የመጽሐፉ ስም፡- ወንበዴው መነኩሴ እና ሌሎች አጫጭር ታሪኮች
ደራሲ፡- አበረ አዳሙ
የሕትመት ዘመን፡- 2014 ዓ.ም
የገጽ ብዛት፡- 114
ዋጋ፡- አንድ መቶ ስልሳ ብር
የመጽሐፍ ሕትመት ገበያው የስነ ጽሑፍ መጽሐፎች ናፍቆታል። የወቅቱ ባህሪ ሆነና የሚወጡ መጽሐፎች ልክ እንደ ጋዜጣና መጽሔቶች ትኩረታቸው ፖለቲካ ላይ ሆነ። በፖለቲካ ውስጥ ደግሞ የስነ ጽሑፍን ውበት ማግኘት ከባድ ነው። ምንም እንኳን በ1960ዎቹ የነበሩ የፖለቲካ ልቦለዶች የስነ ጽሑፍ ውበት የነበራቸው ቢሆኑም አሁን አሁን ግን ትኩረቱ መልዕክቱን ማስተላለፍ ላይ ብቻ የሆነ ይመስላል።
እንዲህ ዓይነት የስነ ጽሑፍ መጽሐፎች በሳሱበት በዚህ ወቅት አንድ አንጋፋ ደራሲ በአንድ ጊዜ ሁለት መጽሐፎችን አበርክተውልናል። ደራሲው በስነ ጽሑፍ ውስጥ ለረጅም ጊዜ የቆዩ ናቸው። ከግሽ ዓባይ የኪነት ቡድን ጀምሮ በበርካታ የስነ ጽሑፍ መድረኮች ሥራዎቻቸውን ሲያቀርቡ የቆዩ፣ መጻሕፍትን እና የተውኔት ጽሑፎችን ሲሠሩ የቆዩ ናቸው።
በብዙዎች ዘንድ የሚታወቀው ‹‹ውዳሴ ሞት›› የግጥም መድብል፣ ‹‹ፍቅር በሲኦል›› ውስጥ እና ከሌሎች ደራሲያን ጋር በመሆን ‹‹የዘመን ቀለማት›› የተሰኙ መጻሕፍትን ጽፈዋል።
ደራሲ አበረ አዳሙ የደራሲያን ማህበር ፕሬዚዳንት ሲሆኑ በአሁኑ ጊዜ ደግሞ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ናቸው። ለበርካታ ዓመታት በጋዜጠኝነት ሙያም አገልግለዋል። በስነ ጽሑፍ እና ጋዜጠኝነት ውስጥ ያለፈ ሕይወት ለታሪክና ማህበራዊ ጉዳዮች ቅርብ አድርጓቸዋል። ለዚህም ይመስላል መጽሐፋቸው ታሪክና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ያተኩራል። ቱባ የሆኑ የአገር ቤት የስነ ጽሑፍ ቃላትን ይጠቀማሉ።
የደራሲ አበረ አዳሙ ሁለት መጻሕፍት በሰኔ ወር መጀመሪያ ሳምንት በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ተመርቀዋል። አንደኛው መጽሐፍ ‹‹አገሬን አፋልጉኝ›› የግጥም መድብል ሲሆን ሁለተኛውና በዚህ ዓምድ በሰፊው የምናየው ደግሞ ‹‹ወንበዴው መነኩሴ እና ሌሎች ታሪኮች›› ይሰኛል።
መጽሐፉ ‹‹መዘክር›› ሲል በገለጸው መግቢያ ላይ መታሰቢያነቱን ለጀግናው በላይ ዘለቀ አድርጓል። ከበላይ ዘለቀ በተጨማሪም አብረውት ለተሰቃዩ ሽፈራው ጋርባው፣ አያሌው መሸሻ፣ ለወንድሙ እጅጉ ዘለቀ፣ ለልጁ የሻሽወርቅ በላይ እና ለባለቤቱ ሸክሚቱ አለማየሁ ሆኗል መታሰቢያነቱ።
መጽሐፉ ‹‹ሣተናው! በላይ ዘለቀ›› በሚል ርዕስ ደራሲው ከዚህ በፊት የሰራው የተውኔት ጽሑፍ በሰፊው ይገኝበታል። በጽሑፉ ውስጥ የተገለጹ ቃላት ራሱ ተውኔቱን እንደማየት ማለት ነው። ወኔ የሚቀሰቅሱ ናቸው። በዚያ ላይ በግጥም የተከሸኑ ናቸው። ወደ ‹‹ሣተናው! በላይ ዘለቀ›› ከመሄዳችን በፊት ግን ከመጽሐፉ ሌሎች አጫጭር ታሪኮች በጥቂቱ እንጠቃቅስ።
‹‹ቢዝነሱ›› በሚል ርዕስ በቀረበው ጽሑፍ ውስጥ ቀደም ሲል የነበረችውን አራት ኪሎን ያስቃኘናል። በአራት ኪሎ ጨለማን ተገን አድርገው በየጉራንጉሩ ይደረጉ የነበሩ የምንተፋ፣ የስካርና አሸሸ ገዳሜ ሁካታ፣ የዝሙት ገበያ፣ የሌባና ፖሊስ ፍጥጫን ያሳየናል።
‹‹የለማኝ ቁንጩ›› በተሰኘው ርዕስ ሥር ደግሞ እያሳሳቀ ማህበራዊ ገመናችችን ይነግረናል። ለልመና የሚደረጉ የማጭበርበር ሥልቶችና ለልመና የሚውሉ ፍልስፍናዎች ለምርምር ቢውሉ የሥልጣኔ ማማ ላይ ይሰቅሉን እንደነበር የሚያሳይ አገላለጽ ነው።
‹‹የዝናብ አንሹ ልጅ›› በሚል ርዕስ ሥር ያሉት ታሪኮች ልጅነትን ያስታውሳሉ። የልጅነትን የፍልስፍና ጥያቄዎች፣ ነገሮችን ለማወቅ ያላቸው ጉጉትና ታላላቆች የሚያደርጉትን ነገር አስመስሎ ለማድረግ ጥረት ሲያደርጉ እናያለን። ደራሲው እነዚህን የልጅነት እሳቤዎች አሁን ላይ ሆኖ ማስታወሱ አስተውሎቱን ያሳያል።
በዚህ ምዕራፍ ውስጥ በተለይም በጎጃም አካባቢ የሚደረጉ ባህላዊና ልማዳዊ የማህበረሰብ ድርጊቶች ይታያሉ። ጽሑፉን ማንበብ ልጅነትንና አካባቢያዊ ባህልን በማስታወስ ወደ ቀደመ ሕይወት ይመልሳል።
በስፋት የምናየው ግን ‹‹ሳተናው! በላይ ዘለቀ›› የሚለውን ነው። የተውኔት ቴክኒካዊ እንቅስቃሴዎችን ትተን በውስጡ ያሉ ይዘቶችን ብቻ እናያለን። ተራኪው እንዲህ ይላል።
እውነት ነው ወይ ኮስትር የምንሰማው ወሬ
መች ተጠምዶ ያውቃል አህያ ከበሬ።
አገር ታሟል አሉ ሄደን እንየው
የማይድን እንደሆን እኛ እንቅደመው
እናት አባት ቢሞት በአገር ይለቀሳል
እህት ወንድም ቢሞት በአገር ይለቀሳል
አገር የሞተ እንደሁ ወዴት ይደረሳል?
በተለይም የመጀመሪያዎቹ ስንኞች ቅኔ ለበስ ናቸው። የንጉሡን ሥርዓትም ሸንቆጥ የሚያደርጉ ይመስላል። ‹‹መች ተጠምዶ ያውቃል አህያ ከበሬ›› የምትለዋ ስንኝ ነገረኛ ስንኝ ናት። ንጉሡ በላይ ዘለቀን ማሰቀላቸው በጣም ነው ያስወቀሳቸው። የጣሊያን ወራሪን የተዋጋ አርበኛ አስገድለው የራሳቸውን ታማኞች ሹመት ሰጥተዋል። ‹‹…የሞተልሽ ሳለ የገደለሽ በላ›› የተባለውም ለዚህ ነው።
‹‹መች ተጠምዶ ያውቃል አህያ ከበሬ›› የተባለውም የወቅቱ ሥርዓት ለበላይ ዘለቀ አይመጥነውም የሚል መልዕክት ያለው ነው። ደራሲው በመግቢያው ላይ የንጉሡን ፍርደ ገምድልነት መግለጹ ደግሞ የዚህን ስንኝ መልዕክት የበለጠ ግልጽ ያደርገዋል።
‹‹አገር ታሟል አሉ ሄደን እንየው፤ የማይድን ከሆነ እኛ እንቅደመው›› የሚለውም የጀግናን ስሜት የሚገልጽ ነው። እናስተካክለው፤ ካልሆነ ግን አገር ሞቶ ከማየት እኔ ሞቴን እመርጣለሁ እንደማለት ነው።
እስኪ በተውኔቱ ውስጥ አባ ኮስትር (በላይ ዘለቀ) እና ሸክሚቱ (የበላይ ዘለቀ ባለቤት) ከሚያደርጉት ምልልስ ጥቂት እንጥቀስ፡-
አባ ኮስትር፡- ሸክሜዋ! የአባቴን ደመኞች ከላሁ ብየ ደስ ሲለኝ፣ ቅድም እነ ሽፈራው ያልረባ ነገር ነገሩኝ!
ሸክሚቱ፡- ምነዋ አያ በላይ! ደግሞ ምን መጣ ነው የምትለኝ?
አባ ኮስትር፡- ምን የማይመጣ ነገር አለ ሸክሚቱ!
አገር አማን አይደለም ነው የሚሉት እንደ ትናንቱ
ዘውዱ ታሟል ነው የሚሉት የአገር አንድነት ምልክቱ
ሸክሚቱ፡- እናሳ? (በመደንገጥ)
አባ ኮስትር፡- በረሃ መውረዴ ነው የወደቀውን ዘውድ ላነሳ!
ሸክሚቱ፡- ዘውዱ ቢወድቅ ቢነሳ ለእኛ ምናችን ነው አያ በላይ!
ይልቅ አርፈን ልጆቻችንን እነ የሻሽወርቄን እናሳድግ እባክህ አንለያይ፤
አባ ኮስትር፡- ሸክሜዋ! በጥሞና ካስተዋልነው፤ ዘውድ እኮ የአገር ምልክት፣ ትልቅ ሰንደቅ ማለት ነው፤ ሰንደቅ ዓላማችን ወድቆስ ምኑን ኖርነው? እንዴትስ ነው ልጅ የሚያድገው?
በገዛ አገር ላይ ተዋርዶ ለጠላት አሽከር ከመሆን መሞት በስንት ጣዕሙ ያውም ለአገር ለወገን!
………….. እያለ ተውኔቱ ይቀጥላል።
ተውኔቱ በአርበኛው በላይ ዘለቀ እና በንጉሡ ዘመን የነበረውን ታሪክ በስነ ጽሑፋዊ አጻጻፍና በወኔ ስንኞች ይነግረናል። በላይ ዘለቀ ለአገሩ የነበረውን ቆራጥነትና ውለታ ይነግረናል። በተቃራኒው ግን የንጉሡ ሥርዓት ክህደት ፈጽሞበታል።
ባለቤቱ ሸክሚቱ ‹‹ዘውዱ ቢወድቅ ቢነሳ ለእኛ ምናችን ነው አያ በላይ!›› ትለዋለች። በበላይ ዘለቀ እና በዘውዱ ሥርዓት መካከል የነበረው ታሪክ ለብዙዎቻችን ግልጽ ነው።
ያም ሆኖ ግን በላይ አገሩን ያስቀድማል። ዘውዱ የአገር ምልክት ነው ማለቱ በወቅቱ የአገሩ መለያ የነበረውን ሰንደቅ ዓላማ እና የአገር አስተዳዳሪውን ምልክት ማክበር ማለት አገር ማክበር ማለት ነው ብሎ ያምናል ማለት ነው። በሥርዓት ላይ ቅሬታና በደል ቢኖርበት እንኳን የውጭ ወራሪ ሲመጣ ግን እሱን ወደጎን ብሎ አገር ማስቀደምን የሚያስተምር ነው።
ተውኔቱ ከተውኔትነትም በላይ ነው፤ ምክንያቱም ራሱን ችሎ ታሪክ ነጋሪ ነው። በወቅቱ የነበሩ ጦር መሪዎችን፣ የጦር ግንባሮችን፣ የጠላት መግቢያዎችን… በአጠቃላይ ክስተቶችን ሁሉ ይጠቅሳል።
በተውኔቱ ውስጥ በቀረርቶ ከተነገሩ ስንኞች ይቺን እንውሰድ።
ኧረ ፈረስ ይሙት የመጋዣው ልጅ
ወንድ በቅሎ ሲሞት ያሳዝናል እንጂ!
ኧረ ጀግና ይሙት ፈሪ ይኑር ቢሻው
አተላ መሸከም ይችላል ትክሻው
ፈሪና ተራራ ዝንታለም ይኖራል
ጀግና ብርሌ ነው ቶሎ ይሰበራል
በተለይም የመጀመሪያዎቹ ሁለት ስንኞች ውስጥ ቅኔ አለ። ፈረስ ከበቅሎ በላይ በሊታ ነው ይባላል። በእርግጥ አድካሚ የጉልበት ሥራ የሚሠሩም ፈረሶች ናቸው። ግን በልማድ ፈረስ እንደ ‹‹ሆዳም›› ይቆጠራል። በዚህ ለመመሰል ይመስላል ሆዳም ሰው እንደ ፈሪ ይቆጠራል።
የእነዚህ ስንኞች ቅኔ ‹‹ወንድ በቅሎ ሲሞት›› የሚለው ነው። በቀጥታ በላይ ዘለቀን ማለቱ ነው። ወንድ ‹‹በቅሎ›› ማለት ተወልዶ ማለት ነው። በወቅቱ ሆዳቸውን ብለው ሰጥ ለጥ ብለው የታዘዙ ሰዎች ምንም አልተደረጉም፤ በላይ ዘለቀ ግን ክብሬን በማለቱ በንጉሡ ፍርደ ገምድልነት ተሰቀለ።
‹‹ጀግና ይሙት፤ ፈሪ ይኑር ቢሻው….›› የተባለውም ጀግና ክብሩን አጥቶ መኖር ስለማይችል ነው። ፈሪ ግን ከመጣ ከሄደው ጋር ተመሳስሎና አድርግ ያሉትን ስለሚያደርግ እንደ ተራራ ምንም ሳይሆን ይኖራል። ‹‹አተላ መሸከም ይችላል ትክሻው›› የተባለው ለዚህ ነው። ክብሬ ተነካ አይልም፣ በባርነት መኖር ምንም አይመስለውም፣ የተሰጠውን ሁሉ እየተሸከመ መኖር ይችላል።
በአጠቃላይ ‹‹ወንበዴው መነኩሴ እና ሌሎች ታሪኮች›› መጽሐፍ፤ ለበላይ ዘለቀ የሰጠው ቦታ ሰፊ ነው። በተቀሩት ይዘቶችም ቢሆን ማህበራዊና ባህላዊ እሴቶችን በስነ ጽሑፍ የተገለጸበት ነው። ስነ ጽሑፋዊ ለዛ ያላቸው መጻሕፍት በሳሱበት ወቅት እንዲህ ዓይነት መጽሐፎችን ማግኘት ለስነ ጽሑፉ ተስፋ ነውና ደራሲውን አሁንም ደግመህ ጻፍ እንላለን!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ሰኔ 16/2014