ነገሮችን የምታስተውልበት አንዳች ልዩ ተሰጥኦ አይሉት ችሎታን ታድላለች። በቅርብ የሚያውቋት ወዳጆቿ እንዲያውም «ምትሀተኛ ነች» ይሏታል። እርሷ ባለችበት ሥራ፤ ሥራ ባለበት ሁሉ እርሷ አለች። ሌት ተቀን ለለውጥ ትተጋለች። ሥራ ነብሷ ነው። አዳዲስ የተባሉ ሥራዎች ሁሉ እርሷን ይሻሉ። እርሷም ለዚሁ ታደላለች። አንዱን ይዛ ሌላውን፤ እርሱን ሳትለቅ ደግሞ ሌላ ተግባር ላይ ታማትራለች። ከቴክኖሎጂ ጋር ባላት ጥብቅ ቁርኝት የተነሳ በሰከንዶች ሽርፍራፊ ለቁጥር የበዙ ተግባራትን ታከናውናለች።
መልከመልካምና ዘለግ ያለ ቁመና አላት። ከጸጉሯ ቀለም ጀምሮ የፊቷ ቅላት የውጭ ዜጋ አስመስሏታል። ሰው አክባሪ፣ ተጫዋችና ተግባቢ ናት። ትህትናን ገንዘብ ያደረገ ማንነትም አላት። ቀጠሮ አክባሪና ለጊዜ ትልቅ ዋጋ በመስጠቷ ምክንያት ከልባችን ምት እኩል ከሚነጉደው ጊዜ ጋር አብራ ትጓዛለች። ትወጣለች ትወርዳለች። ‹‹ስምን መልአክ ያወጣዋል›› እንዲሉ ምግባሯ ከመጠሪያ ስሟ ፍጹም የተስማማ ነው። ጊዜሽወርቅ ተሰማ ትባላለች። የዝግጅት ክፍላችንም የዕለቱ የስኬት እንግዳ አድርጎ መርጧታል።
ጊዜሽወርቅ፤ አዲስ አበባ ከተማ ልዩ ስሙ ተክለሃይማኖት አካባቢ ነው ተወልዳ ያደገችው። ከትምህርት ሁሉ የጎበዝ ተማሪ መለያ የሆነውን የሒሳብ ትምህርት አብልጣ ትወዳለች። ልዩ ተሰጥኦም አላት። ከመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ጀምራ አብሯት ያደገው የሒሳብ ትምህርት ችሎታ ዛሬ ለደረሰችበት የስኬት ማማ ዓይነተኛ ሚና ተጫውቷል። የሒሳብ ትምህርት ጥልቅ ዕውቀቷና ፍላጎቷ ባለምጡቅ አዕምሮ ትንታግ ሳያደርጋት አልቀረም።
እስከ ስምንተኛ ክፍል በነበራት የላቀ ውጤት የ9ኛ እና 10ኛ ክፍል ትምህርትን እንደእርሷ ጎበዝ ተማሪ ሆነው ከተመረጡ መሰሎቿ ጋር የፋይናንስ ትምህርትን ተምራለች። 10ኛ ክፍል ስትደርስም ከመላው አገሪቱ ከተመረጡ ጎበዝ ተማሪዎች መካከል አንዷ ሆና ወንዶችን ብቻ ይቀበል ከነበረው ጀነራል ዊንጌት ትምህርት ቤት ከጥቂት ሴቶች መካከል አንዷ ሴት ተማሪ በመሆን ተቀላቅላለች።
በሂሳብ ጉብዝናዋ ምክንያት አካውንቲንግ መማር የምትፈልግ ቢሆንም በወቅቱ የወጣላት ዕጣ ግን ሴክሬቴሪያት ሆኖ ተገኘ። ለሒሳብ ትምህርት ያላትን ፍቅር፣ ፍላጎትና ችሎታ ለርዕሰ መምህሩ በማስረዳት ወደ አካውንቲንግ ትምህርት ክፍል ለመመለስ ጥያቄ አቀርባለች። ጥያቄዋን ተከትሎም ከፍላጎቱ ውጭ የተመደበ ተማሪ እንደየ ዕምነቱ የዕምነት መጽሐፍትን በመምታት እንዲመለስ ሆነ።
በዚህ ወቅት ታድያ መጽሐፍ ቅዱስን በምስክርነት በመምታት ወደ አካውንቲንግ ትምህርት ክፍል ለመመለስ ቀዳሚ ያልነበራት ጊዜሽወርቅ፤ የነብስ ጥሪዋ የሆነውን የአካውንቲንግ ትምህርት ክፍል ተከታትላ በዲፕሎማ ተመርቃለች። ትምህርቱን ባጠናቀቀች ማግስትም እርሷን ጨምሮ ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ ስድስት ተማሪዎች ጅማ የእርሻ ምርምር የሒሳብ ሠራተኛ ሆነው ተቀጥረዋል።
ገና በጠዋቱ ወደ ሥራ ዓለም የገባችው ጊዜሽወርቅ፤ በመጀመሪያ ደመወዟ ወላጅ እናቷ የሚወዱትን ዓይነት ቀሚስ መግዛቷን ታስታውሳለች። በወቅቱ የነበራትን ደስታ ስታስታውስም አሁን የሆነ ይመስል ስሜቷ ከገጿ ይነበባል። ወላጅ እናቷ ሦስት ወንዶች ልጆቻቸውን ሞት ከወሰደባቸው በኋላ የተገኘች ብርቅዬና ፈጣኗ ልጅ ተወልዳ በተመለከቷት ቅጽበት ‹‹ይቺማ ጊዜሽወርቅ ናት›› ያሏትም ወላጅ አባቷ አቶ ተሰማ ናቸው።
ከትምህርቷ ባለፈ በቤት ውስጥ ሥራም ጎበዝና ባለሙያ እንደሆነች የምታስታውሰው ጊዜሽወርቅ በዚህ ምክንያትም ገና ተማሪ እያለች በተደጋጋሚ ባል ይመጣላት እንደነበርም አጫውታናለች። እርሷም ሆነች ወላጅ አባቷ ግን በትምህርቷ መግፋት እንዳለባት ነው የሚያምኑት። ስለሆነም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገብታ ትምህርቷን በቀጠለች ጊዜ ለትዳር የሚጠይቋትና የሚዝቱባት ሰዎች በዙ። በዚህ ጊዜ ታዲያ ወላጅ አባቷ አማራጭ ነው ያሉትን የውጭ አገር ጉዞ አመቻቹላት። አጋጣሚው ለሒሳብ ያላትን እምቅ ችሎታና ልዩ ተሰጥኦ በግልጽ ማወቅና አውጥታ መጠቀም እንድትችልም ምቹ ሁኔታን ፈጥሮላታል።
ለመጀመሪያ ጊዜ በሄደችበት አልአይን የእንግሊዝ ጋዜጦችን ስታገላብጥ በአካውንቲንግ ጎበዝ የሆነንና በራሱ የሚተማመን ሰው የሚጋብዝ የሥራ ማስታወቂያ ተመለከተች። በሒሳብ ችሎታዋ የምትተማመነው ጊዜሽወርቅ አላመነታችም አመለከተች። ብዙዎች ‹‹ኧረ ተ…ይ… የእንግሊዞች ካምፓኒ ነው አንቺኮ ኢትዮጵያዊ ነሽ›› ቢሏትም እርሷ ግን እነሱን ሳይሆን ልቧን አድምጣ የመጀመሪያዋ ኢትጵዮጵያዊ በመሆን ከእንግሊዞች ካምፓኒ ሰተት ብላ በመግባት የነብሷ ጥሪ የሆነውን የሒሳብ ሥራዋን መሥራት ጀመረች።
በካምፓኒው በነባራት የ15 ቀን ቆይታ ታድያ በሥራዋ ብቃት ስሟን በከፍተኛ ደረጃ አስጠራች። የማያባራው ፍጥነቷም ወደ ቀጣይ ድል አድራጊነት ሊመራት ያንደረድራት ጀመር በዚህ ወቅት ከምታገኘው ገቢ ለትምህርት ቤት እየከፈለች ከሥራዋ ጎን ለጎን የማኔጅመንት ትምህርቷን አስቀጥላለች። በአጭር ጊዜ ትምህርት ማኔጅመንትን ጨምሮ ማንኛውንም ዓይነት ስልጠና መሰልጠን ቻለች። ይሄኔ ይበልጥ እራሷን ማብቃት የቻለችው ጊዜሽወርቅ፤ በፈለገችው ጊዜ በማንኛውም ቦታ መሰለፍ የምትችል መሆንኑ አረጋገጠች።
እሷን የመሰለ ፈጣን ሰው አገሩ ቢገባ ብዙ ሥራ መሥራትና ለውጥ ማምጣት የሚችል እንደሆነ ከአንድ ኢትዮጵያዊ ያደመጠችውም በዚህ ወቅት ነበር። ወጣትነት በራሱ ከሚሰጠው ኃይል በተጨማሪ እጅጉን ለምትታትረው ፈጣኗ ጊዜሽወርቅ፤ መልዕክቱ ቀላል ግምት የሚሰጠው አልነበረምና በዚያው ቅጽበት ወደ ኢትዮጵያ አቀናች። እንደተባለው ኢትዮጵያ ውስጥ መሥራት የምትችለው ሥራ ምን እንደሆነ በውል ባታውቀውም አዲስ አበባን ከእግር እስከ ራሷ በእግሯ እየዞረች ቃኘቻት።
ለመጀመሪያ ጊዜ ከኦሮሚያ ፋይናንስ ቢሮ እግር ጥሏት ስትገባ ወረቀት ይዘው ከወዲህ ወዲያ የሚሉ ሴቶች ትመለከታለች። ምክንያቱ ደግሞ ታይፕራይተር ፍለጋ ነው። ፈጣኗ ጊዜሽወርቅ፤ ሥራ አስኪጁ ጋር ቀርባ ቀልድ የሚመስል ጥያቄ ‹‹ታይፕራይተር ከጀርመን አገር ላስገባላችሁ›› ስትል ጠየቀች። ምላሹን ሳትጠብቅ ፕሮፎርማ ሰብስባ ከሁሉም ባነሰ ዋጋ ለማስመጣት ቃል ገባች። ሥራ መሥራት እንደምትችል ማሳየት የፈለገችው ጊዜሽወርቅ፤ ትርፍ የማግኘት ሂሳብ ውስጥ አልገባችምና ከጀርመን ካምፓኒዎች ጋር ተጻጽፋ ቃሏን በተግባር አስመስክራ በዚህም እራሷን አስተዋወቀች።
ከዚህ በኋላ መሰል ሥራዎች እሷን ብለው እየተግተለተሉ ይጎርፉ ጀመር። እችላለሁ የሚል ወኔዋን ሰንቃ ለማንኛውም ጥያቄ ፈጣን ምላሽ ያላት ጊዜሽወርቅ፤ ከጃፓን መኪናን ጨምሮ የተለያዩ ጨረታዎችን በመወዳደር መንግሥትን ከወጪ የሚያድን ሥራዋን በልበ ሙሉነት ታሳልጠው ጀመር። ሥራ ባለበት ሁሉ የምትገኘው ጊዜሽወርቅ፤ አንደኛው ሥራ ሌላ ሥራ እየወለደላት በበርካታ ዘርፎች ተሰማርታ ውጤታማ መሆን ችላለች።
ወቅቱ በሁሉም የሥራ ዘርፎች ከፍተኛ መነቃቃት መታየት የጀመረበት እንደመሆኑ በርካታ ሥራዎችን በቀዳሚነት ማከናወን ችላለች። ለአብነትም ከግለሰብ በተበደረችው 15 ሺ ብር በ500 ብር ወረቀት እና በ14500 ብር ደግሞ ፎቶ ኮፒ ማሽን በመግዛት ወቅቱ የሚጠይቀውን የፎቶ ኮፒ ሥራን ተቆጣጠረችው። በዚሁ ሥራ ላይ ሆና የተዋወቀቻቸው የውጭ ዜጎች ፍጥነቷንና ቅልጥፍናዋን አስተውለው አብራቸው እንድትሠራ ያሳዩትን ፍላጎት ተቀበለች። በወቅቱ ጊዜ የፈጀባቸውን የህትመት ጥራዝ በተለያዩ ማተሚያ ቤቶች ወስዳ ባጠረ ጊዜ ከእጃቸው አስገባች። በዚህ ጊዜ ታድያ ማንኛውንም ነገር መሥራት እንደምትችል በተግባር ከማረጋገጥ ባለፈ ጠቀም ያለ ገንዘብም ከነጮቹ ማግኘት ችላለች።
በሥራዋ አጋጣሚ ሁሉ ከምታገኛቸው ሰዎች በተለይም ከውጭ ዜጎች ጋር በቀላሉ መግባባት በመቻሏና ባላት ቅልጥፍና አጠቃላይ ሥራዋ ከተለያዩ የውጭ ዜጎች ጋር ሆነ። ኢትዮጵያ ውስጥ የተለያዩ የግንባታ ሥራዎችን ሊሠሩ ከመጡ የውጭ ዜጎች ጋር አብራ ለመሥራት ቀዳሚ አልነበራትም። ከውጭ ዜጎች ጋር ጥብቅ ትስስር የነበራት ጊዜሽወርቅ፤ በተለይም ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሚገነባበት ወቅት በሎጅስቲክስ ሥራ ትልቅ ድርሻ ነበራት ቢባል ማጋነን አይሆንም።
ሌሎች ትላልቅ ሥራዎችንም እንዲሁ በኃላፊነት እየወሰደችና ለሌሎች እያከፋፈለች ሥራዋን ማስፋፋት ቀጠለች። እንቅልፍ የሌላት ጊዜሽርቅ፤ ለመንገድ ሥራም ይሁን ለሌሎች የግንባታ ሥራዎች ወደ አገሪቱ ከመጡ የውጭ ዜጎች ጋር በመሆን የተለያዩ ግብአቶችን ከአገር ውስጥና ከውጭ አገር በማስመጣት ሰፊ አበርክቶ ነበራት። በርካታ የአውሮፓ አገራትና አሜሪካ የመመላለስ ዕድል አግኝታለች። በተለይም አልላይንና አሜሪካ በርካታ ጊዜያትን አስቆጥራለች።
አጋጣሚው የፈጠረላትን ሁሉ ወደ ሥራ በመቀየር በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ተሰማርታ ፍሬ ማፍራት የቻለችው ጊዜሽወርቅ፤ ጊዜ ስቴሽነሪ ከሚለው አነስተኛ ድርጅት ጀምራ ጊዜ ትራቭል ኤንድ ቱሪዝምንም ከፍታለች። በዚህ ጊዜ ታድያ ከ2000 በላይ ለሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል ከመፍጠር ባለፈ በርካታ የውጭ አገር አምባሳደሮችን የመተዋወቅ ዕድልም አግኝታለች። ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ በርካታ የውጭ ዜጎች በሎጅስቲክስ ዘርፍ የሚያገኙት አገልግሎት በቂ አለመሆኑን ባነሱበት ወቅት አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ ወስና አስፈላጊውን ስልጠና በመውሰድ ሎጅስቲክስና ሺፒንግ ድርጅት አቋቋመች። መማርና መሥራት የነብሷ ጥሪ በመሆኑ ስለ ጉምሩክ ተምራ አገልግሎቱን ተደራሽ ማድረግ ችላለች።
ከትምህርቱ ባሻገር በተፈጥሮ የተሰጣትን ፍጥነት፣ ቅልጥፍናና የእንግሊዝኛ ቋንቋ ችሎታዋን ተጠቅማ የውጭ ዜጋ የሆኑ ደንበኞቿ የሚፈልጉትን ማንኛውም ግብዓት ከዓለም ዙሪያ በማሰባሰብ ታቀርብ ጀመር። በዚሁ ድርጅቷም ኢትዮጵያን ወክላ በበርካታ የዓለም መድረኮች ተቀምጣለች። ‹‹ይሄኔ ሎጅስቲክስና ሺፒንግ ለእኔ የተፈጠረ ሥራ እንደሆነ አመንኩ›› የምትለው ጊዜሽወርቅ፤ የዩናይትድ ኔሽን እና የዓለም ባንክ የኢትዮጵያ ተወካይ በመሆን ወደብ የሌላቸው አገራት ያላቸውን ችግርና መፍትሔዎቹ በሚለው የውይይት መድረክ ኢትዮጵያን ወክላ ተሳትፋለች።
ከዚህ በኋላ ከፍተኛ ተቀባይነትን ያገኘችው ጊዜሽወርቅ፤ በዓለም መድረክ አግዋን ጨምሮ በብዙ መድረኮች ላይ የተለያዩ ጉዳዮች ላይ ስለ ኢትዮጵያ ሞግታለች። በዚህም በርካታ ሰርተፍኬቶችን አግኝታለች። በደረሰችበት ሁሉ ሥራ ሥራን እየወለደ በአገሪቱ ትላልቅ ፕሮጀክቶች ላይ የመሰማራት ዕድል ያጋጠማትና ከፍተኛ ፍላጎትም ያላት ጊዜሽወርቅ፤ በኢነርጂ ኢንቨስትመንትም ተሰማርታለች። ይህንንም ተግባራዊ ለማድረግ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር አስፈላጊውን ሁሉ በማሟላት የውጭ ባለሀብቶቹ ወደ አገር ውስጥ ገብቶ ሥራውን ለመጀመር በዝግጅት ላይ ይገኛሉ።
አማርኛ፣ እንግሊዝኛና አረብኛን አቀላጥፋ የምትናገረው ጊዜሽወርቅ፤ ወርቅ የሆነውን ጊዜ በአግባቡና ተጠቅማ ሁሉም ቦታ አለች። አሁን ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በከተማው የሚስተዋለውንና ፍጹም አልታረቅ ያለውን የመኖሪያ ቤት አቅርቦትና ፍላጎት ለማስታረቅ ከባለሀብቱ ጋር በጋራ ተቀናጅቶ መሥራትን አንደኛው አማራጭ አድርጓል። ለዚህም ታድያ ትጉና ታታሪዋ ጊዜሽወርቅን ጨምሮ ሌሎችም ተመርጠው ከአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ጋር ሥራ ጀምረዋል።
ዕውቀታቸውን፣ ጊዜያቸውንና ገንዘባቸውን ተጠቅመው አገራቸውን ማገልገል ከሚፈልጉ ሰዎች መካከል አንዷ ነኝ ከማለት ባለፈ በተግባርም አገሯን ዘርፈ ብዙ በሆኑ ተግባራት እያገለገለች ያለችው ጊዜሽወርቅ፤ በተለይም በፋይናንስ ዘርፍ ያላትን እውቀትና የሰው ሀብት ተጠቅማ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን መገንባት የሚያስችል ከውጭ ባለሀብቶች ለማምጣት ኃላፊነት ወስዳ ደፋ ቀና ትላለች።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አንደኛው ልጇ የሆነ ያህል የሚሰማት ጊዜሽወርቅ፤ ለግድቡ ግንባታ ከባለሀብቶች ገንዘብ በማሰባሰብ በኩል ከፍተኛ ድርሻ ያላትና አሁንም በግድቡ ዙሪያ በመጻፍ ከፍተኛ ንቅናቄ እያደረገች ትገኛለች።
‹‹አገር ካለኛ ማንም የላትም›› የምትለው ጊዜሽወርቅ፤ በአገር ውስጥ ሠርቶ መለወጥንና አገርን መለወጥ ማሳደግ እንደሚቻል ሙሉ ዕምነት አላት። ለብዙዎች መትረፍም ያስደስታታል። ለዚህም ሲባል አገርና ሕዝብን ይጠቅማል በተባለ ማንኛውም ዘርፍ ላይ ትሰማራለች። በቀጣይም የጀመረቻቸውን ሥራዎች አጠናክራ በውጤት የመፈጸምና ኢትዮጵያን በሁሉም ዘርፈ ከፍ የማድረግ ዕቅድ አላት።
ለሴቶችም ልዩ ምልከታ አላት። በዚህ ምክንያት አገርን ማቆም የቻሉ ሴቶች እንደሆኑ ተናግራ ዕምቅ ችሎታና ብቃት አላቸው ትላለች። በተለይም ወጣቱ በአገር ውስጥ ሰርቶ መለወጥ እንደሚችልና እያንዳንዱ ዕድል አጠገቡ እንደሆነ በመምከር በውጭው ዓለም በግልጽ የማይታይ ቅኝ ግዛት ስለመኖሩ በበርካታ አገራት የነበራትን ቆይታ ምስክር በማድረግ ወጣቱ ከስደት ይልቅ በአገሩ ሰርቶ መለወጥ የሚያስችሉ በርካታ ዕድሎችን እንዲያማትር መክራለች።
ፍሬሕይወት አወቀ