በጣም ግርም ስላለኝ አንድ መረጃ ሳነብ ካየሁት ልነሳ ፤ አሸባሪው ሕወሓት ከዛሬ 40 ዓመት በፊት የትግራይን ሕዝብ ብሎም ኢትዮጵያን ነጻ አወጣለሁ፤ በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ እንዲሁም በማኅበራዊ መስክ ታይቶ የማይታወቅ እመርታን አስመዘግባለሁ ብሎ ጫካ ሲገባ እነ ሳዑዲ ነዳጃቸውን አላገኙም ነበር ፤ ይህ ማለት ደግሞ አሁን እኛ ያለንበትን አይነት ኑሮ ወይንም ደግሞ ከዚህም የባሰ ዝቅተኛ ኑሮ ውስጥ ነበሩ ማለት ነው።
ቻይናም የዛሬ ገናናነቷን ብሎም የዓለም ኢኮኖሚ ሞተር የሆነውን ብልጽግናዋን አልተቆናጠጠችም ነበር። ግን ሆዳቸውን ወይም ስልጣናቸውን ከዛች የሚያገኟትን ትርፍራፊ ብቻ እየለቀሙ ሀገራቸውን በመበዝበዝ ለመኖር ያልፈቀዱት የሳዑዲም የቻይናም መንግሥታት ሕዝባቸውን ይዘው ወደፊት በመጓዛቸው ዛሬ ያሉበት ደረጃ ደርሰዋል። እኛስ?
እኛማ! አሸባሪው ሕወሓት ነጻ አወጣችኋለሁ ብሎ በጀመረው የ 17 ዓመት መራራ ጦርነት የሀገር ሃብት መተኪያ በሌለው ሁኔታ ከመውደሙም በላይ ሀገርን በጠንካራ መሠረት ላይ ሊገነቡ የሚችሉ ውድ የአገር ወጣቶች ሕይወት በከንቱ ተቀጥፏል። ከዛም በኋላ በነበረው የአገዛዝ ዘመን ሀገርን ከማሳደግ ይልቅ የስልጣን ሽሚያ ፣ ኋላም በስልጣን መባለግና ሙስናን በማስፋፋት አገር እንኳን እንደነ ሳዑዲና ቻይና ቀርቶ በነበረችበት ሁኔታ እንኳን እንዳትቀጥል በሚያደርግ መልኩ እንድትንኮታኮት ሆናለች።
ወጣቶች በሀገራቸው ተስፋ ከመቁረጣቸው የተነሳ ሀገራቸው ላይ ለመኖር፣ ለመሥራት፣ ለመለወጥ ከማሰብ ይልቅ የባዕዳን ደጅ ናፋቂና ተሰዳጅ ሆነው እንዲቀሩ በዚህም የኢትዮጵያ ስም ደሃ ተሰዳጅ እንዲሆን አድርጓል። እንደ ሕዝብ በቡድኑ የስልጣን ዘመንም የከፈልነው ዋጋ ዘርዝሮ ለመጨረስ የሚመች አይደለም ።
የቡድኑ ግፍና መከራ የታከታቸው የሕዝብ ልጆች ባደረጉት መራራ ትግል ከስልጣን ቢወገድም ፤ በሕዝብ ትግል የመጣውን ለውጥ በመቀልበስ ከተቻለው ተመልሶ ወደ ስልጣን ለመምጣት ካልተቻለው ሀገርን ለማተራመስ ያልፈነቀለው ድንጋይ የለም ። የትግራይን ሕዝብ እንደ ማስያዣ በማድረግ በመላው ሀገሪቱ ችግር መፍጠርን እንደ ትልቅ ሥራ ይዞ መቆየቱ የሁላችንም የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው። ዛሩም ከዚህ የተለየ ነገር የለም ።
ከፍጥረቱ ጀምሮ በተጠናወተው ጀብደኝነት ፤ሀገርና መንግሥትን ወደ ጦርነት ገፋፍቶ አስገብቶት እነሆ ሀገርን ችግር ውስጥ ከከተተ ወራት አልፈው ዓመታት አንድ ሁለት ማለት ይዘዋል ። በዚህም የትግራይን ሕዝብ ጨምሮ መላው ሕዝባችን አላስፈላጊ ዋጋ እየከፈለ ነው ።
በኋላ ከስልጣን ዘመኑ ጀምሮ በራሱ አምሳያ ቀርጾ የሠራቸው የሱ ተላላኪ ቡድኖች በሚፈጥሩት ሁከትና ግርግር ሕዝብ የሰላም አየር እንዳይተነፍስ ሆኗል።ግድያና መፈናቀል በሀገር አቀፍ ደረጃ ተስፋፍቷል ።
የትግራይን ሕዝብ መያዣ አድርጎ እየሄደበት ባለው የፖለቲካ ቁማር የትግራይ ሕዝብ ከፍ ላለ ችግር ተዳርጓል ። ልጆቹን ከንቱ ለሆነ ጦርነት ከመገበር አንስቶ፣ የሚበላውና የሚጠጣው እስኪያጣ ድረስ በስቃይ ውስጥ ለመኖር ተገድዷል ።
ብዙ መስዋዕትነት የከፈለለት ትግል የሚመኘውን እኩልነት፣ ሰላም፣ ፍትህና ዲሞክራሲ ከማምጣት ይልቅ ፣የከፋ መከራና ስቃይ ካመጣለት ውሎ አድሯል። መስዋዕትነቱ ለብድኑ ጥቂት አመራርና ቤተሰቦች የቅንጦት ሕይወት ከመፍጠር ባለፈ የፈየደው አንዳች ነገር የለም።
የትግራይ ሕዝብ የቀደመ የትግል መስዋዕትነቱ ተስፋ ያደረገውን እውነት ከማስጨበጥ ይልቅ ፤ ላልጠበቀውና ላልገመተው ችግርና መከራ አሳልፎ ሰጥቶታል ፤ ይህ ደግሞ ለሕዝቡ ተጨባጭ አስተምሮ ሊሆን እንደሚችል ይታመናል ።
ይህ ሕዝብ ከትናንት ተሞክሮው በመነሳት በቀደመው መስዋዕትነቱ የባርነት አገዛዝ ቀንበር የጫኑበትን የአሸባሪው ሕወሓት አመራሮች በቃችሁ ሊላቸው ይገባል ። ተስፋው ተነጥቆ ፤ ፍትሕ ተነፍጎ ብሎም በማያባራ የጦርነት እሳት ሊለበለብ ፣ ልጆቹንም ሊገብር አይገባም። ግድም የለበትም።
የትግራይ ሕዝብ የወያኔ አምባገነን አገዛዝ በፈጠረው እኩልነት የጎደለው የፖለቲካ ሥርዓት ሰለባ ከመሆኑ አንጻር ፤ አገዛዙ ያበቃ ዘንድ ፤ ከሌሎች ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ጋር በመሆን ሊንቀሳቀስ ይገባል። በፍትሕ የመዳኘት ፣ሠርቶ የመብላት ፣ራሱንና ሀገሩን የመለወጥ መብቱን ተግባራዊ ማድረግ ይጠበቅበታል ።
ይህንን መብቱን ከማንም ሊያገኘው እንደማይችል ተገንዝቦ የችግሩ ዋነኛ ባለቤት የሆነውን አሸባሪውን ሕወሓት በማስወገዱ ከፊት ሊሰለፍ ይገባል። ሞት፣ መፈናቀል፣ ረሃብ እና ስቃይ እንዲያበቃ ፤ ትናንቶቹ በተስፋ የተሞሉ እንዲሆኑ ሌላ አማራጭ የለውም ።
እስካሁን ባለው ታሪኩ የስልጣን ጥማቱን ለማርካት ሕዝብን ከሕዝብ ፤ ሃይማኖትን ከሃይማኖት ከማጋጨት፤ በዚህም ሀገርን ከማተራመስ ያለፈ አጀንዳ ኖሮት አያውቅም። ይህ እኩይ ተግባሩ ደግሞ የትናንት ብቻ ሳይሆን የዛሬም መገለጫው ነው ።ከዚህ ቡድን ጋር ሕብረት መፍጠር የትግራይን ሕዝብ አይመጥነውም ።
ቡድኑ በስልጣን በቆየባቸው ዓመታት እንደ መንግሥት ከሀገርና ከሕዝብ ጥቅም ይልቅ ለራሱ ህልውና ሲሠራ የቆየ ፤ለምንም አይነት አማራጭ አስተሳሰብ ሆነ ሰጥቶ የመቀበል ባህሪ እራሱን ያላስገዛ ነው ። ይህ ባህሪው ደግሞ ከሁሉም በላይ የትግራይን ሕዝብ ዋጋ አስከፍሏል ፤እያስከፈለም ነው ።
አሸባሪውን ሕውሓት በሀገር ሆነ በሱ ላይ ለፈጸማቸው መጠነ ሰፊ ጥፋቶች ለፍርድ ለማቅረብ በሚደረገው የሕግ ማስከበር ሂደት ውስጥ የትግራይ ሕዝብ የቡድኑን እኩይ ተግባርና ተግባሩ ያደረሰበትን ስቃይና መከራ ተገንዝቦ በቃህ የሚልበት ጊዜ አሁን ነው ።
የትግራይ ሕዝብ በቡድኑ ራስ ወዳድነትና ጀብደኝነት ምክንያት ከዚህ በላይ ዋጋ መክፈል የሚያስችል አቅም አይኖረውም ፤ላለፉት 50 ዓመታት ገደማ የከፈለው ዋጋ ያስገኘለት ጥቅም አለመኖሩ ፤ቡድኑን በቃ ለማለት በቂና ከበቂ በላይ ነው ።
በእምነት
አዲስ ዘመን ሰኔ 18 /2014