ከላቲን አሜሪካ አገራት መካከል በመሬት ስፋትም ሆነ በህዝብ ብዛት በቀዳሚነት በምትጠራው ብራዚል፤ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከሙስና ጋር በእጅጉ ተቆራኝታለች። በአሁን ወቅትም አገሪቱ በዓለም በዓቀፍ ደረጃ ስሟ የሚነሳው እንደወትሮ በእግር ኳስ ሃያልነቷ ሳይሆን በሙስና ቅሌት ሆኗል።
ይህን ያስተዋሉ መገናኛ ብዙሃንና የፖለቲካ ምሁራን ታዲያ በብራዚል የሚስተዋለውን ሙስና ከሌሎች አገራት በእጀጉ የሚለይበት አንድ ባህሪ እንዳለው ያትታሉ። ይኸውም በአብዛኛው በመንግስት ከፍተኛ ሹማምንት የሚፈፀምና ከሁሉ በላይ ከአገሪቱ ፕሬዚዳንቶች ጋር በእጅጉ የሚቆራኝ መሆኑ ነው።
ይህ በርካታና ታላላቅ የንግድ ተቋማትን እንዲሁም ፖለቲከኞችና ከፍተኛ የመንግስት ሹማምንትን ያሳተፈ የሙስና ተግባርም የአገሪቱን ሁለንተናዊ ገፅታ ጥቁር ጥላሸት ቀብቶታል። ሹማምንቱ የመንግስት በጀት እንደፈለጉ መጠቀምና ወደ ግል አካውንታቸው መሸጎጣቸውም በሃሜት ደረጃ የሚነገር ሳይሆን በምርመራ የተረጋገጠም ጭምር ነው።
በተለይ ድህነት ጥርሱን አግጥጦ የሚታይባትና ከፍተኛ ወንጀል የሚፈጸምባት በአገሪቱ ዋና ከተማ ሪዮ ዴጄኔሮ ያለው ሙስና አይጣል የሚያሰኝ መሆኑ ተደጋሞ ይነገርለታል። የከተማዋ አስተዳደር የነበሩት ሰርጂዮ ጋብሬል ሳይቀሩ ለአንድ የጋዝ ኩባንያ ከውል በላይ ክፍያ እንዲፈፀምለት በማድረግ ጉቦ መቀበላቸው በመረጋገጡ ዘብጥያ መውረዳቸው የቅርብ ጊዜ ትውስታ ሆኖ ይጠቀሳል።
በላቲን አሜሪካዋ ታላቅ አገር ብራዚል ሙስና እና ሙሰኞች ምን ያህል እንደተስፋፉ በተለይ በመንግስት ሹማምንቶች የሚፈፀሙ ወንጀሎች መጠን ከፍ ስለማለቱ ለማረጋጋጥ ያለፉት ሶስት የአገሪቱ ፕሬዚዳንቶችን የስልጣን ቆይታና የሙስና ቅሌት መመልከት ብቻ በቂ ነው።
እ.ኤ.አ ከ2003 እስከ 2011 ብራዚልን በፕሬዚዳንትነት የመሩት የአገሪቱ ሰራተኞች ፓርቲ የቀድሞ መሪ ሉዊዝ አናሲዮ ሉላ ዳሲልቫ በላቲን አሜሪካው ታሪክ እጅግ ግዙፍ በተባለለት የሙስና ቅሌት እኤአ 2014 የተጀመረውና ካርውሽ በተባለው ዘመቻ ሙስና ወንጀል መፈፀማቸው ተረጋግጦባቸዋል። ጥፋተኛ ተብለውም የ12 ዓመት ፍርድ ተፈርዶባቸዋል።
እርሳቸውን በመተካት ወደ ስልጣን የመጡት ዴልማ ሩሴፍ ቢሆኑ፤ ሙሰኛ ተብለው ስማቸው ከሚነሱ የአገሪቱ ከፍተኛ ሹማምንቶች መካከል ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ናቸው። በተለይ በታሪክ የአገሪቱ የመጀመሪያ ሴት ፕሬዚዳንት ከሆኑት ሩሴፍ ላይ ከቀረቡት የሙስና ክሶች መካከል የአገሪቱ ሕግ በማይፈቅደው ሁኔታ የመንግስት በጀትን ወይም ወጪዎችን ለግል ምርጫ በሚጠቅም ሁኔታ ለማህበራዊ መርሃግብሮች ማስፈፀሚያ አውለዋል የሚለው ከሁሉ ይገዝፋል። በወቅቱ ምንም እንኳን ሩሴፍ ‹‹ውንጀላው መሰረት አልባ ነው፤ እኔ ከደሙ ንፁህ ነኝ›› ሲሉ ቢከራከሩም፤ የተካሄደባቸው ምርምራ ግን ነፃ ያወጣቸው አልሆነም።
ዴልማ ሩሴፍን በመተካት አገሪቱን በፕሬዚዳንትነት የማስተዳደር ከባድ ህዝባዊ ሃላፊነት የተረከቡት ሚቼል ቴመርም መንበረ ስልጣኑን እንደተረከቡ ሙስናን ከስር መሰረቱ ለማድረቅ ቃል ለመግባት ጊዜ አላባከኑም። ከጉቦ ቅሌት ጋር በተዛመደ ዋነኛ አማካሪያቸውና የካቢኔ አባል የነበሩትን ግለሰብ በማባረርም ወንጀሉን መፋለም በቃል ብቻ ሳይሆን በተግባርም የሚሰሩት ስለመሆኑ አስመስክረዋል። በአገሪቱ የሚካሄደውን ሙሰኞች የማደን ዘመቻም በይፋ ሲደግፉ መታየታቸው በርካቶች ዘንድ አድናቆትን አስችሯቸዋል።
‹‹እውነትና ንጋት እያደር ይጠራል›› እንዲሉ፤ ፕሬዚዳንቱ ስልጣን ከያዙ ዓመት እንኳን ብቅጡ ሳይሞላቸው ግን ስማቸው ከሙስና ቅሌት ጋር ተዳምሮ ተነስቷል። የአገራቸው ሙሰኞች የማደን ዘመቻም ብዙም ሳይቆይ እርሳቸውንም አግኝቷል። በሙስና እና በህገወጥ የገንዘብ ዝውውር ሁለት ወንጀሎች ተጠርጥረዋል።
ከፕሬዚዳንቱ ክስ መካከል ‹‹ከአንድ ግዙፍ የስጋ ማቀነባበሪያ ኩባንያ ገንዘብ ተቀብለዋል›› በሚል ሲሆን፤ ዓቃቢ ህግ ክሱን ያቀረበው ፕሬዚዳንቱ ከጄ.ቢ.ኤስ የስጋ ማቀነባበሪያ ኩባንያ ሊቀመንበር ከሆኑት ጆስሌይ ባቲስታ ጋር በጉቦ ዙሪያ የተነጋገሩት የተቀዳ ድምፅ መውጣቱን ተከትሎ ነው፡፡
መሰል የሙስና ክሶች ግን ምንም እንኳን ሳይጠበቁ ፕሬዚዳንቱንም ሆነ አፍቃሪዎቻቸውን ማስደንገጥና ማስጨነቃቸው ባይቀርም የሰውዬውን መንበር የመነቅነቅ አቅም ግን አልነበ ረውም። ሰውዬው በስልጣን ቆይታቸው ሁለት ሶስተኛ የሚሆነው የኮንግረሱ የታችኛው ምክር ቤት ተቀማጮች መቆጣጠራቸውም የሚነሱ ናቸው ክሶች ብዙም ርቀት እንዳይጓዙ ምክንያት መሆኑም ይመሰክራል።
በመሰል ሁኔታ ፕሬዚዳንቱ በአደባባይ ንፅህናቸውን ተረጋግጦ በስልጣን እንዲቆዩ መደረጉ ታዲያ የተለያዩ አስተያየቶችን አስተናግ ዷል። አንዳንዶችን በደስታ ጮቤ ሲያስርገጥ፤ አንዳንዶችን ደግሞ ለተቃውሞ ሰልፍ አደባባይ አስወጥቷል።
ይህም ሆኖ ፕሬዚዳንቱ ከተጠረጠሩበት የሙስና ወንጀል ማምለጥ ቢችሉና ባልተጠበቀና አስገራሚ በሆነ መልኩ ነፃ መሆናቸውን ማረጋገጥ ቢችሉም፤ ስለ ሰውዬውና ሙስና ያልተፈቱት እንቆቅሎሾች መጠየቃቸው ግን አልቆመም።
የሙስናው ቅሌትም በአገራዊ ምርጫ ሰውዬው ፕሬዚዳንትነታቸውን ለማስቀጠል በሚያደረጉት የምረጡኝ ቅስቀሳ ጉልህ ጠባሳ ነው። እናም ስልጣናቸውን ለወቅቱ የአገሬቱ ፕሬዚዳንት ጃዬል ቦልሴናሮ ማስረከብ ግድ ብሏቸዋል።
የ78 ዓመቱ ቴመር፣ ስልጣን በለቀቁ ሶስት ወራት ሳይሞላቸው ታዲያ ዳግም ክስ ተመስረቶባቸዋል። ከዚህ ክስ ቀድሞ በጉዳዩ ላይ አስተያየት የተጠየቁት ቴመር፤ ‹‹ምንም ስጋት አይሰማኝም፤ ወንጀለኛ ባለመሆኔም ማንም የእስር ትዕዛዝ ሊያሳልፍበኝ አይችልም›› ሲሉ ቢደመጡም ባሳልፈነው ሳምንት ግን የሰውየው ቃል ስህተት፤ መተማመናቸውም ከንቱ መሆኑ ታይቷል።
ስልጣን መልቀቃቸውን ተከትሎም ቀደም ሲል ያገኙ የነበረው የሴኔት ድጋፍና የህግ ከለላም አጥተውታልና ክሱን መሻገር ተስኗቸዋል። የብራዚል ዓቃቤ ህግም ‹‹ፕሬዚዳንቱ የጊዜ ጉዳይ እንጂ ዘብጥያ እንደሚወርዱ አትጠራጠሩ›› ባለው መሰረት ቃሉን በተግባር አሳይቷል።
እኤአ 2014 የተጀመረውና ካርውሽ በተባለው ዘመቻ ሪዮ ዴጄኒሮ ፖሊስ ቢሮ በ10 ግለሰቦች ላይ የእስር ማዘዣ ያወጣ ሲሆን፣ ከእነዚህም አንዱ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ሚሼል ቴመር ሆነዋል፡፡ በሌሎች 26 ተጠርጣሪዎች ላይም ሌላ የእስር ማዘዣ እንደወጣባቸው ተመላክቷል፡፡ በሰውዬው ዘመን የማዕድንና የሃይል ሚኒስትር የነበሩት ሞራራ ፍራንኮ በቁጥጥር ስር መዋላቸው ታውቋል።
ምንም እንኳን በሰውዬው ላይ ስለቀረበው ክስ በይፋ ባያሳውቅም፤ የአገሬው መገናኛ ብዙሃንም የቀድሞው ፕሬዚዳንት ሳኦፖሎ ከተማ ከመኖሪያ ቤታቻቸው ተይዘው ወደ እስር ማምራታቸውን አስንብበዋል። ብራዚላውያንንም በቴመር መታሰር የተሰማቸውን ደስታ በሪዮ ዴጄኖሮ መንገዶች ላይ ከመግለፅ ባለፈ ‹‹ሌባ! ሌባ!›› የሚል ድምጽ ሲያስተጋቡም ተደምጠዋል።
ሌሎች ሰልፈኞችም ‹‹ሹማምንቱ የሚመዘብ ሩት ረብጣ ገንዘብም የአገሪቱን የማህበራዊ አገልግሎት በእጅጉ የማሻሻል አቅም አለው›› ሲሉ ተደምጠዋል። የሰውዬው ጠበቃና ፓርቲያቸው በሌላ በኩል የአገሬውን ዓቃቤ ህግ ተግባር «የህግ የበላይነት የሚፃረር፣ በህግ ላይ የተቃጣ ጥቃት›› ብለውታል።
ይህን የተመለከቱት አሶሽየትድ ፕሬስን ጨምሮ ሌሎችም በርካታ መገናኛ ብዙሃን፤ ‹‹ካርውሽ በተባለው ሙስናን በመፋለሙ ሩጫ ብራዚል ዝግመት ላይ አይደለችም» ሲሉ አስነብበዋል። የብሉንበርግ ፀሃፍቱ ዴቪድ ቢለርና ሳማይ አድህሪን በበኩላቸው፤ ‹‹የቀድሞው ፕሬዚዳንት ለእስር መዳረግ፤ እኤአ 2014 የተጀመረውና ካርውሽ በተባለው ታላቁ የሙስና ምርምራ ዘመቻ ሃያልነት ከማስመስከር ባለፈ፤ ለአገሪቱ መንግስት ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጥ ወሳኝ እርምጃ ነው›› ሲሉ አመላክተዋል።
የኒውዮርክ ታይምሶቹ ፀሃፍት ኤርንስቴ ሎንዶኖ ላቲሺያ ካሳዶ በበኩላቸው፤ የቴመር መታሰር በአጭርና በረጅም ጊዜያት ውስጥ በብራዚል ምድር የሚኖረውን ፋይዳ አትተዋል። በተለይ ለወቅቱ የብራዚል ፕሬዚዳንት ጃየል ቦልሴናሉ ከድሎች ሁሉ የላቀው ድል መሆኑን አስምረውበታል። በሰውዬው ዘመን የሙስና ፍልሚያ ይበልጥ እንደሚፋፋም ፍንጭ የሚሰጥ መሆኑንና ይህም በዓለም ዓቀፉ ደረጃ እውቅናቸውን እንደሚያጎላላቸው ተመላክቷል።
የቴመር ለእስር መብቃት ዜና የዓለምን መገናኛ ብዙሃን ቀልብ መግዛት በመቻሉ፤ ከሁሉ በላይ በቦልሴናሮና በቤተሰባቸው ላይ የሚነሱ ቅሌቶችና የመገናኛ ብዙሃኑ ለጉዳዩ ሲሰጡት የከረሙት ትኩረት እንዲቀነስ ያሰጋልም ነው ያሉት።
በአጠቃላይ መገናኛ ብዙሃንና የፖለቲካ ፀሃፍቱም ከሁሉ በላይ በብራዚል ሹማምንትና የሙስና ቅሌት ትስስር እያደር በርካቶችን እያነጋገረ መቀጠሉን ያመላከቱ ሲሆን፣ ብራዚል ወንጀልና ወንጀሎቹን ለማፋታትም በቀጣይም በሹማምንቱ ላይ የተጠናከረ ምርመራ ማድረግ ብቻውንም ሳይሆን በአገሪቱ የተንስራፋውን ሙስና ለማስወገድ የፖለቲካ ስርዓት ለውጥ እጅግ አስፈላጊ ስለመሆኑ አስምርውበታል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 17/2011
በታምራት ተስፋዬ n;