በዓለም ላይ ገዳይ ተብለው በግንባር ቀደምትነት ከተያዙ ሱስ አስያዥ እጾች መካከል ትምባሆ ግንባር ቀደሙ ነው። ትምባሆ በባህርይው የሚገድለው የሚያጨሰውን ሰው ብቻ ሳይሆን አብሮት የሚኖረውን፤ የሚሠራውን በጠቅላላው በአካባቢው ያለውን በሙሉ መሆኑ ነው ግንባር ቀደም ጎጂ ወይም ገዳይ ተብሎ ትልቁን ቦታ እንዲይዝ ያደረገው።
የዓለም ጤና ድርጅት የትምባሆ ኢንዱስትሪ በአካባቢ ላይም ሆነ በሰው ጤና ላይ ምን ያህል ጉዳት እንደሚያደርስ ሰሞኑን አዲስ መረጃ አውጥቷል። እያሳደረ ላለው ውድመት የበለጠ ተጠያቂ ለማድረግ እርምጃ እንዲወሰድ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል።
ድርጅቱ የትምባሆን አሳሳቢነት በተለይም በአሁኑ ወቅት እያደረሰ ያለውን ጉዳት ትኩረት አድርጎ በማየትም ‹‹ፕላኔታችንን የመረዘው ትምባሆ›› በሚል ባወጣው መግለጫው እንደገለጸው፣ በየዓመቱ የትምባሆ ኢንዱስትሪ ከስምንት ሚሊዮን በላይ የሰው ሕይወት፣ 600 ሚሊዮን ዛፎች፣ 2መቶ ሺ ሔክታር መሬት፣ 22 ቢሊዮን ቶን ውኃ እና 84 ሚሊዮን ቶን ካርቦን ዳይኦክሳይድን ያስከፍለናል ብሏል።
ትምባሆ በአብዛኛው የሚመረተው ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ባላቸው አገሮች መሆኑን የጠቀሰው የድርጅቱ መረጃ ለአካባቢው ምግብ ለማምረት በጣም የሚያስፈልጉት ውኃና የእርሻ መሬቶች የትምባሆ ዕፅዋትን ለማልማት እየዋሉ መሆናቸው በዓለም ችግሩ አሳሳቢ እንዲሆን እያደረገው መሆኑንም ያትታል። የደን ምንጣሮውም ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥሩ እየጨመረ መጥቷል።
በሪፖርቱ እንደተመለከተው ‹‹ትንባሆ ከማምረት፣ ከማቀነባበርና ከማጓጓዝ የሚገኘው የካርበን ዱካ በየዓመቱ በንግድ አየር መንገዶች ኢንዱስትሪ ከሚወጣው ካርቦን ዳይኦክሳይድ አንድ አምስተኛው ጋር እኩል መሆኑ አሁን ላይ ለዓለም ሙቀት መጨመር አስተዋጽኦ ከፍ እያለ እንደመጣም ነው ሪፖርቱ የሚያትተው።
‹‹የትምባሆ ምርቶች በምድራችን ላይ ከ7ሺ በላይ መርዛማ ኬሚካሎችን ይዘዋል የሚለው የዓለም ጤና ድርጅት አሁናዊ ሪፖርት እነዚህም ሲወገዱ ደግሞ ወደ አካባቢያችን ዘልቀው ይገባሉ፣ በየዓመቱ 4 ነጥብ 5 ትሪሊየን የሲጋራ ፊልተሮች (ማጣሪያዎች) ውቅያኖሶችን፣ ወንዞችን፣ የከተሞች የእግረኛ መንገዶችን፣ ፓርኮችን፣ አፈርን እና የባህር ዳርቻዎችን ይበክላሉ፤›› ያለው የድርጅቱ መረጃ እንደ ሲጋራ፣ ጭስ አልባ ትምባሆና ኢ-ሲጋራዎች ያሉ ምርቶች የፕላስቲክ ብክለትን ይጨምራሉም ይላል።
ማይክሮ ፕላስቲኮችን የሚይዙት የሲጋራ ፊልተሮች በዓለም አቀፍ ደረጃ ሁለተኛው ከፍተኛውን የፕላስቲክ ብክለት የያዙ መሆኑንም ያክላል።
የትምባሆ ምርት የሚባለው በከፊልም ሆነ ሙሉ ለሙሉ ከትምባሆ ቅጠል የተዘጋጀ በማጨስ፣ በመሳብ፣ በማኘክ፣ በማሽተት ወይም በሌላ መንገድ የሚወሰድ ማንኛውም ንጥረ ነገር ነው። ይህም ሆኖ ግን ጉዳቱ በሰው ልጆች ጤና፣ ሥነ አዕምሮአዊ ሁኔታና ማኅበራዊ ሕይወት፣ ብሎም በኢኮኖሚያዊ ላይ የሚያስከትለው ችግር በእጅጉ ከፍተኛ ነው።
ትምባሆ የደም ዝውውርን ያስታጉላል። ከዚህ ዓይነቱ ዝውውር ጋር ተያይዞ የሚመጡ የልብና የጭንቅላት ላይ ደም መፍሰስንም ሊያስከትል ይችላል። ከዚህም ሌላ የአጥንት መሳሳት የድድ፣ የጥርስ፣ የመስማትና የማየት እንዲሁም የመውለድ አቅም ላይ ከፍተኛ ችግር ሊያስከትል እንደሚችል፣ ሁለት ሦስተኛው የሚሆነውም አጫሽ የሚደርስበት የሞት አደጋ ከሚያጨሰው ሲጋራ ጋር ተያያዥነት ባለው በሽታ መሆኑን መረጃው ያመለክታል።
ሪፖርቱ እንደሚያመለክተው ሲጋራ የሚያጨሱ ሰዎች ሲጋራ ከማያጨሱ ሰዎች መካከል ከ30 እስከ 40 በመቶ ያህሉ ለደረጃ ሁለት የስኳር በሽታ የተጋለጡ ናቸው፣ ሲጋራ ለረዥም ጊዜ የሚያጨሱ ሰዎች አሟሟታቸው ከማያጨሱ ሰዎች አሥር ዓመት የቀነሰም ነው።
ኢትዮጵያም እንደ ሌሎች አገሮች በየዓመቱ ትምባሆን በቀን ደረጃ እያሰበች፤ ቀኑንም ትምባሆ ለእኛና ለምድራችን ሥጋት መሆኑንም እያመለከተች ማክበሯን ቀጥላለች። ከዚህም በላይ የጉዳዩን አሳሳቢነት የገዳይነቱን መጠን እንዲሁም በአረንጓዴ ልማት ላይ የሚያስከትለውን ችግርም በመረዳት ሕገ ወጥ የትምባሆ ንግድ ቁጥጥርና ማስወገድ ፕሮቶኮልን ለማፅደቅ የተለያዩ ሥራዎች እያከናወነች ነው።
በኢትዮጵያ በትምባሆ ሰበብ በዓመት 17 ሺ ሰዎች ሕይወታቸውን እንደሚያጡ በቅርቡ የተጠና አንድ ጥናት ማመላከቱን መረጃዎች ያመለክታሉ፤ አጫሾች በተለይም በካንሰር፣ በልብ፣ በሳንባና በጨጓራ ሕመም የመሞት ዕድላቸው ከፍተኛ መሆኑንም እነዚሁ በዘርፉ ላይ የሚሰራጩ መረጃዎች ያሳያሉ።
በኢትዮጵያ በመፍትሔነትም ግንዛቤ ከመፍጠር ባለፈ በትምባሆ ሥርጭት ላይ ጠንካራ የቁጥጥር ሥርዓትን ለመተግበር የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው። ከነዚህም ውስጥ ሕገ ወጥ የትምባሆ ንግድ ቁጥጥር ማስወገድ ፕሮቶኮልን ለማፅደቅ የሚከናወነው ዋነኛው ነው ።
ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ የትምባሆ ምርቶች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ለማድረግ ከፌዴራል የምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣንና ከጉምሩክ ኮሚሽን ጋር በመሆንም እየተሠራ ነው።
ኢትዮጵያ የዓለም ጤና ድርጅት የትምባሆ ቁጥጥር ማዕቀፍ ኮንቬንሽንን በ 2006 ዓ.ም. ማፅደቋን፣ በ2011 ባወጣችው አዋጅ መሠረትም የትምባሆ ምርትን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ማስተዋወቅ፣ ስፖንሰር ማድረግ መከልከሉ ይታወሳል።
እፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን ሰኔ 18 /2014