ኢትዮጵያ በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ግዙፍ አቅም እንዳላት ይገለፃል። ይሁን እንጂ በ2014 ዓ.ም የበጀት ዓመት በ10 ወራት ውስጥ ያገኘችው የውጭ ምንዛሬ ግማሽ ቢሊዮን ዶላር እንኳ አልሞላም፡፡ በእነዚሁ ወራት ገቢ ምርቶችን በአገር ውስጥ ምርት በመተካት ረገድ ደግሞ ማሳካት የተቻለው ከሁለት ቢሊዮን ዶላር ያነሰ ነው፡፡
የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል ሰሞኑን የሚኒስቴሩን የ10 ወራት የሥራ አፈፃፀም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡት ሪፖርት፣ በ2014 ዓ.ም የበጀት ዓመት በ10 ወራት ውስጥ ከአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ 498 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት ታቅዶ 418 ሚሊዮን ዶላር (84%) መገኘቱን ተናግረዋል፡፡
ይህ ገቢ በ2013 ዓ.ም የበጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከተገኘው 315 ሚሊዮን 500 ሺ ዶላር ገቢ ጋር ሲነፃፀር የ101 ሚሊዮን 500 ሺ ዶላር ብልጫ አለው፡፡ ጨርቃ ጨርቅና አልባሳት 153 ሚሊዮን ዶላር፣ ሥጋና ወተት 98 ሚሊዮን ዶላር፣ ምግብና መጠጥ 93 ሚሊዮን 800 ሺ ዶላር፣ ቆዳና የቆዳ ውጤቶች 33 ሚሊዮን ዶላር፣ የኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብዓቶች 22 ሚሊዮን 600 ሺ ዶላር እንዲሁም የማኑፋክቸሪንግ ቴክኖሎጂና ኢንጂነሪንግ ምርቶች 16 ሚሊዮን 700 ሺ ዶላር የውጭ ምንዛሬ አስገኝተዋል፡፡
ገቢ ምርቶችን በአገር ውስጥ ምርት በመተካት ረገድ ደግሞ በ10 ወራት ውስጥ ሁለት ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ዶላር ዋጋ ያላቸውን ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ ምርት ለመተካት ታቅዶ እንደነበርና አንድ ቢሊዮን 891 ሚሊዮን 600 ሺ ዶላር (85%) ዋጋ ያላቸውን ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት መተካት እንደተቻለ ገልፀዋል፡፡
105 ሚሊዮን 400 ሺ ዶላር እንዲተካ እቅድ ተይዞለት የነበረው የቆዳና የቆዳ ውጤቶች ንዑስ ዘርፍ 144 ሚሊዮን 800 ሺ ዶላር ዋጋ ያላቸውን ተኪ ምርቶችን በማምረት ከእቅዱ የበለጠ አፈፃፀም አስመዝግቧል፡፡ በምግብና መጠጥ ንዑስ ዘርፍ አንድ ቢሊዮን 89 ሚሊዮን ዶላር፣ በኬሚካልና ኮንስትራክሽን ንዑስ ዘርፍ 471 ሚሊዮን 700 ሺ ዶላር እንዲሁም በማኑፋክቸሪንግ ቴክኖሎጂ ንዑስ ዘርፍ ደግሞ 186 ሚሊዮን 100 ሺ ዶላር ዋጋ ያላቸውን ተኪ ምርቶችን ማምረት ተችሏል፡፡
አቶ መላኩ የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ በርካታ መሰናክሎች እንዳሉበትና የሀገሪቱ አቅምና የገበያ ፍላጎትም ከተመዘገበው አፈፃፀም በላይ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ ‹‹ከ10 ዓመቱ የሀገራችን ብሔራዊ የልማት እቅድ ውስጥ ለአምራች ዘርፉ የተቀመጡት ግቦች በጥረት ሊሳኩ የሚችሉ ቢሆኑም አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ግን አምራች ኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅማቸውን እየተጠቀሙ እንዳልሆነ በጥናት ማረጋገጥ ተችሏል›› ብለዋል፡፡
በእርግጥ ለአምራች ዘርፍ የሚሆን እጅግ ከፍተኛ አቅም ያላት ሀገር በ10 ወራት ጊዜ ውስጥ ያገኘችው የውጭ ምንዛሬ ገቢ ግማሽ ቢሊዮን ዶላር የሚሞላ አለመሆኑና ከዚህ ገቢ በብዙ እጥፍ የሚበልጥ ዋጋ ያለው ምርት ማስገባቷ አፈፃፀሟ ከፍላጎቷና ከአቅሟ በእጅጉ የራቀ ስለመሆኑ ጉልህ ማስረጃ ተደርጎ ሊቀርብ ይችላል፡፡
በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህርና በ‹‹ፍሮንቲየርአይ (Frontieri)›› ጥናትና አማካሪ ድርጅት ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር ሞላ አለማየሁ፣ ሀገሪቱ በአምራች ዘርፉ ካላት ትልቅ አቅም አንፃር ከዘርፉ ወደ ውጭ ከተላከው ምርት የተገኘው ገቢም ሆነ የገቢ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በማምረት ማዳን የተቻለው የውጭ ምንዛሬ በቂ ነው ብሎ መናገር እንደማይቻል ያስረዳሉ፡፡
እርሳቸው እንደሚሉት፣ ኢትዮጵያ ለአምራች ዘርፉ የሚሆን እምቅ አቅም አላት፡፡ በ10 ወራት ጊዜ ውስጥ ከዘርፉ ወደ ውጭ ከተላከው ምርት የተገኘው ገቢም ሆነ የገቢ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በማምረት ማዳን የተቻለው የውጭ ምንዛሬ ከአገሪቱ አቅም አንፃር ሲመዘን አነስተኛ ነው፡፡
ዋነኞቹ የወጪ ንግድ ምርቶች እንደቡና፣ የቅባት እህሎችና ጫት ያሉ የግብርና ምርቶች እንደሆኑ የጠቆሙት ዶክተር ሞላ፣ ‹‹ብዙ ሀብት የሌላቸው አገራት ከኢትዮጵያ የተሻለ ገቢ ያገኛሉ፡፡ የበርካታ ሀብቶች ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያ ግን ከወጪ ንግድ የምታገኘው ገቢ ዝቅተኛ ነው፡፡ በተለይ በማምረቻው ዘርፍ የተመዘገበው ውጤት ከአገሪቱ አቅምና ፍላጎት አንፃር ሲመዘን ብዙ ጥረት የሚቀረው ነው›› ይላሉ፡፡
በአገር ውስጥ መመረት እየቻሉ ውድ በሆነ ዋጋና አገሪቱ እጅ አጥሯት በምትሰቃይበት የውጭ ምንዛሬ ከውጭ አገራት ተገዝተው ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ በርካታ ምርቶች አሉ፡፡ እነዚህን ምርቶች በአገር ውስጥ በማምረት ለምርቶቹ ግዥ የሚወጣውን የውጭ ምንዛሬ ለማስቀረት ዓይነተ ብዙ ግብዓቶች ያስፈልጋሉ፡፡
ገቢ እንደሆነ የተናገሩት አቶ መላኩ፤ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን ደረጃ በደረጃ በሀገር ውስጥ ምርቶች ለመተካት የሚደረገውን ጥረት ለማሳካት አምራቾች ሀገሪቱ በዘርፉ ያላትን አቅም መጠቀምና ተወዳዳሪ ምርቶችን ለማምረት አቅማቸውን መገንባት እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል፡፡
የምጣኔ ሀብት ጥናት ባለሙያው ዶክተር ሞላ በበኩላቸው ከወጪ ንግድ የተሻለ ገቢ ለማግኘትም ሆነ የገቢ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በማምረት የውጭ ምንዛሬን ለማዳን በመንግሥት በኩል ሊደረግ የሚገባው ጥረት ለዚህ ተግባር ምቹ የሆኑ ፖሊሲዎችንና ሕጋዊ ማዕቀፎችን ከማዘጋጀት እንደሚጀምር ይናገራሉ፡፡ እንደርሳቸው ማብራሪያ፣ የወጪ ምርቶችን በብዛትና በተሻለ ጥራት አምርቶ ለውጭ ገበያ ለማቅረብና የገቢ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለማምረት አዋጭ የሆነ እንዲሁም የዘርፉን አቅሞችና ችግሮች ከግምት ውስጥ ያስገባ የፖሊሲ ዝግጅትና ድጋፍ ያስፈልጋል፡፡
ለኢንቨስተሮች በቂ የሆነ የግብዓት አቅርቦት ሊመቻችላቸው ይገባል፡፡ ይህ ማለት አምራቾቹ ግብዓቶቹን ከሀገር ውስጥ እንዲያገኙ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር ማለት ነው፡፡ ዘርፉ የሚፈልገው አስፈላጊ የሰው ኃይልም ታሳቢ ሊደረግ ይገባል፡፡ በዚህ ረገድ ተወዳዳሪ የሆኑ ምርቶችን ማምረት የሚችል ብቁ የሰው ኃይል ማዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ‹‹የውጭ ባለሀብቶችን ከሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ጋር በሽርክና ማሰራት የወጪ ንግድን ለማሳደግ እንደአንድ አማራጭ የሚወሰድ ስልት ነው፡፡ የውጭ ባለሀብቶች የተሻለ የቴክኖሎጂ አቅም ስለሚኖራቸው የእውቀት ሽግግር እንዲኖር ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል›› በማለት እውቀትና ልምድ ያላቸውን የውጭ ኩባንያዎችን ከሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ጋር በሽርክና እንዲሰሩ ማበረታታትም ተገቢ እንደሆነ ዶክተር ሞላ ይገልፃሉ፡፡
ሌላው አስፈላጊ ነገር ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በማምረት ላይ ለሚሰማሩ ባለሀብቶች የሚደረጉ ማበረታቻዎች ጉዳይ ነው፡፡ እነዚህ ባለሀብቶች አጠቃላይ ምርትን ከመጨመር ባሻገር ሀገሪቱ ለምርት ግዢ የምታወጣውን የውጭ ምንዛሬ በማዳን ተጨማሪ ሚና ስለሚኖራቸው ለባለሀብቶቹ ማበረታቻዎችን ማድረግ ይገባል፡፡ በሀገር ውስጥ ያመረቱት አምራቾች ራሳቸውን በገንዘብም ሆነ በእውቀት እያዳበሩ አቅማቸውን እንዲያጎለብቱ የሚያግዟቸውን አሰራሮች መተግበር ይገባል፡፡ በሌላ በኩል ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በማምረት ላይ ለሚሰማሩ ባለሀብቶችም ትኩረት በመስጠት ልዩ ማበረታቻዎችን ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ለአምራቾቹ የሚያስፈልጉ የመሰረተ ልማት አቅርቦቶችን ማሟላት እንደሚገባም ዶክተር ሞላ ይገልፃሉ፡፡ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የሚገኙ አምራቾች ያሉባቸውን ችግሮች በማሳያነት የሚጠቅሱት ዶክተር ሞላ፣ ለችግሮቹ መፍትሄ ለማበጀት የባለሀብቶች፣ የኅብረተሰቡና የመንግሥት የተቀናጀ ጥረት ተፈላጊ እንደሆነም ይናገራሉ፡፡ ‹‹ምርቶችን በሀገር ውስጥ ማምረት የተዛባ የንግድ ሚዛንን ያስተካክላል፡፡ ሀገሪቱ ከእድገቷ የምትጠቀመውና ኢኮኖሚዋም የተረጋጋ የሚሆነው ያልተዛባ የንግድ ሚዛን ሲኖራት ነው፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያ የአምራች ዘርፍ ችግሮችን በመፍታት የወጪ ንግዷን ማሳደግና የንግድ ሚዛኗን ጤናማ ማድረግ አለባት›› ይላሉ፡፡
ከሀገር ውስጥ ምርቶች ይልቅ ለውጭ ምርቶች ፍላጎት የማሳየት ዝንባሌ የሚመነጨው የምርቶቹን ትክክለኛ ማንነት በጥንቃቄ ከመለየትና ከማወቅ ብቻ አይደለም፡፡ በሸማቹ ዘንድ የሚስተዋለው የአመለካከት ችግርም የሀገር ውስጥ ምርቶች ትኩረት እንዳያገኙ የራሱ ሚና አለው፡፡ ይህን ጉዳይ በተመለከተ ዶክተር ሞላ ሲናገሩ ‹‹የሀገር ውስጥ ምርቶች ጥራት የላቸውም የሚል አስተሳሰብ አለ፡፡
በተመሳሳይ የጥራት ደረጃ ተመርተው ለውጭና ለሀገር ውስጥ ገበያዎች የቀረቡ ምርቶችን እኩል ያለማየት ዝንባሌን መለወጥ ያስፈልጋል፡፡ በከፍተኛ ጥራት በሀገር ውስጥ ተመርተው ለውጭ ገበያዎች የሚቀርቡ የኢትዮጵያ ምርቶች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ የሀገር ውስጥና የውጭ ምርቶችን የመግዛትና የመጠቀም አወንታዊና አሉታዊ ውጤቶችን ማወቅ ይገባል፡፡ ይህ ሲባል ግን ችግሮችንም ለማስተካከል ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል፡፡
ከወጪ ንግድ የተሻለ ገቢ ለማግኘትም እና የገቢ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በማምረት የውጭ ምንዛሬን ለማዳን የሚደረገውን ጥረት ለማሳካት አስተዋፅዖ ካላቸውና በመንግሥት ትኩረት ከተሰጣቸው የትግበራ አቅጣጫዎች መካከል አንዱ ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› የተሰኘው ንቅናቄ ነው፡፡ የሀገራዊ ንቅናቄው ዋና ዋና ዓላማዎች የአምራች ኢንዱስትሪውን ችግሮች በጋራ በመፍታት ለዘርፉ ዘላቂ ልማትና ተወዳዳሪነት ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር ዘርፉ ለኢኮኖሚያዊ መዋቅራዊ ሽግግር የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲወጣ ማስቻል እንዲሁም በዘርፉ ያለውን የስራ ባህል ማሻሻል ብሎም የኢንዱስትሪ ምርቶችን ጥራትና ተወዳዳሪነት በማሻሻል ገቢ ምርቶችን የመተካት ሽፋንን ማሳደግ ናቸው፡፡
ንቅናቄው የአምራች ኢንዱስትሪዎችን ምርትና ምርታማነት ለመጨመር ብሎም የዘርፉን ልማት ለመደገፍ እንዲሁም አምራች ኢንዱስትሪዎችን በጥራትና በቁጥር ለማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራት የሚከናወኑበት ሲሆን የኢንዱስትሪ ዘርፉን ከተለመደው አሰራር በማሻገር ምርታማነትን ለመጨመር እንደሚያግዝ ታምኖበታል፡፡
በአሁኑ ወቅት ኢንዱስትሪዎች ለሀገር ውስጥ ምርት እድገት እያበረከቱት ያለውን አነስተኛ አስተዋፅኦ እንደሚያሳድግም ተሥፋ ተጥሎበታል፡፡ በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ አስቻይ ሁኔታዎችና በመፍጠር የዘርፉን የማረት አቅም ማሳደግ፣ ለዜጎች ተጨማሪ የስራ ዕድል መፍጠር፣ የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ማሳደግ እና ገቢ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በመተካት የውጭ ምንዛሬን ማዳን ከ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› መርሃ ግብር የሚጠበቁ ውጤቶች ናቸው፡፡
አቶ መላኩ ንቅናቄው የኢንዱትሪዎችን የማምረት አቅም በማሳደግ የወጪ ንግድን ለመጨመርና ገቢ ምርቶችን ለመተካት ለሚደረገውን ጥረት አወንታዊ አስተዋፅዖ እያበረከተ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ንቅናቄው ካስገኛቸው ውጤቶች መካከል አንዱ ማምረት ያቆሙ ኢንዱስትሪዎችን ወደ ሥራ እንዲመለሱ ማስቻሉ መሆኑን ጠቁመው፤ በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ማምረት አቁመው ከነበሩ ፋብሪካዎች መካከል በንቅናቄው ትግበራ 118 የሚሆኑት ወደ ስራ መመለሳቸውን ተናግረዋል፡፡
‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› የተሰኘው ንቅናቄ አንድ ሀገር ባላት እምቅ ሀብት ላይ ተመስርታ ማምረት እንደሚገባት የሚጠቁም መርሃ ግብር እንደሆነ የሚናገሩት የምጣኔ ሀብት ጥናት ባለሙያው ዶክተር ሞላ፤ ‹‹ለማምረት ምን ያስፈልጋል?›› ለሚለው ጉዳይ ትኩረት መስጠት እንደሚስፈልግና የግብዓት እጥረት የሀገሪቱ ኢንዱስትሪዎች ከግማሽ በታች በሚሆነው አቅማቸው እንዲያመርቱ ስላስገደዳቸው የማምረት አቅምን ለማሳደግ የግብዓት አቅርቦትን ማመቻቸት እንደሚገባ ይናገራሉ፡፡
‹‹ንቅናቄው በተገቢው የፖሊሲ ማዕቀፍ እና በተቀናጀ ጥረት ከታገዘ ምርታማነትን ለማሳደግ እንዲሁም የውጭ ምንዛሬ እጥረትንም ለማቃለል አማራጭ መፍትሄ መሆን ይችላል። የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችም ሆኑ የውጭ ኢንቨስተሮች በኢንቨስትመንት ስራዎች ላይ እንዲሰማሩ እድል ይፈጥራል፡፡ ‹ኢትዮጵያ ታምርት› ብሎ መናገር ብቻ ሳይሆን ጠንካራ የተግባር ስራ ይጠይቃል፡፡ ከቃል ያለፈ ነገር ያስፈልጋል፡፡ ለታቀደው ነገር ሁሉ ክትትል ማድረግ ይገባል›› በማለት ይመክራሉ፡፡
በኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት ውስጥ ከፍተኛ የሚዛን መዛባት ከሚታይባቸው መስኮች መካከል አንዱ የገቢና የወጪ ንግድ አለመመጣጠን ነው፡፡ ይህ ሀገሪቱ ወደ ውጭ ከላከቻቸው ምርቶች በምታገኛት ጥቂት የውጭ ምንዛሬ ገቢ እና ለብዙ የገቢ ምርቶች በምታወጣው ግዙፍ የውጭ ምንዛሬ ወጪ አለመመጣጠን ምክንያት ከሚፈጠረው የንግድ ሚዛን መዛባት (ጉድለት) እፎይታ የምታገኘው በአምራች ዘርፉ ያላትን አቅም ተጠቅማ ምርትን በብዛትና በጥራት አምርታ ለውጭ ገበያ ስታቀርብና ከውጭ የምታስገባቸውን ምርቶች በሀገር ውስጥ በማምረት የውጭ ምንዛሬ ወጪዋን ማዳን ስትችል ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ አመለካከትን ከማስተካከል ጀምሮ ፖሊሲዎችን ማዘጋጀትና ጠንካራ ክትትል ማድረግ አማራጭ የሌለው መፍትሄ ነው፡፡
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ሰኔ 16/2014