዲህ በሆነ ማግስት የቆንጆዋ ስምና ዝና ናኘ። ይህን ተከትሎ አድናቂዎቿ ለውጧን ተመኙ። ዳግም በዓለም አቀፍ መድረኮች ሊመለከቷት ናፈቁ። አብነት አስተያየቶችን ሰማች፣ አድናቆቶችን ተቀበለች። ፈላጊዎቿ በረከቱ፣ ውሎና ሥራዋ ከታዋቂ አርቲስቶች ሆነ።
አዲስ ሕይወት…
የቁንጅና ውድድር አሸናፊዋ አብነት ሕይወቷ ሊቀየር ፣ ታሪኳ ሊለወጥ ጊዜው ደረሰ። ዝነኝነቷን ተከትሎ የመጣው አዲስ የሕይወት መንገድ ኑሮዋን በእጅጉ ቀየረው። ከመኪና መኪና ለዋወጠች፣ በበርካታ ሥራዎች ታወቀች። በቂ ገንዘብና ጥሩ የሚባል ሀብት ከእጇ ደረሰ።
የትናንት ማንነቷን የሚያውቁ በጎዎች ከልብ ተደሰቱ። አብነት ድህነትን ለማምለጥ በበረከቱ አማራጮች ስትሻገር ቆይታለች። ራሷን አሸንፋ ቤተሰቦቿን ለማገዝ ያላለፈችበት መንገድ የለም። በሻካራማው ጉዞ ተራምዳ ኑሮን ድል መንሳቷ ብዙ አስተምሯታል።
ከቀናት በአንዱቀን አብነት ከአንድ ነጭ ጓደኛዋ ጋር ስትዝናና ከሌላ ጉብል ዓይን ወደቀች። እሷም ብትሆን ያያትን ሰው ቀድማ አይታው ኖሯል። የዚያች ቀን መተያየት ሰበብ ሆኖ ከትዳር አጋሯ ተጣመረች። አምስት ልጆችንም ወለደች። የውበት ሳሎን፣ የመኪና ማከራያና የባህል ምሽት ቤትን ከፈተች። ከታወቁ ሰዎች እየተጣመረች ታላላቅ የሙዚቃ ኮንሰርቶች ማዘጋጀት ልምዷ ሆነ። የሀብት መምጣትን ተከትሎ ዝነኝነቷ ጨመረ። ሥራዋን የሚያደንቁ፣ ቤቷን የሚያዘወትሩ ደንበኞች በየዕለቱ ከበሯ ተመላለሱ።
አብነት ብዙዎች እሷ ባለፈችበት አስቸጋሪ የሕይወት መንገድ እንዳያልፉ እገዛዋ የበዛ ሆነ። ‹‹መልካሙ ሳምራዊ›› የሚል አገር በቀል ድርጅት አቋቁማ ወጣቶች በራሳቸው ገቢ እንዲተዳደሩ ዕድሉን ከፈተች። የእናቶችን ችግር ለመፍታትም ከጎናቸው ቆመች። ብርታቷ ብዙዎች ያልሞከሩትን የሕፃናት ተጨማሪ ምግብ ማምረቻን እስከመክፈት አደረሳት።
በመሬት ሽያጭና መሰል ሥራዎች ውጤታማ መሆን ቻለች። ከአገር ውጭ ተመላልሳ የጎደሉትን እየደፈነች ፣ የብዙዎችን ፍላጎት አሟላች። ጥረቷን ተከትሎ የመጣው ስኬት ከዝነኝነት ተዳምሮ የአብነትን ስም ከማማው ሰቀለው። በሀዋሳ ምድር ማንነቷ በበጎ ተወሳ። ቆንጆዋና ሞዴሏ ወጣት በሥራዎቿ ታወቀች፣ ደመቀች።
ከዓመታት በኋላ …
ዛሬ በአብነት ሕይወት የትናንቱ ታሪክ የለም። የጀመረችው የስኬት መንገድ ከዳር ባያደርሳት በ ‹‹ነበር›› የምታነሳቸው ድንቅ ታሪኮች ብቻ ከእሷ ቀርተዋል። አሁን የቀድሞው መልካም ዝና፣ አብሯት የኖረው ሀብት ንብረት ከጎኗ የለም። ይህ ብቻ አይደለም። ትናንት በአድናቆት የሚያወሷት ብዙዎች ዛሬ ስሟን ደግመው አይጠሩትም። ስኬቷን ተከትሎ የደረሰባት ድንገቴ ኪሳራ ከብዙ እውነታዎች ነጥሏታል።
አብነት የትናንትናዎቹ የቅርብ ባልንጀሮቿ፣ የደመቀው ኑሮና ትዳሯ ከተለዩዋት ጊዜያት ተቆጥረዋል። ገንዘብ በነበራት ጊዜ ለበርካቶች ደርሳለች፣ ጠቅማለች። በአንጻሩም ብኩን መሆኗ ብዙ አስከፍሏታል። በእጇ ያለውን ገንዘብና ጥሪት በወጉ አለመያዟ ለዛሬው ችግሯ ምክንያት መሆኑን ታውቃለች። እሷ መጠን ባለፈ ኑሮ ማለፏ የእጇን በረከት እንደበተነው ይገባታል። የዛኔ ለሌሎች የምታደርገው መጠን የለሽ ውለታ ለዛሬው ማንነቷ ጥቁር አሻራ ትቷል። አብነት ትናንት የደፋችው ምግብ እስኪናፍቃት በማይታመኑ ችግሮች ታፍናለች፣ አጥታ ያገኘች ቢሆንም አግኝታ ድንገት ማጣቷ ይበልጥ ያስከፋታል።
አብነት ዛሬ…
የትናንቷ ውብ ቆንጆ ዛሬም የመኖር ትግሏ ቀጥሏል። ሕይወቷን በብርታት መርታ ፣ ልጆቿን በወጉ ለማኖር ግን እንደቀድሞው አልሆነችም። እንደትናንቱ በድምቀት አልታየችም። ዛሬ ያቺን ጠንካራ ሴት የሚያውቁ ሁሉ ከቁንጅናው መድረክ፣ ከኢንቨስትመንቱ ጎራ አይፈልጓትም። አሁን የእሷን በረከት ሲሹ የኖሩ እጆች እንደቀድሞው አይመኩባትም። አብነት እንኳን ለእነሱ ለራሷም መሆን ተስኗታል።
ለእሷ ችግርና ፈተና፣ መከራና ትግል ብርቋ አይደሉም። አሁን ያለችበት አጋጣሚ ግን ሆድ አስብሶ ከዕንባ ያተናንቃታል። በትካዜ አንገት አሰደፍቶ በሀሳብ ያናውዛታል። ‹‹አሸነፍኩት›› ያለችው ፈተና ዳግም ሊገጥማት ቢገዳደራት፣ እጅ መስጠት ሞቷ ሆኖ ትታገለው፣ ትተናነቀው ይዛለች።
ለመኖር…
አብነት ዛሬ ቤት ንብረት ይሉትን አጥታለች። ውሎ አዳሯ ከከሰል፣ ጋር ሆኗል። ከሰል ለአብነት ትርጉሙ ይለያል። እንደሌሎች ጥቁር ብቻ አይደለም። ሕይወቷን ለመምራት፣ ልጆቿን ለማሳደግ የእንጀራዋ ብርሃን ነው። ዛሬ እነዛ ለስላሳ እጆች ከከሰሉ ሲታገሉ ይውላሉ። ትናንት ባማሩ ጌጦች የተዋቡት ጣቶች አሁን መገኛቸው ከአመድ ብናኝ ሆኗል።
አንዳንዴ አብነት እህል ባላየ አንጀቷ ማዳበሪያ በትከሻዋ አዝላ በየመንደሩ ትዞራለች። ዓይኖቿ ውዳቂ ቁሶችን አያልፉም። ይበጃሉ የምትላቸውን ሁሉ ትለቅማለች። እጆቿ ያገኙትን ለማንሳት አይጠየፉም። እርግጥ ነው፤ ትናንት የሚያውቋት ሲያተኩሩባት ትሳቀቃለች። ለመኖር፣ ልጆቿን ለማሳደግ ግን እንዲህ ሊሆን ግድ ብሏል።
እሷ የሚቀመሰውን፣ የሚጎረሰውን ይዛ፣ የምታበስልበት እንጨት ያጣችባቸው ጊዜያት አሉ። እንዲህ በሆነ ጊዜ ከሱቅ ዱቤ እስከመከልከል ደርሳለች። ይህ ዓይነቱ እውነታ ብዙ ታደርግ ለነበረው አብነት የኀዘን፣ የአንገት መድፋት ዘመን ነበር። ግን ደግሞ በርሀብ መሞት የለባትም። የትናንት የስኬት መንገዷ ታሪክ ከሆነ በኋላ ብዙ አስባለች። ሕይወቷን ለመቀጠል፣ ልጆቿን ለማሳደግ ቢያንስ ቀምሶ ማደር አለባት። እንደቀድሞው መልካም ነገሮች ከእሷ ቢርቁም ዝምታ ምርጫዋ አልሆነም።
ሰዎች ስለከሰል ሽያጭ መንገዱን በጠቆሟት ጊዜ ዓይኗን አላሸችም። ከጭስ፣ገብታ፣ ከአመድ ተለውሳ፣ በእሳት ተለብልባ እንደ ከሰል ጠቁራ ለመኖር አማራጭ ወሰደች። እናም ከሰሉን እያመረተች መሸጥ እንጀራዋ፣ ሕይወቷ ሆነ። ዛሬ አብነት የጥንካሬዋ መሠረት ፈጣሪዋ መሆኑን ታምናለች። ቢከፋት፣ ብታዝንም ተስፋ አልቆረጠችም። ነገ ሌላ ተስፋዋ ነው። በሀብት አትመካም፣ ዳግም የወደፊቱን በጎነት አጥብቃ ታስባለች።
አብነት ትናንት ስለሆኑባት መጥፎ አጋጣሚዎች በሌሎች ላይ እጅ አትጠቁምም። አዎ! የክንዷ በረከት ተበትኗል። የቅርብ ባልንጀሮቿ እንዳለየ አልፈዋታል። ቤት ትዳሯ ፈርሷል። እሷ ግን ካለፈው ሕይወቷ ለመማር ከራሷ በላይ አጋዥና ብርቱ እንደሌለ ታውቃለች። ከትንሽ እንደተነሳች ሁሉ ወድቃ እንደማትቀር ዕምነቷ ነው። ከውድቀቷ ብዙዎች መማራቸው ደግሞ ከልብ ያስደስታታል።
አብነት ስለፈረሰው ትዳሯ ብዙ ማውራት አትሻም። ልጆቿ ግን ዛሬ ቀና ብላ ለመሄዷ ምክንያት ናቸውና ከአፏ አትነጥላቸውም። ሁሌም በእነሱ ውስጥ ጥንካሬና ብርታትን ታያለች። የታሪኳ አብይ ክፍል በመሆናቸው ለእነሱ ያላት ፍቅርና አክብሮት ለየት ይላል።
የትናንቷ ባለዝና ፣ የቀድሞዋ ቆንጆ ባለሀብት፣ ዛሬን በነበረችበት ቦታ አልቆመችም። አሁን የኖረችበትን ታሪክ ፣ያሳለፈችውን ድንቅ ሕይወት በነበር ታወሳዋለች። ለእሷ በሻካራማ መንገዶች አልፎ ከምቾት ዓለም መድረስ ብርቅ አይደለም። በደልዳላው ሜዳ ተራምዳ ከአስቸጋሪው ገደል መግባትን አልፋበታለች።
እርግጥ ነው። ትናንት እንዳለፈ ሁሉ ዛሬም እንዲያልፍ ታውቃለች። የእሷ ዓለም ግን አሁን ነው። ዛሬን የምትኖረው ፈታኝ ሕይወት። አብነት ሀይሉ ኑሮን ታግላ ሕይወትን ለማሸነፍ እንዲህ መኖር ይዛለች። በተስፋ፣ በጥንካሬ፣ በአይበገሬ ጽናት።
መልካምሥራ አፈወርቅ